አራት ዓይነት አፈጣጠር?

አራት ዓይነት አፈጣጠር?


ሙስሊም ወገኖቻችን የኢየሱስን ከድንግል የመወለድ ምስጢር ለማብራራት የሚጠቀሙት የተለመደ ሙግት አለ። በእስልምና የሰው አፈጣጠር የተለያየ በመሆኑ የኢየሱስ ከድንግል መወለድ ስለ ማንነቱ ምንም ነገር እንደማይነግረን ይሞግታሉ። በዚህም መሠረት በእስልምና አራት ዓይነት የሰው አፈጣጠር አለ ይሉናል፦

1. ያለ እናትና አባት (አዳም)

2. ያለ እናት ከአባት (ሔዋን)

3. ከእናትና ከአባት (የሰው ልጆች ሁሉ)

4. ከእናት ያለ አባት (ዒሳ

ይህ ሙግት የማይሠራባቸው ምክንያቶች አሉ።

1. ሦስቱ ዓይነት የሰው አፈጣጠሮች ዓላማቸው ግልፅ ነው። አዳም ከአፈር የተፈጠረው ሌላ ከእርሱ የሚቀድም ሰው ስላልነበረ ነው። ሔዋን ከአዳም የተፈጠረችው የመጀመርያዋ ሴት ስለነበረች ነው። ወንድና ሴት ከተፈጠሩ በኋላ ግን ይህ ሥርዓት ሳይጣስ ለብዙ ሺህ ዓመታት ኖሯል። የሦስቱ አፈጣጠሮች ዓላማ ግልፅ ነው። ከሰው ልጆች ሁሉ ተለይቶ ግን ዒሳ ከሴትየተፈጠረበትምክንያት ግልፅ ሊሆን ይገባል። ሙስሊሞች ምላሽ ሲሰጡአላህ ዒሳን ምልክት ለማድረግና ተዓምራቱን ለማሳየት ስለፈለገ ነውይሉናል። ነገር ግን ይህ ጉዳይ በቅዱሳት መጻሕፍት የተነገረንና በእምነት የምንቀበለው እንጂ በማስረጃ የምናረጋግጠው አይደለም። አማኞች ብቻ በእምነት የሚቀበሉትን ጉዳይ ለሰው ልጆች ሁሉ እንደ ተዓምራዊ ምልክት መቁጠር የሚያስኬድ አይደለም።

ሌላው መታወስ ያለበት ጉዳይ ሔዋን ያለ እናት ከአባት ተፈጠረች የሚለው ሐሳብ በራሱ ሐሰት መሆኑ ነው። ምክንያቱም አዳም የሔዋን አባት አይደለምና። ከጎን አጥንቱ እንደተፈጠረች እንጂ እርሱ የእርሷ አባት ነው የሚል የመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ የቁርአን ማስረጃ የለም። ሙስሊሞች የኢየሱስን አወላለድና የሔዋንን አፈጣጠር አንድ በማስመሰል መናገራቸው የኢየሱስን ልደት በሰው ልጆች የአፈጣጠር ሒድት ውስጥ ሌላኛው መንገድ ብቻ የማስመሰል ጥረት ቢሆንም እርሷን ለዚህ ሐሳብ አስረጂነት እንደ ምሳሌ መጥቀስና ሁለቱን አቻ ማድረግ የሚያስኬድ አይደለም። ኢየሱስ ያለ አባት ከእናቱ ከማርያም ተወለደ የምንለው ማርያም እናቱ ስለሆነች ነው። አዳም ግን የሔዋን አባት አይደለም። ስለዚህ የሔዋንን አፈጣጠር ሙስሊሞች “ያለ እናት ከአባት” በማለት በሐሰት መጥራታቸውን ማቆም ይገባቸዋል።

2. አላህ ተዓምራቱን ለመግለጥ ብቻ ነው ከተባለ የሰው አፈጣጠር ለምን በአራት ብቻ ተገደበ? ለምሳሌ ያህል፦

  • የመጀመርያው ሰው ከአፈር ከተፈጠረ ለምን ከድንጋይ ወይም ከእንጨት የተፈጠረ ሰው አልኖረም? እንዲሁም ያለ ምንም ቀዳሚ ቁስ ከምንም ነገር የተፈጠረ ሰው ስለ ምን አልኖረም?
  • ሴት ከወንድ የጎን አጥንት እንደተፈጠረችው ሁሉ ለምን ከሴት የጎን አጥንት የተፈጠረ ሰው አልኖረም? 
  • ከወንድ ያለ ልደት ሴት እንደተፈጠረችው ሁሉ ያለ ልደት ወንድ ከሴት ለምን አልተፈጠረም?
  • ሴት ከወንድ እንደተፈጠረችው ሁሉ ያለ ሴት ወንድ ከወንድ ለምን አልተፈጠረም?
  • ሴት ከወንድእንደተፈጠረችውሁሉ ሴት ያለ ወንድ ከሴት ለምን አልተፈጠረችም?
  • ወንድ ያለ ሴት እና ያለ ወንድ (ያለ አባትና እናት) እንደተፈጠረው ሁሉ ሴት ያለ ወንድና ሴት ለምን አልተፈጠረችም?

እነዚህ ሁሉ የአፈጣጠር አማራጮች ባሉበት ሁኔታ በአራት ብቻ መገደብ ትርጉም አይሰጥም። እነዚህ ሁሉ አማራጮች ባለመሟላታቸው የአላህ ፍጥረት ጎዶሎ ነው ይሉን ይሆን?

3. ቁርአን የቱ ጋር ነው የዒሳን አወላለድ ሌላ የሰው አፈጣጠር መንገድ ብቻ አድርጎ የገለጸው? ይህ የሙስሊሞች ማብራርያ ትክክል ቢሆን ኖሮ ቁርአን ሦስቱ ቅደም ተከተሎች ጠቅሶ አራተኛውም ከዚህ ያልተለየ መሆኑን በነገረን ነበር። ነገር ግን አንድም ቦታ ላይ ይህ አልተባለም። ይልቁኑ ቁርአን ሦስቱን አፈጣጠሮች በቅደም ተከተል የሚገልጽባቸው ቦታዎች ቢኖሩም በአንድም ቦታ ላይ የዒሳን አወላለድ አራተኛ አድርጎ አይጠቅስም፦

እርሱ ያ ከአንዲት ነፍስ (ከአደም) የፈጠራችሁ ከእርሷም መቀናጆዋን ወደርሷ ይረካ ዘንድ ያደረገ ነው፡፡ በተገናኛትም ጊዜ ቀላልን እርግዝና አረገዘች፡፡ እርሱንም (ፅንሱን) ይዛው ኼደች፡፡ በከበደችም ጊዜ «ደግን ልጅ ብትሰጠን በእርግጥ ከአመስጋኞቹ እንኾናለን፤» ሲሉ ጌታቸውን አላህን ለመኑ፡፡” (ሱራ 7189)

እናንተ ሰዎች ሆይ! ያንን ከአንዲት ነፍስ (ከአዳም) የፈጠራችሁን ከእርስዋም መቀናጆዋን (ሔዋንን) የፈጠረውን ከእነርሱም ብዙ ወንዶችንና ሴቶች የበተነውን ጌታችሁን ፍሩ፡፡ ያንንም በርሱ የምትጠያየቁበትን አላህንና ዝምድናዎችንም (ከመቁረጥ) ተጠንቀቁ፡፡ አላህ በእናንተ ላይ ተጠባባቂ ነውና፡፡” (ሱራ 41)

ሦስቱ አፈጣጠሮች በዚህ ሁኔታ በቅደም ተከተል የተጠቀሱ ቢሆንም አራተኛው ከዚህ ጋር ተያይዞ የተጠቀሰበት አንድም ጥቅስ የለም። ለምን? ሦስቱንም በአንድነት የጠቀሰው ቁርአን አራተኛውን ለምን አብሮ አልጠቀሰም? ስለዚህ አራተኛው በዓላማም በዓይነትም ከዚህ የተለየ ነው ማለት ነው።

4. ቀደምት ቅዱሳን ነቢያት የክርስቶስን ከድንግል የመወለድ ምክንያት ነግረውናል፤ ይህም መለኮታዊ የእግዚአብሔር ልጅ ስለሆነ ነው የሚል ነው።

ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል [አምላክ ከእኛ ጋር] ብላ ትጠራዋለች።” (ኢሳይያስ 714)

ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።” (ኢሳይያስ 96)

አንቺም ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፥ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፤ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ፥ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል።” (ሚክያስ 52)

መልአኩም ለማርያም ሲያበስራት እንዲህ ነበር ያለው፦

እነሆም፥ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለላም ይነግሣል፥ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም። ማርያምም መልአኩን። ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል? አለችው። መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት። መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል።” (ሉቃስ 131-35)

ቀደምት ቅዱሳት መጻሕፍት ይህንን የሚነግሩን ከሆነ ከክስተቱ ከክፍለ ዘመናት በኋላ የመጣው እስልምና አዲስ ተጻራሪ ሐሳብ ቢያመጣ ልንቀበለው አይገባም።

ስናጠቃልል “አራት ዓይነት አፈጣጠር” የሚለው የሙስሊሞች ማብራርያ ከላይ በተጠቀሱት አራት ምክንያቶች ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም። የመጀመርያው ምክንያት ሦስቱ የአፈጣጠር መንገዶች ለሰው አፈጣጠር ግዴታ ስለነበሩ እንጂ ያለ ዓላማ የተፈፀሙ አልነበሩም። ስለዚህ እንደ ሌሎቹ ሁሉ የአፈጣጠር መንገድ ብቻ አድርጎ መቁጠር ትርጉም አይሰጥም። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ብዙ ዓይነት አፈጣጠሮች ባሉበት ሁኔታ የሰው አፈጣጠር አራት ዓይነት ነው ብሎ መደምደም አያስኬድም። ሦስቱን በዓላማ የሠራው ፈጣሪ አራተኛውን በተለየ ሁኔታ ለሰው ልጆች ምልክት እንዲሆን ነው ከተባለ ሌሎች የአፈጣጠር መንገዶችን ለምን አልተጠቀመም የሚለው ጥያቄ ሊመለስ ይገባዋል። ስላልፈቀደ ነው የሚል ምላሽ ከተሰጠ አራተኛ የተባለውንና ከሦስቱ በተለየ ሁኔታ አስፈላጊነት (necessity) የሌለውን መንገድ ከሌሎች አፈጣጠሮች ተርታ ማሰለፍ የዘፈቀደ ሙግት ይሆናል። ሌላው ምክንያት ቁርአን ሦስቱን የአፈጣጠር መንገዶች በአንድነትና በቅደም ተከተል ቢነግረንም አራተኛውን ግን አንድም ቦታ ላይ ከእነዚህ ጋር በአንድነት በመቁጠር ያስቀመጠበት ቦታ የለም። አራት ዓይነት አፈጣጠር የሚሉን ወገኖች የቁርአን ደራሲ የዘነጋውን ሊያስታውሱት እየሞከሩ ነው። የመጨረሻውና ትልቁ ምክንያት ደግሞ የቀደሙት ነቢያትና ቅዱሳት መጻሕፍት የክርስቶስን ከድንግል የመወለድ ምክንያት በግልጽና በማያሻማ መንገድ ነግረውናል፤ ይህም በማንነቱ መለኮታዊ የእግዚአብሔር ልጅ ስለሆነ ነው የሚል ነው። እውነታው ይህ ከሆነ ደግሞ ስለ ቅዱሳት መሳሕፍት የተሟላ ዕውቀት ያልነበረው አንድ ግለሰብ ወደ ዋሻ ገብቶ በመውጣትተገለጠልኝበሚል ብሒል ይህንን እውነት ሊለውጥ አይችልም።


መሲሁ ኢየሱስ