ከገዛ ቋንቋው ውጪ የተላከ መልእክተኛ የለም?

ከገዛ ቋንቋው ውጪ የተላከ መልእክተኛ የለም?


በቁርአን መሠረት በገዛ ወገኖቹ ቋንቋ እንጂ በሌሎች ቋንቋዎች የተላከ መልእክተኛ የለም፤ ለዚህም ምከንያቱ የገዛ ወገኖቹ የመልእክተኛውን መልእክት በትክክል መረዳት ይችሉ ዘንድ ነው፡-

“ከመልክተኛ ማንኛውንም፤ ለነርሱ ያብራራላቸው ዘንድ በወገኖቹ ቋንቋ እንጂ በሌላ አልላክንም፤ አላህም የሚሻውን ያጠማል፤ የሚሻውንም ያቀናል፤ እርሱም አሸናፊው ጥበበኛው ነው።” (ሱረቱ ኢብራሂም 14፡4)

ቁርአን በአረብኛ “የወረደበትን” ዓላማ ሲገልፅ ተመሳሳይ ምክንያት ይሰጣል፡-

“እኛ ታውቁ ዘንድ ዐረብኛ ቁርአን አደረግነው።” (ሱረቱ አል-ዙኽሩፍ 43፡3)

የቁርአን ደራሲ ከላይ የተጠቀሰውን ሐሳብ በመጻረር እስራኤላዊው ነቢይ ዮናስ ወደ ነነዌ ሕዝቦች እንደተላከ ይናገራል፡-

“(ከዩኑስ በፊት ካለፉት ከተሞች) ያመነችና እምነትዋ የጠቀማት ከተማ ለምን አልኖረችም ግን የዩኑስ ሕዝቦች ባመኑ ጊዜ በቅርቢቱ ሕይወት የውርደትን ቅጣት ከእነሱ ላይ አነሳንላቸው፡፡ እስከ ጊዜም ድረስ አጣቀምናቸው፡፡” (ሱረቱ ዩኑስ 10፡98፤ በተጨማሪም ሱረቱ አልሷፍፋት 37፡139–148)

ዮናስ የተላከባት ከተማ ነነዌ (የዛሬዋ ሞሱል) መሆኗን ኢብን ከሢርን የመሳሰሉት ሙፈሲሮች ጽፈዋል፤ የዮናስ መቃብር እንደሆነ በሚነገርለት ቦታ ላይ እዚያው ኢራቅ ሀገር ነነዌ ውስጥ በዮናስ ስም የተሰየመ መስጊድ ተገንብቷል፡፡

ዮናስን በተመለከተ ቀዳሚ ምንጭ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ እስራኤላዊ መሆኑንና ወደ ነነዌ እንደተላከ ይናገራል፡-

“የጋትሔፌር በነበረው በአማቴ ልጅ በባሪያው በነቢዩ በዮናስ እጅ እንደ ተናገረው እንደ እስራኤል አምላክ እንደ እግዚአብሔር ቃል የእስራኤልን ድንበር ከሐማት መግቢያ ጀምሮ እስከ ዓረባ ባሕር ድረስ መለሰ።” (2ነገሥት 14፡25)

“የእግዚአብሔርም ቃል ወደ አማቴ ልጅ ወደ ዮናስ እንዲህ ሲል መጣ፦ ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፥ ክፉታቸውም ወደ ፊቴ ወጥቶአልና በእርስዋ ላይ ስበክ።” (ዮናስ 1፡1-2)

እውነቱ ይህ ከሆነ ሙስሊም ወገኖቻችን የዮናስን ቋንቋ ጉዳይ ማብራራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የእብራይስጥ ቋንቋ ተናጋሪ የነበረው ነቢዩ ዮናስ ወደ አሦራውያን የተላከው የራሱ ባልሆነው የአሦርያውያን ቋንቋ ነው ወይንስ የራሱ በሆነው የእብራይስጥ ቋንቋ ነው? የራሱ በሆነው የእብራይስጥ ቋንቋ ከነበረ ቁርአን “ለነርሱ ያብራራላቸው ዘንድ በወገኖቹ ቋንቋ እንጂ በሌላ አልላክንም” ስለሚል ዮናስ ለአሦራውያን እነርሱ በማያውቁት ቋንቋ ያብራራላቸው ዘንድ ተልኳል ማለት ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ ትርጉም አይሰጥም፡፡ በአሦራውያን ቋንቋ ከሆነ ደግሞ ከራሱ ሕዝብ ሌላ በሆነ ቋንቋ የተላከ መልእክተኛ እንደሌለው የሚናገረው የቁርአን ቃል ስህተት ሊሆን ነው፡፡

ሌላው ጥያቄ የሚፈጥር ጉዳይ በእስልምና መሠረት ከሙሐመድ በፊት የነበሩት ነቢያት ሁሉ ለራሳቸው ሕዝብ ብቻ እንደተላኩ መታመኑ ነው፡፡ ይህ አስተምህሮ ትክክል ከሆነ ዓለም አቀፋዊ ድንበሮችን ተሻግሮ ነነዌ ድረስ የሄደው የዮናስ ጉዳይ አሁንም ጥያቄ ሊፈጥር ነው፡፡

የዮናስን ታሪክ ካነሳን አይቀር ሌላ ጥያቄ የሚፈጥር ጉዳይ እንጥቀስ፡፡ በቁርአን መሠረት መልእክተኞች የተላኩላቸው ከተሞች በሙሉ ክደዋል፡-

“በከተማም አስፈራሪን አልላክንም፣ ነዋሪዎችዋ እኛ በዚያ በርሱ በተላካችሁበት ከሐዲዎች ነን ያሉ ቢሆኑ እንጂ።” (ሱረቱ አል- አሕዛብ 34:34)

በሌላ ቦታ ላይ ግን ዮናስ የተላከላት ከተማ ሕዝቦች መልእክቱን መቀበላቸውን ይናገራል፡- “ወደ መቶ ሺህ ሰዎችም ዳግመኛ ላክነው ከቶውንም ይጨምራሉ፡፡ አመኑም እስከ ጊዜውም ድረስ አጣቀምናቸው፡፡” (ሱረቱ አል-ፈጢር 35:147-148)

መጽሐፍ ቅዱስም የነነዌ ሕዝቦች የዮናስን መልእክት ሲሰሙ ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ወዲያውኑ ተቀብለው ንስሐ መግባታቸውን ይናገራል፡-

“የነነዌም ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ፤ ለጾም አዋጅ ነገሩ፥ ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ። ወሬውም ወደ ነነዌ ንጉሥ ደረሰ፤ እርሱም ከዙፋኑ ተነሥቶ መጐናጸፊያውን አወለቀ ማቅም ለበሰ፥ በአመድም ላይ ተቀመጠ።” (ዮናስ 3፡5-6)

ቁርአን ከሰማይ የወረደ የፈጣሪ ቃል ከሆነ እንዲህ ያሉ ግጭቶች እንዴት በውስጡ ሊገኙ ቻሉ? ቁርአን የሙሐመድና የተባባሪዎቹ ፈጠራ እንጂ ሌላ አይደለም!

ልዩ ልዩ