መንፈስ ቅዱስ መለኮት ነው

መንፈስ ቅዱስ መለኮት ነው


እግረ መንገዴን ቴሌግራም ገብቼ አንድ የሙስሊሞች ግሩፕ ውስጥ ውይይት እየሰማሁ ሳለሁ አንዱ ክርስቲያን ኢዮብ 33:4 ላይ የሚገኘውን ቃል ጠቅሶ መንፈስ ቅዱስ ፈጣሪ መሆኑን እንደሚያሳይ ለአንድ ሙስሊም ይነግረዋል። ክፍሉ እንዲህ ይላል፦

“የእግዚአብሔር መንፈስ ፈጠረኝ፥ ሁሉንም የሚችል የአምላክ እስትንፋስ ሕይወት ሰጠኝ።”

ሙስሊሙ ልጅ እንዲህ የሚል ምላሽ ሲሰጠ ሰማሁት “የግሪክ ሰፕቱጀንቱ እንደዚያ አያሳይም፤ የዓረፍተ ነገሩ ባለቤት እግዚአብሔር ነው የሚለው። ስለዚህ የእግዚአብሔር መንፈስ ነው እንጂ መንፈሱ እግዚአብሔር አይደለም”። ሙስሊሙ ልጅ ከኡዝታዞቹ የሰማውን እየደገመ ነው እንጂ ቋንቋውን አውቆት አይመስለኝም። እስኪ ክፍሉን እንመልከት። የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም እንዲህ ይነበባል፦

πνεῦμα θεῖον τὸ ποιῆσάν με πνοὴ δὲ παντοκράτορος ἡ διδάσκουσά με

በግሪኩ ንባብ ውስጥ πνεῦμα θεῖον τὸ ποιῆσάν με (ፕኒውማ ቴይዮን ቶ ፖዬሳን ሜ) የሚለው በቀጥታ ሲተረጎም “መለኮታዊው መንፈስ ሠራኝ” “devine spirit made me” ተብሎ ነው፤ ምክንያቱም፦

  1. θεῖον የሚለው ቃል ቀጥተኛ ትርጉም “እግዚአብሔር” አይደለም። መካከል ላይ ያለችው ዮታ “ῖ” ትርጉሙን ትለውጠዋለች። ትርጉሙም “መለኮት” ወይም ደግሞ “አማልክት gods” ማለት ነው። ከአውዱ የምንረዳው ብዛትን ሳይሆን አንዱን መለኮት በመሆኑ ትርጉሙ “መለኮት” ይሆናል ማለት ነው።
  2. θεῖον ግዑዝ ፆታ (neutre gender) ነው። እግዚአብሔር ግን θεος ሲሆን፣ ሰዋሰዋዊ አገባቡ ተባዕታይ ፆታ (masculine gender) ነው። “መለኮት” ለሚለው ቃል በግሪኩ ተባዕታይ ፆታ ደግሞ θεῖος ነው። እዚህ ክፍል ላይ ግን አጨራረሱ ተቀይሮ θεῖον ሆኖ ነው የመጣው። ለዚህም ምክንያቱ πνεῦμα “መንፈስ” የሚለው የግሪክ ቃል ሰዋሰዋዊ አገባቡ ግዑዝ ፆታ (grammatically neuter) ስለሆነ ነው። ስለዚህ “መለኮት” የሚለው ቃል በግሪክ ሰዋሰዋዊ ሕግ የዓረፍተ ነገሩን ባለ ቤት ሲገልፅ በ case, gender, number መመሳሰል ስላለበት ወደ ግዑዝ ተቀይሯል ማለት ነው። ይህም “መንፈስ” የዓረፍተ ነገሩ ባለ ቤት እንጂ ገላጭ አለመሆኑን ያሳያል። ስለዚህ የሙስሊሞቹ ሙግት ውድቅ ነው ማለት ነው። ቅድመ ክርስቶስ የተተረጎመው ይህ የአይሁድ ትርጉም መንፈስ ቅዱስ ፈጣሪ መለኮት መሆኑን በግልጽ ያሳያል። ለዚህም ነው ከግሪኩ ላይ በቀጥታ የተተረጎመው የብረንተን የእንግሊዝኛ ትርጉም እንዲህ በማለት ያስቀመጠው፦

“The Divine Spirit is that which formed me, and the breath of the Almighty that which teaches me.” – Brenton Septuagint Translation

“የፈጠረኝ መለኮት የሆነው መንፈስ ነው፤ የሚያስተምረኝም የሁሉን ቻዩ እስትንፋስ ነው።”

የሆነው ሆኖ ግን መንፈስ ቅዱስ የአብ መንፈስ መሆኑ ማንነት ያሳጣዋል የሚል እሳቤ ምክንያታዊም መጽሐፍ ቅዱሳዊም አይደለም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስን “እርሱ” (He) በማለት ማንነትን በሚገልጽ አገላለጽ ጠቅሶታል፤ ከአብ የሚወጣ መንፈስ ሆኖ ሳለ ከአብ እንደሚሰማና እንደሚናገር ገልጿል (ዮሐንስ 16:7-16)። ለበለጠ ማብራርያ ይህንን ጽሑፍ ያንብቡ።

ዶ/ር ናዖል

ልዩ ልዩ