ኢየሱስ – ከስም ሁሉ በላይ የኾነ ስም
በወንድም ሚናስ
በባለፈው መጣጥፍ እንደተመለከትነው ሐዋርያው ጳውሎስ በፊል.2፥6-7 ላይ ክርስቶስ በባሕርዩ አምላክ እንደኾነ፣ ነገር ግን ስለ ሰው ልጆች መተላለፍ ሲል ሥጋን እንደለበሰ እስከ መስቀል ሞትም ለአባቱ እንደታዘዘ በአጽንዖት ይገልጻል፤ አስከትሎም ከቍጥር 9-11 ላይ ባለው ንባብ ላይ ክርስቶስ ከአባቱ ጋር እኵል ዕሪና ያለው ያህዌ መኾኑን እንዲሁም በአጽናፈ ዓለም አምላካዊ ሥልጣን እንዳለው እንዲህ ሲል ይነግረናል፦
“ስለዚህ እግዚአብሔር እጅግ ከፍ አደረገው፤ ከስምም ዅሉ በላይ የኾነውን ስም ሰጠው፤ ይኸውም በሰማይና በምድር፣ ከምድርም በታች፣ ጕልበት ዅሉ ለኢየሱስ ስም ይንበረከክ ዘንድ፣ ምላስም ዅሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ኾነ ይመሰክር ዘንድ ነው።”ፊል.2፥9-11 (ዐ.መ.ት)
ከዚህ ምንባብ ኹለት መሠረታዊ ነጥቦችን ከግንዛቤ ውስጥ እናስገባለን፦ (1ኛ) ኢየሱስ “ከስምም ዅሉ በላይ የኾነውን ስም” እንዳለው ይህ ደግሞ በአይሁዳውያን ዐውድ የያህዌ ስም መኾኑንና ጳውሎስ ወዲያውኑ ኢየሱስ ጌታ መኾኑን በመናገር ይህ ስም የኢየሱስ መኾኑን ይናገራል። (2ኛ) “ጕልበት ዅሉ ይንበረከክ… ምላስም ዅሉ ይመስክር” የሚለው አገላለጽ በቀጥታ ከኢሳይያስ 45፥23 የተጠቀሰ ሲኾን፣ የብሉይ ኪዳኑ ምንባብ ለያህዌ የተነገረ ነው፤ ጳውሎስ ደግሞ ይህንን ምንባብ ለክርስቶስ መጠቀሙ ኢየሱስ አምልኮ የሚቀበል ያህዌ መኾኑን ፍንትው አድርጐ የሚያሳይ ነው[1]፤ ይኹን እንጂ ፀረ ሥላሴአውያን ይህንን እውነት አይቀበሉም፤ ይህንን ለመረዳት የማያዳግተውን መለኮታዊ ምንባብ፣ ለማስተባበልም አራት የተለመዱ ሙግቶችን ያቀርባሉ። በማስከተል ሙግቶቹን የምንዳሥሣቸው ይኾናል።
አንደኛ ይህ ሙግት ዐማርኛ/እንግሊዝኛ ትርጒምን መሠረት ያደረገ ነው፤ የይሖዋ ምስክሮች ኢሳ 45፥23 “አንደበትም ዅሉ በእኔ ይምላል” ሲል ጳውሎስ ደግሞ “ምላስ ዅሉ ይመሰክራል” ስለሚል፣ “ፊል 2፥10 ከኢሳ.45፥23 የተጠቀሰ ምንባብ አይደለም፤ ከዚህ ተነሥተንም ኢየሱስ ያህዌ ነው ማለት አንችልም[2] ”ይላሉ፤ ነገር ግን ኢሳ.45፥23 ላይ “ይምላል” ፊል.2፥10 “ይመሰክራል” ተብሎ የተተረጐመውም ተመሳሳይ የጽርእ ቃል ነው፤ በተጨማሪም በሠንጠረዡ እንደተመለከትነው በኹለቱ ምንባባት ላይ ፍጹም የኾነ የቃላት መመሳሰል ስላለ፣ ሐዋርያው ከኢሳይያስ መጽሐፍ መጥቀሱ በሊቃውንቱ ዘንድ አከራካሪ ጒዳይ አይደለም[3]።
ኹለተኛው ሙግት ደግሞ “ኢን ቶ ሆኖማቲ” (ኢንἐν τῷ ὀνόματι) በዐዲስ ኪዳን መጻሕፍት “በ…ስም” እንጂ “ለ…ስም” የሚል ትርጒም የለውምና “በኢየሱስ ስም” እንጂ “ለኢየሱስ ስም” ተብሎ መተርጒም የለበትም የሚል ነው[4]፤ ይኸውም ጠቅለል ተደርጐ ሲገለጽ ጳውሎስ “በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ” ሲል በኢየሱስ ስም በኵል ወደ አብ የሚደረግ ስግደትን እንጂ የስግደቱ ተቀባይ ራሱ ኢየሱስ የሚያመለክት አይደለም የሚል ነው። ይህ መከራከሪያ ግን “ኢን ቶ ሆኖማቲ” ( ἐν τῷ ὀνόματι) የሚለው ሐረግ “መመስከር” ( ἐξομολογέω “ኤክሶሞሎጌኦ”) ከሚለው ግስ ጋር ዐብሮ መምጣቱን የዘነጋ ሙግት ነው፤ ፊል 2፥10 ለእንደዚህ ዐይነት አገላለጽ ብቸኛው የዐዲስ ኪዳን ምንባብ ቢኾንም፣ በሰባ ሊቃናት ትርጒም የተለመደ ነው፤ ይኸውም ምስክርነቱ ለራሱ ለስሙ እንጂ በስሙ በኵል (as instrument) ለሌላ አካል ወይም ማንነት የሚመለክቱ አይደሉም፤ የተወሰኑትን ለማሳያ ያኽል፦
“ዅል ጊዜ በእግዚአብሔር እንከብራለን፥ ለስምኽም (ἐν τῷ ὀνόματι σου) ለዘላለም እንመሰክራለን (ομολογέω)።” መዝ.44፥8
“አቤቱ፥ ስለዚህ በአሕዛብ ዘንድ አመሰግንኻለኹ፥ ለስምኽም( ἐν τῷ ὀνόματι) እመሰክራለኹ (ομολογέω)።” 2ኛ ሳሙኤል 22፥50
“እግዚአብሔርን አመስግኑ፥ ስሙን (ἐν τῷ ὀνόματι) ጥሩ፤ ለአሕዛብ ሥራውን መስክሩ (ομολογέω)።” 1 ዜና 16፥8
በተጨማሪም የሰባ ሊቃናት ትርጒም “ኢን ቶ ሆኖማቲ” (ἐν τῷ ὀνόματι) የሚለውን ሐረግ ከሌላ የአኰቴት ግስ (verbs of honor) በማጫፈር ሲጠቀሙ፣ ምስጋና አቅራቢያዎቹ ምስጋናውን የሚያቀርቡት ለራሱ ለእግዚአብሔር ስም እንጂ ለሌላ ኹለተኛ አካል አለመኾኑን ያሳያሉ (መዝ 62፥5፤ 88፥13፣ 17፤ 104፥3 ይመልከቱ)። ስለዚህ “በ…ስም” ወይም “ለ…ስም” ተብሎ ቢተረጐም “የሚመሰክሩለት” “የሚሰግዱለት” ለራሱ ለኢየሱስ እንጂ፣ በስሙ በኵል ለሌላ አካል ወይም ለአብ አይደለም ማለት ነው።
ሦስተኛው ሙግት ሐዋርያው ጳውሎስ እግዚአብሔር ክርስቶስን “ከፍ ከፍ እንዳደረገው” ብሎ መግለጹ ኢየሱስ ቀድሞ ያልነበረውን ከፍታ ማግኘቱን ያመለክታል የሚል ነው[5]፤ ለዚህም ሐዋርያው ከፍ ማለቱን ለማመልከት ὑπερυψόω “ሁፔሩፕሶ” የሚለውን የጽርእ ግስ መጠቀሙ አስቀድሞ ገንዘቡ ያልነበረውን ነገር ከጊዜ በኋላ መውረሱን፣ ማግኘቱን፣ የሚያመለክት ነው ይላሉ። ይኹን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ὑπερυψόω “ሁፔሩፕሶ” የሚለው ግስ ቀድሞ ከነበረው ደረጃ ጋር የሚያወዳድር አብላጭ ግስ (comparative verb) ሳይኾን፣ ያለ ንጽጽር ፍጹም የበላይነትን አመልካች ግስ (Elative verb) መኾኑን ይናገራሉ[6]። ይህ ግስ በሰባ ሊቃናት ትርጒም[7] ለጌታ ለእግዚአብሔር የሚገባውን ዕሪና በሚገልጽበት ጊዜ የገባ ቃል ሲኾን፣ ግሱ አበላላጭ ሳይኾን ያለ ንጽጽር የሚያልቅ ነው የሚለውን ትርጓሜ በይበልጥ ያጸናል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦
“አንተ፥ እግዚአብሔር፥ በምድር ላይ ዅሉ ልዑል ነኽና፥ በአማልክትም ዅሉ ላይ እጅግ ከፍ ከፍ ብለኻልና (ὑπερυψώθης)”መዝ. 97፥9፤
መዝሙረኛው ጌታ አኹን ከቀድሞው የላቀ ማዕረግ እንዳገኘ እየተናገረ ሳይኾን ከማንም ወይም ከምንም ነገር የበለጠ መኾኑን፣ ይኸውም አምልኮ ከማይገባቸው አማልክት በላይ የላቀ መኾኑን አመልካች ነው። ግሱ በሌላ ምንባብ ላይ ራሱን ከፍ ከፍ ያደረገውን ኋላ ግን በእግዚአብሔር የተዋረደን ሰው በምፀት መልክ ከመጠቀሙ ውጪ [መዝ 37፥35]፣ መዝ. 97፥9 አንዱና ብቸኛው ጥቅስ ነው፤ ስለዚህ ሐዋርያው በቅዱሳት መጻሕፍት ያልተለመደውን ይህንን ግስ ከመዝ 97፥9 ጋር ማጣቀሱ ግልጽ ነው። ጳውሎስ “በሰማይና በምድር ከምድርም በታች” የሚለውን ሐረግ መጠቀሙ (ፊልጵ. 2፥10ለ) ከመዝ 97፥9 ጋር የሚዛመድ ሲኾን ፣ በተለይም “በሰማይ” የሚለው አገላለጹ በሌሎች እንደ “አማልክት” የሚታዩትን ኀይላት ፍጥረታት እንኳን በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት እንደሚሰግዱ የሚያሳይ ምንባብ ነው። ሲጠቃለል በፊልጵስዩስ 2፥9 እና መዝሙረ ዳዊት 96፥9 ὑπερυψόω “ሁፔሩፕሶ” ከሚለው ብርቅዬ ግስ በተጨማሪ በግልጽነት የሚታይ ጭብጣዊ ግንኙነት (Thematic connection) አለ። ስለዚህም “ከፍ ከፍ አለ” የሚለው አገላለጽ የክርስቶስ መለኮትነት ከመናድ ይልቅ በእጅጉ የሚያጠናክር ኾኖ እንናገዋለን።
አራተኛው ሙግት ፊልጵስዩስ 2፥9-11 ኢየሱስን ያህዌ ነው ብሎ ለመደምደም ኹለተኛው ሙግት ከፍ ከፍ “አደረገው” “ሰጠው” የሚሉት ገለጻዎች ናቸው[8]፤ እውን ኢየሱስ የባሕርይ አምላክ ከኾነ፣ እግዚአብሔር ይህንን ክብር እንዴት ከትንሣኤው በኋላ ሰጠው? የሚል ነው። ይህ ሙግት ከዚህ በፊት በሌላ ጽሑፍ ከተመለከትነው https://ewnetlehulu.net/jebel-q1/ ሐሳብ ጋር ተመሳሳይ ነው። ጴጥሮስ በጴንጠቆስጤ “ኢየሱስን ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ዅሉ ይረዳ” የሚለው አገላለጹ እስከ ትንሣኤው ድረስ ኢየሱስ ጌታ እና ክርስቶስ አልነበረም ብለን ልንገምት ብንችልም፣ የሐዋርያት ሥራ ጸሓፊ ሉቃስ በወንጌሉ ኢየሱስ በልደቱ ወቅት እንኳን ጌታና ክርስቶስ እንደነበር ተናግሮአል (ሉቃ. 1፡41-44፣ ሉቃስ 2፡11)፡፡ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ሮሜ 1:4 “ከሙታን በመነሣቱ የእግዚአብሔር ልጅ መኾኑ በኀይል ስለ ተገለጠው” ቢልም ፣ ሐዋርያው በሌላ ክፍል ላይ ክርስቶስ ሰው ከመኾኑ በፊት እንኳን መለኮታዊ የእግዚአብሔር ልጅ መኾኑን ይናገራል (ገላ.4፥4፤ ሮሜ 8፥3)። በተመሳሳይ ፊል 2፥10 ላይ ያለው አገላለጽ ከሞቱ በፊት እንኳን “የክብር ጌታ” መኾኑን ከገለጸበት ምንባባት ጋር በፍጹም አይጋጭም። ሐዋርያው “ሰጠው” “አከበረው” የሚለው አገላለጹ እግዚአብሔር አብ የልጁን ክብር ለዓለም ዅሉ መግለጹን የሚያመለክት ነው፤ ክርስቶስ ከሰማያዊ ክብሩ ራሱን በማውረድ እስከ መስቀል ሞት ድረስ ለአባቱ ታዝዞአል፤ አባቱም ልጁ ያሳየውን የውርደት ጥግ፣ በክብር ጥግ መለኮትነቱን ለዓለም በማሳየት አረጋግጦአል። መዝሙረኛው “እግዚአብሔር ከፍ ከፍ አለ” ሲል ታላቅነቱ የባሕርይ ማንነቱ እንደኾነ እንጂ ከጊዜ በኋላ ያገኘው መኾኑን እንደማያመለክት ዅሉ፣ ለጌታችንም “ተሰጠው” “አደረገው” የሚሉት ገለጻዎች አስቀድሞም የማንነቱ አካል የኾኑ እንጂ በሌላ ማንነት የተሰጠው እንግዳ ክብር አይደለም። ጌታችን ኢየሱስ ራሱ፦ “እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ፤ አሁንም፥ አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ” ብሎ እንደ ተናገረ ቀደም ሲል የነበረውን እንጂ ያልነበረውን ክብር አልተቀበለም (ዮሐ. 17፡4-5)።
በአጠቃላይ ቅዱስ ጳውሎስ የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ምንም እንኳን በሰውነት እኵል ቢኾኑም (ፊልጵ. 2፡1-4)፣ አንዳቸው ካንዳቸው የተሻሉ እንደኾኑ እንዲቈጥሩ ክርስቶስን በአርኣያነት በማንሣት ያሳስባቸዋል፤ ክርስቶስ በእውነት ከእግዚአብሔር (አብ) ጋር እኵል ቢኾንም ሰው በመኾን ራሱን በማዋረድና በመስቀል ላይ በመሞት ለአባቱ ተገዢ ኾነ (2፥5-8)። ክርስቶስም በዚህ መንገድ ራሱን ስላዋረደ፤ እግዚአብሔር አብም ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው። ለኢየሱስም ይህንን ክብር መስጠት ለአብ የሚገባውን ክብርም አይቀንስም። ይልቁኑ ጳውሎስ በአጽንዖት አጥብቆ የሚናገረው፣ ኢየሱስን ከፍ ያለ ስም እንዳለው ስንመሰክርና ለጌትነቱ አምልኮትን ስናቀርብ “ለእግዚአብሔር አብ ክብር” (ፊል 2፥11ለ) መኾኑን ጽፎልናል። ክርስትና ለአብ የሚገባውን መለኮታዊ ክብር ሳይነፍግ፣ ክርስቶስን ማዕከል ያደረገ ሃይማኖት ነው የሚባለው በዚህ አግባብ ነው።
ማጣቀሻዎች
[1] በክርስቶስ አምላክነት ላይ ጤናማ ያልኾነ ምልከታ ያለው የዐዲስ ኪዳን ምሁር ጀምስ ደን እንኳን ይህንን ምንባብ አስመልክቶ እንዲህ ይላል “No one who knew their scriptures could fail to recognize the allusion to Isa. 45.23…. What is monotheistic passages in the whole Bible… At the very least we have to recognize that the Philippian hymn (2.6–11) envisaged acclamation and reverence before Christ which, according to Isaiah, God claimed for himself alone. On any count that is an astonishing transfer for any Jew to make or appropriate” Dunn, Theology of Paul the Apostle, ገጽ 251
[2] “Questions from Readers,” Watchtower, May 15, 1960, 319.
[3] ለምሳሌ ለዘብተኛው ምሁር ባርት ሄርማን Ehrman, How Jesus Became God, 262 – 66. እንዲሁም ሌላኛው ለዘብተኛ ጀምስ ደን መውሰድ ይቻላል Dunn, Jesus according to the New Testament, 133 ።
[4] Andrew Perry, “Philippians 2:5–11—Revisited,” unpub. paper, Academia.edu, n.d. (2019), [22].
[5] Paul A. Holloway, Philippians: A Commentary, ed. Adela Yarbro Collins, Hermeneia (Minneapolis: Fortress Press, 2017), 126
[6] Hellerman, Philippians, 119
[7] የሰባ ሊቃናት ትርጒም ማለት የዐዲስ ኪዳን ጸሓፊያን የብሉይ ኪዳን ምንባባትን ሲጠቅሱ በብዛት የሚጠቀሙት በ250 ዓ.ዓ አካባቢ የተዘጋጀ የብሉይ ኪዳን የጽርእ መጽሐፍ ቅዱስ ነው።
[8] Dixon, “An Arian View: Jesus, the Life-Given Son of God,” in Son of God: Three Views, by Irons, Dixon, and Smith, 81
ተጓዳኝ መጣጥፍ፦ ሰው የኾነው አምላክ – የክርስቶስ መለኮትነትና ቅድመ ህልውና በፊልጵስዩስ 2፥5-11