የተሳሳተ መለኮታዊ መገለጥ?
ሙሐመድ የቀረበለትን የነቢይነት መፈተሻ ደጋግሞ እንዴት እንደወደቀ
በጆከን ካዝ
ትርጉም፦ ወንድም ዳንኤል
ቁርአን ሙሐመድ ከአንዳንድ አይሁዶች ጋር ስላደረገው ግንኙነትና እነርሱም ሙሐመድንና መልእክቱን ለመቃወም ስለተጠቀሙባቸው ሙግቶች ይናገራል። ሱራ 3:183 እንዲህ ይላል፦
“እነዚያ ለማንኛውም መልክተኛ እሳት የምትበላው የኾነን ቁርባን እስከሚያመጣልን ድረስ ላናምን አላህ ወደኛ አዟል ያሉ ናቸው መልክተኞች ከኔ በፊት በታምራትና በዚያም ባላችሁት (ቁርባን) በእርግጥ መጥተውላችኋል እውነተኞች ከኾናችሁ ታዲያ ለምን ገደላችኋቸው? በላቸው፡፡”
ይህ ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳትና ለምን ስህተት እንደሆነ ለማየት ሊተነተን የሚገባው ምስጢራዊ አባባል ነው።
በግልጽ እንደሚታየው፣ ይህ እሳት መሥዋዕትን (ወይም ሌላ ነገርን) ለማቃጠል በሰዎች የሚቀጣጠል ተራ እሳት ሳይሆን ተአምራዊ እሳት ነው። ይህ መልክተኛ እውነተኛ ነቢይ መሆኑን የሚያረጋግጥ ከአምላክ የሚሰጥ ምልክት እንደሆነ ተደርጎ ይወሰዳል፤ ይህም ማለት ይህ አንቀጽ የሚያመለክተው “ከሰማይ የሚወርድ እሳትን” ነው። መሥዋዕቱን እንዲበላ እሳቱን የሚልከው አምላክ ራሱ ነው። ይህ ግንዛቤ በብዙ የሙስሊም ትርጉም ሥራዎች ውስጥ ተንጸባርቋል። ለምሳሌ ያህል፦
Amhad Khan
Those who say, “Allah has agreed with us that we should not believe in any Noble Messenger until he comes with the command to offer a sacrifice, which a fire (from heaven) shall devour”
Hilali & Khan
Those (Jews) who said: “Verily, Allah has taken our promise not to believe in any Messenger unless he brings to us an offering which the fire (from heaven) shall devour.”
Pickthall
(The same are) those who say: Lo! Allah hath charged us that we believe not in any messenger until he bring us an offering which fire (from heaven) shall devour.
Sahih Intl
[They are] those who said, “Indeed, Allah has taken our promise not to believe any messenger until he brings us an offering which fire [from heaven] will consume.”
Yusuf Ali
They (also) said: “Allah took our promise not to believe in an messenger unless He showed us a sacrifice consumed by Fire (From heaven).”
ሁሉም ሙስሊም ሙፈሲሮች ጥቅሱን የሚያብራሩት ይህ እሳት ከሰማይ የሚወርድ ነው በሚል ነው። ተፍሲራቱን እዚህ ገጽ ላይ ማግኘት ይቻላል፦ https://quranx.com/Tafsirs/3.183
ሙሐመድ ስለ እነማን ነው የሚናገረው? ከሰማይ እሳትን አውርዶ መሥዋዕት እንዲበላ ካደረገ በኋላ የተገደለ መልክተኛ ማን ነው? የዚህ አንቀጽ አውድ እንደሚያሳየው ይህ ሙሐመድ ከአንዳንድ አይሁዶች ጋር ያደረገውን ክርክር የሚያመለክት ነው። ስለዚህ፣ ለዚህ ውይይት ዋቢ መሆን ያለባቸው የአይሁድ ቅዱሳት መጻሕፍት (የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት) ናቸው።
መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነታዎች፦ እግዚአብሔር በእስራኤል ነቢይ፣ መስፍን ወይም ንጉሥ የተዘጋጀን መሥዋዕት እንዲበላ እሳት የላከባቸው በርካታ አጋጣሚዎች መኖራቸው እውነት ነው (ዘሌዋውያን 9:23-24፣ መሳፍንት 6:20-22፣ 1 ዜና መዋዕል 21:26፣ 2 ዜና መዋዕል 7:1-3፣ 1 ነገሥት 18)። በተጨማሪም፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሐሰተኛ ነቢያት ይናገራል፤ ለእስራኤል ልጆችም እውነተኛ ነቢያትን ከሐሰተኞች የሚለዩባቸውን በርካታ መመዘኛዎች ሰጥቷል። በአንድ ወቅት ከሰማይ የወረደ እሳት መሥዋዕትን መብላቱ፣ የነቢዩ ኤልያስ መለኮታዊ ሥልጣን በሐሰተኛው አምላክ በበኣል ነቢያት ላይ ማረጋገጫ ሆኖ ማገልገሉም ትክክል ነው (1 ነገሥት 18)።
ሆኖም ግን፣ “ከሰማይ መሥዋዕት የሚበላን እሳት ማውረድ” ነቢይ ነኝ ከሚል ሁሉ እንዲጠይቁት እንደ አጠቃላይ መመዘኛ ወይም መለያ ምልክት ተደርጎ ለእስራኤላውያን አልተሰጠም። እንዲህ ዓይነት ትዕዛዝ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም። እንዲህ ያለ “ቃል ኪዳን” የለም። ከዚህም በላይ፣ በእግዚአብሔር የተላኩት አብዛኞቹ እውነተኛ ነቢያት ይህንን ልዩ ተአምር አላሳዩም።
ስለዚህ መጠየቅ ያለብን ጥያቄ፦ ማን ነው የዋሸው? የሚል ነው።
“ለማንኛውም መልክተኛ እሳት የምትበላው የኾነን ቁርባን እስከሚያመጣልን ድረስ ላናምን አላህ ወደኛ አዟል” የሚለው አባባል ወይ የእነዚህ አይሁዶች ውሸት ነው፣ ወይም የቁርአኑ ደራሲ/ሙሐመድ አይሁዶች እንዲህ ያለ ጥያቄ ባያነሱም እንኳ ይህን የተሳሳተ አባባል በንግግራቸው ውስጥ በመክተት ዋሽቷል።
ሃቁ ሁለተኛው ከሆነ፣ ማለትም ሙሐመድ ይህንን የሐሰት መከራከሪያ ፈጥሮ በአይሁዶች አፍ ውስጥ ካስቀመጠው፣ እርሱ ውሸታም ነውና ለነቢይነት ብቁ አይደለም። የቁርአኑ ደራሲ ስለ አይሁዶች (ወይም ስለ ሌላ ማንኛውም አካል) አሉባልታዎችን የሚፈጥር ከሆነ፣ ቁርአኑ ርካሽ የቃላት ጦርነት (polemics) መሆኑ ይጋለጣል፤ እውነተኛ ከሆነውም አምላክ ዘንድ የመጣ ሊሆን አይችልም።
እውነቱ የመጀመሪያው ከሆነ ደግሞ፣ ሙሐመድ የእነዚህ አይሁዶች ጥያቄ ስህተት መሆኑን በማጋለጥ በእርግጥም በመለኮት የሚመራ ሰው መሆኑን ለማሳየት ፍጹም አጋጣሚ ነበረው። በቀላሉ እንዲህ ማለት ይችል ነበር፦ “እየዋሻችሁ እንደሆነ አምላክ ነግሮኛል። በቅዱሳት መጻሕፍቶቻችሁ ውስጥ ይህ የታዘዘበትን ቦታ አሳዩኝ!”። ሊያሳዩት አይችሉም ነበር። ተቃዋሚዎቹ መልስ ስለማይኖራቸው ዝም ይሉ ነበር፣ ሙሐመድም ተዓማኒነትን ያገኝ ነበር።
የሙሐመድ አጣብቂኝ፦ ሙሐመድ ምንም ዓይነት ተአምር ማድረግ ባለመቻሉ ብዙ ጊዜ ይቸገር ነበር። ቀደምቶቹን ነቢያት ከላከው አምላክ የተላከ ነቢይ እንደሆነ ይናገራል። በአንድ በኩል፣ በእነዚያ ቀደምት ነቢያት የተደረጉ ብዙ የተአምራት ታሪኮችን በራሱ መልእክት ውስጥ አካቷል፤ በሌላ በኩል ደግሞ፣ የእርሱን መለኮታዊ ሥልጣን የሚያረጋግጥ ምንም ዓይነት ተአምር ሳያሳይ እንደነርሱ ያለ ነቢይ አድርገው እንዲቀበሉት ሕዝቡን ይጠይቃል።
በሱራ 3:183 ውስጥ፣ ሙሐመድ የተአምር እጦቱን ለማድበስበስ የተጠቀመው የመከላከያ ስልት፦ “እናንተ የጠየቃችሁትን ተአምር ጨምሮ የተለያዩ ተአምራትን ይዘውላችሁ የመጡትን ቀደምት ነቢያት የገደላችሁ ስትሆኑ፣ አሁን ለምን ተአምር ትጠይቃላችሁ?” የሚል ነበር።
ዋናው ስህተት፦ ሙሐመድ ለጥያቄያቸው በሰጠው ምላሽ ውስጥ ሦስት ነገሮችን እንደ እውነታ አቅርቧል፦
- መልክተኞች ግልጽ ተአምራትን ይዘው መጥተዋል።
- ቢያንስ አንዳንዶቹ “ከሰማይ በወረደ እሳት የሚበላ መሥዋዕት” የተሰኘውን ልዩ ምልክት ይዘው መጥተዋል።
- አይሁዶች እነዚያን መልክተኞች ገደለዋቸዋል።
እዚህ ጋር ነው ትልቁ ስህተት የሚገኘው፦ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው፣ ይህንን “የእሳት” ምልክት ያሳዩት ነቢያት (እንደ ሙሴ፣ አሮን፣ ጌዴዎን፣ ዳዊት፣ ሰሎሞን እና ኤልያስ) መካከል አንድም እንኳ በአይሁዶች የተገደለ የለም። በተለይም ይህ ተአምር ለሕዝብ ማረጋገጫ እንዲሆን የተሰጠው ለኤልያስ ብቻ ሲሆን፣ እርሱ ደግሞ ሳይሞት ወደ ሰማይ እንደተወሰደ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።
ስለዚህ፣ የቁርአኑ ደራሲ ተሳስቷል። አምላክ ይህንን እንደሚያውቅ ጥርጥር የለውም። ነገር ግን ሙሐመድ የመጽሐፍ ቅዱስን ዝርዝር ጉዳዮችን ባለማወቁ ታሪኮቹን ሊያደበላልቃቸው ችሏል። ይህ ስህተት ሙሐመድ ራሱ የቁርአን ደራሲ ለመሆኑና ንግግሩም ከአምላክ እንዳልሆነ ጠንካራ ማስረጃ ነው።
የትርጉም ምንጭ ከማሻሻያ ጋር፦ Divinely Inspired Ignorance? How Muhammad failed the “test of a prophet” again and again
