እውን ወልድ የሚመጣበትን ቀን አያውቅምን?

እውን ወልድ የሚመጣበትን ቀን አያውቅምን?


በክርስቶስ አምላክነትና ከባሕርይ አባቱ ጋር ባለው እኩልነት ላይ ተቃውሞ የሚያነሱ ወገኖች በተደጋጋሚ የሚጠቅሱት ተከታዩን ኃይለ ቃል ነው፦

“ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም።” (ማቴዎስ 24:36፣ ማርቆስ 13:32)

ተቃዋሚዎች ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ላይ ስለሚመጣው የፍርድ ቀንና ሰዓት እንደማያውቅ አድርጎ ራሱን መቁጠሩ ከአብ ጋር እኩል አለመሆኑን ያሳያል በማለት ይከራከራሉ። ሆኖም ይህ ጥቅስ በጥልቀትና በቅዱሳት መጻሕፍት ትስስር ሲመረመር ተቃውሞው መሠረተ ቢስ መሆኑን እንረዳለን።

    1. ማወቅ” (Eido) ማለት ምን ማለት ነው?

ክርስቲያን ምሁራን ለዚህ ጥቅስ ከሚሰጧቸው ማብራሪያዎች መካከል አንዱ በግሪክ ቋንቋ “ማወቅ” (eido) የተሰኘው ቃል “ማስታወቅ” ወይም “ማወጅ” (to make known / declare) የሚል ትርጉም ሊኖረው እንደሚችል ማሳየት ነው። በዚህ መሠረት ጥቅሱ፦ ስለዚያች ቀንና ሰዓት ግን ከአብ በቀር ማንም ሊያስታውቅ (ሊያውጅ) አይችልም፤ የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። ታዋቂው የስትሮንግ ኮንኮርዳንስ ይህንን ቃል በተለያዩ መንገዶች የሚተረጉም ሲሆን ማሳወቅ የሚለው ከትርጉሞቹ መካከል አንዱ ነው።

eidó: To see, to know, to perceive, to be aware

Original Word: εἴδω
Part of Speech: Verb
Transliteration: eidó
Pronunciation: ay’-do
Phonetic Spelling: (i’-do)
KJV: be aware, behold, X can (+ not tell), consider, (have) know(-ledge), look (on), perceive, see, be sure, tell, understand, wish, wot
https://biblehub.com/strongs/greek/1492.htm

ከላይ የተቀመጠውን ስንተረጉመው፦

eidó (ኤይዶ)ማየት፣ ማወቅ፣ መረዳት፣ መገንዘብ

ዋናው የግሪክ ቃል: εἴδω

ንግግር ክፍል: ግሥ 

አጻጻፍ /በአማርኛ/: ኤይዶ

አነባበብ: ኤይ-ዶ

ሥነ ልሳን አጻጻፍ: ኤ-ይ-ዶ

በኪንግ ጄምስ ትርጉም ውስጥ የተፈታበት መንገድ: መገንዘብ፣ መመልከት፣ መንገር (+ መቻል/አለመቻል)፣ ማስተዋል/ማሰብ፣ ዕውቀት/ማወቅ (መኖር)፣ ማየት/መመልከት፣ መረዳት፣ ማየት፣ እርግጠኛ መሆን፣ መንገር፣ ማስተዋል፣ መመኘት፣ ማወቅ።

ከቃሉ ትርጉሞች መካከል መንገር መቻል ወይም አለመቻል እንዲሁም መንገር የሚሉት መኖራቸውን ልብ በሉ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ይህንኑ ቃል በመጠቀም ከክርስቶስ ስቅለት ውጪ ሌላ ነገር ለሰዎች ላለመናገር መወሰኑን ይገልጻል፦

“በመካከላችሁ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደተሰቀለ ሌላ ነገር እንዳላውቅ ቆርጬ ነበርና።” 1ቆሮ. 2:2

እዚህ ላይ ሐዋርያው “አንዳላውቅ” ሲል ስለ ሌሎች ነገሮች ፍጹም ዕውቀት እንደሌለው መናገሩ ሳይሆን ለቆሮንቶስ ምዕመናን ከክርስቶስ ስቅለት ውጪ ሌላ ነገር ላለመናገርና ላለማወጅ መወሰኑን ለማሳየት ነው። በተመሳሳይ መንገድ ጌታችን በወንጌል “ልጅም ቢሆን አያውቅም” ማለቱ የዕውቀት ማነስን ሳይሆን ያችን ሰዓት ለሰዎች የመናገርና የማወጅ ድርሻ የአብ መሆኑን ለመግለጥ የተጠቀመበት ዘይቤ መሆኑን ይህ የጳውሎስ አገላለጽ ፍንጭ ይሰጠናል።

ይህንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አጠቃቀም በዕለት ተዕለት ሕይወታችን በምሳሌ መረዳት ይቻላል። ለምሳሌ፦ ወደ አንድ መሥሪያ ቤት ሄዳችሁ አንድን የሥራ ኃላፊ ስለ አንድ ጉዳይ ብትጠይቁትና እርሱም፦ እኔ ስለዚህ ጉዳይ አላውቅም፤ ዋናውን ሥራ አስኪያጅ ጠይቁ’ ቢላችሁ ያ ሰው የግዴታ ስለ ጉዳዩ ምንም ዓይነት የአእምሮ ዕውቀት የለውም ማለት ነውን? በፍጹም። ይልቁኑ ያንን መረጃ የመግለጥና የማሳወቅ ሕጋዊ ሥልጣን (Prerogative) የሥራ አስኪያጁ ብቻ መሆኑን ለመናገር የተጠቀመበት የአሠራር ሥነ-ሥርዓት መግለጫ ሊሆን ይችላል። ጌታችንም ‘ልጅም ቢሆን አያውቅም’ ሲል ያችን ሰዓት የማወጅ ድርሻ (function) የአብ መሆኑን ለማሳየት የተጠቀመው አነጋገር ነው። በዕለት ተዕለት ኑሯችን ለሰዎች ማሳወቅ የማንፈልጋቸውን ነገሮች ስንጠየቅ “አላውቅም” ብለን እንመልሳለን። ይህ ውሸት ሳይሆን የተለመደ ዘይቤያዊ ንግግር ነው። ይህ ማብራርያ በዘመናችን የመጣ አዲስ ሐሳብ ሳይሆን ቅዱስ አውግስጢኖስን የመሳሰሉት ታላላቅ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ሲያብራሩበት የነበረ መንገድ ነው። ቅዱስ አውግስጢኖስ መሠረት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ 24:36 ላይ “ልጅም ቢሆን አያውቅም” ማለቱ የአምላካዊ ዕውቀት ማነስን የሚያሳይ ሳይሆን፣ “እንዳያውቁ ማድረግ” ወይም “ላለመግለጥ መምረጥ” የሚለውን በመጽሐፍ ቅዱስና በዕለት ተዕለት ሕይወት የተለመደውን ዘይቤያዊ አነጋገር መሠረት ያደረገ ነው። ታላቁ የቤተ ክርስቲያን አባት ይህንን ጥልቅ የነገረ መለኮት ምሥጢር እንዲህ በማለት ጠቅለል አድርጎ ያብራራዋል፦

  • የመምህርነት አገልግሎት ድርሻ፦ ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣው እኛን ሊያስተምረን ነው፤ ነገር ግን እርሱ የሚያውቀውን ሁሉ እኛ ማወቃችን አይጠቅመንም። እንደ እውነተኛ መምህርነቱ ለእኛ ማወቁ የሚበጀንን ነገር አስተምሮናል፤ ማወቁ ለማይጠቅመንና ጊዜው ላልደረሰ ነገር ግን “እንዳናውቅ” አድርጎናል። ስለዚህ ወልድ ሊያስተምረን ያልመረጠውን (ያልፈቀደውን) ነገር “አያውቅም” መባሉ እርሱ እኛ እንዳናውቅ ካደረገበት አገላለጽ አኳያ ነው።

  • መጽሐፍ ቅዱሳዊው የንግግር ዘይቤ፦ ይህ ዓይነቱ አነጋገር በቅዱሳት መጻሕፍት የተለመደ ነው። ለምሳሌ እግዚአብሔር ለአብርሃም “አሁን እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደ ሆንህ አውቄአለሁ” (ዘፍ. 22:12) ሲለው እግዚአብሔር አስቀድሞ ስላላወቀ ሳይሆን አብርሃም ራሱንና እምነቱን በተግባር እንዲያውቅ ስላደረገው ነው። በተመሳሳይ፣ መጽሐፍ ቅዱስ “አምላካችሁ እግዚአብሔር ያውቅ ዘንድ ይፈትናችኋል” (ዘዳ. 13:3) ሲል “እንድታውቁ ያደርጋችኋል” ማለት እንደሆነ ሁሉ ክርስቶስም ቀኑን አያውቅም የተባለው ምሥጢሩን ለደቀ መዛሙርቱ ሳይገልጥ በመሰወሩ (እንዳያውቁ ስላደረጋቸው) ነው።

  • የአብና የወልድ የባሕርይ አንድነት፦ አብና ወልድ በዕውቀትም ሆነ በፈቃድ ፍጹም አንድ ናቸው፤ በመካከላቸው ምንም ዓይነት መበላለጥ የለም። ጌታችን ራሱ “የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው፥ የአንተም የእኔ ነው” (ዮሐ. 17:10) ብሏል። ወልድ የአብ ጥበቡና ቃሉ በመሆኑ አብ የሚያውቀውና ወልድ የማያውቀው ምንም ነገር ሊኖር አይችልም። ነገር ግን የበባሪያን መልክ በመያዝ የመጣው ክርስቶስ  ለሰሚዎቹ የሚበጀውን ብቻ በየወቅቱ ይገልጽ ነበር። ያንን ምሥጢር ለመሸከም ብቁ ባልነበሩት ደቀ መዛሙርቱ መካከል በነበረበት ጊዜ ላለመናገር ያህል “አላውቅም” አለ። ይህ በትክክል በዕለት ተዕለት ንግግር ውስጥ እንደምንጠቀምባቸው ፈሊጣዊ አገላለጾች (Metaphors) ያለ በመሆኑ ውሸት ሊባል አይችልም። (ቅዱስ አውግስጢኖስ፣ ደብዳቤዎች — ወደ ኦሺያነስ (St. Augustine of Hippo, Letters — To Oceanus, Letter 180) 1 2 3 4 )

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሁለተኛው ምጽአቱ የተናገረውን ቃል ይበልጥ ግልጽ አድርጎ የሚያሳየው ሌላው ወሳኝ መንገድ የጥንቱ የአይሁድ የሰርግ ሥነ-ሥርዓት ባሕል ነው። ጌታችን በወንጌላት ላይ የእርሱንና የቤተ ክርስቲያንን ግንኙነት በሙሽራና በሙሽሪት ምሳሌ መግለጹ እንዲሁም ዳግም ምጽአቱን በሙሽራ መምጣትና በሠርግ ድግስ መመሰሉ ይታወቃል። በጥንቱ አይሁድ ባሕል ደግሞ አንድ ሙሽራ ሊያገባ ሲታጭ የሠርጉ ቀን መቼ እንደሚሆን የመወሰን ሙሉ ሥልጣንና ድርሻ የሙሽራው አባት ብቻ ነበር።

ሥነ-ሥርዓቱ በሚከተለው መልክ ይፈጸም ነበር፦

  • የመኖሪያ ዝግጅት፦ ሙሽራውና ሙሽሪት ከታጩ በኋላ ሙሽራው ወደ አባቱ ቤት ተመልሶ ለሙሽሪት የሚሆን መኖሪያ ስፍራ (ክፍል) ማዘጋጀት ይጀምራል። (ጌታችንም፦ በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ… ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና” ማለቱን ያስታውሏል – ዮሐ. 14:2)።
  • አባት ፈቃድ የሚደረግ ማስታወቂያ፦ ሙሽራው ዝግጅቱን ቢጨርስ እንኳ፣ “ሰርጉ መቼ ነው? ሙሽሪትን ለመውሰድ መቼ ልሂድ?” የሚለውን ቀን በራሱ ፈቃድ አይወስንም። የአባቱን ቤት ዝግጅት አይቶ ሁሉ ነገር መጠናቀቁን አረጋግጦ “አሁን ሂድና ሙሽራህን አምጣት!” ብሎ ቀኑንና ሰዓቱን የሚያውጀው የሙሽራው አባት ብቻ ነው። ስለዚህ በዚህ የዝግጅት ወቅት አንድ ሰው ሙሽራውን “ሰርጉ መቼ ነው?” ብሎ ቢጠይቀው ሙሽራው ለአባቱ ሉዓላዊ ሥልጣን ያለውን ክብር ለመግለጽ ሲል፦ “እኔ አላውቅም፣ አባቴን ጠይቁ” ይላል። ይህ ማለት ግን ሙሽራው ሰርግ እንዳለው አያውቅም ወይም ስለ ሠርጉ ምንም መረጃ የለውም ማለት ሳይሆን ቀኑን የማወጅ ድርሻና ሥልጣን የአባቱ ብቻ መሆኑን የሚገልጽበት ባሕላዊ የክብር አነጋገር ነው።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም “ስለዚያች ቀንና ሰዓት ከአባት ብቻ በቀር ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም” ሲል አይሁዳውያን ሰሚዎቹ ወዲያውኑ ከሚረዱት ከዚህ የሠርግ ሥርዓት ባሕል አኳያ ነው። እርሱ የሠርጉ ሙሽራ ቢሆንም ያችን የፍርድና ቤተክርስቲያንን የሚወስድበት የሠርግ ሰዓት የማወጅ መለኮታዊ ቀጠሮና ድርሻ የአብ መሆኑን ለማሳየት የተጠቀመበት ጥልቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዘይቤ ነው። ስለዚህ ጥቅሱ የክርስቶስን አምላካዊ ዕውቀት የሚያሳንስ ሳይሆን በመለኮታዊ አካላት (በአብና በወልድ) መካከል ያለውን የአባትና የልጅ አንድነት የሚገልጽ ነው።

እዚህ ላይ ልንጠነቀቅበት የሚገባው ትልቅ ምሥጢር አለ፦ ይህ አገላለጽ አብና ወልድ ‘ሁለት የተለያየ ዕውቀት’ ወይም ‘ሁለት የተለያዩ ፈቃዶች’ አሏቸው ማለት አይደለም። አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ በባሕርይ፣ በዕውቀት፣ በፈቃድና በሥልጣን ፍጹም አንድ ናቸው። ወልድ የአብ ጥበቡና ቃሉ በመሆኑ አብ የሚያውቀውን ሁሉ ወልድም ያውቃል። ነገር ግን ቀኑንና ሰዓቱን ለፍጥረት ይፋ የማድረግ ድርሻ የአብ ነው። ልክ በአይሁድ ሠርግ ሙሽራውና አባቱ በአንድ ቤት ውስጥ እየኖሩና ሁሉን ነገር እኩል እያወቁ ቀኑን የመወሰንና የማወጅ ሥልጣን ለአባት ብቻ እንደሚተወው ሁሉ፤ በሥላሴም መለኮታዊ አሠራር (Economy of the Trinity) ያችን ሰዓት የማሳወቅ ተግባር የአብ ሉዓላዊ ድርሻ ነው። ስለዚህ ‘ልጅ አያውቅም’ ሲባል ዕውቀት ጎድሎት ሳይሆን ያንን ሰዓት የመግለጥ ሥልጣን (Prerogative) የአብ ድርሻ ስለሆነ ነው። ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ የተጻፈ ነው፦

“ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስኪገለጥ ድረስ ያለ እድፍና ያለ ነቀፋ ሆነህ ትእዛዙን ጠብቅ፤ ንም መገለጡን በራሱ ጊዜ ብፁዕና ብቻውን የሆነ ገዥ፥ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ፥ ያሳያል” (1ጢሞቴዎች 6፡14-15)

ለተቃውሞ ምላሽ

አንዳንድ ሙስሊሞችና የሥላሴ ተቃዋሚዎች ይህንን አተረጓጎም ለመቃወም የዮሐንስ ራዕይን ጥቅስ ይጠቅሳሉ፦

“በምድርም ለሚኖሩ ለሕዝብም ለነገድም ለቋንቋም ለወገንም ሁሉ ይሰብክ ዘንድ የዘላለም ወንጌል ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ መካከል ሲበር አየሁ፤ በታላቅ ድምፅም። የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት፤ ሰማይንና ምድርንም ባሕርንም የውኃንም ምንጮች ለሠራው ስገዱለት አለ።” (ራዕይ 14:6-7)

እነዚህ ወገኖች “መልአኩ የፍርዱን ሰዓት ካወጀ በማርቆስ ላይ ‘መላእክት አያውጁም’ የሚለው ትርጓሜ መጽሐፍ ቅዱስን እርስ በርሱ ያጋጫል” ይላሉ። ሆኖም ይህ ክርክር ክርስቲያናዊውን አስተምህሮ ካለመረዳት የመነጨ ነው።የክርስቲያን አቋም መላእክት ያንን ቀንና ሰዓት በፍጹም ሊያውጁ አይችሉም የሚል አይደለም። ይልቁኑ ያንን መረጃ የመግለጥና የማሳወቅ ሉዓላዊ መብት (prerogative) የአብ ብቻ መሆኑን ማሳየት ነው። አብ ያንን መረጃ ለመግለጥ በሚወስንበት ጊዜ እርሱ ራሱ ከሰማይ ወርዶ በቀጥታ ይናገራል ማለት ሳይሆን በእርሱ በተላኩ መልእክተኞች በኩል ይገልጠዋል።

እዚህ ላይ አንድ ሰው፦ ጌታ እንደ ሌባ በድንገት ይመጣል ከተባለ፣ ሰዓቱ በመልአክ ይታወጃል ማለት የጌታን አንዳች ሳይታወቅ ድንገት መምጣት አይቃረንምን?” የሚል ጥያቄ ሊያነሳ ይችላል። ሆኖም ግን ጥቅሶቹን ስንመረምር መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቀኑ ‘መታወጅ’ እና ‘እንደ ሌባ ስለ መምጣቱ’ የሚናገረው በተለያየ አውድ መሆኑን እንረዳለን። የጌታ መምጣት “እንደ ሌባ” የተባለው ሳይዘጋጁ ለቀሩት፣ በምድር ፍቅርና በኃጢአት እንቅልፍ ለደነዘዙት ዓለማውያን ወገኖች እንጂ በንቃትና በጸሎት ለሚጠባበቁት ለቅዱሳኑ አይደለም። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ልዩነት ግልጽ አድርጎታል፦

“የጌታ ቀን፥ ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ፥ እንዲሁ ይመጣ ዘንድ ራሳችሁ አጥብቃችሁ አውቃችኋልና። ሰላምና ደኅንነት ነው ሲሉ ያን ጊዜ ምጥ እርጕዝን እንደሚይዛት ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል ከቶም አያመልጡም። እናንተ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ቀኑ እንደ ሌባ ይደርስባችሁ ዘንድ በጨለማ አይደላችሁም፥ ሁላችሁ የብርሃን ልጆች የቀንም ልጆች ናችሁና። እኛ ከሌሊት ወይም ከጨለማ አይደለንም።” (1ተሰሎንቄ 5:2-5)

በተጨማሪም፣ የፍርዱ ሰዓት መቃረቡ ፍጹም በሚስጥር የሚጠበቅና ያለ ምንም ማስታወቂያ ድንገት የሚሆን አይደለም። ይልቁኑ መጽሐፍ ቅዱስ ቀኑ ሲመጣ በታላቅ ድምፅና በመለከት አዋጅ እንደሚሆን በግልጽ ያስተምራል፦

1 ተሰሎንቄ 4:16፦ “ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፥ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ”

ማቴዎስ 24:31 “መላእክቱንም ከታላቅ መለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል…”

ስለዚህ አብ የወሰነው የፍርድ ሰዓት በደረሰ ጊዜ መለኮታዊው ትእዛዝ በመላእክት በኩል ታውጆና የመለከት ድምፅ ተነፍቶ ፍርዱ ይፈጸማል። ይህ አዋጅ መኖሩ ለአማኞች የመንቃትና የመዘጋጀት ምልክት ነው። በራእይ 14:6-7 ላይ መልአኩ “የፍርዱ ሰዓት ደርሷልና እግዚአብሔርን ፍሩ” ብሎ ማወጁ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጋጭ ሳይሆን አብ የወሰነውንና የሰወረውን ሰዓት ልክ ጊዜው ሲደርስ በመልእክተኞቹ በኩል ይፋ ማድረጉን የሚያሳይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ነው።

    1. መልአኩ ሰዓቱን ያወጀው ከመለኮት በተገለጠለት መሠረት ነው

መላእክት እግዚአብሔር የገለጠላቸውንና እንዲያደርጉ የፈቀደላቸውን ብቻ እንደሚያውጁና እንደሚያደርጉ ግልጽ ነው፦

ራዕይ 16:1-5፦ ሰባቱ መላእክት የእግዚአብሔርን ቁጣ በምድር ላይ የሚያፈሱት ከመቅደሱ “ሂዱ” የሚል ታላቅ ድምፅ ሲሰሙ ብቻ ነው።

መዝሙር 103:20፦ “ቃሉን የምትፈጽሙ፥ ብርቱዎችና ኃያላን፥ የቃሉንም ድምፅ የምትሰሙ መላእክቱ ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ባርኩ። ሠራዊቱ ሁሉ፥ ፈቃዱን የምታደርጉ አገልጋዮቹ፥ እግዚአብሔርን ባርኩ።”

    1. በራዕይ መጽሐፍ መሠረት ኢየሱስ የመለኮታዊ መገለጥ ምንጭ ነው

በዮሐንስ ራእይ መጀመሪያና መጨረሻ ላይ እንደተገለጸው ኢየሱስ መለኮታዊውን መግለጥ ለመልአኩ የሰጠውና መልአኩን የላከው እርሱ ራሱ እንደሆነ ተገልጧል፦

“ቶሎ ይሆን ዘንድ የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ ያሳይ ዘንድ እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው በእርሱም የተገለጠው ይህ ነው፥ ኢየሱስም በመልአኩ ልኮ ለባሪያው ለዮሐንስ አመለከተ፥” (ራዕይ 1:1)

በተጨማሪም በራዕይ 22:6 እና 16 ላይ መልአኩ የእግዚአብሔርም የኢየሱስም መልአክ ተብሎ ተጠርቷል፦ “እኔ ኢየሱስ በአብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ይህን እንዲመሰክርላችሁ መልአኬን ላክሁ። እኔ የዳዊት ሥርና ዘር ነኝ፥ የሚያበራም የንጋት ኮከብ ነኝ። ይህ የሚያሳየው ኢየሱስ ከመላእክት በላይ የሆነ መለኮታዊ ሥልጣን ያለው አምላክ መሆኑን ነው።

መልአኩ ለዮሐንስ “ለእኔ አትስገድ፣ እኔ ከአንተ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ” ሲል (ራዕይ 22:9)፣ በተቃራኒው ፍጥረት ሁሉ ግን ለእግዚአብሔርና ለበጉ (ለክርስቶስ) እኩል ሲሰግዱና ሲያመልኩ እናያለን፦

“በታላቅም ድምፅ። የታረደው በግ ኃይልና ባለ ጠግነት ጥበብም ብርታትም ክብርም ምስጋናም በረከትም ሊቀበል ይገባዋል አሉ። በሰማይና በምድርም ከምድርም በታች በባሕርም ላይ ያለ ፍጥረት ሁሉ በእነርሱም ውስጥ ያለ ሁሉ። በረከትና ክብር ምስጋናም ኃይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው፥ ለበጉም ይሁን ሲሉ ሰማሁ።” (ራዕይ 5:13፣ 7:9-17)

ኢየሱስ ከፍጡራን ሁሉ ተለይቶ መመለኩና ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ቅዱሳን በደሙ ማንጻቱ እርሱ ፍጡር ሳይሆን ከአብ ጋር በክብር፣ በኃይልና በሥልጣን እኩል የሆነ መለኮታዊ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ያረጋግጣል።

    1. በራዕይ መጽሐፍ መሠረት ኢየሱስ የፍጥረት ሁሉ ንጉሥና የመላእክት ጌታ ነው

ክርስቶስ በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር (ያህዌ) ራሱን በገለጠበት ፍጹም መለኮታዊ ማዕረግ ተገልጧል፦

  • ፊተኛውና መጨረሻው፦ በኢሳይያስ 44:6 ላይ እግዚአብሔር “እኔ ፊተኛ ነኝ እኔም ኋለኛ ነኝ” ሲል፣ በራዕይ 1:17-18 ላይ ኢየሱስ “ፊተኛውና መጨረሻው፥ ሕያውም እኔ ነኝ” ይላል።
  • የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ፦ በዘዳግም 10:17 ላይ እግዚአብሔር “የአማልክት አምላክ የጌቶችም ጌታ” ተብሎ ሲጠራ፣ በራዕይ 17:14 እና 19:16 ላይ ደግሞ ክርስቶስ “የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ” ተብሏል።
  • የቁጣውን ወይን ጠጅ መጭመቂያ ብቻውን የረገጠ፦ በኢሳይያስ 63:1-6 ላይ እግዚአብሔር ብቻውን የቁጣውን መጭመቂያ እንደረገጠ ሲናገር፣ በራዕይ 19:15 ላይ ይህንን ያደረገው “የእግዚአብሔር ቃል” የተባለው ክርስቶስ እንደሆነ ተገልጧል።

ይህ ማስረጃ መላእክት ሁሉ ለኢየሱስ ክርስቶስ ተገዢዎችና ከእርሱ በታች የሆኑ ፍጡራን መሆናቸውን በግልጽ ያሳያል። ስለዚህ መልአኩ የሚያሳውቀው በአብና በወልድ ዕውቀት ያለውን ቀን ነው።

    1. በራዕይ መጽሐፍ መሠረት ኢየሱስ ሁሉን አዋቂና ሁሉን ቻይ ፈራጅ ነው

በመጨረሻም፣ ክርስቶስ የሰውን ልብና ኩላሊት የሚመረምር፣ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው የሚከፍል ፍጹም አምላክ ሆኖ ቀርቧል፦

“አብያተ ክርስቲያናትም ሁሉ ልብንና ኵላሊትን የምመረምር እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፥ ለእያንዳንዳችሁም እንደ ሥራችሁ እሰጣችኋለሁ።” (ራእይ 2:23፣ ራእይ 22:12)

ይህ ቃል በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ስለ ራሱ የተናገረው ፍጹም መለኮታዊ ባሕርይ ነው፦

“እኔ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፥ እንደ ሥራው ፍሬ እሰጥ ዘንድ ልብን እመረምራለሁ ኵላሊትንም እፈትናለሁ።” (ኤርምያስ 17:10፣ መዝሙር 62:12)

ማጠቃለያ

ሐዋርያው ዮሐንስ በራዕይ መጽሐፍ ላይ በግልጽ እንዳሳየው፣ ክርስቶስ ሥጋ የለበሰ የእግዚአብሔር ልጅ በመሆኑ ከፍጥረት ሁሉ በላይና ከአብ ጋር እኩል ነው። ስለዚህ “ልጅም ቢሆን አያውቅም” የሚለው ቃል ክርስቶስ አምላክ አለመሆኑን የሚያሳይ ሳይሆን፣ ያንን ቀንና ሰዓት የመግለጥ (የማወጅ) ድርሻ የአብ መሆኑን የሚያስረዳ ነው።


መሲሁ ኢየሱስ