ለቁርኣን አወቃቀር ዑሥማን ያበረከተው አስተዋጽዖ

ለቁርኣን አወቃቀር ዑሥማን ያበረከተው አስተዋጽዖ


ብዙ ሙስሊም ሊቃውንት ዛሬ በእጃችን የሚገኘው ቁርኣን አምላክ በመልአኩ ጂብሪል አማካይነት ለሙሐመድ ባወረደው መልኩ ያለ ምንም ጭማሪ፣ ቅናሽ ወይም የቅርጽ ልዩነት በትክክል  ተጠብቆ የኖረ እንደሆነ ይሞግታሉ። እንዲያውም ሙሐመድ በየዓመቱ ከጂብሪል ጋር ቁርኣንን ይከልስ እንደነበርና ከመሞቱ በፊት በነበረው ዓመት ሁለት ጊዜ አብረው በመከለስ ማጠናቀቃቸውን እንደ ማስረጃ ያቀርባሉ። የዚህ መከራከሪያ ዋና ዓላማ፦ «ቁርኣን የአምላክ ቃል ስለሆነ ፍጹም ተጠብቋል፤ ፍጹም ስለተጠበቀም የአምላክ ቃል ነው» የሚለውን ድምዳሜ ለማረጋገጥ ነው። ነገር ግን ይህ አባባል እውነት ከሆነ በታመኑ የእስልምና የሐዲሥ ስብስቦች ውስጥ የሚገኙ አያሌ ዘገባዎችን እንዴት ልንረዳቸው እንችላለን? ለምሳሌ «ሚሽካት አል-መሳቢህ» በተሰኘው የታወቀ የሐዲሥ መጽሐፍ ውስጥ የተመዘገበው የሚከተለው ዘገባ ጥያቄ ያስነሳል፦

 ابنُ عبَّاسٍ، قالَ: قلتُ لعُثمانَ بنِ عفَّانَ: ما حَمَلَكُم على أنْ عَمَدْتُم إلى الأنفالِ؛ وهي مِنَ المثاني ، وإلى {بَراءَةٌ}؛ وهي مِنَ المِئينَ، فقَرَنْتُم بيْنَهما، ولمْ تَكْتُبوا بيْنَهما سطْرَ بِسمِ اللهِ الرَّحمنِ الرَّحيمِ ، ووضَعْتُموها في السَّبعِ الطُّوالِ ، فما حمَلَكُم على ذلك؟ فقالَ عُثمانُ: كان رسولُ اللهِ صلَّى اللهُ عليه وسلَّمَ ممَّا يَأْتي عليه الزَّمانُ، وهو يَنزِلُ عليه مِنَ السُّورِ ذَواتِ العددِ. قالَ: وكان إذا نَزَلَ عليه الشَّيءُ دعا بعضَ مَنْ يَكتُبُ له، فيقولُ: «ضَعوا هؤلاء الآياتِ في السُّورةِ الَّتي يُذكرُ فيها كذا وكذا». فلمَّا نَزَلَتْ عليه الآيةُ فيقولُ: «ضَعوا هذه في السُّورةِ الَّتي يُذكرُ فيها كذا وكذا». وكانتِ الأنفالُ مِن أوائلِ ما نَزَلَتْ بالمدينةِ، وكانت {بَراءَةٌ} مِن آخرِ القرآنِ، وكانت قِصَّتُها شبيهةً بقِصَّتِها، فظننتُ أنَّها منها، فقُبِضَ رسولُ الله صلَّى اللهُ عليه وسلَّمَ، ولمْ يُبيِّنْ لنا أنَّها منها، فلمْ أكتُبْ بيْنَهما سطْرَ بِسمِ اللهِ الرَّحمنِ الرَّحيمِ ، فوضعتُها في السَّبعِ الطُّوَلِ.
خلاصة حكم المحدث : صحيح الإسناد

 

ኢብኑ ዐብባስ (ረ.ዐ) እንዲህ ብለዋል፦

«ዑሥማንን (ረ.ዐ) እንዲህ ስል ጠየቅኳቸው፦ ከ‘ል-መሣኒ’ (ከመቶ አንቀጾች ያነሱ ሱራዎች) አንዱ የሆነውን አል-አንፋልን እና መቶ ያህል አንቀጾች ያሏትን በራአትን (አት-ተውባህ) በመካከላቸው በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው’ የሚለውን ሳትጽፉ በማያያዝ ከሰባቱ ረጅሞች (አስ-ሰብዐ አጥ-ጢዋል) መካከል እንዲመደቡ ያደረጋችሁ ምንድን ነው?» ዑሥማንም (ረ.ዐ) እንዲህ ሲሉ መለሱልኝ፦ «በተለያዩ ጊዜያት በርካታ አንቀጾች ያሏቸው ሱራዎች ለአላህ መልእክተኛ (ሶ.ዐ.ወ) ይወርዱ ነበር። አንድ ነገር በተወረደላቸውም ጊዜ ከጸሐፊዎቻቸው አንዱን ጠርተው እነዚህን አንቀጾች እገሌ እና እገሌ በተጠቀሰበት ሱራ ውስጥ አስቀምጧቸው’ ይሉ ነበር። አንድ አንቀጽ ብቻ እንኳን ሲወርድ ይህን አንቀጽ እገሌ በሚወሳበት ሱራ ውስጥ አስቀምጡት’ ይሉ ነበር። ‘አል-አንፋል’ በመዲና ከተወረዱት የመጀመሪያዎቹ ሱራዎች አንዱ ሲሆን፣ ‘በራአት’ ደግሞ ከቁርኣን መጨረሻ ከተወረዱት መካከል ነበር። የሁለቱም ርዕሰ ጉዳይ እርስ በእርስ በጣም ይመሳሰል ስለነበር የዚያ አካል መሆኗን ጠረጠርን፤ የአላህ መልእክተኛም (ሶ.ዐ.ወ) የእርሱ አካል ይሁን አይሁን ሳይገልጹልን ከዚህ ዓለም ተለዩ። በዚህም ምክንያት በመካከላቸው በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው’ የሚለውን ሳልጽፍ አያያዝኳቸው፤ ከሰባቱ ረጅሞች ሱራዎች መካከልም እንዲመደቡ አደረግኳቸው።»

(አሕመድ፣ ቲርሚዚ እና አቡ ዳዉድ እንደዘገቡት፤  ቅጽ 1 ገጽ 470 ወይም አል-ቲርሚዚ 3086)

የአረብኛ ምንጭ፦ https://dorar.net/h/4azRpIpS?osoul=1

ከላይ ከተጠቀሰው ታሪካዊ ዘገባ የምንረዳቸው ቁልፍ ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፦

  • «አል-አንፋል» እና «በረኣት» በተለያዩ ጊዜያት የወረዱ (አንዱ ሂጅራ መጀመሪያ፣ ሌላው በመጨረሻው ዘመን) የተለያዩ ምዕራፎች ነበሩ።
  • ሁለቱን ምዕራፎች አያይዞ ማቀናጀት፣ በመካከላቸው የሚገኘውን «ቢስሚልላህ» መተው፣ እና ከረጅሞቹ ምዕራፎች ተራ መደደብ የነቢዩ ሙሐመድ መመሪያ ሳይሆን፣ ከነቢዩ ሞት ከብዙ ዓመታት በኋላ የተደረገ የዑሥማን ግላዊ ውሳኔ ነበር።
  • ይህ ውሳኔ በቁርኣን መዋቅርና ቅርጽ ላይ ግልጽ ተጽዕኖ አሳድሯል። ከዑሥማን ውሳኔ በፊት እነዚህ ሁለት ምዕራፎች እንዴት ይነበቡና ይዋቀሩ እንደነበር በእርግጠኝነት ማወቅ አይቻልም። እንዲያውም «ቢስሚልላህ» የሚለው መግቢያ በሱራ 9 መጀመሪያ ላይ በመጀመሪያው ነበረ ወይስ አልነበረም የሚለው የይዘት ጥያቄም ይነሳል።

ይህ የሐዲሥ ዘገባ የሚያሳየው ዛሬ በቁርኣን ውስጥ የምናየው የምዕራፎች አደረጃጀት ሙሉ በሙሉ በሙሐመድ ዘመን የተጠናቀቀ ሳይሆን ከእርሱ ህልፈት በኋላ በዑሥማን ውሳኔ የተፈጸመ መሆኑን ነው። ይህም «ቁርኣን ከተወረደበት ጊዜ ጀምሮ በቅርፁም ሆነ በአደረጃጀቱ ፍጹም ያልተለወጠ የአምላካዊ ንግግሮች ስብስብ ነው» የሚለውን መከራከሪያ ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል።


ቁርኣን