አብ በሥጋ ተገልጧልን? የ1ኛ ጢሞቴዎስ 3:16 መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንተና

አብ በሥጋ ተገልጧልን? 

የ1ኛ ጢሞቴዎስ 3:16 መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንተና

አማኑኤል እንዳለ


የኢትዮጵያ “ሐዋርያትዊት” ቤተ ክርስቲያን መምህራን “በሥጋ የተገለጠው ማን ነው?” ለሚለው መሠረታዊ ጥያቄ “እግዚአብሔር አብ ነው” የሚል በእጅጉ የተሳሳተ ምላሽ ይሰጣሉ። የቤተ እምነቱ የመጀመሪያው ዋና አስተዳዳሪ የነበሩት ቢሾፕ ተክለማያም ገዛኸኝ «ቃሉ ይናገር» በሚለው መጽሐፋቸው ገጽ 36 ላይ ሐሳባቸውን እንዲህ ሲሉ አስፍረዋል፦

«1ኛ ጢሞቴዎስ 3:16 በሥጋ የተገለጠው አምላክ አብ ነው ወይስ ወልድ? ብለው ለሚጠይቁ መልሱ፣ አንድ አምላክ ብቻ ስላለ በሥጋ ገጽታና በመንፈስ ገጽታ ማለትም መንፈስና ሥጋ ሆኖ በአንድ አካል የተገለጠው አማኑኤል የተባለው አንዱ ፈጣሪያችን አብ ብቻ ነው። ስሙም ኢየሱስ ክርስቶስ ተብሏል።»

በዚህ አባባል መሠረት «ኢየሱስ ክርስቶስ» የተባለው መጠሪያ በሥጋ የተገለጠውን አብ የሚያሳይ ሲሆን፣ «አማኑኤል» ተብሎ የተጠራውም ያው «አምላካችን» የሚሉት አብ ራሱ ነው። በዚህ መጣጥፍ ውስጥ «አብ በሥጋ ተገልጧል» ለሚለው የቢሾፑ ትምህርት መሠረት የሆነውን የ1ኛ ጢሞቴዎስ 3:16 ቃል በመፈተሽ፣ አብ በሥጋ አለመገለጡን ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር እናሳያለን።

) «እግዚአብሔር» (Theos) የሚለው ቃል አብን ብቻ የሚያሳይ አይደለም

የቤተ እምነቱ መምህራን እና ተከታዮች 1ኛ ጢሞቴዎስ 3:16 ላይ የሚገኘውን «በሥጋ የተገለጠ» የሚለውን ሐሳብ ለማጠናከር የKJV መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉምን ይጠቀማሉ። ሙግታቸውም በእንግሊዝኛው ላይ <And without controversy great is the mystery of godliness: God was manifested in the flesh> በሚለው ቃል ላይ የተመሠረተ ሲሆን፤ «በዚህ ስፍራ God was manifested in the flesh ስለሚል አብ እግዚአብሔር ስለሆነ ቃሉ አብን ያመለክታል» ይላሉ።

ይህ አባባል ግን መሠረተ ቢስ ነው። ምክንያቱም በአዲስ ኪዳን «እግዚአብሔር» ወይም «አምላክ» (Θεός) የሚለው ቃል ለአብ ብቻ የተሰጠ ብቸኛ መጠሪያ (exclusive term) አይደለምና። ወልድም በተመሳሳይ መልኩ «እግዚአብሔር» (God) ተብሎ ተጠርቷል። ለምሳሌ፦

  • 1ኛ ዮሐንስ 5:20፡ “…እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው።” እዚህ ላይ እውነተኛ አምላክ የተባለው ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

(“…And we know that the Son of God has come… He is the true God (Θεός) and eternal life.” — ESV)

  • ዕብራውያን 1:8 የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ ስለ ወልድ ሲናገር «ስለ ልጁ ግን፦ አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ እስከ ዘላለም ድረስ ይኖራል…» ይላል።

(“But regarding the Son He says, ‘YOUR THRONE, GOD, IS FOREVER AND EVER…’ ” — NASB)

ስለዚህ፣ በ1ኛ ጢሞቴዎስ 3:16 ላይ «እግዚአብሔር በሥጋ ተገለጠ» የሚለው ሐሳብ አብን ብቻ እንደሚያሳይ መደምደም ስህተት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አብን እግዚአብሔር እንደሚለው ሁሉ ወልድንም መንፈስ ቅዱስንም እግዚአብሔር (God) ይላቸዋል። ቃሉን ልክ አብን ብቻ የሚያመለክት አድርጎ መተርጎም ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ውጪ መሄድ ነው። የቅዱሳት መጽሐፍትን ሌሎች ምስክርነቶች ትተን እንኳ በKJV ብቻ ተገድበን «አብ ወይም ወልድ ወይም መንፈስ ቅዱስ በሥጋ ተገልጧል ግን እርግጠኛ መሆን አንችልም» ማለት ይቻል እንደ ሆን እንጂ በዚህ ጥቅስ ብቻ «አብ በሥጋ ተገልጧል» ብሎ ማጠቃለል ፍጹም ስህተት ነው። ይሁን እንጂ ሙሉውን ዐውደ-ሐሳብ ስንመረምር በሥጋ የተገለጠው ማን እንደሆነ ፍጹም ግልጽ የሆነ መልስ እናገኛለን።

) በጥቅሱ ውስጥ የተገለጡትን ድርጊቶች የፈጸመው ማን ነው?

የ1ኛ ጢሞቴዎስ 3:16ን ሙሉ ዐውደ-ሐሳብ በጥልቀት ስንመረምር በጥቅሱ የተዘረዘሩት ድርጊቶች በሙሉ የባለቤታቸው የወልድ እንጂ የአብ እንዳልሆኑ በግልጽ እንረዳለን። ነጥቦቹን በቅደም ተከተል እንመልከት፦

  1. በመንፈስ የጸደቀው ማን ነው?

በዚህ ስፍራ «የጸደቀ» የሚለው ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ «ኃጢአተኛ ነበረና ጻድቅ ሆነ» ማለት አይደለም፤ ምክንያቱም እርሱ ምንም ኃጢአት የሌለበት ቅዱስ አምላክ ነውና (1ኛ ጴጥሮስ 2:22)። ይልቁንስ በግሪክ ቋንቋ «ጸደቀ» (edikaiōthē) የሚለው ቃል ትርጉም «እውነተኛነቱ ተረጋገጠ»፣ «ንጹሕነቱና መለኮታዊ ኃይሉ በራ»፣ «የተነሳበት ሐሰተኛ ውንጀላ ተሽሮ እውነቱ ወጣ» ማለት ነው።

በሥጋ የተገለጠው ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር በነበረበት ዘመን በብዙዎች ዘንድ ተንቋል፣ ተሰድቧል፣ እንደ ወንጀለኛም በመስቀል ላይ ተሰቅሏል። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ የእርሱን ማንነት፣ እውነተኛ አምላክነትና የሥጋ መገለጡን ቅድስና በተአምራት፣ በኃይልና ከሙታን በማንሣት አጽድቆታል (እውነተኛነቱን አስመስክሯል)።

ወልድ «በመንፈስ የጸደቀው» (እውነተኛነቱ የተረጋገጠው) መቼና እንዴት ነው?

  • በማኅፀን ፅንሰቱ በሕይወቱ ቅድስና፦ ኢየሱስ ክርስቶስ የተጸነሰው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነው (ሉቃስ 1:35)። በምድር ላይ በኖረበት ዘመን ሁሉ ኃጢአት ሳይኖርበት በመንፈስ ቅዱስ ቅባትና ኃይል ተአምራትን እያደረገ የእግዚአብሔር ልጅነቱ ተመስክሯል (የሐዋርያት ሥራ 10:38)።
  • በጥምቀቱ ወቅት፦ በዮርዳኖስ ወንዝ ሲጠመቅ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል በእርሱ ላይ አረፈ፤ አብም «የምወደው ልጄ ይህ ነው» በማለት ምስክርነቱን ሰጥቷል (ማቴዎስ 3:16-17)።
  • በትንሣኤው የወልድ «በመንፈስ መጽደቅ» ትልቁ ማረጋገጫ ከሙታን መነሣቱ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 1:3-4 ላይ «ይህም ወንጌል… እንደ ቅድስና መንፈስ ግን ከሙታን መነሣት የተነሣ በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስለ ተገለጠ ስለ ልጁ ነው» በማለት በግልጽ አስቀምጦታል (ሮሜ 1:3-4)።
  • በመንፈስ ቅዱስ መውረድና በሐዋርያት ምስክርነት፦ ከዕርገቱ በኋላ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በሐዋርያት ላይ በወረደው ኃይልና በተአምራት የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤና ጽድቅ ለዓለም ሁሉ ታውጇል (ዮሐንስ 16:8-10)።
  1. «ለመላእክት የታየው ማን ነው

በዚህ ስፍራ «በሥጋ ተገልጦ መላእክት አብን አይተውት ነበርን?» ብለን መጠየቅ ይገባናል። ማንም ሰው «አዎ፣ አብ በሥጋ ተገልጦ መላእክትም አይተውታል» ብሎ በድፍረት ሊመልስ አይችልም። ታዲያ ወልድ ነው ወይስ መንፈስ ቅዱስ ለመላእክት የታየው? መንፈስ ቅዱስ በሥጋ ተገልጦ ለመላእክት መታየቱን የሚያሳይ ማስረጃ ስለሌለ መልሱ «አዎ፣ ወልድ ነው!» የሚል ይሆናል።

ወልድ በሥጋ ተገልጦ በዚህ ምድር ሳለ መላእክት በእርግጥም አይተውታል፣ አገልግለውታልም፦

  • በፅንሰቱና በልደቱ ጊዜ፦ መላእክት በሥጋ የተወለደውን ሕፃን (ወልድን) በዓይናቸው አይተውታል፣ አመስግነውታልም (ሉቃስ 2:10-14)።
  • በምድረ በዳ ሲፈተን፦ ከሰይጣን ፈተና በኋላ «መላእክት ቀርበው ያገለግሉት ነበር» (ማቴዎስ 4:11)። መላእክት የማይታየውንና ያልተገለጠውን መለኮታዊ አካል ሊያገለግሉ አይችሉም፤ ያገለገሉት በሥጋ የተገለጠውን ወልድን ነው።
  • በጌቴሴማኒ የጸሎት ስፍራ፦ በሥጋዊ ድካም ውስጥ ሳለ «መልአክ ከሰማይ ታይቶ ያበረታው ነበር» (ሉቃስ 22:43)።
  • በትንሣኤውና በዕርገቱ ወቅት፦ በመቃብሩ ዘንድ መላእክት ተቀምጠው ታይተዋል (ዮሐንስ 20:12)፤ ወደ ሰማይ ሲያርግም አጅበውታል (የሐዋርያት ሥራ 1:10-11)።
  1. «በአሕዛብ የተሰበከው ማን ነው

«እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው» (1ኛ ቆሮንቶስ 1:23)።

በዚህ ስፍራ «አሕዛብ» የሚለው ቃል ከእስራኤል ሕዝብ ውጪ የነበሩትን ሕዝቦች ለማመልከት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለአሕዛብ የሰበከው የወንጌል ማዕከል የተሰቀለውና የተነሣው ክርስቶስ መሆኑን ኤፌሶን 2:14-19 ላይ በግልጽ አስፍሮታል። በአሕዛብ ዘንድ የተሰበከው ስብከት ዐቢይ መልእክት ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ በመገለጡና በመስቀል ሥራው አማካኝነት ሁሉም በክርስቶስ እኩል ወራሾች መሆናቸውን ማብሰር ነው።

  1. «በዓለም የታመነው ማን ነው

<<በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና>> (ዮሐንስ 3:16)።

በዓለም የታመነው ማን ነው? የዚህ ጥያቄ መልስ ሰዎች ለኃጢአታቸው ይቅርታ የእምነታቸው ማረፊያ (Object of Faith) ያደረጉት ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አንድም ስፍራ ላይ «አብ በሥጋ ተገልጧል፣ አብ ሞቶልናል፣ አብም ከሙታን ተነስቷል» ብሎ አያስተምርም። ስለዚህ «አብ በሥጋ ተገልጧል» ብሎ ማመን ምንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የለውም፤ ይልቅስ ልጁ በሥጋ መገለጡንና ያደረገልንን የማዳን ሥራ በእምነት መቀበል ይገባናል።

  1. «በክብር ያረገው ማን ነው

<<ኢየሱስም፦ ‘ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ…’ አላት>> (ዮሐንስ 20:17)።

በዚህ ጥቅስ መሠረት «ወደ አባቴ ዓርጋለሁ» ብሎ የሚናገረው ወልድ ራሱ ነው። እንደ «ሐዋርያት» ቤተ እምነት አረዳድ «አብ ነው» ቢባል ኖሮ፣ አብ «አባቴ» የሚለው ማንን ነው የሚለው ጥያቄ አሻሚ ይሆናል። በደመና ወደ ሰማይ ያረገውና በአብ ቀኝ የተቀመጠው በሥጋ የተገለጠው ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው (የሐዋርያት ሥራ 1:9-11፣ ዕብራውያን 1:3)።

ማጠቃለያ

የኢትዮጵያ “ሐዋርያትዊት” ቤተ እምነት ተከታዮች አብ በሥጋ ተገለጠ ለማለት የሚያነሱት 1ኛ ጢሞቴዎስ 3:16 አውዱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ እውነት ጋር ሲገናዘብ የሚያረጋግጠው ወልድ አምላክ መሆኑንና እርሱ ራሱ በሥጋ መገለጡን እንጂ አብ በሥጋ መገለጡን አይደለም።

ወልድ እውነተኛ ሥጋ፣ ደም እና ነፍስ ያለው ፍጹም ሰው ነው፤ በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ እውነተኛ አምላክ ነው (1ኛ ዮሐንስ 5:20)። በመሆኑም በሥጋ የተገለጠው፣ ለመላእክት የታየው፣ በአሕዛብ የተሰበከውና በክብር ያረገው ራሱ ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው!


መልስ ለሰባልዮሳውያን