የሽረት ሕግ – ቁርኣን ሰው ሠራሽ መሆኑን የሚያረጋግጥ አስተምህሮ

የሽረት ሕግ

ቁርኣን ሰው ሠራሽ መሆኑን የሚያረጋግጥ አስተምህሮ

በወንድም ትንሣዔ


ሙስሊም ወገኖች እርስ በርስ የሚጋጩና እጃችን ላይ ያለው የቁርኣን ቅጂ ውስጥ የማይገኙ የቁርኣን ትዕዛዛትን ለማብራራት ከሚጠቀሙባቸው መንገዶች መካከል ሽረት/ነስኽ/Abrogation ተብሎ የሚጠራው እሳቤ አንዱ ነው። ይህ እሳቤ እንደ ቁርኣን 2:106 ፣ 87:6-7 እና 16:101 ባሉ አንቀጾች ላይ የተመሰረተ ሲሆን አሏህ ያወረደውን አንድ የቁርኣን አንቀጽ/ሕግ በሌላ የቁርኣን አንቀጽ/ሕግ መለወጡን የሚያመለክት ነው። 

ሱረቱል በቀራህ 2:106

مَا نَنسَخْ مِنْ ءَايَةٍ أَوْ نُنسِهَا نَأْتِ بِخَيْرٍ مِّنْهَآ أَوْ مِثْلِهَآۗ أَلَمْ تَعْلَمْ أَنَّ ٱللَّهَ عَلَىٰ كُلِّ شَىْءٍ قَدِيرٌ 

«ከአንቀጽ ብንለውጥ ወይም እርሷን ብናስረሳህ ከርሷ የሚበልጥን ወይም ብጤዋን እናመጣለን፤ አሏህም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ መኾኑን አታውቅምን?»

ከነዚህና ከሌሎች የቁርኣን አንቀጾች በመነሳት ሙስሊም ሊቃውንት የተለያዩ መስፈርቶችን በመጠቀም የተለያዩ የሽረት ዓይነቶችን መስርተዋል። ከነዚህ ውስጥ 

1- ቁርኣንን በቁርኣን መሻር

2- ሱናን በሱና መሻር

3- ሱናን በቁርኣን መሻርና

4- ቁርኣንን በሱና መሻር ይጠቀሳሉ።

አብዛኞቹ ሙስሊም ሊቃውንት የመጀመሪያዎቹ ሁለቱን ሽረቶች ሲቀበሉ እንደ ኢማም አሽ’ሻፊ ያሉ ሊቃውንት ግን ከላይ የተጠቀሰው አንቀጽ “ከእርሷ የሚበልጥን አያህ እናመጣለን” ስለሚልና ቁርኣንና ሱና ደግሞ ሊበላለጡ ስለማይችሉ ሱና ቁርኣንን ወይም ቁርኣን ሱናን ሊሽር ይችላል የሚለውን እሳቤ አጥብቀው ይቃወሙ ነበር።[1] 

ሙስሊም ሊቃውንት የተጠቀሙት ሌላው መስፈርት የቁርኣን የሽረት ዘዴን የተመለከተ ሲሆን በዚህም ሦስት የሽረት አይነቶች እንዳሉ ይስማማሉ።

1- የንባብና የሕግ ሽረት፦ የቁርኣን ጽሕፈት ከሕጉ ጋር አብሮ ይሻራል። (ሕጉ ሲሻር ጽሑፉም ከቁርኣን ይወጣል)

2- የንባብ ሽረት ብቻ፦ የቁርኣን ጽሕፈት ተሽሮ ሕጉ ይቀመጣል። (ሕጉ አሁንም ድረስ ቢሰራም ጽሑፉ ግን ከቁርኣን  ይወጣል)

3- የሕግ ሽረት ብቻ፦ የቁርኣን ሕግ ተሽሮ ጽሕፈቱ ይቀመጣል። (ሕጉ ከዚህ በኋላ ባይሰራም ጽሑፉ ግን ከቁርኣን አይወጣም)

ሙስሊም ሊቃውንት እነዚህ የሽረት ዓይነቶች ከራሱ ከቁርኣን የተወሰዱ እንደሆነና ከነዚህ ውጪ የሆነ የቁርኣን አንቀጾች የመጥፋት ክስተት ሊኖር እንደማይችል  ሲናገሩ መስማት የተለመደ ቢሆንም እውነታው ግን በተቃራኒው ለመሆኑ ጠንካራ ማረጋገጫ አለ። ነገሩን ለመረዳት ሦስቱንም የሽረት አይነቶች አንድ በአንድ ማየት አስፈላጊ ነው።

1) የሕግና የንባብ ሽረት

ከሁለቱ የሽረት ዓይነቶች በተሻለ ተቀባይነት የነበረው ይህ የሽረት ዓይነት አንድ ሕጉ የተሻረ አንቀጽ ከዚህ ወዲህ አላስፈላጊ ስለሆነ ከንባብ መሻር አለበት የሚሉ ሊቃውንትን ሀሳብ የሚያንጸባርቅ ነው። ምንም እንኳን አብዛኞቹ ቀደምት ሙስሊም ሊቃውንት ይህንን የሽረት ዓይነት ቢቀበሉም ሀሳቡ ግን ከሌሎች እስላማዊ ምንጮች ጋር የሚጋጭ ነው። ለምሳሌ የሙሐመድ ተከታዮች ሕጋቸው የተሻሩ አንቀጾችን ከቁርኣን ላለማስወገድ ጥንቃቄ ያደርጉ እንደነበር ተዘግቦ እናገኛለን።

“አብደላህ ኢብን አዙባይር ዘግቦታል- ቁርኣን 2:240ን በተመለከተ ለዑስማን ኢብን አፋን እንዲህ አልኩት- ‘ይህ አንቀጽ በሌላ አንቀጽ (2:234) ተሽሯል ፤ ታዲያ ለምን ትጽፈዋለህ?’ እርሱም ‘የወንድሜ ልጅ ሆይ ከቁርኣን ውስጥ ምንም ነገርን ከቦታው አልቀይርም’ አለ።”[2]

ይህና ሌሎች ብዙ ሕጋቸው የተሻረ ነገር ግን ከቁርኣን ያልወጡ አንቀጾች መኖራቸውን ተከትሎ የመጣውን “አሏህ በዚህ መልኩ ሕጉን ሽሮ ጽሑፉን ማስቀረት ከቻለ ለምን የአንዳንዶቹ አያዎች ጽሑፍ እንዲወገድ ተፈለገ?” የሚለውን ጥያቄ ሙስሊም ሊቃውንት በአሳማኝ መልክ መመለስ አልቻሉም ነበር። በእርግጥም ፈጣሪ ትዕዛዙን መቀየር ከፈለገ ይህንኑ ማድረግ እንጂ መጽሐፉን ወይም የመጽሐፉን ክፍል ማስወገድ ምንም ዓይነት አመክንዮአዊ መሠረት ሊቀርብለት የሚችል አልነበረም።

2) የንባብ ሽረት ብቻ

ይህ የሽረት ዓይነት ብዙ አመክንዮአዊና ታሪካዊ ጥያቄዎችን የሚያስነሳ ነው። የመጀመሪያውና ቀላሉ ጥያቄ “ፈጣሪ ለምንድነው እንድንከተለው የሚፈልገውን ሕግ ከመጽሐፉ የሚያወጣው?” የሚለው ነው። በእርግጥም ፈጣሪ ሕጉ የተሻረውን አንቀጽ በመጽሐፉ አስጽፎ ሕጉ የሚሠራውን አንቀጽ ከመጽሐፉ እንዲወገድ ማድረጉ ለአንዳንድ ሙስሊም ሊቃውንትም “ግራ አጋቢ” ነበር።[3]

ሙስሊም ሊቃውንት ይህንን የሽረት ዓይነት በሙሐመድ የመርሳትና ማስታወስ ችሎታ ላይ መመሥረታቸው ደግሞ ጉዳዩን የበለጠ ችግር ውስጥ የሚከተው ነው። ኢማም አልጠበሪ ቁርኣን 87:6-7ን ሲያብራራ ይህንን ትርጓሜ ይጠቅሳል:-

“ቁርኣንን እናስነብብሃለን አትረሳምም፤ አሏህ ከሻው በቀር  ማለቱ አሏህ ከቁርኣን ውስጥ ንባባቸው እንዲወገዱ ያደረጋቸውን አያዎች ያመለክታል።”[4] 

ስለዚህ በአልጠበሪ መሠረት አሏህ በንባብ ደረጃ ማስወገድ የፈለጋቸውን አያዎች የሚያስወግደው ከሙሐመድ ትውስታ በመሰረዝ ነበረ። ሌሎች እስላማዊ ትውፊቶችም ይህ የሽረት ዓይነት የሙሐመድና ተከታዮቹ የማስታወስ ችሎታ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ይናገራሉ።

“ነቢዩ አንድን የቁርኣን ክፍል እንዲይዝ ለአብደላህ ኢብን መስዑድ ነግሮት ነበር። እርሱም በቃሉ ሸምድዶ በግል መጽሐፉም ከትቦት ነበር። ምሽት ላይ አብደላህ ይህንን አንቀጽ ጸሎቱ ውስጥ ለማካተት ፈልጎ ሲነሳ ግን አንቀጹን ማስታወስ አልቻለም። ጠዋት ላይ መጽሐፉን ሲከፍት አንቀጹ የተጻፈበት ገጽ ነጭ ወረቀት ሆኖ አገኘው። ለነቢዩ ይህንን ሲነግራቸው “ይህ አንቀጽ ትላንት ምሽት ተሽሯል” አሉት።”[5]

ከዚህ ሐዲስ እንደምንረዳው አሏህ ከንባብ እንዲወጣ የፈለገውን አንቀጽ ከሙሐመድና ተከታዮቹ አእምሮና መጽሐፍ ያጠፋ ነበር። ሙሐመድም “የቁርኣን አንቀጽን ረሳሁ አትበሉ፤ እንድረሳ ተደረግሁ እንጂ” ማለቱን የሚገልጹ ሐዲሳት መኖራቸው የቁርኣን አንቀጽ ፈጣሪ ለፈለገው ዓላማ ካልሆነ ከሙሐመድና ተከታዮቹ አእምሮ እንደማይጠፋ የሚያመለክት ነው።[6] በዚህ እስላማዊ ትምህርት መሠረት የቁርኣን የንባብ ሽረቶች እንዲፈጸሙ ሙሐመድ አንቀጹን መርሳት የሚገባው ሲሆን በተጨማሪም ንባባቸው ከተሻሩ አንቀጾች ውጪ ሙሐመድ ምንም አንቀጽ መርሳት የለበትም፤ አሏህ ንባባቸው ያልተሻሩ አንቀጾች እንዲረሱ አይሻምና። እስላማዊ ምንጮችን ስናገላብጥ ግን ከዚህ በተቃራኒው ሙሐመድ ብዙ ያልተሻሩ አንቀጾችን ይረሳ እንደነበር እናነባለን።

“አብዱረሕማን ቢን አውፍ ዘግቦታል- ነቢዩ በቅዳሜ ቀን ከሕዝቡ ጋር በመስጂድ እየጸለዩ ነበር። ሱረቱል ፉርቃንን እያነበቡ እያለም የተወሰኑ አያዎችን ዘለሉ። ጸሎቱን ከጨረሱ በኋላም “ዑበይ ኢብን ካዕብ መስጂድ ውስጥ አለ እንዴ?” ሲሉ ጠየቁ። ዑበይም “እዚህ ነኝ የአሏህ መልእክተኛ” አለ። እርሳቸውም “ታዲያ ለምን አላስቆምከኝም?” አሉት ፤ እርሱም “አያው ተሽሮ እንዳይሆን ፈርቼ ነው” አላቸው። ነቢዩም “አልተሻረም” አሉት።”[7]

“አይሻ ዘግባዋለች- ነቢዩ አንድ ሰው በምሽት ቁርኣንን ሲቀራ ሰሙና “አሏህ ምሕረቱን ይስጠው፤ ከዚህ ሱራ እንድረሳ የተደረግሁትን ይህንን አያህ አስታውሶኛልና አሉ።”[8] 

ከነዚህ ትውፊቶች እንደምንረዳው ሙሐመድ እንደ ተከታዮቹ ሁሉ ከንባብ ያልወጡ የቁርኣን አንቀጾችን ይረሳ ነበር። ይህ በሆነበት ሁኔታ የሙሐመድ ማስታወስና መርሳት ላይ ተመስርቶ የቁርኣን አንቀጾችን ለመሻርና ለማጽደቅ መሞከር ይዞ የሚመጣው ታሪካዊ ችግር እጅግ ግልጽ ነው።

3) የሕግ ሽረት ብቻ

ይህ ሦስተኛው የሽረት ዓይነትም የራሱ ችግሮች አሉት። ከላይ ያየናቸው እስላማዊ ምንጮች አንድ አንቀጽ ከቁርኣን እንዲሻር ከሙሐመድና ተከታዮቹ አእምሮና ከመጽሐፋቸው እንዲወገድ መደረግ እንዳለበት በግልጽ እንደማስቀመጣቸው ሕጋቸው የተሻሩ አያዎች በቁርኣን መገኘታቸው ለሙስሊሙ ሕዝብ ጥያቄ የሚፈጥር ነበር። ፈጣሪ ሕጋቸው የተሻሩ አያዎችን በመጽሐፉ ካስቀመጠ ለምንድነው ሕጋቸው ያልተሻሩትን ከመጽሐፉ እንዲወጡ ያደረገው? የሚለው ከላይ ያየነው ጥያቄም በዚህ አግባብ የተጠየቀ ነበር።

ማጠቃለያ

ሙስሊም ሊቃውንት እነዚህን የሽረት ዓይነቶች ሲዘረዝሩ ቁርኣንን ከመመሥረት ይልቅ ቁርኣን ውስጥ ያሉ ግጭቶችና የጠፉ አንቀጾችን ለማብራራት እንደነበር ግልጽ ነው። ለምሳሌ ምንም እንኳን ቁርኣን ዝሙት ሲሠሩ የተገኙ ሰዎች መቶ ግርፋት እንዲገረፉ ብቻ ቢያዝዝም (24:2) እስላማዊ ትውፊት ሙሐመድና ተከታዮቹ ዝሙተኞችን ይወግሩ እንደነበር ይናገራል። ይህንን ግጭት ለማስታረቅ አንዳንድ ሊቃውንት ይህ ሱና ቁርኣንን የሻረበት አንድ ምሳሌ ነው ሲሉ እንደ ኢማም አሽ’ሻፊ ያሉ ሱና ቁርኣንን መሻሩን የማይቀበሉ ሊቃውንት ግን ከዑመር የተላለፈው ይህንን ሐዲስ በመጠቀም ቁርኣን በሱና እየተሻረ ሳይሆን ቁርኣን በቁርኣን እየተሻረ መሆኑን ተናግረዋል።

“አብደላህ ኢብን ዐባስ ዘግቦታል- ዑመር ቢን አል-ኸጣብ እንዲህ አለ- በእርግጥም አሏህ ሙሐመድን እውነትን አስይዞ ልኮታል። መጽሐፉንም ገልጦለታል ከመጽሐፉ ውስጥም የመውገር አንቀጾች ነበሩ ፤ እናነበው እንሸመድደውና እንረዳው ነበር። እኛም የአሏህ መልእክተኛም የመውገር ቅጣትን እንፈጽም ነበር። ሰዎች ግን ጊዜ ሲያልፍ “የመውገር ቅጣትን ቁርኣን ውስጥ አናገኝም” ብለው እንዳይተዉት እሰጋለሁ።…”[9]

በእርግጥም ሕጉ የሚሠራን የቁርኣን አንቀጽ ከንባብ ማስወገድ ሰዎች ለሕጉ ቸልተኛ እንዲሆኑ ከማድረግ ባለፈ ምንም ዓላማ እንደማያሳካ ግልጽ ነበር። ሌላው ሙስሊም ሊቃውንትን የከፋፈለው ጉዳይ አዋቂዎችን ጡት ስለማጥባት የሚናገረው የቁርኣን አንቀጽ ነበር።

“አይሻ ዘግባዋለች- ቁርኣን ውስጥ ጋብቻን የሚከለክለው አስር ጡት ማጥባት መሆኑ ተገልጦ ነበር ፤ ከዚያም በአምስት ተቀየረ ፤ የአሏህ መልእክተኛ ሲሞቱም ይህ አንቀጽ ቁርኣን ውስጥ ሆኖ ይቀራ ነበር።”[10]

አብዛኞቹ ሙስሊም ሊቃውንት ይህ አንቀጽ በሕግ ደረጃ እንዳልተሻረና ከንባብ ብቻ እንደወጣ ቢያመለክቱም ይህ ሀሳብ ግን ብዙ የቁርኣን ክፍሎች ላይገኙ የመጥፋታቸውን ሀቅ ለማድበስበስ የመጣ መሆኑ ግልጽ ነው። አይሻ እንዳለችው ይህ አንቀጽ ሙሐመድ በሞተበት ጊዜ ቁርኣን ውስጥ ከነበረና በጸሎት ይነበብ ከነበረ ከሙሐመድ ሞት በኋላ በንባብም ሆነ በሕግ ደረጃ ሊሻር አይችልም ማለት ነው ፤ ከሙሐመድ ሞት በኋላ ነስኽ/ሽረት አይሰራምና። ይህ ደግሞ ወደ አንድ ብቸኛ ድምዳሜ ይመራናል። ጡት የማጥባት ትዕዛዝን ቁርኣን ውስጥ የማናገኘው ሙሐመድ በንባብም ሆነ በሕግ ደረጃ መሻራቸውን ስለተናገረ ሳይሆን (ይህንን የሚገልጽ አንድም እስላማዊ ትውፊት አለመኖሩን ልብ ይሏል) ቁርኣን ከሙሐመድ በኋላ በነበሩ ሙስሊሞች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ቅነሳና መቆራረጥ ስለተደረገበት ነው።

እንደ ኢማም ማሊክ ያሉ ሊቃውንት ይህንን ድምዳሜ ላለመቀበል ይመስላል የአይሻን ዘገባ ከነአካቴው አንቀበልም ያሉት።[11]

ከዚህ በዘለለ ብዙ ትዕዛዝ አልባ የሆኑ ማለትም ሕግን ለማቆም ሳይሆን ታሪካዊ ወይም ሐይማኖታዊ እውነታዎችን ለማሳወቅ የተነገሩ የቁርኣን አያዎች ከዑስማን መጽሐፍ መጥፋታቸው ሲታወቅ (የኢብን አዳምና የቢእር ማውና ጥቅሶች ይጠቀሳሉ) ሦስቱም የሽረት ዓይነቶች መሰል ክስተቶችን ማብራራት አልቻሉም። ኢማም አልጠበሪ ይህንን ችግር ለመፍታት ሁለት ዓይነት የንባብ ሽረቶች እንዳሉ ይናገራል።

1- ጥቅም ስለሌላቸው ከንባብ የተሻሩ

2- ከንባብ ስለተሻሩ ጥቅም የሌላቸው

የመጀመሪያው የሽረት ዓይነት ሕጉ የተሻረ የቁርኣን አንቀጽ በመጽሐፉ መካተቱ ጥቅም ስለሌለው መወገዱን የሚገልጽ ሲሆን ሁለተኛው የአልጠበሪ ሽረት ግን በምንም መልኩ ቁርኣንን መሠረት ያደረገ ሳይሆን ከላይ ያየናቸውን የኢብን አደምና የቢእር ማውና ጥቅሶች ከቁርኣን መጥፋት ለማብራራት የተፈጠረ እንደሆነ ግልጽ ነው። “ስለተሻሩ ጥቅም የሌላቸው” የሚለው ንግግርም ቀድሞውኑ ለምን ከንባብ ተሻሩ የሚለውን ጥያቄ መመለስ የማይችል ነው። እንደውም ኢማሙ ከገዛ ምልከታው ጋር በሚጋጭ መልኩ “ሽረት የሚደረገው የተከለከለን ለመፍቀድ የተፈቀደን ለመከልከል ወዘተ ብቻ ነው” ማለቱ የኢብን አደምና ቢእር ማውና አንቀጾች ምንም ዓይነት ክልከላም ሆነ ትዕዛዝ ሳይኖራቸው በዑስማን ቅጂ አለመገኘታቸው ለሊቃውንቱ የፈጠረውን ከባድ አጣብቂኝ የሚያሳይ ነው።[12]


[1] Burton, John.(1990). The Sources of Islamic law: Islamic theories of abrogation.p.160. Edinburgh University press.
[2] Sahih al-bukhari Volume 6 Book 60 Hadith 60.
[3] Burton, John.(1990) The Sources of Islamic law: Islamic theories of abrogation.p.160. Edinburgh University press.
[4] Tafseer al-tabari Volume 24 p.314-5.
[5] Abu ubaid’s kitab al-nasikh wal-mansukh p.11.
[6] Sahih Muslim Book 4 Hadith 1726.
[7] Al-Mudawwana al-kubra by Sahnun Volume 1 p.107.
[8] Sahih al-bukhari Volume 6 Book 61 Hadith 558.
[9] Sahih Muslim Book 17 Hadith 4194.
[10] Muwatta Malik Book 30 Hadith 17.
[11] Ibid.
[12] Tafseer al-tabari Volume 2 p.388.