“አሻራኪው አደም…”

ሙሽሪኩ አደም…”

ወንድም ትንሣኤ


ሙስሊሞች ሁሉም ነቢያት ከአበይት የኃጢአት አይነቶች (ማጋራት፣ መግደል፣ ዝሙት) ወዘተ. እንደተጠበቁና በፍጹም እነዚህን በደሎች ሊሠሩ እንደማይችሉ ያምናሉ። ሙስሊም ሊቃውንት እንደሚነግሩን ከሆነም ሙስሊም ነቢያት አነስተኛ ኃጢአቶችን ሲሠሩ እንኳን ወዲያውኑ በንስሐ ይመለሳሉ። የቁርኣን ደራሲ ግን በሱራ አል-አዕራፍ 7:190 ላይ በእስልምና አስተምህሮ የመጀመሪያ ነቢይ እንደሆነ የሚነገረው አደም ከሚስቱ ጋር በመሆን በአሏህ ላይ የማጋራት ኃጢአትን እንደሠራ ይነግረናል።

እርሱ ከአንዲት ነፍስ (ከአደም) የፈጠራችሁ ከእርሷም መቀናጆዋን ወደርሷ ይረካ ዘንድ ያደረገ ነው፡፡ (ሃዋን) በተገናኛትም ጊዜ ቀላልን እርግዝና አረገዘች፡፡ እርሱንም (ፅንሱን) ይዛው ኼደች፡፡ በከበደችም ጊዜ «ደግን ልጅ ብትሰጠን በእርግጥ ከአመስጋኞቹ እንኾናለን፤» ሲሉ ጌታቸውን አላህን ለመኑ፡፡ መልካም ልጅ በሰጣቸውም ጊዜ በሰጣቸው ልጅ (ስም) ለእርሱ ተጋሪዎችን አደረጉለት፡፡ አላህም ከሚያጋሩት ሁሉ ላቀ፡፡7:189-90 (በቅንፍ የተጨመረው በዐረብኛው የለም)

ሙስሊም ሊቃውንት የነቢያት መጀመሪያ የሆነው አደም ከእስልምና ወጥቶ ሽርክ ይፈጽማል የሚለውን ሐሳብ መቀበል ስላልቻሉ የተለያዩ እርስ በርስና ከቁርኣን ጋር የሚጋጩ ማብራሪያዎች አስቀምጠዋል። ለምሳሌ ያህል ኢብን ከሢር እንዲህ ይላል፦

“…ይህን አያህ በዚህ መልኩ ነው መረዳት ያለብን። ስለ አደምና ሐዋ ሳይሆን ስለ ሙሽሪክ ዘሮቻቸው ነው የሚናገረው። አሏህ መጀመሪያ አደምና ሐዋን ጠቀሰ፤ ከዚያም ስለ ሙሽሪኮቹ ተናገረ።[1]

ኢማም አልጠበሪና ቁርጡቢይም ተመሳሳይ ትርጓሜ ይጠቅሳሉ።[2][3] ነገር ግን ይህ ማብራሪያ የአንቀጹን ሰዋሰው በእጅጉ የሚንድ ነው። በመሰረቱ ተጋሪዎችን ‘አደረጉለት’ የሚለው ዐረብኛ ቃል ‘ጀአላ’ خعلآ ሲሆን ሁለት ባለቤቶችን የሚያመለክት ግሥ ነው። ‘በሰጣቸው’ (ءَاتَىٰهُمَا) የሚለው ቃልም በተመሳሳይ ሁለት ባለቤቶችን ብቻ የሚያመለክት ነው። መሰል ግሦች በዐረብኛ ሙተና (dual) ግሦች ሲባሉ የዐረፍተ ነገሩ ባለቤቶች ሁለት ሲሆኑ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ ናቸው። ስለዚህ በአሏህ ላይ ተጋሪ አደረጉ የተባሉት አካላት ማንም ይሁኑ ማን ብዛታቸው ከሁለት ሊበልጥ አይችልም። የአንቀጹ አውድ ላይ የተጠቀሱት ብቸኛ ሁለት አካላት ደግሞ አደምና ሚስቱ መሆናቸው እርግጥ ስለሆነ የድርጊቱ ባለቤት እነርሱው መሆናቸው ግልጽ ነው። 

የድርጊቱ ባለቤት ሌሎች የሰው ልጆች ናቸው የሚለውን ማብራሪያ ከሚደግፉት ሊቃውንት አንዱ የሆነው ኢማም ቁርጡቢይ የሚያቀርበው ምክንያት “የአንቀጹ መጨረሻ ላይ የሚገኘው ከሚያጋሩት ‘ዩሽሪኩና’ (يُشۡرِكُونَ) የሚለው ቃል እንደ ሌሎቹ ግሦች ሙተና (dual) ሳይሆን ከሁለት በላይ ባለቤቶችን የሚገልጽ ነው ይህም አንቀጹ ለሁለት ሰዎች እንዳልተነገረ ያሳያል” የሚል ነው።[4] ይህ ግን ሲበዛ ደካማ ሙግት ነው። ጀላሉዲን አስ-ሱዩጢ እንደሚገልጸው “ከሚያጋሩት ሁሉ ላቀ” የሚለው ዐረፍተ ነገር የግድ ከአደምና ሐዋ አንቀጽ ጋር አንድ ላይ ተደርጎ የሚነበብበት ምክንያት የለም።[5] የቁርኣን ደራሲ የአደምና የሐዋን ማጋራት ከተረከ በኋላ ትኩረቱን የመካን ጣዖታውያን ወደ መገሰጽ እየለወጠ ስለሆነ ከሁለት በላይ አካላትን የሚገልጽ ግሥ ቢጠቀም ችግር የለውም።[6]

የድርጊቱን ባለቤት ማስተባበል አዋጪ አለመሆኑን የተረዱት ሌሎች ሙስሊም ሊቃውንት በአንጻሩ የድርጊቱ ባለቤት አደምና ሐዋ መሆናቸውን ተቀብለው የሽርኩን ዓይነት ለማሳነስ ሞክረዋል። ከኢብን ዐባስ በተላለፈ ትውፊት ላይ ይህን እናነባለን፦

 “ሐዋ ለአደም ልጆች ከወለደች በኋላ አብደላህ ብላ ትሰይማቸው ነበር ፤ ልጆቿም ይሞቱባት ነበር። ከዚያ ኢብሊስ መጣና ‘አብደላህ ብላችሁ ባትሰይሙት በሕይወት ይኖራል’ አላቸው። እነርሱም አብደል-ሃሪስ (ሃሪስ የቀድሞ የሰይጣን ስም ነበር) ብለው ሰየሙት።” [7]

በዚህ ማብራሪያ መሠረት የአደም ኃጢአት ከአሏህ ውጪ ሌላ አካልን ማምለክ ሳይሆን ልጁን “የሰይጣን ባሪያ” ብሎ መሰየሙ ነው። ይህ ማብራሪያም ቢሆን ግን የራሱ ችግሮች አሉበት። በመጀመሪያ ቁርኣን “ተጋሪዎች” (شُرَكَآءَ) አደረጉለት እንጂ ተጋሪ (شريك) አደረጉለት ብሎ ስላልተናገረ የአደምን ሽርክ ከአንድ ጣዖት (ሰይጣን) ጋር ብቻ ለማያያዝ መሞከር ትክክል አይሆንም። በሁለተኛ ደረጃ ይህ የቁርኣን ጥቅስ  የተወለደው ልጅ የመጀመሪያ ልጅ መሆኑን እንጂ አደምና ሐዋ ሌሎች ልጆች ከሞቱባቸው በኋላ የተወለደ ልጅ መሆኑን አይጠቁምም። አደም አሻረከ የተባለው ጣዖት በማምለኩ ሳይሆን ልጁን የሰይጣን ባሪያ ብሎ በመሰየሙ ነው ቢባል እንኳን አደም በሰይጣን ጌትነት ሳያምን እንዴት ልጁን የሰይጣን ባሪያ ብሎ ይሰይማል? ብለን መጠየቅ ይኖርብናል። ሌላው ቢቀር በዚሁ ትውፊት መሠረት አደምና ሐዋ ሰይጣን ልጆቻቸውን ከሞት የመጠበቅ ኃይል አለው ብለው ማሰባቸው ግልጽ ነው፤ ስለዚህ በዚህ ማብራሪያ መሠረት ብንሄድ እንኳን አደም በአሏህ ላይ ሰይጣንን እንዳጋራ ለመደምደም እንገደዳለን።

ከዚህ ባለፈ ይህ ትርጓሜ አንቀጹ ከሚገኝበት አውድ ጋር የሚስማማ አይደለም። የቁርኣን ደራሲ ይህን ታሪክ የሚተርከው ጣዖት አምላኪዎቹ የመካ ነዋሪዎችን ለመገሰጽ እንደመሆኑ ልጁን የሰይጣን ባሪያ ብሎ የሰየመውን አደም እንደ ምሳሌ መጥቀሱ አያስኬድም። እነዚህን ሐሳቦች ከግምት ውስጥ በማስገባት ይመስላል ኢማም ቁርጡቢይ ይህን ትውፊት “በስሑት ሰነዶች የመጣ” በሚል ውድቅ ያደረጉት።[8]

ስናጠቃልል ይህ የቁርኣን አንቀጽ “ዒስማ” የሚባለውን ነቢያት ከአበይት ኃጢአት ይጠበቃሉ የሚለውን እስላማዊ ትምህርት በእጅጉ የሚጻረር ነው። የነቢያት መጀመሪያ የነበረው አደም ከእስልምና ወጥቶ ኢብሊስን ወይም ሌላ አካልን ካመለከ ሌሎቹ የእስልምና ነቢያትም ሙሐመድን ጨምሮ በተመሳሳይ ትላልቅ በደሎችን ላለመፈጸማቸው እርግጠኛ መሆን አንችልም።


[1] Tafseer Ibn kathir Surah 7:190.

[2] Tafseer al-qurtubi volume 9 p.411.

[3] Tafseer al-tabari volume 10 p.628.

[4] Tafseer al-qurtubi volume 9 p.411.

[5] Tafseer al jalalayn English translation by Feraz Hamza p.181.

[6] Tafseer al-tabari volume 10 p.630.

[7] Ibid.p.624.

[8] Tafseer al-qurtubi volume 9 p.411.


ቁርኣን