አዶናይ የኾነው መሲሕ

አዶናይ የኾነው መሲሕ

የመሲሑ አምላክነት በመዝሙር 110፥1

ወንድም ሚናስ


לדוד מזמור נאם יהוה לאדני שב לימיני

 עד־אשית איביך הדם לרגליך

“ጌታ ጌታዬን፦ ጠላቶችኽን ለእግርኽ መቀመጫ እስካደርግልኽ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው።” መዝ 110፥1 [የዐማርኛ ትርጒም]

“ይቤሎ እግዚእ ለእግዚእየ ንበር በየማንየ እስከ ኣገብኦሙ ለጸላእትከ ታሕተ መከየደ እገሪከ” መዝ 110፥1 [የግእዝ ትርጒም]


በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተገለጸው፣ የምድር ነገሥታት ዅሉ ለዳዊት ተገዢ ናቸው (መዝ.2፥10-12)፤ እንዲያውም በመዝሙር 89፥27 ላይ፣ “እኔም ደግሞ በኵሬ አደርገዋለኹ፤ ከምድር ነገሥታትም በላይ ከፍ ይላል” የሚል ኀይለ ቃል ተጽፎ ይገኛል፤ ይህም ማለት የዳዊት ጌታ  ሊኾን የሚችል አንዳችም ምድራዊ ፍጥረት የለም ማለት ነው። ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ግን በመግቢያው ላይ ያነበብነውን ኀይለ ቃል በመናገር ከርሱ የሚበልጥ ጌታ እንዳለው ይናገራል። እንግዲህ ከዳዊት የሚበልጥ አንዳችም ምድራዊ ፍጥረት ከሌለና፣ ዳዊት ደግሞ ጌታዬ ብሎ በእግዚአብሔር ቀኝ መቀመጡን የመሰከረለት አካል ካለ፣ ይህ አካል መለኮታዊ   መኾኑ አያጠያይቅም። ፀሓየ ጽድቅ ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዳዊት መለኮትነቱ የተመሰከረለት መሲሕ ርሱ መኾኑ በቅዱስ ወንጌሉ ላይ በመናገር መለኮትነቱን ያጸናል (ማቴ 22፥43-45)።  ኾኖም ግን ፀረ ሥላሴያውያን የኾኑ ወገኖች፣ “በመዝ.110፥1 ላይ ልብ አምላክ ቅዱስ ዳዊት መሲሑን ጌታ ያለው ‛አዶኒ’ በሚል የዕብራይስጥ ቃል መኾኑንና በዚህ ቃል ደግሞ ምድራዊ እና ሰማያዊ ፍጥረታትን እንጂ እውነተኛውን የእሥራኤል አምላክ ለማመልከት አንዳችም ጊዜ እንዳልገባ ይሞግታሉ፤ ይልቁንም ዳዊት መሲሑን መለኮት መኾኑን ቢገነዘብ ‛አዶኒ’ ከሚለው ቃል ይልቅ ‛አዶናይ’ የሚል ይጠቀም ነበር” ይላሉ። እንግዲህ በ אֲדֹנִ֖י “አዶኒ” እና אֲדֹנָי “አዶናይ” መኻከል ያለው ልዩነት፣ “አዶኒ” በሚለው ቃል ሥር “ሔሬቅ” የምትባል አናባቢ (Vowel) ስታርፍ፣  “አዶናይ”  በሚለው ላይ ደግሞ “ቃሜጽ” የምትባል አናባቢ ማረፏ ነው። ኾኖም ግን መታወቅ ያለበት መሠረታዊ ነገር ቢኖር የዕብራይስጥ ቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፉት ያለ ምንም አናባቢ ነቁጦች (Vowel Marks) በተነባቢ ሆህያት (Consonants) ብቻ ነው። በዕብራይስጥ ቅዱሳት መጻሕፍት አናባቢ ነቁጦች የተጨመሩት ከመኻከለኛው ክፍለ ዘመን በዃላ ነው፤ ይህንም ማለት ‛አዶናይ’ እና ‛አዶኒ’ ምንም ልዩነት በሌላቸው በአራቱ ተነባቢ ፊደላት፣ ማለትም፣ א(አሌፍ)፣ ד(ዳሌት)፣ נ(ኑን)፣ እና י(ዮድ) ብቻ  የተጻፉ ናቸው ማለት ነው። ስለዚህ የፀረ ሥላሴያውያን ሙግት በመኻከለኛው ክፍለ ዘመን በተጨመሩት አናባቢ ነቁጦች (በእብራይስጥ ኒቁድ ነው የሚባሉት) ላይ የተመሠረተ ስለኾነ  ሙግታቸው ከጅምሩ ውድቅ  ይኾናል።

ኹለተኛ፦ እንዲሁ ለውይይት ያኽል አናባቢ ነቁጦች ተጨምረው መሲሑ ‛አዶኒ’ ቢባል እንኳ መለኮታዊነቱን ቢያጐላ እንጂ አይቀንሰውም፤ እንዴት ከተባለ በቍጥር 1 ላይ “አዶኒ” የተባለው መሲሕ በእግዚአብሔር ቀኝ መኾኑን ከነገረን ከተወሰኑ ቍጥሮች በዃላ በቍጥር 5 ላይ “አዶናይ” በሚል ቃል ተጠርቶ፣ በእግዚአብሔር ቀኝ መኾኑን ይነግረናል። ምዕራፉን ይዘን ቍጥር 7 ላይ ስንደርስ ደግሞ ይህ በቍጥር 5 “አዶናይ” ተብሎ የተገለጸው አካል በአሕዛብ ላይ ፍርድን የሚያመጣ ደግሞም ራሳቸውን የሚሰብር የዳዊት ጌታ እንደኾነ በመናገር፣ ከድሉ በዃላ ከወንዝ ውሃ እንደሚጠጣ ይናገራል፤ ይህ ደግሞ የሰውኛ ግብር በመኾኑ መሲሑን የሚመለከት ነው። ጥቅሱን እናንብብ፦

ቊጥር 5፥7፦ “ጌታ (አዶናይ) በቀኝኽ ነው፤ በቍጣውም ቀን ነገሥታትን ያደቃቸዋል። በሕዝቦች መካከል ይፈርዳል፤ በየአገሩ ያሉትንም ራሶች ከስክሶ ሬሳ በሬሳ ያደርጋቸዋል። መንገድ ዳር ካለች ፈሳሽ ውሃ ይጠጣል፤ ስለዚህ ራሱን ቀና ያደርጋል።”

በቊ.7 ላይ መሲሑ ራሱን (ዐንገቱን) ቀና አድርጐ ውሃ መጠጣቱ የሚያመለክተው፣ የጠጣው ውሃ በጦርነት ያሳለፈውን ሥጋዊ ኀይሉን ለማደስ  የተደረገ መኾኑን ነው። ዐዲሱ የእንግሊዘኛ ትርጒም (NET) የተሰኘ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ባዘጋጀው የጥናት ማብራሪያ ይህንን ክፍል አስመልክቶ የሚከተለውን ብሏል፦

“ራሱን ቀና ያደርጋል” የሚለው አገላለጽ የሚያመለክተው ከውጊያው በዃላ ኀይልን የሚሰጠውን ውሃ ጠጥቶ መጠንከሩን ነው፤ አሸናፊ ተዋጊ ከውጊያ በዃላ ውሃ በመጠጣት ኀይሉን እንደሚያድስ ሌላ ምሳሌ፣ በመሣ. 15፥18-19 ተመልከት።[1]”

 ይህ ወደ ቀጣዩ ነጥባችን ያሻግረናል። በመዝሙረ ዳዊት 2 መሠረት የብሔራትን ነገሥታት የሚያጠፋው መሲሐዊው ንጉሥ ነው። የሚከተሉትን ያነጻጽሩ፦

መዝ. 110፥5-6 “ጌታ በቀኝኽ ነው፤ በቍጣውም ቀን ነገሥታትን ያደቃቸዋል። በሕዝቦች መካከል ይፈርዳል፤ በየአገሩ ያሉትንም ራሶች ከስክሶ ሬሳ በሬሳ ያደርጋቸዋል።” (ዐዲሱ መ.ት)

መዝ.2፥7-12 “የእግዚአብሔርን ሕግ ዐውጃለኹ፤ ርሱም እንዲህ አለኝ፤ “አንተ ልጄ ነኽ፤ እኔ ዛሬ ወለድኹኽ፤ ለምነኝ፤ መንግሥታትን ርስት አድርጌ፣ የምድርንም ዳርቻ ግዛት እንዲሆንኽ እሰጥኻለኹ። አንተም በብረት በትር ትቀጠቅጣቸዋለኽ፤ እንደ ሸክላ ዕቃ ታደቃቸዋለኽ።” ስለዚህ እናንት ነገሥታት ልብ በሉ፤ እናንት የምድር ገዦችም፣ ተጠንቀቁ። እግዚአብሔርን በፍርሀት አገልግሉት፤ ለእርሱ መራድም ደስ ያሰኛችኹ። እንዳይቈጣና በመንገድ እንዳትጠፉ፣ ዝቅ ብላችሁ ልጁን ሳሙት፤ ቍጣው ፈጥኖ ይነዳልና። ርሱን መጠጊያ የሚያደርጉ ዅሉ የተባረኩ ናቸው።”

ስለዚህ አሕዛብን የሚያጠፋው ያህዌ ሳይኾን በቀኙ ያለው መሲሑ ነው፤ ስለዚህም ርሱ አዶናይ ነው።

[1] https://netbible.org/bible/Psalms+110


መሲሁ ኢየሱስ