ጎልማሳ ወንዶችን ጡት ማጥባት ዝሙትን ይከላከላል? አሳፋሪ የሙሐመድ አስተምህሮ

ጎልማሳ ወንዶችን ጡት ማጥባት ዝሙትን ይከላከላል? አሳፋሪ የሙሐመድ አስተምህሮ

በወንድም ትንሣኤ


ሙስሊም ሰባኪያን የተለያዩ አሳፋሪ እስላማዊ አስተምህሮዎችን ሸፋፍኖ ለማለፍ ሲሉ ብዙ አይነት ውሸትና ማታለል ሲጠቀሙ ማየት የተለመደ ነው። ከነዚህ አሳፋሪ ትምህርቶች አንዱ የጉርምስና እድሜ የደረሱ ወንድ አማኞችን ጡት በማጥባት ከሴቶቹ ጋር ዝሙት እንዳይሰሩ ማድረግ እንደሚቻል ሙሐመድ የሰጠው ትዕዛዝ ይጠቀሳል። ይህ ከ ‘እሳት ላይ ቤንዚን መጨመር’ ጋር የሚመሳሰል ትዕዛዝ ታዲያ በሰባተኛ ክፍለዘመን አረቦች አዕምሮ እንኳን ተቀባይነት ያጣ መሆኑን ብዙ እስላማዊ ምንጮችን ዋቢ አድርገን ማየት እንችላለን። ለዚህም ይመስላል ሙስሊም ሰባኪያን ከካሊፎች ዘመን ጀምሮ እስካሁን ድረስ የተለያዩ ውሸቶችን በመፈብረክ ይህንን የሙሐመድ አሳፋሪ ትዕዛዝ ‘የተሻለ’ አስመስለው ለማቅረብ ሲሞክሩ የሚስተዋለው ፤ ከነዚህ ውስጥ የተወሰኑትን እንመልከት።

፩- “ይህ ጡት የማጥባት ትዕዛዝ የተሰጠው ሳህላ ለተባለች አንድ እንስት ብቻ እንጂ ለሁሉም ሙስሊሞች የተሰጠ ትዕዛዝ አይደለም።”

ይህ የመጀመሪያውና ብዙ ጊዜ ደጋግመን የምንሰማው ትርክት ማስረጃ ቢስ ከመሆኑ ባለፈ ከእውነት የራቀም ጭምር ነው። ምንም እንኳን ሙሐመድ በመጀመሪያ «አጥቢው» የሚለውን ትዕዛዝ የሰጠው ለሳህላ ቢሆንም ይህ ግን ትዕዛዙን ለእርሷ ብቻ የተሰጠ አያደርገውም። መሰረታዊ የሱኒ ኢስላም አስተምህሮ ሙሐመድ ያዘዘውንና ያደረገውን በሙሉ በመከተል የተመሰረተ እንደመሆኑ ማንኛውም ሙስሊም አንድን የሙሐመድ ትዕዛዝ ከመከተል ታቅቦ ‘ለአንድ ሁኔታ ብቻ የተሰጠ ነው’ ሲል ለዚህ በቂ ማስረጃ ማቅረብ አለበት። የቱም ሙስሊም ስኮላር በሙሐመድ ሐዲሳትም ሆነ በቁርኣን ተመስርቶ እስካሁን ይህንን ሊያደርግ እንዳለመቻሉ ‘የጡት ማጥባት ትዕዛዙ ለአንድ ሁኔታ ብቻ የተሰጠ ነው’ የሚለው ሀሳብ መሰረተ ቢስ እንደሆነ ግልጽ ነው።

ለምሳሌ ሙሐመድ ከዒድ ጸሎት በኋላ ሁለት በጎች ለመስዋዕት ማረድ እንደሚገባና ከዒድ ጸሎት በፊት የሚታረድ በግ ለአላህ እንደሚሰጥ መስዋዕት እንደማይቆጠር አስተምሯል። ይህንን ትዕዛዝ ባለማወቅ የተላለፈ አቡ ቡርዳ የተባለ አንድ ሙስሊም መጥቶ «የቀረችኝ አንድ በግ ናትና እሷን አሁን ባርዳት እንደ መስዋዕት ይቆጠርልኝ ይሆን?» ብሎ ሙሐመድን በጠየቀበት ሰዓት “አዎ ይቆጠርልሃል ፤ ካንተ በኋላ ግን ለማንም አይቻልም” በማለት ፍቃዱ ለአቡ ቡርዳ ብቻ የተሰጠ መሆኑን በግልጽ ተናግሯል።[1] ታዲያ ለምን በተመሳሳይ ለሳህላም “ጡትሽን እንድታጠቢው ተፈቅዷል ፤ ካንቺ በኋላ ግን ለማንም አይፈቀድም” ብሎ አልነገራትም? ሙስሊም ወገኖች ይህ በሆነበት ሁኔታ ከምን ተነስተው ነው ትዕዛዙ ለሳህላ ብቻ ነው የሚሉን ከተባለ የሙሐመድ ትዕዛዝ ያሳፈራቸው ሚስቶቹና (አይሻን ሳይጨምር) ሰሃቦቹ ያለ ምንም ማስረጃ ይህ ትዕዛዝ ለሳህላ ብቻ የተሰጠ እንደሆነ ይናገሩ ስለነበር ብቻ ነው።[2]

ከሙሐመድ ሚስቶች አንዷ የሆነችው ኡም ሳላማ ለምሳሌ ይህንን ትዕዛዝ ትቃወም ነበር። 

“ኡም ሳላማ ለአይሻ እንዲህ አለቻት- «ጉርምስና የደረሰ ወጣት ወንድ ሊያይሽ (ወደቤት) ይገባል። እኔ ግን ማንም ቢሆን በዚህ መልክ (ጡት በመጥባት) እንዲመጣብኝ አልፈልግም።» አይሻም «የአላህ መልእክተኛ አርአያሽ አይደሉምን?» አለቻት።…”[3] በእርግጥም አይሻ እንዳለችው ሙሐመድ አርአያዬ ነው የሚል ሰው በሙሉ ትዕዛዙ ለአንድ ሁኔታ የተሰጠ እንደሆነ ማስረጃ ከሌለው በቀር ሙሐመድ ያዘዘውን ተቀብሎ ሊተገብረው ይገባል። ኢብን ማጃህ በሐዲስ ስብስቡ ላይ ትላልቅ ሰዎችን ጡት የማጥባት ትዕዛዝ በቁርኣንም ጭምር እንደነበረ ጠቅሶ እንዲህ ይላል-

“ይህ ትዕዛዝ በሕግ ደረጃ ሳይሻር በንባብ ደረጃ ከተሻሩ የቁርኣን አንቀጾች አንዱ ነው። ሌሎች ሐዲሶች ጡት ማጥባቱ አምስቴ መደረግ እንዳለበት ይደነግጋሉ።”[4]

ጡት ማጥባት በአጠቃላይ የስጋ ዝምድና የሚከለክለውን ሁሉ እንደሚከለክል በግልጽ ከሙሐመድ በአይሻ በኩል የተዘገበ ሐዲስ መኖሩ ደግሞ ይሄንን የመጀመሪያው መልስ እጅግ ደካማ ያደርገዋል።[5] ኢማም ሙሐመድ አል-ሻውካኒ ይደመድማል-

“አብዛኞቹ ኡላማዎች ጡት ማጥባት ዝምድና የሚያስገኘው በሕጻንነት ከተፈጸመ ብቻ እንደሆነ ይናገራሉ ፤ የነቢዩ ሚስቶችን ተከትለውም ለሳሊም የተሰጠው ትዕዛዝ ለእርሱ ብቻ የተሰጠ እንደሆነ ይናገራሉ። አይሻ ግን ለአንድ ሁኔታ ብቻ የተሰጠ ከሆነ ለእርሱ ማስረጃ እንዲያቀርቡ ጠይቃለች ፤ እነርሱም አይሻ ያመጣችውን ሙግት ተቀብለዋል።… ትዕዛዙ ለአንድ ሁኔታ የተወሰነ ነው ለማለታቸው ምንም ምክንያት የላቸውም። ለዚህም ነው አይሻ «ነቢዩ አርአያሽ አይደሉምን?» ብላ በጠየቀቻት ጊዜ ኡም ሳላማ ዝም ያለችው። ይህ ትዕዛዝ ለሳሊም ብቻ የተሰጠ ቢሆን ኖሮ ነቢዩ ለአቡ ቡርዳ የሰጠውን ትዕዛዝ ውስንነት እንደገለጸ ሁሉ የዚህንም በገለጸው ነበር።”[6]

፪- “ሳህላ ወተቷን ያጠባችው ቀጥታ ከጡቷ ሳይሆን በብርጭቆ ወይም መሰል እቃ ነው”

ይሄኛው መልስ ደግሞ ጡት የማጥባት ሂደቱን ከመካድ ይልቅ የድርጊቱን ሂደት የተሻለ አስመስሎ ለማቅረብ የተደረሰ ነው። ሙስሊም ወገኖች ለዚህ የሚያቀርቡት ማስረጃ አንድ ዳኢፍ ሐዲስ ነው:-

“ኢብን ሰዓድ- አልዋቂዲ- ሙሐመድ ኢብን አብደላህ ቢን አሂ ዙህሪ ከአባቱ ዘግቦታል- ሳህላ (ለሳሊም) ወተቷን በእቃ አድርጋ ትሰጠውና ለአምስት ቀን ይጠጣ ነበር ፤ ከዚያም ወደ እርሷ መግባት ጀመረ።”[7]

ከላይ እንደምታዩት ከሐዲሱ ተራኪዎች አንዱ አልዋቂዲ ነው። ይህ ተራኪ ደግሞ ኢማም ቡኻሪይ ፣ ኢማም ሙስሊም ፣ አቢ ዳዉድና ኢማም አሽ-ሻፊን ጨምሮ በብዙ ትላልቅ ሙስሊም ስኮላሮች “ሐዲስ ፈብራኪ” ተብሎ የተፈረጀ ነው።[8] ይህ ሆኖ ሳለ ሙስሊም ሰባኪያን የእርሱን ሐዲስ እየጠቀሱ መሰል አስተምህሮዎችን ለማስተባበል ሲሞክሩ ማየት ያሳዝናል።

በሱኒ ኢስላም ሰፊ ተቀባይነት ያለው ሼኽ ኢብኑ ተይሚያህ ግን ማጥባትን የሚገልጸው በዚህ መልኩ ነው።

“ጡት መጥባት ማለት (የሴቷን) ጡት ይዞ የተወሰነ ወተት ከጠጣ (ከጠባ) ነው።…”[9]

የጡት መጥባት ቀጥተኛ ትርጓሜ ይህ ሆኖ ሳለና ሳህላ ለሳሊም ወተቷን በእቃ ታጠጣው እንደነበር ምንም ማስረጃ በሌለበት ሁኔታ እንዴት ነው ሙስሊሞች ይህንን ሀሳብ እንድንቀበል የሚጠብቁት?

ይህ ትርጓሜ እንደ ኢብን ሃዝም ባሉ ስኮላሮችም የሚደገፍ አይደለም። ኢብን ሃዝም በመጽሐፉ “ሰውየው የሴትየዋን ወተት ቀኑ ሙሉ እንደ ምሳው ቢመገበው እንኳን በእቃ የሚጠጣው ወተት ሰውየውን ማህረም ለማድረግ በቂ አይደለም።” ይላል።[10]

ማጠቃለያ 

ሙስሊም ምሁራን ይህንን አሳፋሪ የሙሐመድ ትዕዛዝ ለመጣል የሚጠቀሙበት መንገድ በሙሉ ደካማ መሆኑ ግልጽ ነው። አንዲት ሴትና አንድ ወንድ ዝሙት እንዳይፈጽሙ ሲባል ወንዱ የሴቷን ጡት እንዲጠባ ማድረግ በሃያ አንደኛ ክፍለዘመን ለሚኖር ሰው ቀርቶ በሙሐመድ ዘመን ሰዎች ንቃተ ህሊና እንኳን ሊታመን የማይችል እብደት ነው። ይባስ ብሎ ቀደምት እስላማዊ ምንጮችን ስናገላብጥ ይህ አሳፋሪ ትዕዛዝ በቁርኣን ሳይቀር ተጠቅሶ እንደነበር አይሻ መዘገቧ ደግሞ ሙሐመድ ምን ያህል ሰው ሰራሽ አስተምህሮዎቹን መለኮታዊ አስመስሎ ለማቅረብ የሚተጋ ለፈጣሪ ክብር የሌለው ሀሰተኛ ነቢይ እንደነበር ያሳያል።[11]


[1] Sahih Al-Bukhari, Book 13 Hadith number 7.

[2] Sahih Muslim, Book 17 Hadith number 38.

[3] Ibid. Hadith number 36.

[4] Sunan Ibn majah, Book 9 Hadith number 100.

[5] Sahih Muslim Book 17 Hadith number 1. Muwatta Malik Book 30 Hadith number 16.

[6] Muhammad Al-shawkani, Nayl Al-awtar, Volume 6 pp.254.

[7] Ibn Hajar Al-asqalani, Al-Isabah fi Tamyiz al-Sahabah, Volume 8 pp.193.

[8] Abd al-Ghani al-Maqdisi, Tahdhīb al-kamāl fī asmā’ al-rijāl, Volume 26 pp.185-187.

[9] Ibn Taymiyyah, Majmu al-Fatawa al-Kubra, Volume 34 pp.57.

[10] Ibn Hazm, Kitab al-Muhallā bi’l Athār, Volume 10 pp.185.

[11] Sunan Ibn majah, Book 9 Hadith number 100.


ሙሐመድ