የዕዝራና የነህምያ የቁጥር ልዩነቶች
ዕዝራና ነህምያ በዘሩባቤል መሪነት ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱትን ሰዎች ብዛት በተመለከተ ብዙ ልዩነቶችን ያሳያሉ፡፡ በዕዝራ ምዕራፍ 2 እና በነህምያ ምዕራፍ 7 ላይ ተመሳሳይ 32 ቤተሰቦች ተዘርዝረዋል፡፡ በቁጥር ረገድ ሁለቱ መጽሐፍት በ18 አጋጣሚዎች የሚስማሙ ሲሆን በ14 አጋጣሚዎች ይለያያሉ፡፡ በሁለቱም ዝርዝሮች መጨረሻ ላይ የተቀመጠው ድምር 42,360 ቢሆንም የሁለቱም ዝርዝሮች ተቆጥረው ሲደመሩ ከዚህ ቁጥር በታች ናቸው፤ የዕዝራ ድምር 29,818 ሲሆን የነህምያ ድምር ደግሞ 31,089 ይመጣል፡፡ በዓረፍተ ነገሮች አሰካክና በቃላት ረገድ መመሳሰሎች ቢኖራቸውም በመካከላቸው መጠነኛ የስም አጻጻፍ ልዩነቶችም ይስተዋላሉ፡፡ ይህ እንዴት ሊፈጠር ቻለ? አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት እነዚህ ልዩነቶች የእጅ ጽሑፎቹን በገለበጡ ጸሐፍት የተፈጠሩ የግልበጣ ስህተቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ ማስረጃ የሌለው ግምት ቢያስቀምጡም ችግሩን ለመፍታት በቂ ማብራርያ መስጠት ይቻላል፡፡
ሁለቱ መጻሕፍት ለንባብ እንዲያመቹ ተብለው ለሁለት የተከፈሉ ቢሆንም መጀመርያ ሲጻፉ ግን አንድ ነበሩ፡፡ በነህምያ ስም የሚታወቀውን ክፍል ዕዝራ ራሱ የነህምያን ማስታወሻዎች በመጠቀም እንደጻፋቸው ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ይስማሙበታል፡፡ ስለዚህ ጸሐፊው አንድ ከሆነ በሁለቱ ዝርዝሮች መካከል የሚገኘውን ልዩነት ሳያውቅ ይቀራል ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ ልዩነቶቹ እንዲኖሩ የፈቀደበት በቂ ምክንያት መኖር አለበት፡፡
ይህንን ካልን ዘንዳ አጠቃላይ ድምሩ ከዝርዝሩ ድምር የበለጠበትን ምክንያት በመግለፅ እንጀምር፡፡ በአማርኛ ትርጉሞች ግልፅ ባይሆንም ተቆጣሪዎቹ ወንዶች መሆናቸው በእንግሊዝኛ ትርጉሞች ውስጥ በግልፅ ይታያል፡፡ “የእስራኤልም ሕዝብ ሰዎች ቍጥር ይህ ነው” (ዕዝራ 2፡3)፡፡ ጥቅሱ በእንግሊዝኛ ትርጉሞች ቁጥር 2 ላይ የሚገኝ ሲሆን የኪንግ ጀምስ ቅጂ እንዲህ ያስቀምጠዋል፡- “The number of the men of the people of Israel”፡፡ ስለዚህ በአይሁድ ልማድ መሠረት ሴቶችና ህፃናት በቆጠራው ዝርዝር ውስጥ እንዳልተካተቱና የመጨረሻው ድምር እነርሱንም እንደሚያጠቃልል መረዳት ይቻላል፡- “ሌላ ጉባኤው ሁሉ አርባ ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ስድሳ ነበሩ” (ዕዝራ 2፡64)፡፡ “The whole congregation together was forty and two thousand three hundred…” (KJV)፡፡ ስለዚህ ዝርዝሩ የወንዶች ቁጥር ሲሆን ድምሩ ደግሞ የመላው ሕዝብ ነው፡፡ (አንዳንዶች እንደሚሉት ደግሞ ዝርዝር ቆጠራው የይሁዳና የቢንያም ነገዶችን ብቻ የሚጠቅስ ሲሆን ድምሩ ሌሎች ነገዶችንም ያካተተ ሊሆን ይችላል፡፡ በሁለቱም መንገዶች ከሄድን ዝርዝሩና ድምሩ ላለመመሳሰሉ በቂ ምክንያት አለ፡፡) በዚህ ከተግባባን የዕዝራና የነህምያ ጠቅላላ ድምር የሚመሳሰል ሆኖ ሳለ ዝርዝሩ ለምን ተለያየ? የሚለውን ጥያቄ መመለስ እንችላለን፡፡
ዕዝራ በነህምያ ውስጥ ያልተጠቀሱ 494 ሰዎችን የጠቀሰ ሲሆን ነህምያ ደግሞ በዕዝራ ውስጥ ያልተጠቀሱ 1765 ሰዎችን ጠቅሷል፡፡ እዚህ ጋር በሁለቱ መጻሕፍት መካከል የ10 ዓመታት ልዩነት መኖሩን ማስታወስ አስፈላጊ ነው፡፡ ስለዚህ መጽሐፈ ዕዝራ እና መጽሐፈ ነህምያ የዘገቡት ቆጠራ የአንድ ሕዝብ፣ ማለትም ከባቢሎን የተመለሰውን ሕዝብ ቁጥር ቢሆንም በመካከላቸው በነበረው የዘመን ክፍተት ምክንያት የነህምያ ዝርዝር የተሻሻለ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ በርግጥ ነህምያ ቆጠራውን እራሱ እንዳልፈፀመና አስቀድሞ ከተጻፈ መዝገብ ላይ እንዳገኘ ነግሮናል፡-
“አምላኬም ታላቆቹንና ሹማምቱን ሕዝቡንም ሰብስቤ እቈጥራቸው ዘንድ በልቤ አደረገ፤ አስቀድመው የመጡትን ሰዎች የትውልድ መጽሐፋቸውን አገኘሁ፥ በእርሱም እንደዚህ ተጽፎ አገኘሁ። የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከማረካቸው ምርኮኞች ወደ ኢየሩሳሌምና ወደ ይሁዳ ወደ እየከተማቸው የተመለሱት የአገር ልጆች እነዚህ ናቸው።” (ነህምያ 7፡5-6)፡፡
ነህምያ የቆጠራ መዝገብ ማግኘቱን እንጂ መዝገቡ ከዕዝራ ጋር አንድ መሆኑን አልተናገረም፡፡ ስለዚህ ነህምያ ያገኘው መዝገብና የዕዝራ ዘገባ ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም በመጣው ሕዝብ ጠቅላላ ድምር ላይ የሚስማሙ ቢሆኑም ነህምያ ያገኘው መዝገብ የተሻሻለ በመሆኑ ምክንያት ዝርዝራቸው መለያየቱን መገንዘብ ይቻላል፡፡ በሁለቱ ዘገባዎች መካከል በነበሩት ዓመታት ውስጥ የሞቱ ወገኖች ከዝርዝር ወጥተው በመጀመርያ ቆጠራ ወቅት ዕድሜያቸው ለአቅመ ቆጠራ ያልደረሱ ልጆች አድገው በዝርዝሩ ውስጥ እንደተካተቱ መናገር ይቻላል፡፡ ነህምያ በወቅቱ የሕዝቡን ቁጥር ማወቅ የፈለገው ለከተማይቱ ጥበቃ ሕዝቡን ለመመደብ ከመሆኑ አንጻር የቆጠራ መዝገቡ ከአሥር ዓመታት በፊት የነበረውን ሳይሆን በወቅቱ የነበረውን የሕዝብ ሁኔታ ማሳየቱ ግድ ይሆናል (ነህምያ 7፡3-5)፡፡
ሌላው ነህምያ በመዝገብ ተጽፎ ያገኘውን ቁጥር ለአንባብያን በዘገባ መልክ ከማቅረብ በዘለለ ለመዝገቡ ፍፅምና ወይም እንከን የለሽነት ምስክርነት እንዳልሰጠ ልብ ይሏል፡፡ በወቅቱ ተጽፎ ያገኘው መዝገብ ላይ የተጻፈውን ዝርዝርና ቁጥር ብቻ ነው የነገረን፡፡ ስለዚህ ይህ መዝገብ በዕዝራ ከተዘጋጀው የተለየና በማንኛውም ቆጠራ ወቅት እንደሚያጋጥመው ከሌላው ቆጠራ የተለየ ቁጥርና ዝርዝር ቢያስቀምጥ አስገራሚ አይሆንም፡፡ ነህምያ “አስቀድመው የመጡትን ሰዎች የትውልድ መጽሐፋቸውን አገኘሁ፥ በእርሱም እንደዚህ ተጽፎ አገኘሁ” በማለት መዝገቡን እንዳገኘ ነገረን እንጂ ፍፁም ትክክል መሆኑን አልነገረንምና፡፡ ከነ እንከኑም ቢሆን በወቅቱ ለተፈለገበት ዓላማ ተጠቅሟል፡፡ ስለዚህ ጉዳዩን ከልክ በላይ በማጋነን መመልከት አስፈላጊ አይደለም፡፡
ከላይ የቀረበው ሐሳብ ልዩነቶቹን ለማብራራት በቂ ቢሆንም የተሻለ ሐሰብ ያለው ሰው በገጹ የኢሜል አድራሻ ሊያደርሰኝ ይችላል፡፡