መላእክት አላህን ገሰጹት? የቁርኣን ደራሲ የመንፈሳዊው ዓለም ዕውቀት እጥረት

መላእክት አላህን ገሰጹት?

የቁርኣን ደራሲ የመንፈሳዊው ዓለም ዕውቀት እጥረት

በቁርኣን ውስጥ የሚገኙ ብዙ ታሪኮች ስለ መንፈሳዊው ዓለም ዕውቀት በሌለው ሰው የተደረሱ መሆናቸው በግልፅ የሚታዩ ናቸው፡፡ በዚህ ጽሑፍ የቁርኣን ደራሲ ስለ መንፈሳዊው ዓለም ዕውቀት እንደሌለው ከሚያሳዩ ታሪኮች መካከል አንዱን እንመለከታለን፡፡ አላህ ሰውን የመፍጠር ዕቅዱን ለመላእክት ባሳወቀበት ወቅት መላእክት የሰጡት ምላሽ ነው በሚል ደራሲው የሚከተለውን ልበ-ወለዳዊ ትረካ ያስነብበናል፡-

(ሙሐመድ ሆይ) ጌታህ ለመላእክት፡- «እኔ በምድር ላይ ምትክን አድራጊ ነኝ፤» ባለ ጊዜ (የኾነውን አስታውስ፤ እነርሱም) «እኛ ከማመስገን ጋር የምናጠራህ ላንተም የምንቀድስ ስንኾን በርሷ ውስጥ የሚያጠፋንና ደሞችንም የሚያፈስን ታደርጋለህን?» አሉ፡፡ (አላህ) «እኔ የማታውቁትን ነገር አውቃለሁ» አላቸው፡፡ (ሱራ 2፡30)

በዚህ የቁርኣን ጥቅስ መሠረት አላህ ሰውን ከመፍጠሩ በፊት ለመላእክት ዕቅዱን ነግሯቸው ነበር፡፡ የቁርኣን ደራሲ ስህተት የሚጀምረው መላእክት ይህንን የአምላካቸውን ዕቅድ በአክብሮት መስማትና መቀበል ሲገባቸው የፈጣሪያቸውን ዕቅድ እንደነቀፉና እንደተቃወሙ ሲገልፅ ነው፡፡ በሌላ ቦታ ላይ መላእክት እንኳንስ የአምላካቸውን ዕቅድ ሊቃወሙ ይቅርና በንግግር እንኳ የማይቀድሙት ፍፁም ታዛዦች መሆናቸውን በመግለፅ ይህንን ሐሳብ ይፃረራል፡-

“አልረሕማንም (ከመላእክት) ልጅን ያዘ አሉ፤ ጥራት ተገባው፤ አይደለም (መላእክት) የተከበሩ ባሮች ናችው፤ በንግግር አይቀድሙትም፤ (ያላለውን አይሉም)፤ እነሱም በትእዛዙ ይሠራሉ። በፊታቸው ያለውንና በኋላቸው ያለውንም ሁሉ ያውቃል፤ ለወደደውም ሰው እንጅ ለሌላው አያማልዱም፤ እነሱም እርሱን ከመፍራታቸው የተነሳ ተጨናቂዎች ናቸው።” (ሱራ 21፡26-28)

ታድያ መላእክት ከትዕዛዙ ወለም ዘለም የማይሉ እርሱን እጅግ የሚፈሩ ባርያዎች ከሆኑ ዕቅዱን የሚቃወሙበትንና የሚነቅፉበትን ድፍረት ከየት አመጡ? እንዲህ ያለ ድፍረት አሳይተውስ ከቁጣው እንዴት ተረፉ? በእብራይስጥ ቋንቋ ሰይጣን በግሪክ ደግሞ ዲያብሎስ የሚለው ቃል ትርጉሙ ከሳሽ ወይም ተቃዋሚ ማለት ሲሆን ከመላእክት ወገን የነበረውና የወደቀው እርኩስ መንፈስ በዚህ ስም ተጠርቷል፡፡ የቁርኣን ደራሲ ይህንን የሰይጣን ባሕርይ የቅዱሳን መላእክት ባሕርይ አድርጓል፡፡ የእግዚአብሔርን ዕቅድ መቃወምና መተቸት ሁሉን አዋቂነቱንና ሉኣላዊ ሥልጣኑን መቃወም በመሆኑ የከፋ ኃጢአት ነው፡፡

የቁርኣን ደራሲ ቅዱሳን መላእክትን የፈጣሪያቸውን ዕቅድ የሚቃወሙና የሚነቅፉ ብቻ ሳይሆኑ ቀናተኛ ፍጥረታት በማስመሰልም ስሏቸዋል፡፡ «እኛ ከማመስገን ጋር የምናጠራህ ላንተም የምንቀድስ ስንኾን በርሷ ውስጥ የሚያጠፋንና ደሞችንም የሚያፈስን ታደርጋለህን?» በሚለው ንግግር ውስጥ “እኛ እያለን እንዴት ሌላ ትፈጥራለህ!” የሚል የቅንዓት ስሜት መኖሩ ግልፅ ነው፡፡ በተጨማሪም “እኛ ከማመስገን ጋር የምናጠራህ ላንተም የምንቀድስ ስንኾን…” በሚለው አባባል ውስጥ ከቅዱሳን መላእክት የማይጠበቅ ክፉ ሐሳብ አለበት፡፡ እግዚአብሔርን ማምለክና ማወደስ ለመላእክት የደስታቸው ምንጭና የህልውናቸው መሠረት ነው፡፡ እግዚአብሔር በራሱ ሕያውና ሁሉን በሁሉ ስለሆነ ከመላእክት አምልኮና ውዳሴ ቢቀርብለትም ባይቀርብለትም አንዳች አይጎድልበትም፡፡ መላእክት ግን እርሱን ለማምለክ፣ ለማወደስና ለመታዘዝ ስለተፈጠሩ እርሱን ሳያመልኩ የሚኖሩት ኑሮ ከንቱና ትርጉም የለሽ ነው፡፡ ስለዚህ ቅዱሳን መላእክት “እኛ እንዲህና እንዲያ እያደረግንልህ…” በማለት ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡትን አምልኮና ውዳሴ በእርሱ ላይ እንደ ውለታ መቁጠራቸው ከእነርሱ የማይጠበቅና ትህትና የጎደለው በመሆኑ መላእክት ይህንን ተናግረዋል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነው፡፡

የዚህ ጥቅስ ቅጥፈት በዚህ ብቻ የሚያበቃ አይደለም፡፡ የሰው ልጆች ወደፊት በምድር ላይ የሚፈፅሟቸውን ክፉ ተግባራት መላእክት አስቀድመው በማወቅ አምላካቸውን “ተሳስተሃል” በማለት ሲገስፁ ካስነበበን በኋላ አላህ ክርክሩን ለመርታት የተጠቀመበትን ኢ-ፍትሃዊ መንገድ ይነግረናል፡-

“አደምንም ስሞችን ሁሏንም አስተማረው፡፡ ከዚያም በመላእክት ላይ (ተጠሪዎቹን) አቀረባቸው፡፡ «እውነተኞችም እንደኾናችሁ የነዚህን (ተጠሪዎች) ስሞች ንገሩኝ» አላቸው፡፡ «ጥራት ይገባህ፤ ከአስተማርከን ነገር በስተቀር ለኛ ዕውቀት የለንም፡፡ አንተ ዐዋቂው ጥበበኛው አንተ ብቻ ነህና» (አሉ)፡፡«አደም ሆይ ስሞቻቸውን ንገራቸው» አለው፡፡ ስሞቻቸውን በነገራቸውም ጊዜ «እኔ የሰማያትንና የምድርን ሩቅ ምስጢር ዐውቃለሁ፤ የምትገልጹትንና ያንንም ትደብቁት የነበራችሁትን ዐውቃለሁ አላልኳችሁምን?» አላቸው፡፡” (ሱራ 2፡31-33)

ከጥቅሱ እንደሚነበበው አላህ ዕቅዱን ለተቃወሙት መላእክት አዳምን መፍጠሩ ትክክል መሆኑን ለማሳመን የተጠቀመው ዘዴ አዳምን መላእክት ሳይሰሙ በድብቅ የእንስሳትን ስሞች ማስተማርና እርሱ ዳኛ ሆኖ አዳምና መላእክት ስም የመጥራት ውድድር እንዲያደርጉ ማድረግ ነበር፡፡  መላእክት የሰውን መፈጠር የተቃወሙት ሰው በምደር ላይ ደም አፍሳሽ እንደሚሆን በማወቃቸው ምክንያት እንደሆነ ቀደም ሲል ስለተገለፀ ይህ ኢ-ፍትሃዊ የሆነ ስሞችን የማወቅ ውድድር መላእክት መሳሳታቸውንና አላህ ትክክል መሆኑን የሚያረጋግጠው እንዴት ሆኖ ነው? ይህንን ማድረጉ አላህን አታላይ አያስመስለውምን?

በቁርኣን ውስጥ የሚገኘው የሰው አፈጣጠር ትረካ ሌሎች በርካታ ጥያቄዎችን ያስነሳል፡፡ ለምሳሌ ያህል፡-

  • አላህ አዳምን የፈጠረበት ዓላማ በምድር ላይ እርሱን ተክቶ እንዲያስተዳድር መሆኑን «እኔ በምድር ላይ ምትክን አድራጊ ነኝ» በማለት የገለፀ ቢሆንም አዳምን በሰማይ በሚገኘው ገነት ውስጥ ከጭቃ ፈጥሮታል፡፡ መንፈሳዊ ፅንፍ በሆነው ሰማይ ውስጥ ጭቃ አለ ማለት ነውን?
  • እንስሳትም ልክ እንደ አዳም በሰማይ ተፈጥረው ወደ ምድር ወረዱ ወይንስ በምድር ተፈጥረው ለስም ስያሜ ወደ ሰማይ ተወስደው እንደገና ወደ ምድር ተመለሱ?
  • አላህ አዳምን የፈጠረው ለምድር እንጂ ለሰማይ ካልነበረ ለሰው ልጆች ውድቀትና ሥቃይ ኃላፊነቱ የአላህ ነው ማለት ነው? የሰው ልጆች ውድቀት የእርሱ ቅድመ ውሳኔ ከሆነ አዳም የተወቀሰበት ምክንያት ምንድነው?
  • አዳምና ሔዋንን ያሳሳተው ሰይጣን ቀደም ሲል ለአዳም አልሰግድም በማለቱ ከሰማይ የተባረረ ሆኖ ሳለ አዳምና ሔዋንን ያሳሳታቸው እንደገና ወደ ሰማይ ተመልሶ ነው ማለት ነው?

የመጽሐፍ ቅዱሱ የሰው አፈጣጠር ታሪክ ግልፅና እንዲህ ካሉ ግጭቶች የፀዳ ነው፡፡ ኤደን ገነት በምድር ላይ እንጂ በሰማይ የነበረ ቦታ አይደለም (ዘፍጥረት 2፡8-15)፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለእንስሳት ስም እንዲያወጣ እንስሳቱን ወደ አዳም አመጣቸው እንጂ በድብቅ ስሞቻቸውን በማስተማር ከመላእክት ጋር ስም የመጥራት ውድድር እንዲያደርግ አላደረገውም (ዘፍጥረት 2፡19-20)፡፡

ከዚህ ውሉ ከጠፋበት የቁርኣን ታሪክ የምንረዳው የቁርኣን ደራሲ የመጽሐፍ ቅዱስን የፍጥረት ታሪክ አለመረዳቱንና ከምናቡ የፈጠረውን ታሪክ ለማያያዝ ሲሞክር ውጥንቅጥ ውስጥ መግባቱን ነው፡፡ እውን ቁርኣን የፈጣሪ ቃል ነውን?

 

ቁርኣን