ሐዋርያዊያን አበው እና የክርስቶስ አምላክነት
የክርስቶስ አምላክነት ከክርስትና ማዕከላዊ እውነቶች አንዱ ነው። ይህንን የምናምነው በቅዱሳት መጻሕፍት የተረጋገጠ እውነታ ስለሆነ ነው። ነቢያት መሲሁ አምላክ እንደሆነ አስቀድመው ተንብየዋል (ለአብነት ያህል ኢሳይያስ 9:6)። ኢየሱስም መለኮት መሆኑን ተናግሯል። የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎችም ኢየሱስን በቀጥታ “አምላክ” ብለው ጠርተውታል፣ በብሉይ ኪዳን “ያህዌ” ተብሎ ከሚታወቀው ጋርም አነጻጽረውታል። ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን የተባበረ የመጽሐፍ ቅዱስ ምስክርነት እንቀበላለን። (እነዚህን ሁሉ ማስረጃዎ ያካተተውን “ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ መሆኑን ተናግሯልን?“ በሚል ርዕስ የተዘጋጀውን ጽሑፍ ይመልከቱ።)
ይሁን እንጂ ከአዲስ ኪዳን ውጭ የነበሩት የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖችም ይህንን ተረድተው ያምኑ እንደነበር ማስተዋሉ ተጨማሪ እገዛ ያደርጋል። እነዚህ ቀደምት አማኞች ቅዱሳት መጻሕፍትን ሲያነቡና የኢየሱስን ንግግሮች እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ የተመሩ ጸሐፊዎችን ቃላት ሲያጠኑ፣ እኛ የደረስንበት ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። ከሐዋርያት በኋላ የነበሩትና “ሐዋርያዊያን አበው” በመባል የሚታወቁት የክርስቲያን ጸሐፊዎች ትውልድ፣ ኢየሱስ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ መሆኑን በአንድ ድምፅ አረጋግጠዋል። የተወሰኑ ምሳሌዎችን እንደሚከተለው እናቀርባለን፦
የአንጾኪያው ኢግናጥዮስ፦ የሐዋርያዊያን አበው መልእክታት
በ107/108 ዓ.ም ገደማ በሰማዕትነት ያለፈው የአንጾኪያው ኤጲስ ቆጶስ ኢግናጥዮስ፣ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ለተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት በርካታ ደብዳቤዎችን ጽፏል። በእርግጥም ከሌሎቹ የሐዋርያት አባቶች በበለጠ የእርሱ ጽሑፎች በብዛት በእጃችን ይገኛሉ! በእነዚህ ደብዳቤዎች ውስጥ ኢግናጥዮስ በተደጋጋሚ ኢየሱስን በሚከተሉት ሐረጎች ይጠራዋል፦
- አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ (ወደ ኤፌሶን ሰዎች መልእክት፣ ምዕራፍ 1፤ ወደ ሮሜ ሰዎች መልእክት፣ ምዕራፍ 1)።
- ክርስቶስ አምላካችን (ወደ ሰምርኔስ ሰዎች መልእክት፣ ምዕራፍ 10)።
- አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ (ወደ ኤፌሶን ሰዎች፣ ምዕራፍ 18፤ ወደ ፖሊካርፕ፣ ምዕራፍ 8)።
- አምላክ፣ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ (ወደ ሰምርኔስ ሰዎች፣ ምዕራፍ 10)።
- አምላክ ራሱ በሰው አምሳል ተገለጠ (ወደ ኤፌሶን ሰዎች፣ ምዕራፍ 19)።
- በሥጋ ውስጥ የሚኖር አምላክ (ወደ ኤፌሶን ሰዎች፣ ምዕራፍ 7)።
ስለ ኢየሱስ እንዲህ ሲል በጠንካራ ቃላት መስክሯል፦
“ስለ እግዚአብሔር ስንል ሁሉንም ነገር ልንታገስ ይገባናል፣ እርሱም እኛን ይታገሰን ዘንድ። ካለህበት ይበልጥ አብዝተህ ትጉህ ሁን። ዘመኑንም በሚገባ መርምር። ከዘመን ሁሉ በላይ የሆነውን፣ የማይታየውንና ዘላለማዊውን፣ ነገር ግን ስለ እኛ የታየውን፤ የማይዳሰሰውንና መከራ የማይቀበለውን፣ ነገር ግን ስለ እኛ መከራ የተቀበለውን፤ እንዲሁም በሁሉም መንገድ ስለ እኛ መከራን የታገሰውን እርሱን ተጠባበቅ” (ወደ ፖሊካርፕ መልእክት፣ ምዕራፍ 3)።
እንደ ማንኛውም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ክርስቲያን ኢግናጥዮስ አብንና ወልድን ለይቶ ቢያሳይም፣ ሁለቱም ግን አንድ እውነተኛ አምላክ መሆናቸውን በግልጽ አስቀምጧል።
ፖሊካርፕ፦ ታዋቂው ቀደምት ሰማዕት
ፖሊካርፕ በ69 ዓ.ም አካባቢ ተወልዶ በሁለተኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ በሰማዕትነት አልፏል። በጥንታውያን ምንጮች መሠረት የሐዋርያው ዮሐንስ ደቀ መዝሙር የነበረና በሰምርኔስ በኤጲስ ቆጶስነት ያገለገለ የእምነት አባት ነበር። በፖሊካርፕ ተጽፎ በደረሰን አንድ ደብዳቤ ላይ እንዲህ ሲል ጽፏል፦
“አሁንም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት፣ እንዲሁም ዘላለማዊው የክህነት አለቃ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ፣ በእምነትና በእውነት፣ በየዋህነትም ሁሉ፣ ከቁጣ በመራቅና በትዕግሥት፣ በጽናትና በንጽሕና ያሳድጋችሁ፤ በቅዱሳኑም መካከል ዕድልንና ክፍልን ይስጣችሁ፣ ለእኛም ከእናንተ ጋር፣ ከሰማይ በታች ላሉትና በጌታችንና በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ፣ እርሱንም ከሙታን ባስነሳው በአባቱ በሚያምኑ ሁሉ ዘንድ ዕድልን ይስጣችሁ” (ፖሊካርፕ፣ ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች መልእክት፣ ምዕራፍ 12)።
እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው፣ በታወቁት የ “Ante Nicene Fathers” ስብስቦች ውስጥ የሮበርትስ-ዶናልድሰን ትርጉም፣ በጥቂት የላቲን ጥንታዊ ጽሑፎች ላይ በመመሥረት ሐረጉን “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ” ብቻ ብሎ ይተረጉመዋል። ይሁን እንጂ በአብዛኞቹ ጥንታዊ ጽሑፎች፣ እንዲሁም ለዚህ ምዕራፍ እጅግ ጥንታዊና ምርጥ በሚባሉት ጽሑፎች ላይ ፖሊካርፕ ኢየሱስን “ጌታም አምላክም” ብሎ ይጠራዋል። የታወቁት የላይትፉት (Lightfoot) እና ሌክ (Lake) ትርጉሞች “ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ” የሚለውን ንባብ ያጸናሉ። የሊቃውንት ስምምነትም የፖሊካርፕ ትክክለኛ ንባብ “ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ” የሚለው መሆኑን ነው።
ስለ ፖሊካርፕ ሰማዕትነት በሚገልጹ የቀድሞ ዘገባዎች መሠረት፣ በሞተበት ቀን እንዲህ ብሎ ጸልዮአል፦
“ስለዚህም ስለ ነገር ሁሉ አመሰግንሃለሁ፣ እባርክሃለሁ፣ ካንተና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር፣ ከዘላለማዊውና ሰማያዊው ከተወዳጁ ልጅህ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አከብርሃለሁ፤ ዛሬም ለዘላለሙም ክብር ይሁን። አሜን” (The Encyclical Epistle of the Church at Smyrna Concerning the Martyrdom of the Holy Polycarp, Chapter 14)።
የሚያስደንቀው ግን፣ ከፖሊካርፕ ንግግሮች ባሻገር ሌሎች የማስረጃ መስመሮችም አሉ። ከላይ እንደተጠቀሰው፣ የአንጾኪያው ኢግናጥዮስ ለፖሊካርፕ በጻፈው ደብዳቤ ውስጥ ኢየሱስ አምላክ መሆኑን በሚመለከት ያላቸውን የጋራ እምነት የሚያሳዩ በርካታ ማጣቀሻዎችን እናገኛለን። በኋላም በሁለተኛው ክፍለ ዘመን የነበረው የቤተክርስቲያን መሪ የሊዮኑ ኢሬኔዎስ (Irenaeus of Lyons) በፖሊካርፕ እግር ሥር እንደተማረ ተናግሯል። ኢሬኔዎስም በተመሳሳይ የክርስቶስን አምላክነት አጽንቷል። ስለዚህ፣ ከራሱ ቃላት በተጨማሪ፣ የፖሊካርፕ ባልደረቦች በተናገሯቸው ቃላት ውስጥ የክርስቶስ አምላክነት የእርሱ የግል እምነት ብቻ ሳይሆን በዙሪያው የነበሩትም የጋራ እምነት እንደነበር የሚያሳዩ ተያያዥ ማስረጃዎች አሉን። ስለዚህ ሁላቸውም ኢየሱስ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንዱ እውነተኛ አምላክ መሆኑን አረጋግጠዋል።”
አርስቲዴስ፦ ሐዋርያዊ አባት እና ቀደምት ዐቃቤ እምነት (Apologist)
በአቴንስ ይኖር የነበረ አርስቲዴስ የተሰኘ ክርስቲያን በ125 ዓ.ም አካባቢ ሲጽፍ የክርስትናን እምነት እንዲህ ሲል ገልጾታል፦
“እንግዲህ ክርስቲያኖች የሃይማኖታቸውን መጀመሪያ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ብለው ይናገራሉ፤ እርሱም የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ተብሎ ይጠራል። እግዚአብሔርም ከሰማይ እንደወረደ፣ ከዕብራዊት ድንግልም ሥጋን እንደተዋሐደ ይነገራል። ይህም በመካከላቸው ለጥቂት ጊዜ በተሰበከውና ወንጌል ተብሎ በሚጠራው ውስጥ የሚገኝ ትምህርት ነው፤ አንተም ብታነበው በውስጡ ያለውን ኃይል ልታስተውል ትችላለህ። ይህ ኢየሱስ እንግዲህ ከዕብራውያን ዘር የተወለደ ነው፤ የትሥጉቱ ዓላማ በጊዜው እንዲፈጸም አሥራ ሁለት ደቀ መዛሙርት ነበሩት። ነገር ግን እርሱ በአይሁድ ተወግቶ ሞተ፣ ተቀበረም፤ ከሦስት ቀንም በኋላ ተነሥቶ ወደ ሰማይ ዐረገ ይላሉ። ከዚያም እነዚህ አሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት በዓለም ወደ ታወቁት ክፍሎች ሁሉ ሄደው ክብሩን በሙሉ ትህትና ና ቅንነት ማሳየት ቀጠሉ። ስለዚህም ዛሬ ያንን ስብከት የሚያምኑት ‘ክርስቲያኖች’ ተብለው ይጠራሉ” (Apology of Aristides, Chapter 2)።
አሪስቲዴስ እውነተኛው አምላክ በሰው መልክ እንደወረደ ብቻ ሳይሆን ይህ ግንዛቤ ከወንጌላት ንባብ እንደተገኘና የክርስትያን ማህበረሰብ የጋራ እምነት እንደነበር በግልጽ ይነግረናል!
ወደ ዲዮግኔጦስ የተላከ መልእክት (Epistle to Diognetus)
በሁለተኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ አካባቢ የነበረ ስሙ ያልተጠቀሰ ክርስቲያን ጸሐፊ፣ የኢየሱስን አምላክነትና ከአብ ጋር ያለውን ልዩነት እንዲህ ሲል ያብራራል፦
“ሁሉን የሚችል፣ የሁሉ ፈጣሪና የማይታይ የሆነው እግዚአብሔር ራሱ፣ እውነት፣ ቅዱስና የማይመረመረውን ቃሉን ከሰማይ ልኮ በሰዎች መካከል አኖረ። እንዲህም ሊታሰብ እንደሚችል፥ ማንኛውንም አገልጋይ ወይም መልአክ ወይም ገዥ ወይም በምድራዊ ነገሮች ላይ ሥልጣን ያላቸውን ወይም የሰማያት አስተዳደር ከተሰጣቸው መካከል አንድም አልላከም፤ ነገር ግን ሁሉን የፈጠረና የሠራ እርሱን ራሱን ላከው—ሰማያትን በእርሱ የሠራበትን፤ ባሕርንም በወሰን የከለለበትን፤ ከዋክብት ሁሉ በትጋት የፍርዱን ሥርዓት የሚጠብቁትን፤ ለፀሐይም ዕለት ዕለት እንድትዞር ትእዛዝ የሰጣትን፤ ጨረቃም በሌሊት እንድታበራ ያዘዛትን፤ ከዋክብትም ጨረቃን ተከትለው የሚታዘዙትን፤ ሁሉ በእርሱ ሥርዓት ተይዞ በየቦታው የተደረደሩበትን፤ ሰማያትና በውስጣቸው ያሉት ምድርና በውስጧ ያሉት ባሕርና በውስጡ ያሉት እሳትና ነፋስ እንዲሁም ጥልቁ በከፍታዎች ያሉት በዝቅታዎች ያሉት በመካከልም ያሉት ለእርሱ የሚገዙለትን ይህንን ላከላቸው። ታዲያ እንደምናስበው ለማስፈራራትና ሽብርን ለመፍጠር ነበርን? አይደለም፤ ነገር ግን በየዋህነትና በትሕትና ነው። ንጉሥ ልጁን እንደሚልክ እርሱም ልጁን ላከ፤ እንደ አምላክነቱ ላከው፤ ወደ ሰዎችም ላከው፤ መድኃኒት ሊሆንም ላከው፤ እንድንገደድ ሳይሆን እንድንታመን ፈልጎ ላከ፤ በኃይል ማስገደድ በእግዚአብሔር ባሕርይ ውስጥ ስፍራ የለውምና። (Epistle to Diognetus, Chapter 7)።
የበርናባስ መልእክት (Pseudo-Barnabas)
በእጃችን ካሉት እጅግ ቀደምት ጽሑፎች አንዱ “የበርናባስ መልእክት” በመባል የሚታወቀው ሰነድ ነው። ይህ ሰነድ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ያለውን የኢየሱስን አምላክነት እንዲህ ሲል ይገልጻል፦
“ጌታ ስለ ነፍሳችን መከራን ለመቀበል ታገሰ፣ እርሱ የዓለም ሁሉ ጌታ ሲሆን፣ እግዚአብሔርም በፍጥረት ጅማሬ ላይ ‘ሰውን በመልካችንና በምሳሌያችን እንፍጠር’ ያለው እርሱን ነው።” (የበርናባስ መልእክት፣ ምዕራፍ 5)።
ይህ አባባል ቢያንስ ኢየሱስ በፍጥረት ጊዜ ከአብ ጋር የነበረ ቅድመ-ሕልውና ያለው አካል መሆኑን ያሳያል። ጸሐፊው በመቀጠል እንዲህ ይላል፦
“ነቢያት ከእርሱ ጸጋን አግኝተው ስለ እርሱ ትንቢት ተናገሩ። እርሱም (በሥጋ መገለጥ ስለተገባው) ሞትን ያጠፋ ዘንድ ከሙታንም የሙታን ትንሣኤንም ይገልጥ ዘንድ ለአባቶች የተሰጠውን ተስፋ ይፈጽም ዘንድ፥ ለራሱም አዲስ ሕዝብን አዘጋጅቶ በምድር ሳለ የሰውን ልጆች ከፍ ከፍ ከፍ እንዳደረገው ሁሉ እንዲፈርድባቸው ያሳይ ዘንድ [ይህንን አደረገ]። ደግሞም እስራኤልን እያስተማረ ታላላቅ ተአምራትንና ምልክቶችን እያደረገ [እውነቱን] ሰበከላቸው እጅግም ወደዳቸው። ነገር ግን ወንጌሉን እንዲሰብኩ የራሱን ሐዋርያት በመረጠ ጊዜ፥ “ጻድቃንን ልጠራ ሳይሆን ኃጢአተኞችን ንስሐ እንዲገቡ ልጠራ መጣሁ” ያለውን ያሳይ ዘንድ ከኃጢአተኞች ሁሉ የበለጡትን መረጠ። ያን ጊዜ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ገለጠ። በሥጋ ባይመጣስ፥ ሰዎች እርሱን በማየት እንዴት ሊተርፉ ይችሉ ነበር? ሊጠፋ ያለውንና የእጆቹ ሥራ የሆነውን ፀሐይን ቢመለከቱ እንኳ ዓይኖቻቸው ጨረሩን መቋቋም አይችሉምና። ስለዚህ የእግዚአብሔር ልጅ ነቢያቱን ያሳደዱትን የኃጢአታቸውን ድምር ወደ መቋጫው ያመጣ ዘንድ በሥጋ መጣ።” (የበርናባስ መልእክት፥ ምዕራፍ 5)
ስለዚህ ነቢያት ከኢየሱስ ጸጋን እንዳገኙ ይናገራል፣ እንዲያውም “የእርሱ ነቢያት” ተብለው ይጠራሉ። ፀሐይም የእጁ ሥራ ናት፣ እርሱም ለራሱ ሕዝብን ያዘጋጃል። በዚህ ረገድ በርካታ ተመሳሳይ ጥቅሶች አሉ፣ ለምሳሌ፦
“ስለዚህ ኃጢአታችንን በማስተሰረይ ስለ አደሰን፣ በሌላ አርዓያ መሠረትም ስላደረገን፣ እርሱ በመንፈሱ አዲስ አድርጎ ስለ ፈጠረን የልጆች ሕይወት እንዲኖረን [የእርሱ ዓላማ ነው]። መጽሐፍ ስለ እኛ ሲናገር ለወልድ እንዲህ ይላልና፤ ‘ሰውን በመልካችንና በአምሳላችን እንፍጠር፤ በምድርም ላይ ባሉ አራዊት፣ በሰማይም ላይ ባሉ አዕዋፍ፣ በባሕርም ላይ ባሉ ዓሦች ላይ ይግዙ።’ ጌታም የተዋበውን ፍጡር ሰውን ሲመለከት፤ ‘ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት’ አለ። እነዚህ ነገሮች ለወልድ ተነገሩ።” (የበርናባስ መልእክት፣ ምዕራፍ 6)
ደራሲው ኢየሱስን በብሉይ ኪዳን የተገለጠው ያህዌ (Yahweh) እንደሆነ በሚከተሉት ክፍሎች በቀጥታ ይገልጻል፦
“እነሆ፣ በሌላ ነቢይ አማካኝነት ደግሞ ‘እነሆ ይላል ጌታ፣ ከእነዚህ ማለት የጌታ መንፈስ አስቀድሞ ካያቸው ሰዎች፣ የድንጋይ ልባቸውን አወጣለሁ፣ የሥጋንም ልብ እሰጣቸዋለሁ’ እንዳለ እኛ እንደገና ተሠርተናል። ምክንያቱም እርሱ በሥጋ ሊገለጥና በመካከላችን ሊያድር ነበርና። ወንድሞቼ ሆይ፣ የልባችን ማደሪያ ለጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ ነውና” (የበርናባስ መልእክት፣ ምዕራፍ 6)።
በተመሳሳይ መልኩ፣ የተወሰኑ የብሉይ ኪዳን የሕግና የሥርዓተ መሥዋዕት ትውፊቶችን እግዚአብሔር ለካህናቱ እንዲህ እንደሚላቸው አድርጎ ይተረጉመዋል፦
“ስለ አዲሱ ሕዝቤ ኃጢአት ሥጋዬን መሥዋዕት አድርጌ ላቀርብ ባለሁ ጊዜ፣ ሐሞት ከሆምጣጤ ጋር ለመጠጥ ስለምትሰጡኝ፣ ሕዝቡ ማቅ ለብሰውና አመድ ነስንሰው እየጾሙና እያለቀሱ ሳለ እናንተ ብቻችሁን መብላት አለባችሁ” (የበርናባስ መልእክት፣ ምዕራፍ 7)።
ስለዚህ ለሕዝቡ ሕግጋትን የሰጠው እግዚአብሔር (ያህዌ)፣ ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ሥጋውን መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበው ያው ጌታ ራሱ ነው። በዚህም መሠረት በርናባስ የእግዚአብሔርን ልጅ ከአብ የተለየ አካል ቢሆንም፣ ከአብ ጋር አንድ የሆነው ያሕዌ አምላክ እንደሆነ ይገልጻል። በእርግጥም ደራሲው በመቀጠል እግዚአብሔር በኢሳይያስ በኩል የተናገራቸውን ቃላት ይጠቅሳል፦
“ቀኑን ሙሉ እጆቼን ወደማይታዘዝ፣ በገዛ አሳቡ ክፉ በሆነ መንገድ ወደሚሄድ ሕዝብ ዘረጋሁ” (ኢሳይያስ 65፥2)።
እርሱም እግዚአብሔር “እጆቼን ዘረጋሁ” ብሎ የተናገረው ስለ ክርስቶስ መስቀል እንደሆነ ይሞግታል (የበርናባስ መልእክት፣ ምዕራፍ 12)! ኢየሱስ በመስቀል ላይ በተቸነከረ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ራሱ ለማይታዘዝ ሕዝብ እጆቹን ዘርግቶ ነበር። ስለሆነም የበርናባስ መልእክት ደራሲና እርሱ የሚወክላቸው በርካታ የቀድሞ ክርስቲያኖች፣ ኢየሱስ እርሱ አንዱ እውነተኛ አምላክ መሆኑን ተስማምተዋል።
ሄርማስ፦ የሄርማስ እረኛ (The Shepherd)
ሌላው ታዋቂ የቀድሞ ጽሑፍ “እረኛው” (The Shepherd) የተሰኘው የሄርማስ መጽሐፍ ነው። መጽሐፉ በዋናነት ስለ ንስሐ የሚያስተምር ቢሆንም፣ አብና ወልድ በፍጥረት ውስጥ አጋር መሆናቸውን እንዲህ ሲል ይገልጻል፦
“የእግዚአብሔር ልጅ ከፍጥረት ሁሉ በፊት የነበረ ነው፣ ስለዚህም በፍጥረት ሥራው ከአብ ጋር አብሮ አማካሪ ነበር።” (89:2 ወይም ምሳሌ 9፣ ክፍል 12)።
መደምደሚያ
የክርስቶስ አምላክነት በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ዘግይቶ የመጣ አስተሳሰብ አይደለም። ይህ የቀደሙት ክርስቲያን ጸሐፊዎች ሁሉ በአንድ ድምፅ የመሰከሩት እውነት ነው። ይህ እምነት በእነዚህ ጸሐፊዎች ዘንድ በስፋት የታወቀበት ምክንያት፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ስለሚገኝ ነው! መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ አምላክ መሆኑን በግልጽ ያስረዳል፣ በየዘመናቱ የነበሩ ክርስቲያኖችም የእግዚአብሔርን ቃል ሲመለከቱ ያንን ታላቅ እውነት ተረድተዋል። ይህ ገና ከመጀመሪያው ጀምሮ የነበረ እውነት ነው።
የትርጉም ምንጭ ከመጠነኛ ማሻሻያ ጋር፦ The Apostolic Fathers and the Deity of Christ by Luke Wayne
