የዋሻው ሰዎች (አስሃብ አልካህፍ) እና የቁርኣን ኩረጃ

የዋሻው ሰዎች (አስሃብ አልካህፍ) እና የቁርኣን ኩረጃ

በወንድም ትንሣኤ


በቁርኣን ውስጥ የሚገኙ የብዙ ታሪኮችን ምንጮች የመረመረ ሰው ቁርኣን መለኮታዊ ግልጠት ሳይሆን የተለያዩ የዓረብ ምድር ትረካዎችና አፈታሪኮች ስብስብ መሆኑን ለመደምደም ብዙ ጊዜ አይፈጅባቸውም። ለምሳሌ ያህል ቁርኣንን ያጠኑ ብዙ የሥነ-ቋንቋ ምሑራን መጽሐፉ ምን ያህል ከሲሪያክ ቋንቋና አፈታሪኮች እንደሚዋስ ተገንዝበዋል።[1][2] የበለጠ የሚያስገርመውና ትኩረትን የሚስበው ጉዳይ ግን ቁርኣን ውስጥ ከሲሪያክ የተወሰዱ ቃላትና አባባሎች እንዳሉ ቀደምት ሙስሊም ሙፈሲሮች ማስተዋላቸውና በአደባባይ መናዘዛቸው ነው። አንድን የቁርኣን አንቀጽ ወይም አያ ከአረብኛው ተነስቶ ማብራራት ካልተቻለ ሲሪያክ ቋንቋን ማጣቀስ የተለመደ ነበር።[3]

ከነዚህ ብዙ ውሰቶች መካከል አንዱ የሆነው በቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ በስድስተኛው ክፍለዘመን እንደተጻፈ የሚገመተው “የኤፌሶን ወጣቶች” በመባል የሚታወቀውና በቁርኣን ደግሞ እስላማዊ መልክ እንዲይዝ ሆኖ የተቀረጸው የዋሻዎቹ ሰዎች ታሪክ ነው።[4] የኤፌሶን ወጣቶች የተባለው ጽሑፍ ምን ያህል ከቁርኣን ዘገባ ጋር አንድ ዓይነት እንደሆነ ለማመሳከር ታሪኩን በአጭሩ መመልከት አስፈላጊ ነው። (ጽሑፉ ከኤፌሶን ወጣቶች ታሪክ የተወሰደ ሲሆን በቅንፍ የተቀመጠው የቁርኣን አቻው ነው)

በዚህ ታሪክ መሠረት ዴሲየስ  የተሰኘ ጣዖት አምላኪ ንጉሥ (ከ249-251ዓ.ም መካከል ሮምን ያስተዳደረ) የተወሰኑ ክርስቲያኖችን በግድ ለጣዖታቱ እንዲሰዉ ያዝዛቸዋል (18:14)። በቁጥር ሰባት ወይም ስምንት የሆኑት እነዚህ አማኞች ግን ለጣዖት በፍጹም እንደማይሰዉ በመናገር ንጉሡን አንታዘዝም ይላሉ (18:14)። ከዚህ በኋላ ንጉሡ ወደ ሌላ የመንግሥቱ ግዛት መሄድ ስለነበረበት ለጊዜው ወጣቶቹ በእስር እንዲቆዩ አዝዞ ጉዞ ይጀምራል። ወጣቶቹም ከታሠሩበት በማምለጥ ወደ አንድ የድንጋይ ዋሻ ገብተው ይደበቁና (18:16) አምላካቸው ከክፉ እንዲጠብቃቸው ጸሎት ያደርጋሉ (18:10)። በማስከተልም አምላካቸው ነፍሳቸውን ከእነርሱ በመውሰድ ጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ አስገብቷቸው ሰውነታቸውን የሚጠብቅ “ዘበኛ” በዋሻው ያኖራል (18:18)። ይህ ጠባቂ ውሻ ተደርጎ ቢቀርብም እንደ አል-ያቁቢ ያሉ ሙስሊም ታሪክ ዘጋቢዎች ጠባቂው ሰው እንደሆነና ውሻው የዚህ ሰው እንደሆነ ተናግረዋል።[5] ከረጅም ጉዞው የተመለሰው ንጉሥ ዴሲየስ ታዲያ ወጣቶቹ ያደረጉትን ተግባር ሲሰማ እጅግ በመናደድ ዋሻውን ሊያስደፍነው ይወስናል። ሁለት ሰዎች ግን አምላክ ወጣቶቹን ከእንቅልፍ እንደሚቀሰቅሳቸው በማመን የሊድ ሰሌዳ ቀርጸው (18:9) በሰሌዳው ላይ የወጣቶቹን ስም፣ የተደበቁበትን ምክንያትና መቼ ጀምሮ እንደተደበቁ የሚገልጽ ጽሑፍ ያስቀምጣሉ። በመጨረሻም አምላክ ወጣቶቹን ጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ ይከታቸዋል (18:11)።

ከብዙ ዘመናት በኋላ ከጥልቁ እንቅልፋቸው በክርስቲያኑ ንጉሥ ቴዎዶሲየስ ዘመን (ከ408-450 ዓ.ም) የነቁት ወጣቶቹ ከመካከላቸው አንዱን ስለ ከተማዋ እንዲያጣራና ምግብ እንዲሸምት ይልኩታል (18:19)። ንጉሡም በከተማዋ መለወጥ ግራ ከተጋባው ከዚህ ሰው የወጣቶቹን ታሪክ ሲሰማ ወደ ወጣቶቹ በመሄድ ወደ ከተማዋ እንዲመለሱና ሲሞቱም “በሰውነታቸው ላይ መቅደስ እንደሚገነባ” ሊያሳምናቸው ይሞክራል (18:21)። ወጣቶቹ ግን አምላካቸው የሠራው ሥራ እንደተፈጸመና “እግዚአብሔር ይህንን ተዓምር ሰዎች ሁሉ እነርሱን አይተው ትንሣኤ ሙታን እንዳለ እንዲያምኑ እንዳደረገው” በመናገር (18:21) ሕይወታቸውን በዋሻው ለማገባደድ እንደወሰኑ ያሳውቁታል።[6]

የዚህ ታሪክ ዋና ዓላማ በግልጽ እንደሚታየው የክርስቲያኖች ትንሣኤ ሙታን እውነተኛ ትምህርት መሆኑን ማሳወቅ ነው። በግልጽ እንደሚታየው ታዲያ ቁርኣን በቃላትና በሐረጋት ደረጃ ሳይቀር ከዚህ ታሪክ ተውሷል። የሲሪያክ እና ዓረብ ምድር ክርስትናን በሰፊው ያጠኑት ፕሮፌሰር ሲድኔይ ግሪፍዝ እንዲህ ይላሉ፦

“የቁርኣንን የዋሻው ሰዎች ታሪክ ከሲሪያኩ ታሪክ ጋር እያስተያየን ስናነብ ብዙ ትኩረት የሚስቡ መመሳሰሎችን እናገኛለን … በጣም አስደናቂው ነገር ደግሞ ይህ ትረካ አንዳንዴ ከሲሪያኩ ዘገባ ጋር በቃላት፣ በሐረጋትና በትረካ መንገድ ጭምር መመሳሰሎች ይስተዋሉበታል።”[7]

ይህ ምስስሎሽ ተራ አጋጣሚ ሳይሆን የውሰት ውጤት መሆኑን የሚያስረግጠው ደግሞ ቁርኣን እነዚህን ወጣቶች “የሰሌዳው ባለቤቶች” ብሎ መጥራቱ ነው። ሙስሊም ሙፈሲሮች ከኢብን ዐባስ ጀምሮ ሰሌዳ ተብሎ የተተረጎመውን የአረብኛ ቃል (አል-ረቂም) ተራራ፣ ሸለቆ፣ የተደበቁበት ግንባታ፣ የከተማው ስም፣ የወጣቶቹ መሪ ወዘተ የሚል ጉራማይሌ ትርጉም ሰጥተውታል።[8]  ይህ ሰፊ የትርጓሜ ልዩነት ሰሌዳ የሚለው ቃል ከዋሻው ባለቤቶች ጋር ያለውን ግንኙነት ካለማወቅ የመነጨ መሆኑ ግልጽ ነው። በአንጻሩ ግን የሲሪያክ ጽሑፉን ያነበበ ሰው ሰዎቹ ለምን የሰሌዳው ባለቤቶች እንደተባሉ በደንብ ይረዳል። ከላይ እንዳየነው ሰዎቹ ከመተኛታቸው በፊት በሰሌዳ ላይ የጻፉት ጽሑፍ በንጉሥ ቴዎዶሲየስና ሕዝቦቹ ተገኝቶ ለትንሣኤ ሙታን ማረጋገጫ ሆኗል። ይህንን ስንመለከት ቁርኣን ለምን ሰሌዳውን “ከምልክቶቻችን (አያት) ነው” እንዳለ ግልጽ ይሆናል።

ይህንን ካልን ዘንዳ ይህ የሲሪያክ ትረካ ወደ ቁርኣን ደራሲ ጆሮ የሚደርስበት አስተማማኝ ሰንሰለት እንዳለ ሳናይ ማለፍ የለብንም። የቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ መጽሐፍ በስድስተኛው ክፍለዘመን መጻፉ ታሪኩን ወደ ዓረብ ምድር ለመስፋፋት ከበቂ በላይ ጊዜ ይሰጠዋል። ይህ ታሪክ በሲሪያክ ክርስትያኖችም በንስጥሮሳውያንም ሰፊ ተቀባይነት ማግኘቱ ደግሞ በሙሐመድ ዙሪያ የነበሩ ዓረብ ክርስቲያኖችም ታሪኩን ያውቁ እንደነበር ያመለክታል።[9] ለታሪኩ በስፋት መታወቅ ዋናው ጠቋሚ ደግሞ ቁርኣን ራሱ ታሪኩን አድማጮቹ ቀድሞም ያውቁት እንደነበር ቅድመ ግንዛቤ በመያዝ ትረካውን ከመጀመሩ ባለፈ በሙሐመድ ዙሪያ የነበሩት ሰዎች ወደ ዋሻው የገቡት ሰዎች ብዛት ላይ ክርክር ውስጥ እንደገቡ በመዘገብ ሙሐመድ ከዚህ ክርክር ራሱን እንዲያቅብ መምከሩ ነው (18:22)። በሙሐመድ ዙሪያ የነበሩት ሰዎች ስለዚህ ታሪክ ካላወቁ በቀር የወጣቶቹ ቁጥር ላይ መከራከራቸው ትርጉም ስለማይኖረው በእርግጥም የቅዱስ ያዕቆብ ጽሑፍ ላይ የተዘገበው ታሪክ በሙሐመድ አካባቢ ታዋቂ እንደነበር መደምደም እንችላለን።

ማጠቃለያ 

ከላይ እንዳየነው ይህ የቁርኣን ዘገባ ከሲሪያክ ጽሑፎች ለመገልበጡ በቂ ማስረጃ በመኖሩ የቅዱስ ያዕቆብን ጽሑፍ ከሲሪያክ የተረጎሙት ፕሮፌሰር ኢግናዚዮ ግዊዲ እንኳን “ታሪኩ ከቃል ወግ መንጭቶ በክርስቲያን መነኩሴዎች በኩል ሙሐመድ ጋር ለመድረሱ ጥርጥር የለውም … ታሪኩ በሲሪያክ መነኩሴዎች መታወቁና በተደጋጋሚ መሰበኩ ይህንን እሳቤ ይደግፋል” በማለት ደምድመዋል።[10] ይህ ታሪክ ክርስቲያናዊ ዓላማ ይዞ የተጻፈ ቢሆንም ከአካባቢው የሰማቸውን ታሪኮች በማስለም መተረክ ልማዱ የሆነው ሙሐመድ ታሪኩን በራሱ መንገድ በማሻሻል መለኮታዊ ግልጠት አስመስሎ አቅርቧል። ሙስሊም ወገኖች ይህንን ግልጽ ኩረጃ ተመልክተው የቁርኣንን ሰው ሠራሽነት ይገነዘቡ ዘንድ እንመክራለን።


[1] Luxenberg, Christoph. (2000). Die Syro-Aramäische Lesart des Koran: Ein Beitrag zur Entschlüsselung der Koransprache.(German edition) pp.254-294.

[2] Mingana, Alphonse. (1927). “Syriac influence on the style of the Koran,”  pp.77–98. Bulletin of the John Rylands Library.

[3] Reynolds, Gabriel. (2007). The Quran in Its Historical Context. pp.249. Routledge Taylor & Francis e-Library.

[4] Baring-Gould, Sabine. (1877). Curious Myths of the Middle Ages. pp.100.

[5] Ibn Wadhih Qui Dicitur al-Ja‘qubi Historiae. Ed. M.Th. Houtsma (1969), pp.173.

[6] Reynolds, Gabriel. (2007). The Quran in Its Historical Context. pp.122-124. Routledge Taylor & Francis e-Library.

[7] Ibid. pp.124.

[8] Tafsir Ibn Kathir, Surah 18:9.

[9] Reynolds, Gabriel. (2007). The Quran in Its Historical Context. pp.130. Routledge Taylor & Francis e-Library.

[10] Guidi, Ignazio. (2012). Testi Orientali Inediti Sopra i Sette Dormienti di Efeso. pp.429. Georgias Press.


ቁርኣን