የአትናቴዎስ የሃይማኖት መግለጫ

የአትናቴዎስ የሃይማኖት መግለጫ

  1. ለመዳን የሚፈልግ ሁሉ ከሁሉም ነገር አስቀድሞ የሁሉ የሆነች የቤተ ክርስቲያን ሃይማኖትን እውነተኛ አድርጎ ሊቀበል ያስፈልገዋል።
  2. ንጹሕና ሙሉ አድርጎ ያልጠበቀው ሁሉ ያለ ጥርጥር የዘላለም ጥፋት ይደርስበታል።
  3. በሦስትነቱ አንድነቱን፥ በአንድነቱም ሦስትነቱን አምነን አንድ አምላክን እናመልካለን። ይህም እውነተኛ የክርስትና ሃይማኖት ነው።
  4. ይህንንም የምናደርገው አካላቱን ሳንደባልቅ መለኮታዊ ህልውናውንም ሳንከፍል ነው።
  5. ምክንያቱም የአብ አካል ለብቻው የወልድ ለብቻው፥ የመንፈስ ቅዱስም ለብቻው ስለሆነ ነው።
  6. ሆኖም የአብ፥ የወልድና የመንፈስ ቅዱ መለኮት አንድ ነው፥ ክብሩ ሥልጣኑም እኩል ሆኖ ይኖራል።
  7. ወልድ በህልውናው እንደ አብ ነው፥ መንፈስ ቅዱስም እንደዚሁ ነው።
  8. አብ አልተፈጠረም፥ ወልድ አልተፈጠረም፥ መንፈስ ቅዱስም አልተፈጠረም።
  9. አብ ወሰን የለውም፥ ወልድ ወሰን የለውም፥ መንፈስ ቅዱም ወሰን የለውም።
  10. አብ ዘላለማዊ ነው፥ ወልድ ዘላለማዊ ነው፥ መንፈስ ቅዱስም ዘላለማዊ ነው።
  11. ቢሆነም ዘላለማዊ የሚሆን አንድ እንጂ ሦስት አይደሉም።
  12. ያልተፈጠረና ወሰን የሌለው ሦስት እንዳልሆነ እንደዚሁም ያልተፈጠረና ወሰን የሌለው አንድ ነው።
  13. እንዲሁም አብ ሁሉን የሚችል ነው፥ ወልድ ሁሉን የሚችል ነው፥ መንፈስ ቅዱስም ሁሉን የሚችል ነው።
  14. ቢሆንም፥ ሁሉን የሚችል አንድ አንጂ ሦስት አይደሉም።
  15. ስለዚህ አብ አምላክ ነው፥ ወልድ አምላክ ነው፥ መንፈስ ቅዱስም አምላክ ነው።
  16. ሆኖም አንድ አምላክ እንጂ ሦስት አማልክት አይደሉም።
  17. ስለዚህ አብ ጌታ ነው፥ ወልድ ጌታ ነው፥ መንፈስ ቅዱስም ጌታ ነው።
  18. ሆኖም አንድ ጌታ እንጂ ሦስት ጌቶች አይደሉም።
  19. ምክንያቱም የክርስትና እምነት እውነተኛነት እያንዳንዱ አካል አምላክና ጌታ መሆኑን እንድናምን እንደሚያስገድደን ሁሉ የክርስትና ሃይማኖት ሦስት አማልክት ወይም ሦስት ጌቶች እንዳንል ይከለክለናል።
  20. አብ በማንም አልተሠራም፥ አልተፈጠረም፥ አልተወለደምም።
  21. ወልድ ከአብ ተወለደ እንጂ አልተሠራም አልተፈጠረምም።
  22. መንፈስ ቅዱስ አልተሠራም፥ አልተፈጠረም፥ አልተወለደምም፥ ነገር ግን ከአብ የሚሠርጽ ነው።
  23. ስለዚህ አብ አንድ ስለሆነ ሦስት አብ አይደለም፥ ወልድም አንድ አንጂ ሦስት ወልድ አይደለም፥ መንፈስ ቅዱስም አንድ እንጂ ሦስት አይደለም።
  24. ከሦቱ አካላት አንዱ ከሌላው ቀዳሚነት ወይም ደኃሪነት የለውም፤ አንዱም ከሌላው የሚበልጥ ወይም የሚያንስ አይደለም።
  25. ስለሆነም፥ ሦስቱ አካላት በእኩልነትና በዘላለማዊነት አንድ ናቸው። ከዚህ የተነሣም ከፍ ብሎ እንደተጠቀሰው ሦስቱ አካላት በአንድ መለኮት አንድ አምላክም በሦስት አካላት ይመለካል።
  26. ለመዳን የሚፈልግ ሁሉ ስለ ሥላሴ እንደዚህ ማሰብ ይገባዋል።
  27. ከዚህም ሌላ የዘላለምን ደኅንነት ለማግኘት የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን በሥጋ መገለጽ በእውነት ማመን አስፈላጊ ነው።
  28. ምክንያቱም ትክክለኛው እምነት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ አምላክም ሰውም መሆኑን አምነን ማስታወቅ ነው።
  29. እርሱም ከዘመናት አስቀድሞ ከአብ የተወለደ አምላክ ከእናቱም በሥጋ በዓለም የተወለደ ሰው ነው።
  30. የሚያስብ ነፍስ ያለችውና የሰውን ሥጋ የለበሰ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ነው።
  31. በአምላክነቱ ከአብ ጋር የተካከለ፥ በሰውነቱም ከአብ ያነሰ ነው።
  32. አምላክም ሰውም ቢሆንም አንድ ክርስቶስ እንጂ ሁለት ክርስቶስ አይደለም።
  33. አንድ ነው ስንል ግን የሰውን ሥጋ ለበሰ እንጂ መለኮት ወደ ሥጋ አልተለወጠም።
  34. በእርግጥ አንድ የሆነውም በባሕርያት መደባለቅ ሳይን በአካል አንድ በመሆኑ ነው።
  35. ምክንያቱም የሚያስብ ነፍስና ሥጋ አንድ ሰው እንደሆኑ ሁሉ አምላክና ሰው በክርስቶስ አንድ ናቸው።
  36. እርሱም ለደህንነታችን ሲል መከራ የተቀበለ፥ ወደ ሲኦል የወረደ፥ ከሙታን የተነሣ፤
  37. ወደ ሰማይ የወጣ፥ በአብ ቀኝ የተቀመጠ፥ በሕያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ከዚያ የሚመለስ ነው።
  38. በመምጣቱ ጊዜም ሰዎች ሁሉ በሥጋ ተነስተው ስለ ሥራቸው መልስ ይሰጣሉ።
  39. መልካም የሠሩ ወደ ዘላለም ሕይወት ክፉ የሠሩም ወደ ዘላለም እሳት ይገባሉ።
  40. ይህ እውነትኛው የክርስትና እምነት ነው። ይህን የማያምንና አጥብቆ የማይዝ ሊድን አይችልም።