እውን “ዓቫድ” ለመሲሁ ጥቅም ላይ አልዋለምን?
በወንድም ሚናስ
አንድ ሙስሊም ጸሓፊ “ኢየሱስ ይመለካልን?” በሚል ርዕስ עָבַד “ዓቫድ” (አምልኮ፣ መገዛት) የሚለው ግስ ፈጽሞ ለመሲሑ ግልጋሎት ላይ እንዳልዋለ በመናገር የጌታችንን መለኮትነት እንዲህ በማለት ለማስተባበል ሞክሯል፦
“ክርስቲያኖች ኢየሱስን በቀጥታ ያመልካሉ፤ “አምልኮ” የሚለው ቃል በእብራይስጥ “አባድ” עָבַד ሲሆን፤ ይህም ለአንዱ አምላክ ብቻ በሙሉ ሁለንተና የሚቀርብ ልመና፣ ስእለት፣ማጎብደድ፣ መተናነስ፣ ስግደት፣ መገዛት ፣ አገልግሎት Adoration ነው። ኢየሱስ፦ አምልኩኝ ያለበት፣ ሀዋርያት እና ነብያት፦ ኢየሱስን አምልኩ ያለበት እና ሰዎች ኢየሱስን ያመለኩበት አንድ አንቀጽ የለም።”
በርግጥም עָבַד “ዓቫድ” የሚለው ግስ አማኞች ከአንዱ እውነተኛ አምላክ በቀር ለሌላ አማልክት እንዳያቀርቡ በጥብቅ የሚከለክሉ ምንባባት አሉ፦
“ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሩህ። በላይ በሰማይ ወይም በታች በምድር ካለው ወይም በውሃ ውስጥ ከሚኖሩት ነገሮች በማናቸውም ምስል ለራስህ ጣዖትን አታብጅ። አትስገድላቸው፤ #አታምልካቸውም(עָבַד) ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ የሚጠሉኝን ልጆች ከአባቶቻቸው ኀጢአት የተነሣ እስከ ሦስትና አራት ትውልድ ድረስ የምቀጣ ቀናተኛ አምላክ ነኝ፤” —ዘጸአት20፥3-5
“እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ጋር ኪዳን ሲገባ እንዲህ ሲል አዞአቸው ነበር፤ “ሌሎችን አማልክት #አታምልኳቸው(עָבַד)፤ አትስገዱላቸው፤ አታገልግሏቸው፤ አትሠውላቸውም” — 2ኛ ነገሥት 17፥35
ቅዱሳን ነብያት ከአምልኮ ቃላት አንዱ የሆነውን “ዓቫድ” የሚለውን ግስ ለመሲሑ ጥቅም ላይ ያዋሉባቸው በርካታ ምንባባት ቢኖሩም፣ ለናሙና ያኽል ኹለቱን እንመልከት፦
1ኛ.
“እግዚአብሔር ሆይ፤ ፍትህን ለንጉሥ፣ ጽድቅህንም ለንጉሥ ልጅ ዐድል፤…ከባሕር እስከ ባሕር ድረስ፣ ከታላቁም ወንዝ እስከ ምድር ዳርቻ ይገዛል።…ነገሥታት ሁሉ ይሰግዱለታል፤ ሕዝቦችም ሁሉ ይገዙለታል (יַֽעַבְדֽוּהוּ)።… ስሙ ለዘላለም ጸንቶ ይኑር፤ ዝናው ፀሓይ የምትኖረውን ዘመን ያህል ይዝለቅ፤ ሕዝቦች ሁሉ በእርሱ ይባረኩ፤ ሕዝቡ ሁሉ ቡሩክ ነህ ይበለው።” — መዝ 72፥1,8,11,17
ብዙ አይሁዳውያን ሊቃውንት ይህ መሲሑን እንደሚያመለክት ይናገራሉ። ይህ ማለት በዘመኑ ለሰሎሞን ቢመስልም ፍጹማዊው የትንቢቱ ምልዓት ስለ መሲሑ ነው (ማቴ. 2፥11)። የአረማይኩ ትርጉም ይህንን ጥቅስ ለመሲሑ የተነገረ መሆኑን እንዲህ አስቀምጦታል፦ “አቤቱ ጽድቅህን ለንጉሥ መሲህ ጽድቅህንም ለንጉሥ ዳዊት ልጅ ስጥ”[1]
የባቢሎናውያን ታልሙድም በተመሳሳይ፦ “ስለ መሲሑ በሚናገረው ምዕራፍ ላይ “ስሙ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል፤ ስሙም ከፀሐይ በፊት ነበረ” (መዝሙረ ዳዊት 72፡17) ተብሎ እንደ ተጻፈ የመሲሑ ስም ዓለም ሳይፈጠር ነበረ።”[2]
ታዲያ በዚህ ምንባብ በቍጥር 11 ላይ፣ “ይገዙለታል” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ግስ יַֽעַבְדֽוּהוּ “ያዓቬዱሁ” የሚል ሲሆን፣ የ עָבַד “ዓቫድ” ሦስተኛ መደብ፣ ብዜት ነው። ስለዚህ עָבַד “ዓቫድ” የሚለው ግስ ለመሲሑ ውሏል ማለት ነው።
2ኛ.
የሚከተለው ትንቢት ደግሞ እስራኤላውያን አምላክንና መሲሑን በአንድነት የሚያገለግሉበትን ጊዜን ያስታውቃል፦
“ ‘በዚያን ቀን’ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ‘በጫንቃቸው ላይ ያለውን ቀንበር እሰብራለሁ፤ እስራታቸውንም እበጥሳለሁ፤ ከእንግዲህ ባዕዳን አይገዙአቸውም። ነገር ግን ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር፣ ለማስነሣላቸውም (קוּם) ለንጉሣቸው፣ ለዳዊትም ይገዛሉ (יַעַבְדוּ) ።… መሪያቸው ከራሳቸው ወገን ይሆናል፤ ገዣቸውም ከመካከላቸው ይነሣል፤ ወደ እኔ አቀርበዋለሁ፤ እርሱም ይቀርበኛል፤ አለዚያማ ደፍሮ፣ ወደ እኔ የሚቀርብ ማን ነው? ይላል እግዚአብሔር።” ኤርምያስ 30፥8-9,21
ከላይ እንዳየነው በዚህም ቦታ በተመሣሣይ “ይገዛሉ” ለሚለው የገባው የዕብራይስጥ ግስ יַעַבְדוּ “ያዓቬዱ”የሚል ሦስተኛ መደብ፣ ብዜት ሲሆን ዋና ግሱ עָבַד “ዓቫድ” ነው። ዳዊት እዚህ ላይ የቀረበው ለሚመጣው መሲሕ እንደ ማሳያነት እንጂ ጥቅሱ ዳዊትን የሚመለከት አለመሆኑን በቀጣዩ አንቀጽ ማረጋገጥ ይቻላል፦
“እነሆ፤ ለዳዊት፣ ጻድቅ ቅርንጫፍ የማስነሣበት (קוּם) ጊዜ ይመጣል፤ እርሱም ፍትሕንና ጽድቅን የሚያደርግ፣ በጥበብ የሚገዛ ንጉሥ ይሆናል” ይላል እግዚአብሔር። በእርሱም ዘመን ይሁዳ ይድናል፤ እስራኤልም በሰላም ይኖራል፤ የሚጠራበትም ስም፣ ‘ያህዌ ጽድቃችን’ የሚል ነው።” — ኤርምያስ 23፥5-6
እግዚአብሔር በእውነትና በጽድቅ በእስራኤል ላይ ለዘለዓለም እንዲነግሥ ያስነሣው ጻድቅ ቅርንጫፍ የሆነው መሲሑን እንጂ ንጉሥ ዳዊትን አይደለም። የመሲሑን ክብር ለማላቅ ጥቅሱን አዛብታችሁ ተርጉማችኋል፣ ተብለን እንዳንከሰስ፣ የሚከተሉት የረበናተ አይሁድ ምንጮች ይኽንን ክፍል እንዴት እንደተረጎሙት እናቀርባለን፦
“እግዚአብሔር ንጉሡን መሲሕ ብሎ በስሙ ይጠራዋል። ምክንያቱ ደግሞ ስለ ንጉሡ መሲህ የሚጠራበት ስሙ ይህ ነውና ፡- ያህዌ ጽድቃችን (ኤር. 23፡6)።”[3]
“…መሲሑን በተመለከተ እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ፦ “የሚጠራበትም ስሙ ይህ ነው፤ እግዚአብሔር ጽድቃችን ነው”[4]
መሲሑ እንዲሁ ከዳዊት ዘር የመጣ ተራ ሰው አይደለም፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ለአገልጋዩ ለዳዊት የገባውን ቃል ለመፈጸም የመጣ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ነው። ስሙ ለዘለዓለም ሕያው ይሁን!
ማጣቀሻዎች
[1] Aramaic Targum to Psalms
[2] Babylonian Talmud, Pesachim 54a
[3] The Midrash on Psalms, William G. Braude, Translator (New Haven: Yale, 959), Yale Judaica Series, Volume 13, Leon Nemoy, Editor, Book One, Psalm 2.2
[4] Talmud, Bava Batra 75b