እንስሳትን በተመለከተ የተሳሳተው መጽሐፍ ቅዱስ ወይስ ቁርአን?

እንስሳትን በተመለከተ የተሳሳተው መጽሐፍ ቅዱስ ወይስ ቁርአን?


አንዳንድ ሙስሊሞች መጽሐፍ ቅዱስ ሳይንሳዊ ስህተቶችን ፈጽሟል በሚል ከሚጠቅሷቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ እንስሳትን በተመለከተ ነው። በነዚህ ሰዎች ውንጀላ መሠረት የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፍት የእንስሳትን ዓይነታትና ባሕርያት በተመለከተ ስህተቶችን ሠርተዋል። ተከታዩ ጽሑፍ ለነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ለተዘጋጀ የቀጥታ ስርጭት መርሃ ግብር የተጠቀምኩት የግል ማስታወሻ ሲሆን ለአንባቢያን ጥቅም ሲባል የተወሰነ ማሻሻያ በማድረግ ላስነብባችሁ ወደድኩ። መልካም ንባብ።

ኦሪት ዘሌዋውያን 116 ጥንቸል ታመሰኳለችን?

ሽኮኮ ያመሰኳል፥ ነገር ግን ሰኰናው ስላልተሰነጠቀ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው። ጥንቸልም ያመሰኳል፥ ነገር ግን ሰኰናው ስላልተሰነጠቀ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው።” (ዘሌ. 11፡5-6)

በዚህ ጥቅስ ውስጥ “ሽኮኮ” ተብሎ የተተረጎመው በእብራይስጥ “ሻፋን” የሚል ነው። ቃሉ በብዙ ቦታዎች ይገኛል ዘዳ. 14፡7፣ 2ነገ. 22፡3፣ 22፡8፣ 22፡9፣ 22፡10፣ 22፡12፣ 22፡14፣ 25፡22፣ 2ዜና 34፡8፣ 34፡15፣ 34፡16፣ 34፡18፣ 34፡20፣ መዝ. 104፡18፣ ምሳ. 30፡26፣ ኤር. 26፡24፣ 29፡3፣ 36፡10፣ 36፡11፣ 36፡12፣ 39፡14፣ 40፡5፣ 40፡9፣ 40፡11፣ 41፡2፣ 43፡6፣ ሕዝ. 8፡11።

አንዳንድ የእንግሊዝኛ ትርጉሞች coney በማለት የተረጎሙ ቢሆንም ትክክለኛ ትርጉሙ hyrax ነው።

“ጥንቸል” የሚለው ቃል በዕብራይስጥ “አርነቤት” የሚል ሲሆን ከዚህ ክፍል ሌላ ተጠቅሶ የምናገኘው ዘዳግም 14፡7 ላይ ብቻ ነው። የእንግሊዝኛ ትርጉሞች Hare, Rabbit ብለው ተርጉመውታል።

እነዚህ ሁለቱ እንስሳት በዓይን ዕይታ የሚያመሰኩ ቢመስሉም ነገር ግን የምግብ መፍጨት ስርአታቸውን ስንመለከት በተግባር አያመሰኩም። ለምንድነው ታድያ ያመሰኳሉ የተባለው?

1.      የእንስሳት ዝርያ ክፍፍል (Taxonomy) በየዘመናቱ ሲለዋወጥ የኖረ ሳይንስ ነው። ዘመናዊው ሳይንስ እንሰሳትን አሁን በምናውቀው መንገድ ከመከፋፈሉ በፊት የሰው ልጆች በተለያዩ መንገዶች ሲከፋፍሉ ነበር። በሙሴ ዘመንም ሽኮኮና ጥንቸል በዚህ መልኩ ተመድበው ነበር። በአሥራ ስምንተኛ ክፍለ ዘመን የኖረው “father of modern taxonomy” በመባል የሚታወቀው ስዊድናዊው ቦተኒስት Carl Linnaeus (1739–1778) ራሱ ሽኮኮና ጥንቸል የሚያመሰኩ (ruminants) ናቸው በማለት መድቦ ነበር። ይህም የሆነው ሁለቱ እንስሳት ብዙ ጊዜ እያመነዠጉ የሚታዩ በመሆናቸው ምክንያት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የታወቀው የእንስሳቱ መደብ ከሚያመሰኩት በመሆኑ ከሕጉ ዓላማ አንጻር በዘመኑ ሕዝቡ ያላወቀውን ሳይንሳዊ መረዳት መናገር አስፈልላጊ አልነበረም።

2.  በዘመኑ የነበሩት እስራኤላውያን ሁለቱን እንስሳት ከሚያመሰኩት መደብ ስለመደቧቸው ሰኰናቸው የተሰነጠቀ አለመሆኑን በማሳሰብ እንዳይበሏቸው ተከልክለዋል። ሕጉ የተሰጠው የእንስሳትን ተፈጥሯዊ መደብ ለሚመራመሩ ሳይንቲስቶች ሳይሆን እንስሳትን ለሚያድኑ አዳኞች ነው። አዳኞቹ ደግሞ እንስሳቱን ከሚያመሰኩት ወገን ስለመደቧቸው ያንን ሁኔታ በመመልከት እንዳይሳሳቱ “ቢያመሰኩም ሰኰናቸው የተሰነጠቀ ባለመሆኑ አትብሏቸው” የሚል ትዕዛዝ ተሰጥቷል።

3.   ከሳይንስ አንጻር ስንመለከት ደግሞ ጥንቸሎች (hares) ከሚያመሰኩት ወገን ለመመደብ የሚያስችል በቂ ሰበብ አለ። ይህንን በተመለከተ የዞንደርቫን ባሕረ ዕውቀት እንዲህ ሲል ያትታል፦

      Hares, like rabbits, are now known to practice “refection”: at certain times of day, when thehare is resting, it passes droppings of different texture, which it at once eats. Thus the hare appears to be chewing without taking fresh greens into its mouth. On its first passage through the gu, indigestible vegetable matter is acted on by bacteria and can be better assimilated the second time through. Almost the same principle is involved as in chewing the cud (“Hare,” in Tenney, Zondervan Pictorial Encyclopedia, 3:33)

ትርጉም፦ “ከፍ ያሉት ጥንቸሎች (hares) ልክ እንደ ጥንቸል ሁሉ መልሶ ማላመጥን እንደሚተገብሩ ታውቋል። ትልቁ ጥንቸል በቀን የተወሰኑ ጊዜያት፣ በሚያርፍበት ጊዜ፣ ትንንሽ ኮረኮሮችን ይጥላል። የሆነ ጊዜ ደግሞ ያንን መልሶ ይመገባል። ስለዚህ ጥንቸል ትኩስ ተክሎችን ወደ አፉ ሳይወስድ እያኘከ ያለ የሚመስለው ለዚያ ነው። በአንጀት ውስጥ ባለው የመጀመሪያው መተላለፊያ ላይ የማይፈጩ አትክልቶች በባክቴሪያዎች ይብላላሉ። እናም ለሁለተኛ ጊዜ ሲበላቸው በተሻለ ሁኔታ ሊዋሃዱ ይችላሉ። ማመሰኳት ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ተግባር ነው።”

ከዚህ አንጻር ካየነው መጽሐፍ ቅዱስ ጥንቸሎች እንደሚያመሰኩ መናገሩ ስህተት አይደለም ማለት ነው።

 ኦሪት ዘሌዋውያን 113-4 ግመል ሰኰናው የተሰነጠቀ ነውን?

“የተሰነጠቀ ሰኰና ያለውንና የሚያመሰኳውን እንስሳ ሁሉ ብሉ። ነገር ግን ከሚያመሰኩት፥ ሰኰናቸው ስንጥቅ ከሆነው ከእነዚህ አትበሉም፤ ግመል ያመሰኳል፥ ነገር ግን ሰኰናው ስላልተሰነጠቀ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው።”

አንዳንድ ሙስሊም ወገኖች የተሰነጠቁ የሚመስሉ የግመል ሰኰና ፎቶግራፎችን እያሳዩ “መጽሐፍ ቅዱስ ተሳስቷል” ይላሉ።

1.      እነዚህ ወገኖች የተሰነጠቀ ሰኰና ሲባል ምን ማለት እንደሆነ አላወቁም። ግመል እንደ ጣቶች ያሉ ስንጥቆች አሉት እንጂ ሰኰናው ሙሉ በሙሉ የተሰነጠቀ አይደለም። መሃል ላይ በቆዳ መሰል ነገር የተጣበቀ ነው። ይህንን አይቶ ማረጋገጥ ይቻላል። የዕብራይስጡ ቃል ግን ሙሉ በሙሉ መሰንጠቅን የሚያመለክት ነው። ዘሌዋውያን 11፡3 ላይ “የተሰነጠቀ ሰኰና ያለውንና የሚያመሰኳውን እንስሳ ሁሉ ብሉ” ሲል ጥቅም ላይ የዋለው ቃል “ማፍሬሴት” የሚል ቃል ሲሆን “ፋራስ” ከሚል ቃል የተገኘ ነው። “ለሁለት መሰንጠቅ” የሚል ትርጉም አለው። ይኸውም ዳቦ ወይም እንጀራ በሚቆረስበት መንገድ ነው። (ኢሳይያስ 58፡7)።

 6536. paras 

NAS Exhaustive Concordance

Word Origin
a prim. root
Definition
to break in two
divide
NASB Word Usage
break (1)
breaks (1) divide (8) divides (4) hoofs (1).

 

በዚህ ትርጓሜ ረገድ ግመል ትክክለኛ የተሰነጠቀ ሰኰና የለውም።

2.    በጥንት ሕዝቦች መረዳት መሠረት ግመል በዝርያም ሆነ በአገልግሎት ሰኰናቸው ካልተሰነጠቀ የጋማ ከብት የሚመደብ እንጂ ሰኰናቸው ከተሰነጠቁት የሚመደብ አልነበረም። አረቦች ራሳቸው እንዲህ ያለ መረዳት ነበራቸው። ለምሳሌ ያህል ኢብን ከሢር ሱራ 6፡146 ላይ የሚገኘውን ቃል ሲያብራራ እንዲህ ብሏል፦

Foods that were Prohibited for the Jews Because of their Transgression

Allah says We forbade for the Jews every bird and animal with undivided hoof, such as THE CAMEL ostrich duck and goose. Allah said here …

ትርጉም፦ “አይሁድ በመተላለፋቸው ምክንያት የተከለከሏቸው ምግቦች። አላህ እንዲህ አለ፣ ሰኮናው ያልተሰነጠቀ ወፍና እንስሳ ሁሉ እንደ ግመል፣ ሰጎን፣ ዳክዬ እና ዝይ ያሉትን ሁሉ ለአይሁዶች ከልክለናል።”

አረብ ሙስሊሞች ራሳቸው በቆዳ የተያያዘ ስንጥቅ ሰኰና ያላቸውን እንስሳት ሰኰናቸው ከተሰነጠቁት አይመድቡም ነበር። የዘመናችን ሙስሊሞች ምን ቤት ናቸውና ነው አዲስ አመዳደብ የሚፈጥሩት?

3.     ዘመንኛ የእንስሳት ምደባ ግመልን ሰኰናቸው ከተሰነጠቁት እንስሳት እርግጠኛ ሆኖ አይመድብም።

Camels do not walk on their hooves. On each leg፣ weight is borne on two large toes that spread apart to keep the animal from sinking into the sand. Dromedaries have a soft wide-spreading pad for walking on sand… https፡//www.britannica.com/animal/camel

ትርጉም፦ “ግመሎች በሰኮናቸው አይራመዱም። በእያንዳንዱ እግር ላይ፣ እንስሳው በአሸዋ ውስጥ እንዳይሰምጥ ክብደቱ በተነጣጠሉ ሁለት ትላልቅ ጣቶች ላይ ይጫናል። ድሮሜዳሪዎች በአሸዋ ላይ ለመራመድ ለስላሳ ስፋት ያለው ንጣፍ አላቸው።”

ሌላ ስለ ግመሎች የሚጽፍ ድረ ገጽ እንዲህ ይላል፦

Camels do not have hooves.  They are not like horses or even like the feet of goats፣ cattle, giraffe, etc. They have a soft, padded foot with toenails.  In many ways, they are very similar to our own foot or a dog’s foot with the obvious exception of having only two toes on each foot.  https፡//cameldairy.com/top-ten-camel-answers

ትርጉም፦ “ግመሎች ሰኮና የላቸውም። እንደ ፈረስ ሰኮና ወይም እንደ ፍየል፣ ከብት፣ ቀጭኔ፣ ወዘተ እንኳ አይደሉም። የጣት ጥፍሮች ያሉት ለስላሳ ሰፊ ኮቴ አላቸው። በእያንዳንዱ እግር ሁለት ጣቶች ብቻ ከመያዝ በስተቀር ከእኛ እግር ወይም ከውሻ እግር ጋር በጣም ተመሳሳይ ናቸው።”

እውነታው ይህ ከሆነ ተቺዎች መጽሐፍ ቅዱስ ተሳስቷል የሚሉበት መሠረት የላቸውም። ይልቁኑ መጽሐፍ ቅዱስን ለመተቸት ካላቸው ጉጉት የተነሳ ከእስላማዊ ምንጮች ብሎም ከታወቀው ሃቅ ጋር ተጋጭተዋል።

 ኦሪት ዘሌዋውያን1119 የሌሊት ወፍ የወፍ ዝርያ ወይስ አጥቢ እንስሳ?

“ከወፎችም ወገን የምትጸየፉአቸው እነዚህ ናቸው አይበሉም የተጸየፉ ናቸው … ይብራ፥ ጥምብ አንሣ አሞራ፥ ሽመላ፥ ሳቢሳ በየወገኑ፥ ጅንጁላቴ ወፍ፥ የሌሊት ወፍ።” (ዘሌ 11፡13፣ 19)

የሌሊት ወፍ አጥቢ እንስሳ እንጂ የወፍ ዝርያ እንዳልሆነች ይታወቃል። በዚህ መነሻ አንዳንድ ወገኖች መጽሐፍ ቅዱስ ተሳስቷል ይላሉ። እነዚህ ወገኖች ያልተገነዘቧቸው ሁለት ጉዳዮች አሉ።

1.      የእንስሳት ክፍፍል በዝርያ ላይ ብቻ የተመሠረተ ሳይሆን በሌሎች ብዙ ሁኔታዎች ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ የመኖርያ ቦታ፣ የአመጋገብ ሁኔታ፣ የእንቅስቃሴ ሁኔታ፣ ራስን የመከላከል ሁኔታ፣ ወዘተ. በዚህ ቦታ መጽሐፍ ቅዱስ የሌሊት ወፍን በዚህ ሁኔታ ሲመድብ እንቅስቃሴያቸውን መሠረት ያደረገ እንጂ ዝርያቸውን መሠረት ያደረገ አይደለም።

2.     በዚህ ቦታ የተጠቀሰው “ኦውፍ” የሚለው የእብራይስጥ ቃል በራሪ የሆኑ እንስሳትን ሁሉ ለማመልከት ጥቅም ላይ ይውላል። እዚሁ ምዕራፍ ላይ 11፡20 ላይ ክንፍ ያላቸውን ነፍሳት ለማመልከት ጥቅም ላይ ውሏል። የዕብራይስጥ መዝገበ ቃላትም ቃሉን እንዲህ ይተረጉማል፦

 5775. oph 

NAS Exhaustive Concordance

Word Origin
from 
uph
Definition
flying creatures
NASB Word Usage
bird (17)
birds (49) fowl (1) winged (3) wings (1).

 

አራት እግር ያላቸው ነፍሳት አሉን?

“ነገር ግን ከሚበርሩት፥ አራትም እግሮች ካሉአቸው፥ ከእግሮቻቸውም በላይ በምድር ላይ የሚዘልሉባቸው ጭኖች ካሉአቸው ተንቀሳቃሾች እነዚህን ትበላላችሁ። ከእነርሱም እነዚህን ትበላላችሁ፤ አራቱን ዓይነት አንበጣዎች በየወገናቸው።” (ዘሌ. 11፡21-22)

የጥንት እስራኤላውያን የአንበጣ ዝርያዎችን አራት እግር እንዳላቸው ነበር የሚያውቁት። የሚስፈነጠሩባቸውን ከኋላ ያሉ ጭኖች እግር አድርገው አይቆጥሩም፤ ምክንያቱም የኋላ ጭኖቻቸውን ለመስፈንጠር እንጂ ለመራመድ አይጠቀሙምና። በዘመናችንም አንበጦችን በተመሳሳይ መንገድ የሚገልጹ ሰዎች አሉ። በነዚህ ድረገፆች ላይ እንደሚታየው ከአራት እግሮች በተጨማሪ ሁለት መስፈንጠርያ እግሮችና የፊት መያዣ እግሮች ያሏቸው ነፍሳት አራት እግር ብቻ እንዳላቸው ተገልጸዋል፤ እንዲሁም አራት እግሮች ብቻ ያሏቸው ነፍሳት ይገኛሉ፦ https፡//naturenoon.com/4-legs-insects/ https፡//scvnews.com/four-legged-insects-commentary-by-paul-a-levine/

 ኢዮብ 41 ያለው እንስሳ ዳይኖሰር ነውን?

ኢዮብ 41 ላይ የሚገኘው ሌዋታን የሚለው ቃል ትክክለኛ ትርጉም ሊቃውንትን አከራክሯል። ነገር ግን በባሕር ውስጥ የሚኖር ግዙፍ እንስሳ ነው። አንዳንዶች አዞ ሊሆን እንደሚችል አስተያየት ቢሰጡም አገላለጹ ከአዞ የተለየና የገነነ እጅግ አስፈሪ አውሬ ነው። እንዲሆም ኢዮብ 40፡15-32 ላይ የተገለጸው ብሄሞት (አውሬ) የተሰኘ እንስሳ ጉማሬ ነው ቢባልም አገላለጹ ከጉማሬ የተለየ ነው።

“ከአንተ ጋር የሠራሁትን ጉማሬ፥ እስኪ፥ ተመልከት፤ እንደ በሬ ሣር ይበላል። እነሆ፥ ብርታቱ በወገቡ ውስጥ ነው፤ ኃይሉም በሆዱ ጅማት ውስጥ ነው። ጅራቱን እንደ ጥድ ዛፍ ያወዛውዛል፤ የወርቹ ጅማት የተጐነጐነ ነው።” (40፡15-17)።

እነዚህን እንስሳት የሚመስሉ እንስሳትን በዚህ ዘመን ማየት አይቻልም። በጥንት ሰዎች የሚታወቁ በርካታ አውሬዎች ከምድረ ገጽ መጥፋታቸው ይታወቃል። ሳይንሳዊ ጥናቶች ዳይኖሰሮች ሰዎች በምድር ላይ ሳይኖሩ በፊት እንደኖሩ ቢያሳዩም አንዳንድ ታሪካዊ ቅርሶች ዳይኖሰሮችን የሚመስሉ እንስሳት እንደነበሩ እንደሚያሳዩ ማስረጃዎችን የሚያቀርቡ ወገኖች አሉ። እርግጠኛ ሆኖ ግን መናገር አይቻልም። ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥያቄን የሚያስነሳ ጉዳይ አይደለም።

 ኢሳይያስ  3415 ዋሊያ እንቁላል ትጥላለችን?

“በዚያም ዋሊያ ቤትዋን ትሠራለች እንቍላልም ትጥላለች ትቀፈቅፈውማለች ልጆችዋንም በጥላዋ ትሰበስባለች፤ በዚያም ደግሞ አሞራዎች እያንዳንዳቸው ከባልንጀሮቻቸው ጋር ይሰበሰባሉ።”

በዚህ ክፍል ዋልያ ተብሎ የተተረጎመው ቃል “ቂፖዝ” የሚል ሲሆን እዚህ ቦታ ብቻ ነው ጥቅም ላይ የዋለው። አንዳንድ ትርጉሞች “የዛፍ እባብ” ቢሉም ብዙዎች ግን “ጉጉት” በማለት ተርጉመዋል። አዲሱ መደበኛ ትርጉም “ጉጉት” ይላል። በሀገራችን የሚገኘውን ዋልያ አይቤክስ ለማለት እንዳልሆን ማወቅ ያስፈልጋል።

የቁርአን ስህተቶች በእንስሳት ዙርያ

ከላይ እንደ ተመለከትነው ሙስሊም ወገኖቻችን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያነሷቸው ጥያቄዎች ሁሉ ከትክክለኛ መረዳት ጉድለት የመነጩ መሆናቸውን አረጋግጠናል። እስኪ አሁን ደግሞ ስህተት ማለት ምን ማለት እንደ ሆነ ይገነዘቡ ዘንድ ከቁርአን አንዳንድ ጥያቄዎችን እንጠይቃቸው።

ጉንዳኖች መናገር ይችላሉ?

በቁርአን መሠረት ጉንዳኖች መናገር ይችላሉ፤ ቋንቋቸውም ልክ እንደ ሰዎች ቋንቋዎች ከቃላትና ውስብስብ ዓረፍተ ነገሮች የተገነቡ ፅንሰ ሐሳቦችን ጭምር መሸከም የሚችሉ ናቸው፦ “በጉንዳንም ሸለቆ በመጡ ጊዜ አንዲት ጉንዳን «እናንተ ጉንዳኖች ሆይ! ወደ መኖሪያዎቻችሁ ግቡ፡፡ ሱለይማንና ሠራዊቱ እነርሱ የማያውቁ ሲኾኑ አይሰባብሩዋችሁ» አለች፡፡” (ሱራ 27፡18)

የሚገርመው ነገር በቁርኣን ውስጥ እንደተናገረች የተጠቀሰችው ጉንዳን፡-

  • ·         የሰለሞንን ስም አውቃለች
  • ·         ሰለሞን ሠራዊት እንዳሉት አውቃለች
  • ·         የሰለሞን ሠራዊት ወደዚያ ስፍራ እንደሚመጡ አውቃለች
  • ·         የሰለሞን ሠራዊት ሳያውቁ ከረጋገጧቸው ጉንዳኖቹን እንደሚሰባብሯቸው አውቃለች

·         ይህንን ኹሉ መረጃ ደግሞ በማቀናበር ልክ እንደ ሰዎች ውስብስብ የኾነን ዓረፍተ ነገር ሠርታ መናገር ችላለች።

የቁርአኑን ንባብ በአንክሮ ስናጤን የጉንዳኖች መናገር እንደ ተፈጥሯዊ ጉዳይ እንጂ እንደ ተዓምር ያልቀረበ ሲሆን ተዓምር ሆኖ የቀረበው የሰለሞን እነርሱን መረዳት ነው። ለዚህ ነው በዘመናችን የሚገኙት በርካታ ሙስሊሞች ጉንዳኖች መናገር እንደሚችሉ ሳይንስ ያረጋገጠ በማስመሰል የሐሰት ወሬ የሚያሰራጩት።

መጽሐፍ ቅዱስ ሰለሞንን በተመለከተ የሚከተለውን ቃል ይናገራል፡-

1ነገሥት 4.29-34፡- “እግዚአብሔርም ለሰሎሞን እጅግ ብዙ ጥበብና ማስተዋል በባሕርም ዳር እንዳለ አሸዋ የልብ ስፋት ሰጠው። የሰሎሞንም ጥበብ በምሥራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ጥበብና ከግብጽ ጥበብ ሁሉ በለጠ። ከሰውም ሁሉ ይልቅ ከኢይዝራኤላዊው ከኤታንና ከማሖል ልጆች ከሄማንና ከከልቀድ ከደራልም ይልቅ ጥበበኛ ነበረ። በዙሪያውም ባሉ አሕዛብ ሁሉ ዝናው ወጣ። እርሱም ሦስት ሺህ ምሳሌዎች ተናገረ፤ መኃልዩም ሺህ አምስት ነበረ። ስለ ዛፍም ከሊባኖስ ዝግባ ጀምሮ በቅጥር ግንብ ላይ እስከሚበቅለው እስከ ሂሶጵ ድረስ ይናገር ነበር፤ ደግሞም ስለ አውሬዎችና ስለ ወፎች ሰለተንቀሳቃሾችና ስለ ዓሣዎች ይናገር ነበር። ከአሕዛብም ሁሉ፥ ጥበቡንም ሰምተው ከነበሩ ከምድር ነገሥታት ሁሉ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ሰዎች ይመጡ ነበር።”

ከሁለቱ ትርክቶች የትኛው አሳማኝ እንደ ሆነ ኅሊና ካለው ሰው ሁሉ የተሰወረ አይደለም።

በቁርአን መሠረት የቤት እንስሳት ስምንት ወይም አራት ጥንዶች ናቸው

“ከአንዲት ነፍስ ፈጠራችሁ፡፡ ከዚያም ከእርሷ መቀናጆዋን አደረገ፡፡ ለእናንተም ከግመልና ከከብት፣ ከፍየል፣ ከበግ ስምንት ዓይነቶችን (ወንድና ሴት) አወረደ፡፡ በእናቶቻችሁ ሆዶች ውስጥ በሦስት ጨለማዎች ውስጥ ከመፍጠር በኋላ (ሙሉ) መፍጠርን ይፈጠራችኋል፡፡ ይህ ጌታችሁ አላህ ነው፡፡ ስልጣኑ የርሱ ብቻ ነው፡፡ ከእርሱ ሌላ አምላክ የለም፡፡ ታዲያ ወዴት ትዞራላችሁ፡፡” (ሱራ 39፡6)

እነዚህ ስምንት የተባሉት አራት ጥንዶች ሱራ 6፡142-146 ላይ ተዘርዝረዋል፦

“ከለማዳ እንስሳዎችም የሚጫኑትንና የማይጫኑትን (ፈጠረ)፡፡ አላህ ከሰጣችሁ ሲሳይ ብሉ፡፡ የሰይጣንንም እርምጃዎች አትከተሉ፡፡ እርሱ ለእናንተ ግልጽ ጠላት ነውና፡፡ ስምንትን ዓይነቶች ከበግ ሁለትን (ወንድና ሴትን) ከፍየልም ሁለትን (ፈጠረ)፡፡ «ከሁለቱም ክፍሎች አላህ ወንዶቹን እርም አደረገን ወይስ ሴቶቹን ወይስ በርሱ ላይ የሁለቱ ሴቶች ማሕፀኖች ያጠቃለሉትን እውነተኞች እንደሆናችሁ በዕውቀት (በአስረጅ) ንገሩኝ» በላቸው፡፡ ከግመልም ሁለትን ከከብትም ሁለትን (ፈጠረ)፡፡ «አላህ (ከሁለቱ) ወንዶቹን እርም አደረገን ወይስ ሴቶቹን ወይስ የሁለቱ ሴቶች ማሕፀኖች በእርሱ ላይ ያጠቃለሉትን በእውነቱ አላህ በዚህ ባዘዛችሁ ጊዜ የተጣዳችሁ ነበራችሁን ሰዎችንም ያለ ዕውቀት ሊያጠም በአላህ ላይ ውሸትንም ከቀጠፈ ሰው ይበልጥ በደለኛ ማን ነው አላህ በደለኞችን ሕዝቦች (ቅኑን መንገድ) አይመራም፡፡»”

ኢብን ከሢር እንዲህ ይላል፦

(And He has sent down for you of cattle eight pairs.) means, He has created for you from among the cattles, eight pairs. These are the ones that are mentioned in Surat Al-An`am, eight kinds — a pair of sheep, a pair of goats, a pair of camels and a pair of oxen. https፡//quranx.com/tafsirs/39.6

ትርጉም፦ “(ለእናንተም ከከብቶች ስምንት ጥንድ አወረደ) ማለት፣ ከከብቶች፣ ስምንት ጥንድ ጥንድ አድርጎ ፈጠረላችሁ ማለት ነው። እነዚህም በሱረቱል አንዓም የተገለጹት ስምንት ዓይነት ናቸው — ጥንድ በግ፣ ጥንድ ፍየል፣ ጥንድ ግመሎች እና ጥንድ በሬ (ላም)  ናቸው።”

ነገር ግን ሌሎች ከአረብያ ውጪ የሚገኙ የቤት እንስሳት (ከብቶች) አሉ፦ ጎሽ በሕንድና ቻይና፣ ሬንዲር ደግሞ በሰሜን ንfቀ ክበብ ጫፍ ይጠቀሳሉ። የቁርአን ደራሲ አህዮች፣ ፈረሶችና በቅሎዎችን ከከብቶች (አል-አንአም) ለይቶ የሚያይ ይመስላል (ሱራ 16፡5-8)። ነገር ግን በእስልምና ፈረስ እንደ ግመል ሁሉ ለመጓጓዣነትም ለምግብነትም ስለሚውል ግመል ተጠቅሶ እርሱ ለምን እንዳልተካተተ ግልጽ አይደለም። የሆነው ሆኖ የቁር አንደራሲ አስተሳሰቡ በአረብያ ምድር የተገደበ መሆኑ ግልጽ ነው።

 ሁሉም እንስሳት የሚኖሩት ልክ እንደ ሰዎች በሕብረት እንደ ማሕበረሰብ ነው

“ከተንቀሳቃሽም በምድር (የሚኼድ)፤ በሁለት ክንፎቹ የሚበርም በራሪ መሰሎቻችሁ ሕዝቦች እንጅ ሌላ አይደሉም፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ ምንንም ነገር አልተውንም ከዚያም ወደ ጌታቸው ይሰበሰባሉ፡፡” (ሱራ 6፡38)

ነገር ግን የእንስሳት የጋራ ኑሮ ከሰው አኗኗር ጋር በብዙ መልኩ ካለመመሳሰሉም በላይ ለብቻቸው ተነጥለው የሚኖሩ በርካታ እንስሳት አሉ። ለምሳሌ ያህል ሊኦፓርድና ጃጉዋርን የመሳሰሉት የነብር ዝርያዎች በነጠላ ነው የሚኖሩት። የሚገናኙት ደግሞ ለመራባት አልፎ አልፎ ብቻ ነው። የእንስሳት አኗኗር ከሰው ማሕበራዊ ኑሮ በብዙ መልኩ ይለያል።

ወፎች የሚበርሩት ተዓምራዊ በሆነ መንገድ ነው

“ወደ በራሪዎች በሰማይ አየር ውስጥ (ለመብረር) የተገሩ ሲኾኑ (ከመውደቅ) አላህ እንጂ ሌላ የማይዛቸው ኾነው አይመለከቱምን በዚህ ውስጥ ለሚያምኑ ሕዝቦች በእርግጥ ተዓምራቶች አሉ፡፡” (ሱራ 16፡79)

የወፎች መብረር እግዚአብሔር ለዚህ ፍጥረተ ዓለም በሰጠው የፊዚክስ ስርዓት ሊብራራ የሚችል ተፈጥሯዊ ጉዳይ እንጂ ተዓምራዊ ሊባል የሚችል አይደለም። ፍጥረት ሁሉ ተዓምር ቢሆንም የሰው መራመድና የዓሣ በውሃ ውስጥ መዋኘት ተፈጥሯዊ እንጂ ተዓምራዊ እንደማይባል ሁሉ የወፎች መብራርም እንደዚያው ነው። የወፎችን መብረር ተዓምር ለማለት የሌሎች እንስሳትን ሁሉ እንቅስቃሴ ተዓምር አድርጎ መቁጠር ያስፈልጋል። አምላክ ለሰው መራመድን እንደሰጠ ሁሉ ለወፎችም መብረርን ገና ሲፈጥራቸው ሰጠ እንጂ የቁርአን ደራሲ ለማስመሰል እንደሞከረው ወፎች በበረሩ ቁጥር ጣልቃ እየገባ ተዓምር እየሠራ አያበራቸውም። ለዚህ ነው የወፎችንና የሌሎች እንስሳትን መብረር ተፈጥሯዊ ሕግ የተረዱት የሰው ልጆች አውሮፕላንን የመሳሰሉ በራሪ መጓጓዣዎችን መፍጠር የቻሉት። ተፈጥሯዊ ሁኔታዎችን ተዓምራዊ ክስተቶች አድርጎ መናገር የተዓምርን መሠረታዊ ትርጉም የሳተ ነው።

ሁሉም ነገር የተፈጠረው ጥንድ ሆኖ ነው

“ያ ምድር ከምታበቅለው ከነፍሶቻቸውም ከማያውቁትም ነገር ዓይነቶችን ሁሏንም የፈጠረ (አምላክ) ጥራት ይገባው፡፡” Exalted is He who created all pairs – from what the earth grows and from themselves and from that which they do not know. (ሱራ 36፡36)

“ትገነዘቡም ዘንድ ከነገሩ ሁሉ ሁለት (ተቃራኒ) ዓይነትን ፈጠርን፡፡” And of all things We created two mates; perhaps you will remember. (ሱራ 51፡49)

አብዱላህ ዩሱፍ አሊ የተሰኙ ሙስሊም ሊቅ ሁለተኛውን ጥቅስ ሲያብራሩት እንዲህ ብለዋል፡-

“ሁሉም ነገር ጥንድ ነው፤ የእፅዋትና የእንስሳት ፆታ… የማይታዩት የተፈጥሮ ኃይላት፣ ቀንና ሌሊት፣ ፖዘቲቭና ኔጌቲቭ የኤሌክትሪክ ሞገዶች…”

የአማርኛ ቁርኣን የግርጌ ማስታወሻም ጥቅሱን በተመሳሳይ መንገድ ይተረጉመዋል፡፡

እንስሳትና እፅዋት ወንዴና ሴቴ እንዳላቸው ከጥንት ጀምሮ የሚታወቅ በመሆኑ እንዲህ ያለው ንግግር ሳይንሳዊ ቅድመ ዕውቀት ሊባል አይችልም፡፡ ዳሩ ግን የቁርኣን ጸሐፊ ሁሉም ነገር ጥንድ ሆኖ እንደተፈጠረ በመናገር መገለጡ መለኮታዊ አለመሆኑን ይፋ አውጥቷል፡፡ ወንዴና ሴቴ የሌላቸው ብዙ የእፅዋት ዝርያዎች አሉ፡፡ ባክቴርያን የመሳሰሉት ባለ ነጠላ ሴል ፍጡራን ተባዕታይና እንስታይ ፆታ የላቸውም፡፡ ብዙ የፈንገስ ዝርያዎችም ተመሳሳይ ተፈጥሮ አላቸው፡፡ ተቃራኒ ፆታ የሌላቸው በዓይን የሚታዩ ብዙ የእንስሳት ዝርያዎችም አሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል በኒው ሜክሲኮ የምትገኝ ዊብቴይል ሊዛርድ የተሰኘች የእንሽላሊት ዝርያ እንስታይ ፆታ ብቻ ያላት ስትሆን የራሷን ምስለኔ (Clone) ዕንቁላል በመጣል ራሷን ትተካለች፡፡[3] የቁርኣን ደራሲ መገለጡ ከሰማይ የመጣለት ቢሆን ኖሮ ይህንን ሐቅ ማወቅ ባልተሳነው ነበር፡፡ አቶ ሐሰን ቁርኣን ሳይንሳዊ ሐቆችን በውስጡ መያዙን ለማሳየት የጠቀሱት አንቀፅ አንድ የሰባተኛው ክፍለ ዘመን አረባዊ ከነበረው ዕውቀት ያልተሻለ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡

አላህ የረሳቸው እንስሳት

“አላህም ተንቀሳቃሽን ሁሉ ከውሃ ፈጠረ፡፡ ከእነሱም በሆዱ ላይ የሚኼድ አልለ፡፡ ከእነሱም በሁለት እግሮች ላይ የሚኼድ አልለ፡፡ ከነሱም በአራት ላይ የሚሄድ አለ። አላህ የሚሻውን ሁሉ ይፈጥራል፡፡ አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነውና፡፡” (ሱራ 24፡45)

በዚህ ጥቅስ መሠረት እንስሳት በአጓጓዛቸው ላይ ተመሥርቶ በሦስት መደባት ተከፍለዋል፦ በሆዱ የሚሄድ፣ በሁለት እግሮች የሚሄድና በአራት እግሮች የሚሄድ። ሌሎቹስ እንስሳት ለምን አልተጠቀሱም? አላህ የሚያውቀው እነዚህን ብቻ ነውን? ምናልባት ሙስሊም ወገኖቻችን አላህ እነዚህን ብቻ መርጦ መጥቀስ ስለፈለገ ነው ይሉን ይሆናል። ይህ ግን የማያስኬድበት አንድ ምክንያት አለ። ከኡሥማን ቅጂ ጋር ተፎካካሪ የነበረው የኡበይ ቢን ካዕብ ቅጂ የተለየ ንባብ እንደነበረው እስላማዊ ምንጮች ያስረዱናል።

ተፍሲር አልቁርጡቢ ይህንን አንቀጽ በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦

The walking on the belly is for snakes and fish and the likes of worms and others. Upon two feet is for humans and birds when they walk. Upon four is for all other animals. In Ubayy’s (copy of the) Qur’an፡ “and of them who walks upon more”. Hence in this addition he included all animals such as crab፣ however this is a copy of the Qur’an which did not gain consensus. https፡//www.altafsir.com/Tafasir.asp?tMadhNo=0&tTafsirNo=5&tSoraNo=24&tAyahNo=45&tDisplay=yes&UserProfile=0&LanguageId=1

ትርጉም፦ “በሆድ ላይ መኼድ ለእባቦችና ለዓሳዎች እንዲሁም ለትሎችና ለሌሎችም ነው። በሁለት እግሮች ላይ መኼድ ለሰዎችና ወፎች ነው። በአራት ላይ መኼድ ለሁሉም እንስሳት ነው። በኡበይ የቁርኣን ቅጂ ውስጥ፡- “ከእነርሱም ከዚህ በላይ በኾኑት ላይ የሚራመዱ አሉ ይላል። ስለዚህ በዚህ ጭማሪ ውስጥ እንደ ሸርጣን (ክራብ) ያሉ እንስሳትን ሁሉ አካቷል፤ ነገር ግን ይህ የቁርኣን ቅጂ መግባባት ያላገኘ ነው።”

የኡሥማን ቁርአን በኡበይ ቁርአን ውስጥ የነበረውን ዓረፍተ ነገር በመቀነሱ ምክንያት አላህ ሌሎቹን እንስሳት የረሳ አስመስሏል። በዚህ ሁኔታ “ቁርአን አንድ ነው፤ ምንም መለዋወጥ አልደረሰበትም” የሚለው የሙስሊሞች አሰልቺ መፈክር ቦታ የለውም። የጥንት ሙስሊሞችም የቁርአንን ችግር መረዳታቸውንና ማስተካከያ ለማድረግ መሞከራቸውን እንረዳለን።

ከላይ እንደተመለከትነው እንስሳትን በተመለከተ ትክክለኞቹ ስህተቶች የሚገኙት በቁርአን ውስጥ እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይደለም። ከዚህ አልፈን ሐዲሳትን የመሳሰሉ እስላማዊ ምንጮችን ብንዳስስ በርካታ ስህተቶችን እናገኛለን። ሙስሊም ወገኖቻችን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተግባራዊ ለማድረግ የሚሞክሯቸውን መስፈርቶች በገዛ መጻሕፍታቸው ላይ ተግባራዊ ቢያደርጉ ሃቁን ተረድተው ወደ እውነት መንገድ በተመለሱ ነበር። እግዚአብሔር አምላክ ማስተዋልን ይሰጣቸው ዘንድ የዘወትር ጸሎታችን ነው።


 

መጽሐፍ ቅዱስ