ምዕራፍ 5
ለኃጢአታችን ሲል ተሰቀለ፣ ዳንን፣ አሜን!
ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች ምላሽ ካቆምንበት እንቀጥላለን
- ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ መስጠቱ ወንጀል ነውን? ለመሆኑ ማን እንደ ይሁዳ መልካም ሰራ? እርሱ ኢየሱስን አሳልፎ ባይሰጠው ይሰቀል ነበርን? ታድያ በኢየሱስ መሰቀል ክርስትያኖች “ዳንን” ይሉ የለ? ይህ ሁሉ ክርስቲያን “ገነት እንዲገባ” ምክንያት የሆነው የይሁዳ ስራ አይደለምን? ታዲያ ይወገዝ ወይስ ይወደስ? እንደ ክርስትና አስተሳሰብ ሰው ሁሉ የዳነው እና ከገሀነም ነፃ የሆነው በኢየሱስ መሰቀል ነው፡፡ ታዲያ እንደ ክርስትና አስተምህሮት ክርስቲያን ሁሉ በይሁዳ ትከሻ ላይ አይደል ገነት የገባው?
ይህ ጥያቄ በምዕራፍ 1 ቁጥር 2 ላይ ከተነሳው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ የአንድ ሰው ምግባር ጥሩነት የሚለካው በውጤቱ ብቻ ሳይሆን በፍላጎትና በዓላማውም ጭምር ነው፡፡ ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ሲሰጠው ኢየሱስን በማጥፋት ገንዘብ ለማትረፍ እንጂ የኢየሱስን ተልዕኮ ከግብ በማድረስ ዓለምን ለማዳን አልነበረም፡፡ ይሁዳ ለክፋት ያሰበውን እግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ዕቅዱን ለማስፈፀም መጠቀሙ ይሁዳን ከወንጀሉ ነፃ አያደርገውም፡፡ የጠያቂው አመክንዮ ትክክል ከሆነ በየዘመናቱ የእግዚአብሔርን አገልጋዮች በመግደል እና በማስገደል ለተሻለው የሰማዕትነት ክብር እንዲበቁ ምክንያት የሆኑ ክፉ ሰዎች ሁሉ ሊሸለሙ ይገባል ማለት ነው፡፡ ለምን ቢሉ እነዚያ ሰዎች ባይገድሏቸውና ባያስገድሏቸው ኖሮ ለሰማዕትነት ክብር በመብቃት የተሻለውን ሽልማት ባልተቀበሉ ነበር፡፡ አሕመዲን ይህንን የወደቀ ሙግት በመጠቀም የኢየሱስን ስቅለት ለማጣጣል መሞከራቸው በገዛ ሃይማኖታቸው ምን ያህል ተስፋ እንደቆረጡ ያሳያል፡፡
- በማቴዎስ 9:13 ላይ “ከመስዋዕት ይልቅ ምህረትን እወዳለሁ” ይላል፡፡ አምላክ “ከመስዋዕት ይልቅ ምህረትን እወዳለሁ” እያለ እንዴት ዓለም በሰራው ኃጢአት ምህረት ማድረግ ሲችል ኢየሱስን በማሰቃየት መስዋዕት አደረገው?
ጠያቂው የጠቀሱት ክፍል ስለ እግዚአብሔር ምህረት ሳይሆን ሰዎች ለባለንጀሮቻቸው የሚያደርጉትን ምህረት እና ለእግዚአብሔር ያላቸውን ታማኝነት የተመለከተ ነው፡፡ ጌታችን ቃሉን የጠቀሰው ከትንቢተ ሆሴዕ 6፡6 ላይ ሲሆን በዕብራይስጥ “ኼሲድ” የሚለው “ምህረት” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ሰው ለባለንጀራው የሚያሳየውን ቀና ባሕርይ ወይም ለእግዚአብሔር ያለውን ሎሌነት እንዲሁም እግዚአብሔር ከአገልጋዮቹ የሚጠብቀውን ሁሉ በጥቅሉ የሚያመለክት ነው፡፡ ሆሴዕ 6፡4 ላይ ይኸው ቃል “ፍቅር” ተብሎ ተተርጉሞአል፡፡ ለእግዚአብሔር ፈቃድ ታማኝ ሳይሆኑ መሥዋዕት ማቅረብ በእርሱ ዘንድ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም (1ሳሙኤል 15፡22-23፣ ኢሳይያስ 1፡11-20፣ ኤርምያስ 7፡21-22፣ አሞፅ 5፡21-24፣ ሚክያስ 6፡6-8፣ ማቴዎስ 9፡13፣ 12፡7)፡፡[1] ስለዚህ የክፍሉ መልዕክት እግዚአብሔር ከሰው ለእርሱ ከሚቀርብ መስዋዕት ይልቅ ሰው ለባለንጀራው የሚያሳየው ምህረት እና ለእርሱ ያለው ታማኝነት ያስደስተዋል የሚል እንጂ ያለ ክርስቶስ መስዋዕትነት የሰው ልጆች ከኃጢአታቸው ይድናሉ የሚል አይደለም፡፡
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ጠያቂው ክፍሉን የተረዱበት መንገድ ትክክል ቢሆን እንኳ (ስህተት መሆኑ ይሰመርበት) ድምዳሜያቸው ትክክል ሊሆን አይችልም፡፡
እግዚአብሔር ሰዎችን ወደ ገሃነም ከመላክ ይልቅ ምህረትን ቢያደርግ ደስ ይለዋል ነገር ግን ምህረትን መውደዱ ሰዎችን ሁሉ ወደ ገነት እንዲያገባ እንደማያደርገው ሁሉ ከመስዋዕት ይልቅ ምህረትን መውደዱ ያለ መሥዋዕት ኃጢአትን ይቅር እንዲል ያስችለዋል ወደሚል ድምዳሜ አይመራም፡፡ እግዚአብሔር አፍቃሪ አባት የሆነውን ያህል ፍትሃዊ አምላክም ጭምር በመሆኑ ምክንያት በኃጢአተኞች ላይ እንዲፈርድ ፍትሃዊ ባሕርዩ ግድ ይለዋል፡፡ ነገር ግን ከሥላሴ አካላት መካከል አንዱ የሆነው ወልድ የኃጢአት ዕዳችንን በመክፈል ከእግዚአብሔር ፍትሃዊ ፍርድ ነፃ አውጥቶናል፡፡ የእግዚአብሔር ፍትህና የእግዚአብሔር ፍቅር በእኩል ሁኔታ የተገለጡበት ብቸኛ ቦታ ቢኖር የክርስቶስ መስቀል ነው፡፡
- “እግዚአብሔር ወልድ” ሞቷልን? ክርስቲያኖች “አዎን” ይላሉ? ታዲያ አምላክ (እግዚአብሔር) ይሞታል? የአምላክ ክፍልና አካል ይሞታል? እንዲያው እንዴት ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን “እግዚአብሔር ወልድ” ብሏልን? እስቲ የቱ ጋር?
የኢየሱስን ሞት በተመለከተ ቀደም ሲል በምዕራፍ 1 ጥያቄ ቁጥር 8 ላይ መልስ ስለሰጠን አንደግምም፡፡ ጠያቂው ሙግታቸው ደካማ መሆኑን ስለተገነዘቡ ተጨማሪ ጥያቄ በማከል ለማጠናከር ሞክረዋል፡፡ ኢየሱስ ወይም ወልድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በብዙ ቦታዎች ላይ አምላክ ወይም እግዚአብሔር ተብሏል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ወልድ መባሉ ስህተቱ ምኑ ላይ ነው? ወልድ እግዚአብሔር መሆኑ ከተነገረባቸው ጥቅሶች በመነሳት “እግዚአብሔር ወልድ” ማለት ስህተት ከሆነ ሙስሊሞች “ነቢዩ ሙሐመድ”፣ “ቅዱስ ቁርኣን”፣ መልአኩ ጂብሪል፣ ወዘተ. በማለት ስለምን ይናገራሉ? እንዲያው አንዴም ቢሆን ቁርኣን ሙሐመድን “ነቢዩ ሙሐመድ በሉት”፣ ቁርኣንን “ቅዱስ ቁርኣን ብላችሁ ጥሩት” ጂብሪልን “መልአኩ ጂብሪል በሉት” ብሏልን? እስኪ የቱ ጋር?
- ከ2000 አመት በፊት ኢየሱስ ለሰው ልጆች ኃጢአት ቤዛ ሆኖ ከተሰቀለ፣ ዛሬም ከስቅለቱ በኋላ እንዴት “የሰው ልጆች ሁሉ በኃጢአት ውስጥ ናቸው” ይባላል?
የኃጢአታቸውን ይቅርታ በመቀበል ከኃጢአት ባርነት ነፃ የሚወጡት በመስቀሉ ሥራ ያመኑት ክርስቲያኖች እንጂ ሁሉም የሰው ልጆች አይደሉም፡፡ አማኞች ሁሉ ከኃጢአት እዳ ነፃ ናቸው፤ የዘለዓለምንም ሕይወት አግኝነተዋል፡፡ በኃጢአት እና በፍርድ ስር ያሉት የእግዚአብሔርን ልጅ የካዱት ናቸው (ዮሐንስ 3፡16-18)፡፡
- ኢየሱስ ለዓለም ቤዛ ሆኖ ሰውን ነፃ ለማውጣት ከመጣ ስለ ኢየሱስ ጭራሽ ያልሰሙት ከርሱ መወለድ በፊት የነበሩ ህዝቦች በምን ሊድኑ ነው?
እግዚአብሔር በሰዎች ላይ የሚፈርደው በተገለጠላቸው መጠን ነው፡፡ ሕግ የተሰጣቸው ለሕጉ ታማኝ በሆኑት መጠን ሕግ ያልተሰጣቸው ደግሞ ለተሰጣቸው የኅሊና ሕግ ባሳዩት ታማኝነት መጠን የእግዚአብሔርም ፍርድ እንደዚያው ይሆናል (ሮሜ 1፡18-32፣ 2፡14-16)፡፡ እነዚህ ሰዎች በእምነት ፋንታ እንደ ሞግዚት በሚያገለግለው በሕግ ስር ሲኖሩ ሳሉ ለሕጉ የሚያሳዩት ታማኝነት ወደ ክርስቶስ ያደርሳቸዋል (በክርስቶስ ሥራ ውስጥ እንዲጠቀለሉ ያደርጋቸዋል) እንጂ በራሱ አያድናቸውም (ገላቲያ 3፡22-25)፡፡ ለኅሊና ሕግና ለተጻፈው ሕግ ታማኞች የሆኑትን ሰዎች እንዲሁም ስለ ክርስቶስ ሰምተው ያመኑትን ሰዎች ሁሉ ሊያድን ኢየሱስ ደሙን አፍስሷል (ዕብራውያን 9፡22-28)፡፡ ስለዚህ የሰው ልጆችን ታሪክ እንደ ረጅም መስመር ብንስል የክርስቶስ መስቀል መካከል ላይ ቆሟል፡፡ ከመስቀሉ በፊት የሚገኙት ሰዎች ስለ መስቀሉ ባያውቁም ነገር ግን ለሕገ እግዚአብሔር ታማኞች በመሆን ወደፊት በሚመጣው የመስቀሉ ሥራ ውስጥ ይጠቀለላሉ፡፡ ከመስቀሉ በኋላ ያሉት ደግሞ የምስራቹን በማመን መስቀሉን ወደ ኋላ ተመልክተው ይድናሉ፡፡ ከመስቀሉ ውጪ ሌላ የመዳኛ መንገድ የለም! ለዚህ ነው እስልምናን የመሳሰሉት መለኮታዊ ምንጭ የሌላቸው ሃይማኖታት መስቀሉን የሚቃወሙት፡፡
- ምንም ቢሰሩ ሁሉም ክርስቲያኖች በኢየሱስ መሰቀል በማመን ብቻ መንግስተ ሰማያት የሚገቡ ከሆነ የኢየሱስ አስተምህሮት ምኑ ላይ ነው ጥቅሙ? ኢየሱስ “መልካም” “እኩይ” እያለ ሲያብራራቸው የነበሩት አስተምህሮቶች ሁሉ ምን ይፈይዳሉ? ካላችሁ በኢየሱስ መሰቀል አምነው ኢየሱስ «ክፉ» ያላቸውን ተግባራት ቢፈጽሙና ባይፀፀቱ ገሀነም የገባሉ ማለት ነውን?
መጽሐፍ ቅዱስ “ምንም ቢሰሩ ሁሉም ክርስቲያኖች በኢየሱስ መሰቀል በማመን ብቻ መንግሥተ ሰማያት ይገባሉ” አይልም፡፡ ጠያቂው ይህንን ቅጥፈት ከየት እንዳመጡ ማስረጃ እንዲጠቅሱ እንጠይቃቸዋለን፡፡ ከሙስሊሞች ውጪ የሚገኙት የዓለም የታሪክ ተመራማሪዎች ሁሉ ኢየሱስ መሰቀሉን ያምናሉ፡፡ ኢየሱስን የሰቀሉት ሮማውያንና እንዲሰቀል አሳልፈው የሰጡት አይሁዶችም ጭምር መሰቀሉን ያምናሉ፡፡ ሰው የዘለዓለምን ሕይወት የሚያገኘው ኢየሱስ ስለ ኃጢአቱ ሲል መሰቀሉን፣ መሞቱንና መነሳቱን በማመን እርሱን ሲከተል እንጂ “ተሰቅሏል” ብሎ በማመን ብቻ አይደለም፡፡ እምነቱ ደግሞ በሥራ የሚገለጥ መሆን ያስፈልገዋል፡፡ አምኛለሁ እያለ እንደ ልቡ ፈቃድ የሚኖር ሰው እምነቱ የውሸት ነው፡፡ ለበለጠ ማብራርያ ምዕራፍ 4 ቁጥር 8ን ይመልከቱ፡፡
- ከምዕራፍ 4 ጥያቄ ቁጥር 8 ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ታልፏል፡፡
- ኢየሱስ መስቀል ላይ ሆኖ “አምላኬ አምላኬ ስለምን ተውከኝ” ብሎ ሲለምን አምላክ ነበር ወይስ ሰው? ሰው ከሆነ የሞተው ኢየሱስ የተባለው ግለሰብ ነበር ማለት ነው፡፡ እንዴትስ አምላክ ሌላ አምላክ ይለምናል? የማይሞተው እግዚአብሔር አምላክ ሞተ ይባላልን?
ይህ ጥያቄ በምዕራፍ 1 ቁጥር 8 ላይ ከተመለሰው ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ ስለዚህ በዚያ ቦታ የተመለሰውን እዚህ ስለማንደግም አንባቢ አስቀድሞ ያንን ምላሽ ይመለከት ዘንድ እናበረታታለን፡፡
ጠያቂው ላቀረቡት ጥያቄ በብዙ ክርስቲያኖች ዘንድ የታወቀ መልስ ቢኖርም እኔ ግን ኢየሱስ “አምላኬ አምላኬ ስለምን ተውከኝ” ሲል ስለ እርሱ የተተነበየውን ትንቢት ለመጠቆም እንጂ ለመጸለይ እንዳልሆነ አምናለሁ፡፡ በዚያ ቦታ የተከናወኑት ነገሮች ሁሉ እርሱ በጠቀሰው መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ 22 ውስጥ በዝርዝር የተተነበዩ ሲሆን ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ በጸለየው በዚያ ጸሎት ውስጥ የክርስቶስን መከራ የተመለከቱ ብዙ ዝርዝር ጉዳዮች ተተንብየዋል፡፡ በዚያ የቆሙት ሰዎች ያላግጡበት እንደነበር (ሉቃስ 23፡35)፣ ልብሶቹን መከፋፈላቸውን (ዮሐንስ 19፡23)፣ በእጀ ጠባቡ ላይ ዕጣ መጣጣላቸውን (ዮሐንስ 19፡24)፣ ወዘተ. ከሁሉ በላይ ደግሞ ሰዎችን በመስቀል ላይ ቸንክሮ መግደል ባልተጀመረበት በዳዊት ዘመን እጆቹና እግሮቹ ስለመቸንከራቸው የተነገረው ትንቢት በእጅጉ አስደናቂ ነው (ቁ. 16)፡፡ በክፍሉ ውስጥ የተነገሩት አንዳንድ ነገሮች ክርስቶስን የተመለከቱ ባይሆኑም ነገር ግን በጣም ግልፅ የሆኑ ትንቢቶች በውስጡ ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ ክርስቶስ ጌታችን በመስቀል ላይ ሆኖ የመጀመርያውን ስንኝ መናገሩ ትንቢቱ የተነገረበትን ክፍል ለማመልከት እንጂ ለመጸለይ አልነበረም፡፡ “የኃጢአታችንን የመጨረሻ ቅጣት ለመክፈል በአብ እና በእርሱ መካከል መለያየት እንደተፈጠረ (አብ እንደተወው)” የሚናገሩ ወገኖች የላከው አብ ብቻውን እንደማይተወው ኢየሱስ አስቀድሞ መናገሩን ማስታወስ ያሻቸዋል (ዮሐንስ 8፡29)፡፡ የላከው አብ ብቻውን እንደማይተወው ከተነገረ “አሁን ደግሞ ትቶታል” ብሎ ማለት የመጀመርያውን ስለሚጣረስ ትክክለኛ ትርጓሜ ሊሆን አይችልም፡፡
- ዮሐንስ 13፡33 “ልጆቼ ሆይ! ከእናንተ ጋር የምቆየው ለጥቂት ጊዜ ነው እናተም ትፈልጉኛላችሁ፤ ለአይሁድ እኔ ወደምሄድበት ልትመጡ አትችሉም” እንዳልኳቸሁ አሁን ለእናተ ይህንኑ እላችኋለሁ” ይላል፡፡ በዚህ ጥቅስ ላይ ኢየሱስ ለአይሁዶች “እኔ ወደ ምሄድበት ልትመጡ አትችሉም” ብሏል፡፡ ታድያ እንዴት ያለበት ድረስ መጥተው “ያዙት” “ሰቀሉት” ሊባል ቻለ? ወይስ ኢየሱስ ዋሸ? አሊያም እንደሚያዝ አያውቅም ነበርን?
ገናናው ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ መዋሸት ባሕርዩ አይደለም፡፡ እንደሚያዝም ያውቅ ነበር (በዚሁ ምዕራፍ ለጥያቄ ቁጥር 26 በተሰጠው መልስ ላይ የተዘረዘሩትን ጥቅሶች ይመልከቱ)፡፡ ነገር ግን ጠያቂው ቀላሉን ጉዳይ መረዳት ተስኗቸዋል፡፡ በዚህ ቦታ ላይ ለአይሁድ የተናገረውን በመድገም ለደቀ መዛሙርቱ እየተናገረ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ለአይሁድ የተናገረው ቃል በዮሐንስ 7፡33 ላይ ተጽፏል፡፡ ወዴት እንደሚሄድም ግልፅ አድርጓል፡- “ኢየሱስም፦ ገና ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር እቆያለሁ ወደ ላከኝም እሄዳለሁ፡፡ ትፈልጉኛላችሁ አታገኙኝምም፤ እኔም ወዳለሁበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም አለ፡፡” (ዮሐንስ 7፡33-34)፡፡
አይሁድ ኢየሱስን ፈልገው ሊያገኙ የማይችሉበትና እርሱ ወዳለበት ሊመጡ የማይችሉበት ምክንያት ኢየሱስ ወደ ላከው ወደ አብ ስለሚሄድ ነው፡፡ ኢየሱስ ከትንሳኤው በኋላ ወደ አብ ሄዷል፡፡ አሁን መሲሁን ቢፈልጉ ሊያገኙት አይችሉም፡፡ እርሱ ወዳለበትም መሄድ አይችሉም፡፡
- ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሆኖ “በዘጠኝም ሰዓት ኢየሱስ ኤሎሄ ኤሎሄ ለማ ሰበቅታኒ? ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸለ፤ ትርጓሜውም “አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ?” ማለት ነው (የማርቆስ ወንጌል 15: 34 እና ማቴዎስ 27: 46) ሲል አምላክ ከስቅለቱ እንዲያድነው በጩኸት ለምኗል በማቴዎስ 26: 53 ላይ “ካስፈለገ አባቴን ብጠይቀው ከዐስራ ሁለት ክፍል ሰራዊት የሚበልጡ መላእክት የማይሰድልኝ ይመስልሃል?” ሲል ተናግሮ ነበር፡፡ ታድያ ኢየሱስ ‘አምላኬ’ አምላኬ ለምን ተውከኝ? ብሎ በጩኸት እየለመነ እንዴት የተባለው ጦር መጥቶ ከስቅለት ሳያድነው ቀረ?
ምክንያቱም ኢየሱስ በዚህ ቦታ ጸሎት አልጸለየም ነገር ግን ስለ እርሱ የተተነበየውን ትንቢት ክፍል የመጀመርያ ስንኝ ነው የጠቀሰው፡፡ እዚሁ ምዕራፍ ለጥያቄ ቁጥር 8 የተሰጠውን መልስ ይመልከቱ፡፡
- ሉቃስ 22: 36 “እርሱም እንዲህ አላቸው: “አሁን ግን ኮሮጆም ከረጢትም ያለው ሰው ይያዝ፤ ሰይፍ የሌለውም ልብሱን ሽጦ ይግዛ፡፡” ይላል፡፡ ኢየሱስ በዚህ ጥቅስ ላይ “ሰይፍ የሌለውም ልብሱን ሸጦ ይግዛ” ብሏል፡፡ ለምን? በሰይፍ እንዳይሰቀል እንዲከላከሉለት? ሊሰቀል “መጣ” የተባለው ሰው እንዴት ሃሳቡን ሊቀይር ቻለ?
ጠያቂው ከገዛ ምናባቸው ጋር ከሚነጋገሩ ክፍሉን ጨርሰው ቢያነቡ ኖሮ ከስህተት በዳኑ ነበር፡፡
“ደግሞም፦ ያለ ኮረጆና ያለ ከረጢት ያለ ጫማም በላክኋችሁ ጊዜ፥ አንዳች ጐደለባችሁን? አላቸው፡፡ እርሱም፦ አንዳች እንኳ አሉ፡፡ እርሱም፦ አሁን ግን ኮረጆ ያለው ከእርሱ ጋር ይውሰድ፥ ከረጢትም ያለው እንዲሁ፤ የሌለውም ልብሱን ሽጦ ሰይፍ ይግዛ፡፡ እላችኋለሁና፥ ይህ፦ ከዓመፀኞች ጋር ተቁጠረ ተብሎ የተጻፈው በእኔ ሊፈጸም ግድ ነው፤ አዎን፥ ስለ እኔ የሚሆነው አሁን ይፈጸማልና አላቸው፡፡ እነርሱም፦ ጌታ ሆይ፥ እነሆ፥ በዚህ ሁለት ሰይፎች አሉ አሉት፡፡ እርሱም፦ ይበቃል አላቸው፡፡ (ሉቃስ 22፡35-38)፡፡
ኢየሱስ በዚህ ቦታ ላይ ስለ መሲሁ መገደል የሚናገረውን የኢሳይያስ 53 ትንቢት ነው እየጠቀሰ ያለው፡- “ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ከዓመፀኞችም ጋር ተቁጥሮአልና እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፥ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ” (ኢሳይያስ 53፡12)፡፡
ስለ መገደሉ የተተነበየውን ትንቢት ጠቅሶ እየተናገረ ባለበት ሁኔታ “ሐሳቡን ቀይሯል” የሚለው የጠያቂው ድምዳሜ ያስኬዳልን? ለዚህ ድምዳሜያቸው ደግሞ እንደመነሻ የተጠቀሙት ምክንያት በእጅጉ አስገራሚ ነው፡፡ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ሰይፍ እንዲያዘጋጁ ያሳሰበው በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ የመጀመርያ አስቸጋሪ ጊዜ ከፊት እየመጣ በመሆኑ ሳብያ የራሳቸውን ኃላፊነት በራሳቸው እንዲወጡ ቅኔያዊ በሆነ መንገድ ማሳሰብ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ “ከአመፀኞች ጋር ተቆጠረ” የሚለው ትንቢት እንዲፈፀም ነው፡፡ ጠያቂው ይህንን ንግግር በመጥቀስ “እንዳይሰቀል በሰይፍ እንዲከላከሉለት ነው” የሚል ነገር ፈራ ተባ እያሉ ጽፈዋል፡፡ ኢየሱስ ግን “በዚህ ሁለት ሰይፎች አሉ” ሲሉት “ይበቃል” የሚል መልስ ነበር የሰጣቸው፡፡ ሊይዙት ከሚመጡት ስልጡን ወታደሮች ጋር በሁለት ሰይፍ ተፋልመው እንደማያስጥሉት ሳያውቅ ቀርቶ ይሆን ሁለት ሰይፍ በቂ እንደሆነ የተናገረው? ጠያቂው በጠቀሱት በዚሁ ምዕራፍ ላይ ከአፍታ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ሰይፍ ተጠቅመው ሊያስጥሉት ሲሞክሩ ከልክሏቸዋል፡፡ በሰይፋቸው የጎዱትንም ሰው ፈውሶታል፡-
“በዙሪያውም የነበሩት የሚሆነውን ባዩ ጊዜ፦ ጌታ ሆይ፥ በሰይፍ እንምታቸውን? አሉት፡፡ ከእነርሱም አንዱ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቁረጠው፡፡ ኢየሱስ ግን መልሶ፦ ይህንስ ፍቀዱ አለ፤ ጆሮውንም ዳስሶ ፈወሰው፡፡” (ሉቃስ 22፡49-51)
የዚህ ተጓዳኝ ንባብ በሆነው በማቴዎስ 26፡51-54 ላይ እንዲህ ይላል፡-
“እነሆም፥ ከኢየሱስ ጋር ከነበሩት አንዱ እጁን ዘርግቶ ሰይፉን መዘዘና የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ጆሮውን ቁረጠው፡፡ በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለው፦ ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ፡፡ ወይስ አባቴን እንድለምን እርሱም አሁን ከአሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበዙ መላእክት እንዲሰድልኝ የማይቻል ይመስልሃልን? እንዲህ ከሆነስ፦ እንደዚህ ሊሆን ይገባል የሚሉ መጻሕፍት እንዴት ይፈጸማሉ?”
ኢየሱስ ለአስቸጋሪ ጊዜ ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ቅኔያዊ በሆነ መንገድ መልዕክት ለማስተላለፍ እንዲሁም “ከአመፀኞች ጋር ተቆጠረ” የሚለው ትንቢት ተፈፃሚ ይሆን ዘንድ ደቀ መዛሙርቱ ሰይፍ እንዲያዘጋጁ ቢነግራቸውም እርሱ እንዳይያዝ ለመከላከል እንዳይጠቀሙ ከመከልከልም አልፎ ያንን ለማድረግ ሲሞክሩ ገስጿቸዋል፡፡ አሕመዲን ኢየሱስን ሰይፍ የሚመዝ ጂሃዳዊ በማስመሰል ለማጠጋጋት ያደረጉት ሙከራ አልተሳካላቸውም፡፡
- ማቴዎስ 4፡17 “ከዚያ ዘመን ጀምሮ ኢየሱስ፦ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ እያለ ይሰብክ ጀመረ” ይላል፡፡ ክርስትና መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ “ኢየሱስ ለኛ ሲል ተሰቅሎ መሞቱን ማመን ግዴታና ብቸኛው መዳኛ ነው” ሲል ያስተምራል፡፡ ኢየሱስ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” በማለት ከሚሰብክ ብቸኛው መዳኛ እርሱ ለሰው ልጅ ኃጢአት ቤዛ ሆኖ መሰቀሉንና መሞቱን ማመን ከሆነ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና እኔ ለእናንተ ተሰቅዬ ልሞት መሆኑን እመኑ” በማለት እንዴት ሳይሰብክ ቀረ?
ኢየሱስ በአገልግሎቱ መጀመርያ ላይ መሠረታዊ የሆነውን የእግዚአብሔር መንግሥት ትምህርት በማስተማር ነበር የጀመረው፡፡ ትምህርቱን ተቀብለው ይበልጥ ለማወቅ ወደ እርሱ ለቀረቡት ኒቆዲሞስን ለመሳሰሉት ተከታዮቹ እና ለሐዋርያቱ መንግሥተ ሰማያት የመግቢያው መንገድ የእርሱ መስዋዕትነት መሆኑን ያስረዳ ነበር (ዮሐንስ 3፡13-18፣ ማቴዎስ 26፡26-28)፡፡ የጠያቂው ድምዳሜ ከሰንበት ትምህርት ቤት ህፃናት እንኳ የሚጠበቅ አይደለም፡፡
- መዝሙር 34፡17 ላይ “ቅኖች” ወደ እግዚአብሔር ይጮኻሉ እርሱም ይሰማቸዋል ከችግራቸውም ሁሉ ያድናቸዋል” ይላል፡፡ ታዲያ «አምላኬ አምላኬ ስለምን ተውከኝ?» እያለ ኢየሱስ ሲጮህ «ቅን» ስላልሆነ ነው ያልተሰማው? ከሞትስ ያላዳነው? ወይስ ቅን ስለሆና ከሞት ድኗል?
ኢየሱስ ለምን ይህንን እንዳለ እዚሁ ምዕራፍ በቁጥር 8 ላይ አብራርተናል፡፡ ጠያቂው ይህንን ጥቅስ የተረጎሙበት መንገድ ትክክል ከሆነ በብዙ ስቃይና ሰቆቃ ውስጥ ሆነው ወደ አምላካቸው እየጮኹ የሞቱት ቅዱሳን ሁሉ ቅኖች ስላልሆኑ ነው እግዚአብሔር ያልሰማቸው የሚል የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ልንደርስ ነው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ቅኖችን ከመከራቸው የሚያድናቸው በመከራ ውስጥ እንዳያልፉ በማድረግ ብቻ ሳይሆን መከራቸውን የሚቋቋሙበትን ኃይል በመስጠት እና ከመከራቸው በኋላ እውነተኛነታቸውን በማረጋገጥ ጠላቶቻቸውን በማሳፈርም ጭምር በመሆኑ የጠያቂው ትርጓሜ በእጅጉ የተሳሳተ ነው፡፡
- ማቴዎስ 8፡17፣ ኢሳያስ 53፡12፣ ኢሳያስ 53፡4፣ ሉቃስ 2፡30፣ ኢሳይያስ 52፡10 እና ሉቃስ 22፡32 ላይ «ይመጣል» ተብሎ የተተነበየው መሲህ ኢየሱስ ከነበረ ይህ መሲህ እንደማይገደልም ተገልጿል፡፡ ታድያ እንዴት ኢየሱስ «ሊገደል ቻለ »ተብሎ ይታመናል?
ከእነዚህ ጥቅሶች መካከል አንዳቸውም መሲሁ እንደማይገደል አይናገሩም፡፡ ይልቁኑ ኢሳይያስ 53ን መጥቀሳቸው ጠያቂው ስለ መሲሁ አለመገደል ሳይሆን ስለ መሲሁ መገደል ማስረጃ እየሰጡ ያሉ ያስመስላቸዋል፡-
የሰማነውን ነገር ማን አምኖአል? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገልጦአል? በፊቱ እንደ ቡቃያ ከደረቅም መሬት እንደ ሥር አድጎአል፤ መልክና ውበት የለውም፥ ባየነውም ጊዜ እንወድደው ዘንድ ደም ግባት የለውም፡፡ የተናቀ ከሰውም የተጠላ፥ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው፤ ሰውም ፊቱን እንደሚሰውርበት የተናቀ ነው፥ እኛም አላከበርነውም፡፡ በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል፤ እኛ ግን እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም ቁጠርነው፡፡ እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቁሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን፡፡ እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ፤ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ፡፡ ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም፡፡ በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ፤ ስለ ሕዝቤ ኃጢአት ተመትቶ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ ከትውልዱ ማን አስተዋለ? ከክፉዎችም ጋር መቃብሩን አደረጉ፥ ከባለጠጎችም ጋር በሞቱ፤ ሆኖም ግፍን አላደረገም ነበር፥ በአፉም ተንኮል አልተገኘበትም ነበር፡፡ እግዚአብሔርም በደዌ ያደቅቀው ዘንድ ፈቀደ፤ ነፍሱን ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ካደረገ በኋላ ዘሩን ያያል፥ ዕድሜውም ይረዝማል፥ የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል፡፡ ከነፍሱ ድካም ብርሃን ያያል ደስም ይለዋል፤ ጻድቅ ባሪያዬም በእውቀቱ ብዙ ሰዎችን ያጸድቃል፥ ኃጢአታቸውን ይሸከማል፡፡ ስለዚህም እርሱ ብዙዎችን ይወርሳል፥ ከኃያላንም ጋር ምርኮን ይከፋፈላል፤ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ከዓመፀኞችም ጋር ተቁጥሮአልና እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፥ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ፡፡
ይህንን ክፍል በመጥቀስ መሲሁ እንደማይሰቀልና እንደማይሞት ለመሟገት የሚሞክር ሰው ምንኛ የታወረ ነው!
- የሰው ልጅ አደም በፈፀመው ኃጢአት ምክንያት ኃጢአት የመስራት ዝንባሌንና ባህሪን ከወረሰ እንዲሁም ይህ ዝንባሌ በኢየሱስ ስቅለት በደሙ ከነፃ ለምን ያ ዝንባሌ አሁንም ቀጥሎ ሰው ወንጀል እየሰራ ሊቀጥል ቻለ?
ጠያቂው ቀደም ሲል ሲቃወሙት የነበሩትን የውርስ ኃጢአት ተቀብለው ሲሟገቱ መታየታቸው በእጅጉ አስገራሚ ነው (ምዕራፍ 4 ጥያቄ ቁጥር 12ን ይመልከቱ)፡፡
በክርስቶስ አምኖ ዳግም የተወለደ ሰው በሕይወቱ ከሚከናወኑት የጸጋ ሥራዎች መካከል ኃጢአትን እምቢ የማለት ችሎታ አንዱ ነው (ሮሜ 8 ፡ 3-4፣ ገላትያ 5፡24፣ ቲቶ 2፡11-12)፡፡ ከአሮጌው ሥጋችን ተለይተን የተለወጠውንና አዲሱን የትንሣኤ ሥጋ እስክንለብስ ድረስ ከኃጢአት ጋር የምናደርገው ትግል ቀጣይነት ያለው ቢሆንም ነገር ግን የኢየሱስ መንፈስ ዕለት በዕለት እንድንቀደስና እርሱን ወደ መምሰል እንድናድግ ይረዳናል፡፡
ደሙ ስለሰው ልጆች ሁሉ የፈሰሰ ቢሆንም በደሙ የመንጻት መብት ያለው የክርስቶስን መስዋዕትነት አምኖ የተቀበለ ብቻ ነው (ዮሐ 1፡12)፡፡ መድኃኒት የሚሰራው ለበሽተኛ ሁሉ ነው፤ ነገር ግን ፈውሱን የሚያገኘው በሽተኛ እንደሆነ አምኖ መድኃኒቱን የተጠቀመ ብቻ ነው፡፡ ጤናማ አስተሳሰብ ያለው ሰው “መድኃኒት ስላለ ሁሉም ለምን አልተፈወሰም?” ብሎ እንዴት ይጠይቃል?
- በምዕራፍ 1 ቁጥር 50 ላይ የተመለሰውን ጥያቄ ስለደገሙ ታልፏል፡፡
- የክርስትና እምነት መሠረቱ “ኢየሱስ ለኛ ኃጢአት ሲል ሞተ ለኃጢአታችን ቤዛ ሆነ፡፡” ነው፡፡ ነገር ግን “ቤዛ” ተብየው በራሱ እኔ ለኃጢአታችሁ ቤዛ እሆናለሁ ኃጢአታችሁን በደሜ አጥባለሁ፡፡ ሲል አስተምሮ ነበርን? የሚል ጥያቄ ቢነሳ ምላሹ አሳፋሪ ነው፡፡ አንዴም አላስተማረም፡፡ ይህ የጳውሎስ ፈጠራና ተጽዕኖ ብቻ ነው፡፡ እንድያውም እንዳይያዝና እንዳይገደል ሲፀልይ፣ ሲደበቅና ሲጨነቅ ነበር፡፡ አልነበረምን?
በዚህ ዓይነት ጠያቂው ኢሳይያስ 53 እና ዳንኤል 9ን የመሳሰሉትን ስለ መሲሁ ሞት እና ቤዛነት የሚናገሩትን የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች “ጳውሎስ ነው የጻፈው!” ከማለት ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ሰው አንዴ ኅሊናውን ጨቁኖ መቀጣጠፍ ከጀመረ ምን ማቆሚያ ይኖረዋል? የተወደደው ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ከኢየሱስ ዕርገት በኋላ ነበር ክርስቲያን የሆነው (የሐዋርያት ሥራ 9)፡፡ ስለ ኢየሱስ ትንሳኤና ቤዛነት የሚሰብኩትን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሲያሳድድ የነበረ ሰው ይህንን ትምህርት እንደፈጠረ መናገር በእጅጉ አስቂኝ ነው፡፡ አሳፋሪ የሆነውን የኡስታዙን አለማወቅ የሚያጋልጡ፣ ኢየሱስ ለሰው ልጆች ነፍሱን ቤዛ ለማድረግ ወደ ምድር እንደመጣና በደሙ የሰው ልጆችን ኃጢአት እንደሚያጥብ መናገሩን የሚገልፁ ሁለት ጥቅሶችን እንጠቅሳለን፡-
“እንዲሁም የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም” (ማቴዎስ 20፡28)፡፡
ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ፦ ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው፡፡” (ማቴዎስ 26፡26-28)፡፡
የኢየሱስን መጨነቅ በተመለከተ አንባቢያንን በድጋሜ ወደ ቁጥር 50 እንመራለን፡፡ ነገር ግን “ኢየሱስ እንዳይያዝ ሲጸልይ፣ ሲጨነቅ እና ሲደበቅ ነበር” የሚለው አባባል የከፋ እብለት ነው፡፡ ኢየሱስ ፅዋው ከእርሱ እንዲያልፍ መጸለዩ እውነት ቢሆንም ነገር ግን እንደ አብ ፈቃድ እንጂ እንደ እርሱ ፈቃድ እንዳይሆን በመጸለይ የአብን ፈቃድ ለመፈጸም ዝግጁ መሆኑን አሳይቷል (ሉቃስ 22፡42)፡፡ ኢየሱስ ጊዜው ሲደርስ አልተደበቀም፡፡ ብዙ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደሚሆንበት የአትክልት ቦታ ነበር የሄደው፡፡ ይሁዳ ያንን ቦታ ያውቀዋል፡፡ መደበቅ ቢፈልግ ኖሮ ወደዚያ ባልሄደ ነበር (ዮሐንስ 18፡1-2)፡፡ ሊይዙት ሲመጡም ከመሸሽ ይልቅ እነርሱ ወዳሉበት በመሄድ ማንን እንደሚፈልጉ ጠየቃቸው፡፡ “የናዝሬቱ ኢየሱስን” ሲሉት “እኔ ነኝ” በማለት በፈቃዱ ራሱን አሳልፎ ሰጠ (ዮሐንስ 18፡4-8)፡፡ ጠያቂው በግምት እና በስሜታዊነት ከሚጽፉ ማስረጃዎችን ካጤኑ በኋላ ተረጋግተው ቢጽፉ ኖሮ ትዝብት ላይ ባልወደቁ ነበር፡፡
- ኢየሱስ ከአብረሃም ልጅ ያንሳልን? አምላክ አብረሃምን ልጅህን እረድ ሲለው ታዛዥ ሆኖ ሊታረድ ቀረበ፡፡ ኢየሱስ ዓለምን የማዳን ተልዕኮ ይዞ ከተሰቀለ ከሦስት ቀናት በኋላ እንደሚነሳ እያወቀ ያ ሁሉ መሸሽና መሸበር ይገባው ነበርን?
አብርሃም ልጁ ይስሐቅን ሊሰዋ በወሰደው ጊዜ ምን እየሆነ እንደነበር ይስሐቅ አላወቀም ነበር (ዘፍጥረት 22፡7-8)፡፡ ቢያውቅ ኖሮ መፍራቱ ግድ ነው፡፡ የአብርሃም ልጅ ለመስዋዕትነት እየተወሰደ መሆኑን እያወቀ እንደ ስሜት አልባ ሮቦት አባቱን ተከትሎ እንደሄደ የሚናገረው እስላማዊ ታሪክ ተዓማኒነት የለውም፡፡ ኢየሱስ ከፊቱ ያለውን መከራ በዝርዝር ያውቅ ስለነበር ተጨንቋል ነገር ግን ቀደም ሲል እንደተመከለትነው በፈቃዱ ራሱን አሳልፎ ሰጠ እንጂ አልሸሸም፡፡ አሕመዲን የመስቀል መከራ ለምን ይሆን እንዲህ የቀለለባቸው? ምናልባት ስለ ስቅለት ዝርዝር ሂደት መረጃ ስለሌላቸው ይሆናል፡፡ አንድ ሰው ከመሰቀሉ በፊት በከባድ ሁኔታ ይገረፋል፡፡ ኢየሱስ በሮማውያን እጅ ብቻ ሳይሆን በአይሁድ ሸንጎም ተገርፏል፡፡ አይሁድ 40 ጅራፍ ነው የሚገርፉት፡፡ ከ40 አልፈው ህጉን እንዳይተላለፉ ምናልባት የቆጠራ ስህተት ካለ በሚል 39 ላይ ያቆማሉ፡፡ ሮማውያን ደግሞ የፈለጉትን ያህል ነው የሚገርፉት፡፡ አለንጋዎቹ ብዙ ቅርንጫፎች ያሏቸው ሲሆኑ በየአንጓዎቹ ላይ የብረት እና የአጥንት ጉጠቶች ይሰካሉ፡፡ ጅራፎቹ በተገራፊው ጀርባ ላይ ሲያርፉ ብረቶቹና አጥንቶቹ ቆዳውንና ሥጋውን ቦጭቀው ያነሳሉ፡፡ ከጥቂት ጅራፎች በኋላ የሰለባው የላይኛው ቆዳ ተገፎ ከስር ያለው ጡንቻ ይከፈታል፡፡ ግርፋቱ ሲቀጥል ጡንቻዎቹ ተበጣጥሰው የደም ስሮች መቆራረጥ ይጀምራሉ፤ ከተቆራረጡት ስሮች ውስጥ ደም ይንዶለዶላል፡፡ ብዙ ጊዜም የተገራፊዎቹ ሆድ ተከፍቶ አንጀታቸው እስከመውጣት ይደርሳል፡፡ ከዚህ የተነሳ ብዙዎቹ እዚያው ይሞቱ ነበር፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ ወደ መሰቀያ ቦታ ተወስደው እጆቻቸውና እግሮቻቸው ሰባት ኢንች በሚረዝሙ ሚስማሮች በእንጨት ላይ ይቸነከራሉ፡፡ የእጅ መዳፎች የአንድን ሰው ክብደት መሸከም ስለማይችሉ ሚስማሮቹ ከመዳፍ ከፍ ብለው በክንድ አጥንቶች መካከል ይመታሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ሚስማሮቹ የእጅ ነርቮችን በጣጥሰው ስለሚያልፉ ሰለባዎቹ ለከፍተኛ የሥቃይ ስሜት ይዳረጋሉ፡፡ ወደ ላይ ቀጥ ተደርገው ስለሚሰቀሉ መተንፈስ በእጅጉ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ተወጥረው ከተሰቀሉ ወዲያውኑ ታፍነው ስለሚሞቱ እግሮቻቸው ትንሽ አጠፍ ተደርገው ይቸነከራሉ፡፡ ለመተንፈስ በእግሮቻቸው ላይ በተሰካው ሚስማር ላይ ቆመው ወደ ላይና ወደ ታች እንደ ፓምፕ መንቀሳቀስ ያስፈልጋቸዋል፡፡ አየር ለማስገባት እግሮቻቸውን አጥፈው ወደ ታች ዝቅ ይላሉ፡፡ ለማስወጣት ደግሞ እግሮቻቸውን ወጥረው ወደ ላይ ይላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ የተሰቀሉበት ደረቅ እንጨት በግርፋት የቆሰለውን ጀርባቸውን ይፈቀፍቃቸዋል፡፡ እንቅስቃሴውን ለአፍታ ካቆሙ ወዲያውኑ ታፍነው ይሞታሉ፡፡ ለዚህ ነው ከኢየሱስ ጋር የተሰቀሉትን ወንበዴዎች ቶሎ እንዲሞቱ ለማድረግ ጭኖቻቸውን የሰበሩት፡፡[2] ይህንን ስቃይ ለማስታገስ ሮማውያን ብዙ ጊዜ ሀሞት፣ ከርቤና የወይን ጠጅ የተቀላቀለበትን አደንዛዥ መጠጥ ይሰጧቸው ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ግን ይህንን መጠጥ በመጠጣት ህመሙን ከማስታገስ ይልቅ ሙሉ ሥቃዩን በመቀበል መሞትን መረጠ (ማርቆስ 15፡23፣ ማቴዎስ 27፡34)፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ለሦስት ሰዓታት ያህል በእንዲህ ዓይነት ሥቃይ ውስጥ በማለፍ ነበር የመጨረሻ እስትንፋሱን የተነፈሰው፡፡ የዓለምን ሁሉ ኃጢአት መሸከም ደግሞ ምን ያህል ለሥቃይ እንደሚዳርግ ከእርሱ በስተቀር ማን አየው? እንግዲህ ጠያቂው እንዲህ ዓይነቱን መከራ እንደሚያስተናግድ በማወቁ ምክንያት ኢየሱስ መጨነቁ ተገቢ አልነበረም የሚል የሞኝ ሙግት ነው የገጠሙት፡፡
- እንደ ክርስቲያኖች አስተሳሰብ ኢየሱስ ለሰው ልጅ ኃጢአት ሲል ተሰውቶ ከሦስት ቀናት በኋላ ነፍሱ ተመልሶለታል፡፡ መስዋዕትነቱ ጊዜያዊ ነበር ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ሰው መስዋዕት ሲያደርግ መሰዋዕቱን መልሶ አይወስድም፤ ኢየሱስ ግን ወሰደ፡፡ ከሰው መስዋዕት ያንስ ነበርን?
በቅዱሳት መጻሕፍት መሠረት ኃጢአትን የሚያስተሰርየው ደም ነው (ዘሌዋውያን 17፡11፣ ዕብራውያን 9፡22)፡፡ ክርስቶስ ደሙን በማፍሰስ ነው ኃጢአታችንን ያስተሰረየው (ማቴዎስ 20፡28፣ ኤፌሶን 1፡7፣ ዕብራውያን 9፡7-14፣ 1ጴጥሮስ 1፡18-19፣ 1ዮሐንስ 1፡7፣ የሐዋርያት ሥራ 20፡28)፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ አካል ሥጋና አጥንት ነበረው (ሉቃስ 24፡39)፡፡ ነገር ግን ስለ ኃጢአታችን ስርየት ያፈሰሰውን ደሙን ይዞ መነሳቱን የሚጠቁም የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ባለመኖሩ የኢየሱስ መስዋዕት ጊዜያዊ እንደነበር ለመናገር የሚያበቃ ምንም ነገር የለም፡፡
- ማቴዎስ 27፡52-53 “መቃብሮችም ተከፍተው ሞተው ለነበሩት ብዙ ቅዱሳን ሰዎች ከሞት ተነሱ፡፡ ከመቃብርም ወጡና ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ወደ ቅድስት ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም ገቡ፤ በዚያም ለብዙ ሰዎች ታዩ፡፡” ይላል፡፡ እነዚህ ሰዎች በኋላ የት ገቡ? ይህን እጅግ አስገራሚ ትዕይንት ሊሆን የሚችል ነገር ለምን ሌሎች ወንጌል ጸሐፊዎች ሳይጽፉት ቀሩ? ይህ ክስተት ተፈፅሞ ቢሆን ኖሮ ከኢየሱስ ተዓምር ይተናነስ ነበርን? በዚሁ ሰበብ ብቻ ከከሀዲያን የሚያምን ሰው ሁሉ አልነበረምን? ሰዎችስ ሞትና ወዲያኛው ዓለም ምን እንደሚመስል ይጠይቋቸው አልነበረምን? ይገልጹስ አልነበረምን? ሰዎች በትንሳኤ ከሙታን ይቀሰቅሳሉ የተባለው ሳይደርስ መቀስቀሳቸውን ለሰው እንዴትስ አብራሩት?
ይህንን ክስተት የዘገበው ማቴዎስ ብቻ በመሆኑ ምክንያት ብዙ ሰዎች ታሪካዊነቱን አጠያያቂ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ የተቀሩት ወንጌላት ለምን እንዳልዘገቡት እርግጠኛ ሆኖ መናገር ባአይቻልም የማቴዎስ ወንጌል የተጻፈው የመስቀሉ ትውልድ ከማለፉ በፊት በመሆኑ እውነት መሆን አለመሆኑን መመስከር የሚችሉ ሰዎች ባሉበት ሁኔታ እንዲህ ዓይነቱን ታሪክ ፈጥሮ መጻፍ የማይታሰብ ነው፡፡ ጠያቂው ያቀረቧቸው የተቀሩት ጥያቄዎች ይህ ክስተት ታሪካዊ አለመሆኑን የሚያሳዩ አይደሉም፡፡ እነዚህን ቅዱሳን ሰዎች አይተው ያመኑ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ሰዎችም ስለ ሞትና ስለ ወዲያኛው ዓለም ጠይቀዋቸው እነርሱም ተናግረው ሊሆን ይችላል፤ ከመጨረሻው ዘመን በፊት እንዴት ከሙታን ሊነሱ እንደቻሉ ተናግረውም ሊሆን ይችላል፡፡ ስላልተጻፈ ብቻ እነዚህ ሁሉ ነገሮች አልተከሰቱም ልንል አንችልም፡፡ ነገር ግን ከተጻፈው በማለፍ መናገርም ተገቢ አይደለም፡፡ ጠያቂው ሙስሊም እንደመሆናቸው እንዲህ ያለውን ጥያቄ ማንሳታቸው በእጅጉ አስገራሚ ነው፡፡ ቁርኣን ሱራ 2፡259 እና 18፡25 ላይ የተወሰኑ ወጣቶች ከውሻቸው ጋር ለ 300 ዓመታት ያህል በእንቅልፍ እንዳሳለፉና እንደነቁ ይናገራል፡፡ ይህ ታሪክ እውነት ቢሆን ኖሮ ስለምን በሌሎች የታሪክ መዛግብት ተጽፎ አላገኘነውም? ዳሩ ግን ይህ ታሪክ እውነተኛ ባለመሆኑና በ 521 ዓ.ም. ገደማ በሦርያ ከተጻፈ የተረት መጽሐፍ ላይ የተወሰደ በመሆኑ በተዓማኒ የታሪክ መዛግብት ውስጥ እንዲገኝ አንጠብቅም፡፡[3] ሙሐመድ ጨረቃን ለሁለት የመግመስ ተዓምር እንዳደረጉ በእስላማዊ ምንጮች ውስጥ ተጽፎ እናገኛለን፡፡ ሱራ 54፡1 ላይ የሚገኘው ቃል ስለዚያ ክስተት እንደሚናገር ብዙ ሙስሊም ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡ ይህ ክስተት በእውነት የተፈፀመ ቢሆን ኖሮ ስለምን በሌሎች የታሪክ መዛግብት ውስጥ አልተጻፈም? ወይስ በዚያ ዘመን ጨረቃ የምትወጣው በአረብያ ብቻ ነበር?
- ኢየሱስ የሰረየው የውርስ ኃጢአትን ነው ወይስ በየጊዜው የሚፈፀምን ኃጢአት? ምላሹ የውርስ ከሆና በየጊዜው ለፈፀሙት ኃጢአቶች ክርስቲያኖች ሊቀጡ ነው ማለት ነው፡፡ ምላሹ ለሁለቱም ከሆነ “መልካም ስራ” መስራት እንደሚገባ የሚያስተምሩ ጥቅሶች ፋይዳቸው ምንድነው?
በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑት ክርስቲያኖች ሁሉም ኃጢአቶች ይሰረዩላቸዋል (1ዮሐንስ 1፡7)፡፡ መልካም ሥራ መሥራት የእውነተኛ እምነት መገለጫ እንጂ ኃጢአትን ማስተሰረያ አይደለም፡፡
- ለሰው ኃጢአት የተሰዋው አምላክ ከሆነ እንዴት አምላክ ራሱን ለራሱ ይሰዋል? ወይስ ከሦስቱ አንዱ ነው ለሁለቱ የሚሰዋው?
ሰው ኃጢአትን ሲሠራ የእግዚአብሔር ፍትህ ባለ ዕዳ ስለሚሆን መስዋዕቱ የሚቀርበው ለእግዚአብሔር ፍትሃዊ ባሕርይ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው ለሌላው ቤዛ ሆኖ ለእግዚአብሔር ወጆ መክፈል እንደማይችል ይናገራል፡-
“የሌላውን ሕይወት መቤዠት የሚችል ሰው፣ ወይም ለእግዚአብሔር ወጆ የሚከፍልለት ማንም የለም፡፡ የነፍስ ቤዛ ውድ ነውና፤ በቂ ዋጋም ከቶ ሊገኝለት አይችልም” (መዝሙር 49፡7-8 አ.መ.ት.)፡፡
ሰው ሁሉ ኃጢአተኛ ስለሆነ ለሌላው ቤዛ መሆን ይቅርና ራሱን እንኳ ማዳን አይችልም (ሮሜ 3፡9-10፣ 3፡23)፡፡ ለዚህ ነው ፍፁም ቅዱስና ፃድቅ የሆነ፣ የሰው ልጆችን ኃጢአት በሙሉ የመሸከም ብቃት ያለው ቤዛ ያስፈለገው፡፡ ነቢዩ ዳዊት ለዚህ የሚበቃውና የሌላውን ነፍስ መቤዠት የሚችለው እግዚአብሔር እንደሆነ ይናገራል፡-
“እግዚአብሔር ግን ነፍሴን ከሲኦል እጅ ይቤዣታል፤ በእርግጥም በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት አለኝ” (መዝሙር 49፡15 አ.መ.ት.)፡፡
ከሦስቱ የሥላሴ አካላት መካከል አንዱ የሆነው ወልድ ወደ ምድር በመምጣት ስለ ኃጢአታችን ሲል ራሱን ለአብ መስዋዕት አድርጎ በማቅረብ እዳችንን ከፈለ፤ ከኃጢአት ባርነትም ነፃ አወጣን፡-
“ክርስቶስም ደግሞ እንደ ወደዳችሁ ለእግዚአብሔርም የመዓዛ ሽታ የሚሆንን መባንና መሥዋዕትን አድርጎ ስለ እናንተ ራሱን አሳልፎ እንደ ሰጠ በፍቅር ተመላለሱ፡፡” (ኤፌሶን 5፡2)
“ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን?” (ዕብራውያን 9፡14)
ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ፡፡ ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ፡፡ (1ዮሐንስ 2፡1-2)
ክርስቶስ ጌታችን የእኛን ኃጢአት ተሸክሞ እኛ መቀጣት የሚገባንን ቅጣት ተቀጣልን፡፡ አብ የክርስቶስን መስዋዕትነት ተቀበለ፤ በእኛ ላይ መፈፀም የነበረበት የእግዚአብሔር ፍትሃዊ ቁጣ ኃጢአታችንን በተሸከመው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ስለተፈፀመ ከቁጣው ዳንን (ሮሜ 3፡25-26፣ ዕብራውያን 2፡9-18)፡፡ ይህ ጉዳይ በዕውቀቱ፣ በጥበቡና በባሕርዩ ከእኛ እጅግ ከላቀው ከቅዱስ እግዚአብሔር ዕይታ አኳያ የተከናወነ በመሆኑ ሚስጥሩን ውሱን በሆነው አዕምሯችን መርምረን ልንደርስበት እንደምንችል በማሰብ ስህተት መስራት የለብንም፡፡ እኛ ማወቅና መረዳት የምንችለው በቃሉ ውስጥ በተገለጠልን መጠን ብቻ እንጂ የእግዚአብሔርን ሥራ በተገደበው አዕምሯችን መርምረን ልደርስበት አንችልም፡፡ የእግዚአብሔርን ሥራ ሙሉ በሙሉ መረዳት የሚችል አዕምሮ እንዳለን በትዕቢት በማሰብ በቃሉ ውስጥ የተገለጠውን እውነት በመፃረር እንዳንጠፋ መጠንቀቅ ያስፈልገናል፡፡
ነገር ግን ጠያቂያችን አላህ የአይሁዶችንና የክርስቲያኖችን ነፍስ መስዋዕት በማድረግ ከገሃነም እንደሚቤዣቸው ስለሚያምኑ ችግር ውስጥ ሊገቡ ነው፡፡ በተከታዩ ሐዲስ መሠረት አላህ መስዋዕቱን የሚከፍለው ለማነው?
“አቡ ቡርዳ አባቱን ዋቢ በማድረግ እንዳስተላለፈው የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) እንዲህ ብለዋል፡- ከሙስሊም አንድም አይሞትም አላህ በእርሱ ፋንታ አይሁዳዊ ወይም ክርስቲያን በገሃነም ውስጥ የሚጥል ቢሆን እንጂ፡፡” [4]
- አምላክ አዳምን እንዲሁ መማር እየቻለ ለምን የኢየሱስ ደም እንዲፈስ ፈለገ? ደም ማፍሰስ የፈጣሪ ባህሪ ነውን?
በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የኃጢአት ውጤቱ ሞት ነው (ምሳሌ 10፡16፣ ሮሜ 6፡23)፡፡ እግዚአብሔር የፍቅር አምላክ የሆነውን ያህል የፍትህም አምላክ ነው (ኢሳይያስ 28፡17፣ 61፡8፣ ምሳሌ 24፡12፣ ሮሜ 1፡18-32፣ 2፡5)፡፡ የፍትህ አምላክ የሆነው እግዚአብሔር ያለ ቅጣት ኃጢአተኛን ማሰናበት ከባሕርዩ ጋር ይጣረሳል፡፡ ነገር ግን የፍቅር አምላክ እንደመሆኑ መጠን ደግሞ የሰው ልጆች ለዘለዓለም ከእርሱ ተለይተው እንዲጠፉ አልፈለገም፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር ፍትህ ባለዕዳዎች የሆንነውን እኛን እዳችንን በመክፈል ነፃ የሚያወጣንን ቤዛ በማዘጋጀት ፍትሃዊ ባሕርዩን ሳይጣረስ ፍቅሩን ገለጠልን፡፡ የክርስቶስ ደም እንዲፈስስ ማድረጉ እግዚአብሔር ደም አፍሳሽ የሆነ ባሕርይ እንዳለው እንድንናገር አያስችለንም፡፡ ለምሳሌ ያህል አንድ ሕግ አስፈፃሚ የሞት ፍርድ የተፈረደበትን ሰው እንዲገደል ሲያደርግ ፍትህን ለማስፈፀም ያንን ይፈፅማል እንጂ ደም ማፍሰስ ባሕርዩ ስለሆነ አይደለም፡፡ ፍርድ በተላለፈበት ሰው ላይ ፍትህን ተፈፃሚ ማድረጉ እንደ ትክክለኛ እርምጃ የሚቆጠር እንጂ ደም ማፍሰስ የሰውየው ባሕርይ እንደሆነ በመናገር ሰውየውን አያስወቅስም፡፡
- በዮሐንስ 19፡32 -36 ላይ “ስለዚህ ወታደሮቹ ሄደው ከኢየሱስ ጋር የተሰቀሉትን ሰዎችን ጭን ሰበሩ፤ ወደ ኢየሱስ በሄዱ ጊዜ ግን እርሱ ቀደም ብሎ እንደ ሞተ አይተው ጭኑን አልሰበሩም፡፡ ነገር ግን ከወታደሮቹ አንዱ ጎኑን በጦር ወጋው፡፡ ወዲያውም ከጎኑ ደምና ውሃ ወጣ፡፡ ይህንን ያየ እናንተ እንደምታምኑ መሰከረ፡፡ ምስክርነቱም እውነት ነው፡፡ የሚናገረውም እውነት እንደሆነ እርሱ ያውቃል፡፡ ይህም የሆነው “ከእርሱ አንድ አጥንት እንኳ አይሰበርም” የሚለው የመፅሐፍ ቃል እንዲፈፀም ነው” ይላል፡፡ “ትንቢት” የተባለው የሚከተለው ነው “ደግ ሰው በብዙ መከራ ይፈተናል፤ እግዚአብሔር ግን ከዚህ ሁሉ ያድነዋል፡፡ እግዚአብሔር በጥንቃቄ ስለ ሚጠብቀው ከአጥንቶቹ አንዱ እንኳ አይሰበርም» (መዝሙር 34: 19-20)፡፡
ሀ). የሞተ ሰው ቢወጋ ደም ይፈሰዋልን?
የሞተ ሰው ልቡ አካባቢ ከተወጋ የተጠራቀመ ደም ይፈስሳል፡፡ ወታደሩ ኢየሱስን ሲወጋው ደም ብቻ ሳይሆን ደምና ውኀ ተለያይቶ ነበር የፈሰሰው፡፡ ይህ በሁለት ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል፡፡ የመጀመርያው ሰው ሲሞት ደም ስለሚረጋ ከውኀ ይለያል፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ልብ አካባቢ ውኀ መሳይ ፈሳሽ ስላለ የሞተ ሰው ሲወጋ ይህ ፈሳሽ ከደም ተለይቶ ይወጣል፡፡ በዚህም ሆነ በዚያ ደምና ውኀ መውጣቱ የኢየሱስን መሞት መቶ በመቶ ያረጋገጠ ክስተት ነበር፡፡[5] ይህንን ጉዳይ ያጠኑ የጤና ተመራማሪዎች የጥናታቸውን ውጤት ማርች 21፣ 1986 ዓ.ም. በታተመው Journal of the American Medical Association ላይ ያሰፈሩ ሲሆን ደምና ውኀ መውጣቱ ኢየሱስ በጦር ከመወጋቱ በፊት መሞቱን መቶ በመቶ ያረጋገጠ ክስተት መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡[6] የተሰቀለ ሰው ከመስቀል ላይ ከመውረዱ በፊት ጭኑን በመስበር ወይም ልቡን በጦር በመውጋት ሞቱን ማረጋገጥ የሮማውያን ልማድ ነበር፡፡ ጠያቂው ይህንን ክስተት ኢየሱስ ላለመሞቱ እንደ ማስረጃ መጠቀማቸው ዓለም ከደረሰበት መረጃ ምን ያህል የራቁና ወደ ኋላ የቀሩ መሆናቸውን ያመለክታል፡፡
ለ). ትንቢቱ “እግዚአብሔር ግን ከዚህ ሁሉ ያድነዋል” ይላል፡፡ ግና በተቃራኒው ክርስትና እንደሚለው ኢየሱስ ሳይድን ሞቷል፡፡ ታድያ ጸሐፊው ለምን ያለመሞቱን ትቶ የአጥንቱን አለመሰበር ብቻ ተረከልን?
ሐ). ወይስ ትንቢቱ በትክክል ሳይፈፀም ቀረ?
ትንቢቱ በትክክል ተፈፅሟል ነገር ግን ጠያቂው “እግዚአብሔር ግን ከዚህ ሁሉ ያድነዋል” የሚለውን ሐረግ “ደግ ሰው በብዙ መከራ ይፈተናል” ከሚለው ለይተው በማንበባቸው ምክንያት ለጥቅሱ የተሳሳተ ትርጓሜ በመስጠት ግራ ተጋብተዋል፡፡ ይህ ጥቅስ ቅዱሳን ሰዎች በብዙ መከራ እንደሚፈተኑ ይናገራል፡፡ ብዙ የእግዚአብሔር ሰዎች እስከ ሞት ድረስ በብዙ መከራ መፈተናቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል (ዘፍጥረት 4፡3-8፣ ዮሐንስ 16፡1-4፣ የሐዋርያት ሥራ 14፡19-22፣ ፊልጵስዩስ 1፡29፣ 2ጢሞቴዎስ 3፡10-13፣ ዕብራውያን 11፡32-38፣ ራዕይ 6፡9-11)፡፡ እግዚአብሔር ለቅዱሳኑ በመከራ ውስጥ የሚፀኑበትን አቅም በመስጠትና ካለፉ በኋላ ንፅህናቸውን በተዓምራቱ በማረጋገጥ እንዲሁም ደማቸውን በመበቀል ድልን ይሰጣቸዋል፡፡ የጠያቂው መመርያ የሆነው ቁርኣን እንኳ በመከራ ውስጥ ያለፉና የተገደሉ ነቢያት ስለመኖራቸው ይናገራል (ሱራ 2፡87፣ 2፡91)፡፡ ኢየሱስ በብዙ መከራ ውስጥ በማለፍ ቢፈተንም ነገር ግን በትንሳኤው አማካይነት መከራውን ድል ነስቷል፡፡ የክርስቶስ ምሳሌ የሆነው የፋሲካው በግ አጥንት እንዳይሰበር እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ውስጥ ትዕዛዝን በመስጠቱ ምክንያት የክርስቶስ አጥንት ቢሰበር ኖሮ የፋሲካውን መስዋዕት መስፈርት ስለማያሟላ ቤዛችን መሆን ባልቻለም ነበር (ዘጸአት 12፡46፣ ዘኁልቁ 9፡12፣ 1ቆሮንቶስ 5፡7)፡፡ “ከእርሱ አጥንት አይሰበርም” የሚለው ቃል በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ ከሚገኘው ትንቢት ይልቅ ይኸኛውን ትዕምርታዊ ትንቢት እንደሚያመለክት ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ይስማሙበታል፡፡
- ዕብራውያን 5፡8-10 “የእግዚአብሔር ልጅ ቢሆንም እንኳ ከተበቀለው መከራ መታዘዝን ተማረ፡፡ በዚህም ፍፁም ሆኖ ከተገኘ በኋላ እርሱን ለሚታዘዙ ሁሉ የዘለዓለም ድነት ምክንያት ሆነላቸው፡፡ እንደ መልከ ፄዴቅ ሹመትም ሊቀ ካህናት ተብሎ በእግዚአብሔር ተሾመ፡፡” ይላል፡፡ በዚህ ጥቅስ ኢየሱስ እንደ መልከ ፄዴቅ ሊቀ ካህናት ተብሎ መሾሙ ተገልጿል፡፡ ሳይሾም በፊትስ ምን ነበር?
ለዚህ ጥያቄ መልስ ቁጥር 59ን ይመልከቱ፡፡
ኢየሱስ የዘለዓለም ድነት ምክንያት የሆነው በርሱ ለሰው ኃጢአት መሰቀል ላመኑት ነው ወይስ እርሱን ለታዘዙት? ጥቅሱ የሚለው “ለሚታዘዙ ነው” ታድያ ክርስቲያኖች ትዕዛዛቱን በጳውሎስ አስተምህሮት ተመርተው “የዘለዓለም ህይወት እናገኛለን” በማለት ለምን ተቃረኑ?
እውነተኛ እምነት በመታዘዝ ስለሚገለፅ እምነትና መታዘዝን ለያይቶ ማየት አይቻልም፡፡ ይህንን ደግሞ ከሐዋርያው ጳውሎስ በላይ ያስተማረ ማንም የለም፡፡ ለዚህም በምዕራፍ 4 ጥያቄ ቁጥር 8 ላይ በቂ ማስረጃዎችን ጠቅሰናል፡፡ ጠያቂው ጳውሎስን በጭፍን ጥላቻ የሚጠሉ እንጂ ትምህርቶቹን የሚያውቁ ሰው አለመሆናቸው ግልፅ ነው፡፡
- የዮሐንስ ወንጌል 7፡33-34 “ኢየሱስም እንዲህ አለ ከእናተ ጋር የምቆየው ጥቂት ግዜ ነው ከዛም ወደ ላከኝ እሄዳለሁ፤ ትፈልጉኛላችሁ ግን አታገኙኝም ወዳለሁበት ልትመጡ አትችሉም፡፡” ይላል፡፡ ኢየሱስ “ከእናንተ ጋር የምቆየው ጥቂት ጊዜ ነው፤ ከዛም ወደ ላከኝ እሄዳለሁ፡፡” አለ እንጂ “ከዚያም በኋላ ይዛችሁ ትሰቅሉኛላችሁ፤ ከዚያም በሶስተኛ ቀን እነሳለሁ፤ ከዚያም ወደ ላከኝ እሄዳለሁ” እንዳላለ ልብ ብለዋልን? ምን አናልባት “ከዚያም ወደ ላከኝ እሄዳለሁ” ብቻ ማለቱ ፍፃሜውን በአጭሩ ለመግለፅ ነው የሚል የዋህ ክርክር ሊነሳ ይችላል፡፡ ኢየሱስ ተይዞ፣ ተፈርዶበት፣ ተሰቅሎ ሞቶ፣ ከዚያም ወደ ላከው የሚሄድማ ከሆነ “ትፈልጉኛላችሁ ግን አታገኙኝም፤ ወዳለሁበትም ልትመጡ አትችሉም” ማለቱ ትርጉም አልባ አልሆነምን? ወይስ ኢየሱስ እንደሚያዝ አያውቅም ነበር?
ኢየሱስ እንደሚያዝ ያውቅ ነበር፡፡ ይህንን ደግሞ በብዙ ቦታዎች ላይ ተናግሯል፡፡ ለአብነት ያህል ተከታዮቹን ጥቅሶች ይመልከቱ፡- (ማቴዎስ 12፡38-40፣ 16፡21፣ 17፡22-23፣ 20፡18-10፣ 21፡33-46፣ 26፡21-32፣ 26፡36-40፣ 26፡61-62፣ ማርቆስ 8፡31፣ 9፡9፣ 9፡30-31፣ 10፡33-34፣ 10፡45፣ 12፡1-12 14፡18-28፣ 14፡32-40፣ ሉቃስ 9፡22፣ 11፡29-30፣ 13፡32-33፣ 20፡9-19፣ 22፡15-20፣ 22፡39-46፣ ዮሐንስ 3፡13-14፣ 8፡28፣ 12፡32-34)፡፡ ኢየሱስ በነዚህ ቦታዎች ሁሉ ላይ ስለ ሞቱ ተናግሮ ሳለ በዚህ በአንድ ጥቅስ ውስጥ ሞቱን ሳይጠቅስ ከእርገቱ በኋላ አይሁድ ፈልገው እንደማያገኙት መናገሩ ላለመሞቱ ማስረጃ ሊሆን የሚችለው እንዴት ሆኖ ነው? የአሕመዲን አዕምሮ ኢየሱስ እንዳልተሰቀለ በሚያስተምረው የክህደት ንፅረተ ዓለም ስለታወረ ለማስረጃዎች ሁሉ ዝግ ነው፡፡ ኢየሱስ ስለ ስቅለቱ የተናገረባቸውን እነዚህን ሁሉ ጥቅሶች ካነበበ በኋላ ስለ እርገቱ ብቻ የተናገረበትን አንድ ወይም ሁለት ጥቅሶች በመጥቀስ ሞቱን ለመካድ የሚሞክር ሰው በቃላት በማይገለፅ የክህደትና የጨለማ ዓለም ውስጥ መኖሩ እርግጥ ነው፡፡
- ኢየሱስ በዮሐንስ 18፡37 ላይ “እኔ ንጉሥ እንደሆንኩ መናገርህ ትክክል ነው፤ የተወለድሁት ወደዚህ ዓለም የመጣሁት ስለ እውነት ለመመስከር ነው ከእውነት የሆነ ሁሉ ይሰማኛል፡፡” ብሏል፡፡ ኢየሱስ በዚህ ጥቅስ የተወለድሁት በማለት ስለራሱ መናገር መጀመሩ ምንን ያመለክታል? የርሱ ህልውና ከመወለዱ ጋር የጀመረ መሆኑን አያሳይምን?
አያሳይም፤ ምክንያቱም ኢየሱስ በመወለድ ወደዚህ ዓለም ቢመጣም ነገር ግን ከመወለዱ በፊት በሰማይ በአብ ዘንድ ይኖር እንደነበረ በብዙ ቦታዎች ላይ ተናግሯልና፡- (ዮሐንስ 3፡13፣ 6፡33-48፣ 6፡62፣ 8፡42፣ 56-58፣ 13፡3፣ በተጨማሪም ዮሐንስ 1፡1-3)፡፡
ኢየሱስ ከእናቱ ከማሪያም ተወልዶ ወደዚህ ዓለም የመጣው ለምንድን ነው? ክርስቲያኖች እንደሚሉት ለሰው ልጅ ኃጢአት ቤዛ ሊሆን ነውን? እርሱ ግን ምን አለ? “ወደዚህ ዓለም የመጣሁት ስለ እውነት ለመመስከር ነው፡፡” ታድያ ክርስትያኖች ምነው ኢየሱስን ተቃረኑ?
ለእውነት መመስከር በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባርም ነው፡፡ “ሸሂድ” የሚለው ሰማዕትነትን የሚያሳየው የአረብኛ ቃል ቀጥተኛ ትርጉም “ምስክር” የሚል ሲሆን ጠያቂው በጠቀሱት ጥቅስ ውስጥ ጌታችን የተጠቀመው “ማርቱሬኦ”[7] የሚለው “ለመመስከር” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ሰማዕትነትን ያሳያል፡፡ ኢየሱስ ሰማዕት በመሆን ለእውነት መስክሯል፡፡ ኢየሱስ በሌሎች ቦታዎች ላይ ነፍሱን ለኃጢኣተኞች ቤዛ ለማድረግ መምጣቱን ስለተናገረ (ለምሳሌ ያህል ማቴዎስ 20፡28) ለእውነት ለመመስከር መምጣቱን መናገሩ ተልዕኮው ዘርፈ ብዙ መሆኑን የሚያሳይ እንጂ በዚህ ብቻ የተወሰነ መሆኑን የሚያመለክት አይደለም፡፡ ጠያቂው የተቃርኖን ትርጉም መማር ያስፈልጋቸዋል፡፡
- ሰው ገነት የሚገባው በኢየሱስ በማመን ብቻ ከሆነ ለምን ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 7፡8-16 ላይ ያላመነ ሚስት/ባል ያለው ሰው በአመነው ምክንያት ገነት እንደሚገባ ተናገረ?
ሐዋርያው እንዲህ ዓይነት ትምህርት አላስተማረም፡፡ ይህ የጠያቂው የተሳሳተ መረዳት ነው፡፡ ያላመነው ወገን ትዳሩን መፍታት ባይፈልግ አማኞቹ መፍታት የለባቸውም፤ ምክንያቱም በእነርሱ ሰበብ የመዳን ዕድል ይኖራቸዋልና፡፡ ይህ ማለት ያላመነው ወገን ባመነው ወገን አማካይነት የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቶ በማመን የመዳን ዕድል እንደሚያገኝ ለማመልከት የተነገረ እንጂ ካመነ ሰው ጋር በትዳር በመጣመሩ ምክንያት ይድናል የሚል ትምህርት የለም፡፡
- አሕመዲን ራሳቸውን በመደጋገም አንባቢያኖቻቸውን ማሰልቸታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ምዕራፍ 1 ቁጥር 61 ላይ ስለ ክርስቲያኖች ክፍፍል የጠየቁትን ስለደገሙ ታልፏል፡፡
- ከምዕራፍ 1 ጥያቄ 3 ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ታልፏል፡፡
- አምላክ ነው መስዋዕት የሆነው ወይንስ «ልጁ» ክርስትያኖች ምን ይላሉ?
አምላክ የሆነው የአምላክ ልጅ ነው፡፡ የሥላሴን አስተምህሮ ማስታወስ ያሻል፡፡
- ኢየሱስ አምላክ ከነበረ እንዴት በሰው ይከዳል? አምላክ በሰው ይከዳልን?
ጠያቂው ሰው አምላኩን መካድ አይችልም እያሉ ነውን? እንደርሱ ከሆነ የቁርአኑ አላህ ሰዎች እንዳይክዱት ስለምን በተደጋጋሚ ያስጠነቅቃል? “አስታውሱኝም፤ አስታውሳችኋለሁና ለኔም አመስግኑ፤ አትካዱኝም፡፡” (ሱራ 2፡152)፡፡ ስለምንስ ሰዎችን “አማኞች” እና “ከሃዲዎች” በማለት ለሁለት ይከፍላል? (ሱራ 2፡161፣ 4፡102፣ 4፡140 9፡120፣ 9፡37፣ 42፡48፣ 47፡10፣ ወዘተ.)፡፡ ኡስታዙ ይህንን ጥያቄ የጻፉት የእንቅልፍ ሰዓታቸው ካለፈ በኋላ ይመስላል፡፡
- በዚሁ ምዕራፍ ቁጥር 23 ላይ የጠየቁትን ስለደገሙ ታልፏል፡፡
- አምላክ ፍትሃዊ ነው፡፡ ፍትህ ደግሞ በአንዱ ኃጢአት ሌላውን ያለመቅጣትን ይጠይቃል፡፡ “አምላክ እኛን ሊያድን ኢየሱስን መስዋዕት አደረገው” የሚለው አባባል የፍትህን ፅንሰ ሀሳብ አይፃረርምን? አንድ ሰው ሌላውን ገድሎ ወይም ወንጀል ፈፅሞ ፍርድ ቤት ቢቀርብና ዳኛው እርሱን በቅጣት ፋንታ ልጃቸውን ቢቀጡ ፍትሃዊነት ይሆናልን?
ከላይ የተጠቀሰውን ዓይነት ጥያቄ የሚጠይቅ ሙስሊም ስድስት መሠረታዊ እውነታዎችን ዘንግቷል
I. ሰዎችን በመስዋዕት አማካይነት ከኃጢአታቸው ማንፃት በአዲስ ኪዳን የተጀመረ ሥርኣት አለመሆኑን
በዘመነ ብሉይ ሰዎች እንስሳትን በመሰዋት ኃጢአታቸው ይሸፈንላቸው ነበር፡፡ እግዚአብሔር ለሙሴ የመስዋዕትን ሕግ ከመስጠቱ በፊት ይህንን ሥርኣት ሲፈፅሙ የነበሩ ቅዱሳን ሰዎች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ያህል አቤል (ዘፍጥረት 4፡3-5)፣ ኢዮብ (መጽሐፈ ኢዮብ 1፡5) ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ የፋሲካው በግ መስዋዕትም ቢሆን እግዚአብሔር በሌዋውያን አማካይነት የሚፈፀመውን የመስዋዕት ሥርኣት ለሙሴ ከመስጠቱ በፊት የተደረገ በመሆኑ ከሕጉ በፊት እንደተፈፀመ ሥርኣት ይቆጠራል (ዘጸአት 12፡1-30)፡፡ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር በእንስሳት መስዋዕት አማካይነት ሕዝቡን የማንፃት ሥርኣት ሰጠ (ዘሌዋውያን 6፡1-7፣ 16፡15-22)፡፡ ይህ ሥርኣት ከክርስቶስ እርገት በኋላ ለተወሰኑ ዓመታት ቢቆይም በ70 ዓ.ም. ከቤተ መቅደሱ መፍረስ ጋር ተያይዞ ቀርቷል፡፡ ነቢዩ ኤርምያስ እግዚአብሔር አዲስ ቃል ኪዳን ከሕዝቡ ጋር እንደሚያደርግ ተንብዮ ነበር (ኤርምያስ 31፡31-34)፡፡
II. ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መስዋዕትነት አስቀድሞ በብሉይ ኪዳን ትንቢት መነገሩን
መሲሁ መስዋዕት ሆኖ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው እንደሚዋጃቸው አስቀድሞ የተነገረ በመሆኑ ሐዋርያት ወይም ከእነርሱ በኋላ የተነሱት ክርስቲያኖች የፈጠሩት ትምህርት አይደለም (ኢሳይያስ 53)፡፡
III. ክርስቶስ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ለመዋጀት በገዛ ፈቃዱ መምጣቱን
ጌታችን ወደ ምድር የመጣው እና ራሱን ስለ እኛ ቤዛ ያደረገው በገዛ ፈቃዱ እንጂ በማንም አስገዳጅነት አልነበረም (ዮሐንስ 10፡11፣ 10፡15፣ 10፡17-18 15፡13፣ ማርቆስ 10፡45)፡፡ ራስን ስለሌላው መስዋዕት ማድረግ ደግሞ የሚያስመሰግን እንጂ የሚያስወቅስ ተግባር አይደለም፡፡ የሚከተሉትን ተግባራት የፈፀሙ ሰዎች መጥፎ ሥራ እንደሠሩ መናገር ይቻል ይሆን?:-
- የባንክ ሀራጅ የወጣበትን የወዳጁን ቤት እዳውን በመክፈል የታደገ ሰው፤
- የመኪናው ፍሬን በመበላሸቱ ሕዝቡን ከእልቂት ለመታደግ በራሱ አቅጣጫ ከብረት ምሰሶ ጋር አጋጭቶ በማቆም የሞተ ሾፌር፤
- ሕፃን ልጅ መሃል አስፓልት ላይ በመኪና ተገጭታ ከመሞቷ በፊት ገፍትሮ በማትረፍ የሞተ ሰው፤
- ጓደኞቹን ለማትረፍ በፈንጂ ላይ ተራምዶ የሞተ ወታደር፤
- በከባድ በሽታ የታመመ ሰው ስታክም ተበክላ ሕይወቷን ያጣች ዶክተር፤
- ጠቅላይ ሚኒስቴር እንዳይገደል በመሸፈን በጥይት ተመትቶ የሞተ አጃቢ፤
እነዚህን ድርጊቶች በፈቃደኝነት የሚፈፅሙ ወገኖች እንደ ጀግና ይወደሳሉ እንጂ አይወቀሱም፡፡ ጌታችንም እኛ ልንከፍለው የማንችለውን የኃጢአት እዳችንን በመክፈል ነፃ አውጥቶናል፡፡ እርሱ እዳችንን ባይከፍልልን ኖሮ የመዳን ተስፋ አልነበረንም፡፡ የእርሱ ተግባር እኛን ለማትረፍ በፈቃደኝነት የተፈፀመ መስዋዕትነት በመሆኑ የፍትህ ጥያቄን የሚያስነሳ አይደለም፡፡
IV. የሌላውን ሰው ዕዳ መክፈል ፍትሃዊ መሆኑን
በሰው የፍትህ ሥርአት ውስጥ አንዱ ስለሌላው የማይቀጣባቸው ብዙ ጉዳዮች ቢኖሩም ነገር ግን አንዱ ለሌላው የሚቀጣባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው ያለበትን የገንዘብ ዕዳ ራሱ መክፈል የማይችል ከሆነ ሌላ ሰው በፈቃደኝነት በመክፈል ከቅጣት ሊያተርፈው ይችላል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከጌታው ለሸሸው እና ባለ ዕዳ ለሆነው ኦናሲሞስ ለተሰኘ ባርያ ይህንን አድርጎ ነበር (ፊልሞና 1፡17-19)፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ኃጢአት ሙስሊሞች እንደሚሉት “ወንጀል” ሳይሆን መከፈል ያለበት እዳ ነው (ማቴዎስ 18፡21-35፣ ሉቃስ 7፡36-50፣ ቆላስይስ 2፡13-15)፡፡ እዳን በመክፈል ባለ እዳውን ከቅጣት ማትረፍ በምድራዊው የሰው ፍትህ ሥርአት ውስጥ እንኳ ተቀባይነት ያለው ተግባር ነው፡፡
V. እግዚአብሔር ሉኣላዊ ሥልጣን እንዳለው
ሰዎች የአንዱን ኃጢአት በራሳቸውም ሆነ በሌላ ሰው ላይ የማኖር መብትም፣ ስልጣንም ሆነ ችሎታ የላቸውም፡፡ የእግዚአብሔር ሥልጣን ግን ሉኣላዊ በመሆኑ የገዛ እዳችንን ወደ ራሱ በማስተላለፍ ሊከፍልልን ይችላል፡፡ ከሥላሴ አካላት መካከል አንዱ የሆነው ወልድ ወደ ምድር በመምጣት በኛ ምትክ ሆኖ የኃጢአት እዳችንን በመክፈል ነፃ አወጣን (2ቆሮንቶስ 5፡17-21፣ ዮሐንስ 1፡29፣ 10፡14-18፣ ገላቲያ 2፡20፣ ቆላስይስ 1፡13-23፣ 2፡13-15፣ ራዕይ 1፡5-6)፡፡ እግዚአብሔር ይህንን ማድረግ ከወደደ ስጦታውን በታላቅ አክብሮትና ምስጋና ከመቀበል ውጪ የእርሱን ሉኣላዊነት እንቃወም ዘንድ እኛ ማን ነን?
VI. በመስዋዕት መቤዠት በክርስትና ብቻ ሳይሆን በእስልምና ሃይማኖትም ውስጥ የሚገኝ መሆኑን
በብሉይ ኪዳን ውስጥ የሚገኘውን የመስዋዕት ሥርኣትም ሆነ የኢየሱስ ክርስቶስን ቤዛነት በመቃወም የሚጽፉና የሚሰብኩ ሙስሊሞች በገዛ መጻሕፍታቸው ውስጥ ተመሳሳይ ትምህርቶች ሰፍረው መገኘታቸውን አለማወቃቸው የሚያስገርም ነው፡፡ አላህ አብርሃምን ልጁን እንዲሰዋ እንዳዘዘው ቁርኣን ናገራል፡፡ አብርሃም የታዘዘውን በማድረግ ፈተናውን ማለፉን ካረጋገጠ በኋላ ልጁ እንዳይገደል እንዴት እንዳተረፈው ሲናገር፡- “በታላቅ ዕርድም (መስዋዕት) ተቤዠነው” ይላል (ሱራ 37፡106)፡፡ በመስዋዕት መቤዠት ለዘመናችን ሙስሊም ሰባኪያን እንግዳ ቢሆንም ላለፉት 14 ክፍለ ዘመናት በቁርኣን ውስጥ ተጽፎ የተቀመጠ ትምህርት ነው፡፡ በሌላ ቦታ ላይ ቁርኣን መስዋዕትን የማቅረብ ትዕዛዝ ከሙስሊሞች በፊት በነበሩት ሕዝቦች ሁሉ ላይ እንደተደነገገ ይናገራል፡- “ለሕዝብም ሁሉ (ወደ አላህ) መስዋዕት ማቅረብን ደነገግን፡፡” (22፡34)፡፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ እንዲህ ዓይነት ትምህርት ባለመሰጠቱ ይህ ጥቅስ “ለሕዝብም ሁሉ” በማለት ክርስቲያኖችን በማካተት የተሳሳተ መረጃ ቢያስተላልፍም ነገር ግን መስዋዕት ማቅረብ ከአምላክ የተሰጠ ትዕዛዝ መሆኑን በመመስከር የዘመናችን ሙስሊሞች የሚያስተምሩትን ትምህርት ውድቅ ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሙስሊሞች ወደ ገነት መግባት ይችሉ ዘንድ አላህ የእነርሱን ኃጢአት በአይሁድ እና በክርስቲያኖች ላይ በማስቀመጥ ወደ ገሃነም እንደሚልካቸው እስላማዊ ሐዲሳት በብዙ ቦታዎች ላይ ያስተምራሉ፡- “አቡ ቡርዳ አባቱን ዋቢ በማድረግ እንዳስተላለፈው የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) እንዲህ ብለዋል፡- ከሙስሊም አንድም አይሞትም አላህ በእርሱ ፋንታ አይሁዳዊ ወይም ክርስቲያን በገሃነም ውስጥ የሚጥል ቢሆን እንጂ፡፡”[8] በሌሎች ዘገባዎች ደግሞ በእለተ ትንሣኤ ሙስሊሞች ተራራ የሚያካክሉ ኃጢአቶቻቸውን ተሸክመው እንደሚመጡና አላህ ይቅር ብሏቸው በእነርሱ ፋንታ አይሁድ እና ክርስቲያኖችን ወደ ገሃነም እንደሚልክ ተጽፏል፡፡[9] ሙስሊሞች በኢየሱስ ቤዛነት ባያምኑም የእርሱ የሥጋ ዘመዶች በሆኑት በአይሁዳውያንና የእርሱ ተከታዮች በሆኑት በክርስቲያኖች ቤዛነት ያምናሉ ማለት ነው፡፡ ፍፅምና የሌላቸው አይሁድ እና ክርስቲያኖች የኃጢአት እዳቸውን መክፈል እንደሚችሉ ለማመን ያልከበዳቸው ሙስሊም ወገኖቻችን ንፁህና ቅዱስ የሆነው የእግዚአብሔር ልጅ የኃጢአታቸውን ዕዳ የመክፈል ብቃት እንዳለው ማመን ለምን ይሆን የከበዳቸው?
እንዲህ ዓይነት ትምህርቶችን የተሸከሙ መጻሕፍትን ታቅፈው ክርስትናን ለሚተቹ አሕመዲንን ለመሳሰሉት ሰባኪያን አጸፋ መመለስ አስፈላጊ በመሆኑ እንዲህ በማለት እንጠይቃቸዋለን፡- “አምላክ እኛን ሊያድን አይሁድና ክርስቲያኖችን መስዋዕት ያደርጋል” የሚለው የሙስሊሞች ተስፋ የፍትህን ፅንሰ ሀሳብ አይፃረርምን? አሕመዲንና መሰሎቻቸው መልስ እንዲሰጡን እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን መልስ እንደሌላቸው እናውቃለን፡፡
- በዚሁ ምዕራፍ ቁጥር 22 ላይ የጠየቁትን ስለደገሙ ታልፏል፡፡
- አብያተ ክርስቲያናት በሚያምኑበት መንገድ የአል-መሲህ መሰቀል ከአምላክ ፍትህ ከእዝነቱ ከኃይሉና ከጥበቡ ጋር የሚጣጣም ነው ወይ?
ኢየሱስ መሰቀሉ የእግዚአብሔር ፍትህ ከፍቅሩ ጋር ሳይጣረስ ይቅር እንዲለን አስችሎታል፡፡ እስልምናን ጨምሮ ከክርስትና ውጪ የሚገኝ የትኛውም ሃይማኖት የፈጣሪ ምህረት ፍትሃዊ ባሕርዩን ሳይጣረስ ለሰው ልጆች የኃጢአት ይቅርታ ሊገኝ የሚችልበትን መንገድ ማቅረብ አይችልም፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር ስላዘነልን እንዳንጠፋ ሲል አንድያ ልጁ በቅዱስ ደሙ ይዋጀን ዘንድ ላከልን፡-
“ገና ደካሞች ሳለን ክርስቶስ ዘመኑ ሲደርስ ስለ ኃጢአተኞች ሞቶአልና፡፡ ስለ ጻድቅ የሚሞት በጭንቅ ይገኛልና፤ ስለ ቸር ሰው ግን ሊሞት እንኳ የሚደፍር ምናልባት ይገኝ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል፡፡” (ሮሜ 5፡6-8)፡፡
በሐዋርያት ዘመን እንኳ የመስቀሉን መልዕክት እንደ ድካም እና እንደ ሞኝነት የሚቆጥሩ ሰነፎች ነበሩ፡፡ የሚጠፉት ሰዎች እንደ ድካም በሚቆጥሩት በዚህ ክስተት ውስጥ የሰው ልጆችን ሁሉ ኃጢአት ማስወገድ የሚችል ታላቅ የሆነ የእግዚአብሔር ኃይል ተገልጧል፡፡ ልበ-ዕውራን እንደ ሞኝነት በሚቆጥሩት በዚህ ክስተት ውስጥ የዓለም ጠቢባን ሁሉ ቢሰበሰቡ መድኃኒት ሊያገኙለት የማይችሉትን ወደ ዘለዓለም ሞት የሚወስደውን የኃጢአት በሽታ የሚፈውስ መድኃኒት ተገልጧል፡፡
“የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና፡፡ የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ ተብሎ ተጽፎአልና፡፡ ጥበበኛ የት አለ? ጻፊስ የት አለ? የዚች ዓለም መርማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገምን? በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች፥ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአልና፡፡ መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፥ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው፥ ለተጠሩት ግን፥ አይሁድ ቢሆኑ የግሪክ ሰዎችም ቢሆኑ፥ የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ክርስቶስ ነው፡፡” (1ቆሮንቶስ 1፡18-24)
- ጠያቂው እዚሁ ምዕራፍ ቁጥር 33 ላይ የጠየቁትን ስለደገሙ ታልፏል
- ከቁጥር 36 ጋር ተመሳሳይ ስለሆነ ታልፏል፡፡
- አምላክ ደጋፊዎቻቸውን ከአደጋ ለመጠበቅና የሚወዳቸውንም ሰዎች ለመከላከል የገባውን ቃል ኪዳን ኢየሱስ (ኢሳ) የአምላክ ጠላቶች ቀላል ሰለባ ሆነው እስኪወድቁ ድረስ ችላ ይላል ወይ? ይህ ደግሞ የገባውን ቃል የማስፈፀሚያ መንገድ ወይም የቃል ኪዳኑ ክቡርነት ቅድመ ሁኔታ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ወይ?
ይህ ጥያቄ እግዚአብሔር የሚወዳቸውን ሰዎች በመከራ ውስጥ እንዲያልፉ ፈፅሞ ሊፈቅድ አይችልም የሚል ከቅዱሳት መጻሕፍት ጋር የሚጣረስ ምልከታ ስላለው በእጅጉ የተሳሳተ ነው፡፡ ጠያቂው የነቢያትንና የቅዱሳን ሰዎችን ታሪክ ለማጥናት ጊዜ ቢወስዱ ኖሮ ይህንን ጥያቄ ባልጠየቁ ነበር፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም ሆነ በቁርኣን ውስጥ ብዙ ነቢያት በመከራ ውስጥ ማለፋቸውንና መገደላቸውን የሚናገሩ ታሪኮች አሉ፡፡ ለበለጠ ማብራርያ በዚሁ ምዕራፍ ቁጥር 13 እና 24 ‹ለ፣ሐ› ይመልከቱ፡፡
- ከሁሉም በላይ መሐሪ የሆነው አምላክ የመጀመሪያውን ኃጢአት ለአዳምና ለዝርዮቹ ይቅር ማለት የማይችልና ነብዩ ኢየሱስ መጥተው በደማቸው እስኪቤዙ ድረስ በጥርጣሬና በውዥንብር ውስጥ የተዋቸው አድርጎ ማመኑን ምክንያታዊና አሳማኝ ማድረግ ይቻላል ወይ?
እግዚአብሔር ከክርስቶስ ዘመን በፊት የነበሩትን ሕዝቦች በጥርጣሬና በውዥንብር ውስጥ እንደተዋቸው ክርስቲያኖች አያምኑም፡፡ ይልቁኑ የመሲሁን መምጣት እና ቤዛነቱን ግልፅ በሆነ ሁኔታ በነቢያቱ በኩል አስቀድሞ አስታውቋል (ኢሳይያስ 53፣ ዳንኤል 9፡24-26)፡፡ እግዚአብሔር ኃጢአትን ያለ ቅጣት ዝም ብሎ ይቅር ማለት አለበት የሚለው አመለካከት የእግዚአብሔርን ሁሉን ቻይነት እና ምህረት እንጂ ፍትሃዊ ባሕርዩን እና ለኃጢአት ያለውን አመለካከት ያገናዘበ ባለመሆኑ ተቀባይነት የለውም፡፡
- በስቅለት ወይም በደም ቤዛነት ማመን ከጥንታውያን የግሪክ ጣኦታውያን ከሮማውያን፣ ከህንዶችና ከፔርሺያውያን እምነቶች ውስጥ በስተቀር በየትኛውም ሃይማኖት ውስጥ ተከስቶ ያውቃል ወይ?
ይህ ጥያቄ ሁለት መሠረታዊ ችግሮች አሉበት፡፡ የመጀመርያው በደም መቤዠት በይሁዲ፣ በክርስትናም ሆነ በእስልምና ውስጥ መታመኑን መዘንጋቱ ነው፡፡ (ለጥያቄ 34 የተሰጠውን መልስ ይመልከቱ፡፡) ሁለተኛው ችግር ደግሞ አንድ ነገር በጣዖታውያን ወይም በአረማውያን የሚፈፀም ከሆነ ትክክል ሊሆን አይችልም የሚል የተሳሳተ ድምዳሜ ማንጸባረቁ ነው፡፡ ከአቤል ዘመን ጀምሮ ሰዎች ለእግዚአብሔር መስዋዕትን ያቀርቡ ነበር፡፡ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ኢዮብ፣ ሙሴ፣ ዳዊት እና ሰለሞንን የመሳሰሉት ታላላቅ ስብዕናዎች ይህንኑ ፈፅመዋል፡፡ አረማውያን እውነተኛ ላልሆኑ አማልክት መስዋዕት ማቅረባቸው ነው ትክክል ያልሆነው እንጂ ሥርአቱን መፈፀማቸው አይደለም፡፡
- በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በአፈታሪክ ከሚወሩት ከነባከስ አፖሎ አዶኒስ ሆረስና ከሌሎችም ጥንታውያን አማልክት በስተቀር ከኢየሱስ ጋር የሚነጻጸር አለ ወይ?
እነዚህ የአረማውያን አማልክት ከኢየሱስ ጋር እንደሚያመሳስላቸው የሚነገርላቸው አንዱ ከድንግል ተወልደዋል የመባላቸው ጉዳይ ነው፡፡ አሕመዲን ጀበል የኢየሱስ ታሪክ ከእነርሱ ጋር “መመሳሰሉ” ጥያቄ ከፈጠረባቸው ዒሳ ከድንግል መወለዱ በቁርኣን ውስጥ ስለተነገረ በራሳቸውም ሃይማኖት ላይ ጥያቄ አላቸው ማለት ነው፡፡ ሰውየው ክርስትናን ለማጣጣል ሲታገሉ የራሳቸውን ሃይማኖት ውድቅ አድርገውት አረፉ!
ኢየሱስን ከአረማውያን አማልክት ጋር የማመሳሰል እንቅስቃሴ በአሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን በጀርመን ለዘብተኛ የሥነ መለኮት ሊቃውንት የተጀመረ ሲሆን እንቅስቃሴው ብዙም ሳይቆይ ከሽፏል፡፡ የዚህ እንቅስቃሴ መሠረቱ የጀመርመኖች የፀረ ሴማዊነት አስተሳሰብ በመሆኑ አይሁዳዊ ኢየሱስን “በአረማዊ ኢየሱስ” የመተካት እኩይ ዓላማን ያነገበ ነበር፡፡ ይህ አመለካከት በአሁኑ ወቅት በበይነ መረብ (ኢንተርኔት) ላይ በሚሰብኩ አምላክ የለሾች (Internet Infidels) መካከል በስፋት የሚለፈፍ ሲሆን በታሪክም ሆነ በሥነ መለኮት ሊቃውንት መካከል ምንም ዓይነት ተቀባይነት የለውም፡፡ የዚህ ምክንያቱ ሁለት ነው፡፡ የመጀመርያው እነዚህ አፈ ታሪኮች ከክርስትና በኋላ የተፈጠሩ መሆናቸው የተረጋገጠና ከክርስትና በፊት ስለመኖራቸው ምንም ማስረጃ የሌላቸው መሆኑ ሲሆን ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ኢየሱስን ከመጀመርያው ክፍለ ዘመን የአይሁድ እምነት በማውጣት በእነዚህ የአረማውያን አፈታሪኮች አውድ ማየት ትርጉም የሚሰጥ ባለመሆኑ ነው፡፡ ጠያቂው ይህንን ርዕስ ወደ መድረኩ ማምጣታቸው በተዘዋዋሪ የራሳቸውን ሃይማኖት ውድቅ ከማድረግ ባለፈ መሠረት የለሽ ወሬ መሆኑ ተረጋግጦ ከአንድ ምዕተ ዓመት በፊት በሊቃውንት የተጣለውን ሙግት መጠቀማቸው ዕውቀታቸውንና አስተማማኝ መረጃ የመስጠት ብቃታቸውን እንድንጠራጠር ያደርገናል፡፡
- ከነብዩ ኢየሱስ (ዒሳ) የተላኩትን ቃላት የዓለም መጀመሪያና መጨረሻ (አልፋና ኦሜጋ)፣ የሰውን ልጅ በደም ወደ ቀጥተኛው ለመመለስ ነው የመጣሁት ካለው ከባኮስ ቃላት ጋር ለማነጻጸር ይህን ብሩህ አመለካከት ይሰጠን የለም ወይ? በነዚህ ቃላትና ዘግየት ብሎ በነብዩ ኢየሱስ ላይ በተላኩት ቃላት መካከል ያለው መመሳሰል የጉዳዩን ሁለንተናዊ እውነታ ለማጥናት አዲስ ስሜት ሊቀሰቅስ አይችልም ወይ?
ሮማውያን ባከስ በማለት የሚጠሩት ዲዮኒሰስ የተሰኘው የግሪካውያን ጣዖት ከኢየሱስ ጋር የሚመሳሰሉ ነገሮች እንዳሉት ቢነገርለትም ከልክ በላይ ተለጥጠው ለማመሳሰል የተሞከሩና ታሪኮቹ ከክርስቶስ በፊት ስለመኖራቸው ማስረጃ የሌላቸው በመሆናቸው በምሑራን ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም፡፡ ባከስ “የዓለም መጀመሪያና መጨረሻ (አልፋና ኦሜጋ)፣ የሰውን ልጅ በደም ወደ ቀጥተኛው ለመመለስ ነው የመጣሁት” በማለት እንደተናገረ ጠያቂው ያስቀመጡት ንግግር ምንጭ አልተጠቀሰለትም፡፡ ምንጩንም ለማወቅ ፍለጋ ብናደርግም ለማግኘት አልቻልንም፡፡ ከራሳቸው ፈጥረው የጻፉት ላለመሆኑ ዋስትና የለንም፡፡
- ሮማውያን ባለስልጣናት በኢየሱስ (ዒሳ) ላይ የነበራቸው ቅራኔ ምንድነው? ለበላይ ስልጣናቸው ተቀናቃኝ አልነበሩም፤ ለመሪ ግለሰቦችና ለቤተሰቦቻቸው ጥቅም ብዙ ነገርን ሰርተዋል፡፡ ደቀ መዛሙርቱም «የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር» እንዲሰጡ አስተምረዋል፤ ሰላምተኛ ሰባኪ የነበሩ ሲሆን በሃገር ውስጥ ህግና ስርዐትን ለማስጠበቅ ለሮማውያን ባለስልጣኖች ከፍተኛ አጋዥም ነበሩ፡፡ ታድያ ይህን ሰው ሰቅለው እርሱን የመሰለ ሕግ አክባሪና ታዛዥ ዜጋ ለምን ያጣሉ?
ኢየሱስ በእርግጥ እጅግ ሰላማዊና ሕግ አክባሪ ነበር ነገር ግን ሮማውያን ባለ ሥልጣናት ይህንን ተረድተዋል ወይ የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡ ኢየሱስን በተመለከተ በሮማውያን ባለ ሥልጣናት መካከል የአቋም ልዩነት ነበር፡፡ ጲላጦስ ከመረመረው በኋላ ንፅህናውን መስክሯል፡፡ ነገር ግን ታላቁ ሄሮድስ ኢየሱስን በልጅነቱ የመግደል ሙከራ በማድረጉ ምክንያት ዮሴፍና ማርያም ወደ ግብፅ ይዘውት ለመሰደድ ተገደዋል፡፡ ሙከራው ያልተሳካለት ሄሮድስም ዕድሜያቸው ከሁለት ዓመት በታች የሆኑትን የቤተ ልሔም ህፃናትን ጨፍጭፏል (ማቴዎስ 2)፡፡ ንጉሡ ይህንን እርምጃ የወሰደበት ምክንያት አይሁድ እንደሚወለድ ይጠብቁ የነበሩት መሲህ ሥልጣኑን የሚቀናቀን ስለመሰለው ነበር፡፡ ልጁ ሄሮድስ አንቲጳስም ሊገድለው ይፈልግ ነበር (ሉቃስ 13፡31-33)፡፡ መጥምቁ ዮሐንስንም ያስገደለው እርሱ ነበር (ማቴዎስ 14፡3-12)፡፡ ኢየሱስ ሰላማዊ ሰባኪና ሰዎች ተገቢውን ግብር ለሮማውያን እንዲከፍሉ ያስተማረ ቢሆንም ሮማውያን እርሱን እንደ ሥርአት አስከባሪ በመቁጠር መንከባከባቸው የማይመስል ነው፡፡ ኢየሱስም ደግሞ ከእነርሱ ጋር በመተባበር የፖለቲካ አጀንዳቸውን ስለማራመዱ ምንም ማስረጃ የለም፡፡ ጲላጦስ ንፅህናውን ቢያረጋግጥም በበዓል ወቅት በእርሱ ምክንያት አይሁድ ሊያስነሱት የነበረውን ሁከት በመፍራት እንዲሞት አሳልፎ ቢሰጠው አያስገርምም፡፡ ደግሞም የኢየሱስ ሞት የእግዚአብሔር ዕቅድ በመሆኑ በምንም መንገድ ሊቀር የሚችል አልነበረም፡፡
- ስለ ሮማውያን ገዢ ስለ ጲላጠስ ማንነትና ባህሪ ምን ያህል ነው የምናቀው? እርሱን በመቃወም ሮም ላይ ከከሰሱት ከዘመኑ አይሁዶች ጋር መልካም ግንኙነት ነበረው ወይ? በይሁዳ ላይ ያሳለፈው ውሳኔ በእርሱ የነበረውን ጥላቻና ንቀት አያመለክትም ወይ? ጉቦ (መደለያ) እንዲቀበል አላቀረበም ወይ? ነገሩ እንዲያ ከሆነ ዘንድ ፍላጎታቸውንና ትዕዛዛቸውን ለማስፈጸም ለምን ይቸኩላል?
ጲላጦስ ከአይሁድ ጋር መልካም ግንኙነት እንዳልነበረው ቢታወቅም ነገር ግን በኢየሱስ ላይ ከቀረቡት ክሶች መካከል አንዱ “ንጉሥ ነኝ ብሏል” የሚል ስለነበር እና ከቄሣር ውጪ ንጉሥ እንደሌላቸው በመናገር ጉዳዩን ከቄሣር ጋር ስላያያዙ ኢየሱስን አሳልፎ ሰጣቸው (ዮሐንስ 19፡15)፡፡ ጥያቄያቸውን ባይመልስ ከዚያ ቀደም በቄሣር ዘንድ እንደከሰሱትና እንዳስወቀሱት ሁሉ አሁንም በጥሩ ምክንያት እንዳይከሱት ስጋት እንዳደረበት ግልፅ ነው፡፡
የኢየሱስ አድናቂ የሆነውን ከበርቴ ጉቦ እንደነዮሴፍ ካሉት ለምን አልተቀበለም? ሉቃስ ባለው መሠረት ይህ ዮሴፍ በጣም ባለጸጋ የሆነ ለነብዩ ኢየሱስ በጣም ያስብ የነበረ የምክር ቤቱ አባል ሲሆን አል-መሲሕ እንዲሰቀሉ በሚለው የምክር ቤቱ ውሳኔ ላይ ግን ያልተስማማ ሰው ነበር፡፡ ለብልሹው ገዥ ጉቦ በማቅረብ እንኳ ቢሆን በምክር ቤቱ ውስጥ ባይሳካለትም የዒሳን ሕይወት ለማዳን መምከር ይችል አልነበረም ወይ?
በአይሁድ ክስ ምክንያት ከዚያ ቀደም አስደንጋጭ የግሳፄ መልዕክት ከቄሣር የደረሰው ጲላጦስ[10] ከአርማቲያሱ ዮሴፍ ጉቦ ከመቀበል እና በአይሁድ ሕዝብ በቄሣር ፊት ተከሶ ከሥልጣኑ ከመባረር የትኛውን እንደሚመርጥ ግልፅ ነው፡፡ የአርማቲያሱ ዮሴፍ ያንን አላደረገም፡፡ ጲላጦስም ጉቦ የሚቀበልበት ሁኔታ ውስጥ አልነበረም፡፡ ጠያቂው ምኞታቸውን ከሚያስነብቡን ማስረጃ ቢሰጡን መልካም ነበር፡፡
- የተባለው የኢየሱስ ስቅለት ሲፈጸም የተመለከቱት ደቀ መዛሙርት ቁጥር ስንት ነው? ያሳዩት መስተጋብርስ ምን ነበር? ሐዋርያት በሙሉ ጥለውት ሸሹ የሚለው የማቴዎስ (26፡56) ቃል እውነት ሊሆን ይችላል ወይ? እነዚያ ታላላቅ ሐዋርያት ከታላቁ መምህር ጋር ያላቸው አንድነትና ባህሪ መለክያው ይህ ነው ወይ? ተወዳጁ ዮሐንስ ብቻ ነበር ይህ ሁኔታ ሲፈጸም በቦታው ተገኝቶ ነበር የሚባለው፡፡ ይሁንና ምን ያህል ግዜ ነበር በቦታው የቆየው?
በኢየሱስ ስቅለት ወቅት እናቱ ማርያም፣ አክስቱ፣ የሮማዊው ባለሥልጣን የቀለዮጳ ሚስት ማርያም፣ መግደላዊት ማርያም፣ ሰሎሜ፣ የዮሐንስና የያዕቆብ እናት እና ከገሊላ ጀምረው የተከተሉት ሌሎች ብዙ ሴቶች በቦታው ነበሩ (ዮሐንስ 19፡25-26፣ ማቴዎስ 27፡55-56፣ ማርቆስ 15፡40-41፣ ሉቃስ 23፡49)፡፡ ዮሐንስ እስከ መጨረሻው በቦታው ላይ በመሆን ሞቱን እንደተመለከተ ተጽፏል (ዮሐንስ 19፡35)፡፡ ሐዋርያት ሁሉ ጥለውት እንደሸሹ ማቴዎስ 26፡56 ላይ የተጻፈ ቢሆንም ወዲያው ግን ጴጥሮስ ተመልሶ መምጣቱን እና የፍርድ ሂደቱን መከታተሉን በቁጥር 58 ላይ እናነባለን፡-
“ጴጥሮስ ግን እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ድረስ ሩቅ ሆኖ ተከተለው፥ የነገሩንም ፍጻሜ ያይ ዘንድ ወደ ውስጥ ገብቶ ከሎሌዎቹ ጋር ተቀመጠ፡፡” ጴጥሮስ በሊቀ ካህናቱ ዘንድ ከታወቀ ከሌላ ደቀ መዝሙር ጋር ተመልሶ እንደመጣና ደቀ መዝሙሩ አስፈቅዶ አብረው ኢየሱስ ለፍርድ ወደቀረበበት የሊቀ ካህናቱ ግቢ እንደገቡ ዮሐንስ ይነግረናል (ዮሐንስ 18፡15-16)፡፡ ሐዋርያቱ እንዳይገደሉ በመፍራት ራሳቸውን ባይገልጡም ነገር ግን ሁኔታውን በቅርብ ርቀት ይከታተሉ እደነበር እንገነዘባለን፡፡
- የተፈረደበት ሰው በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እስኪሞት ድረስ ምን ያህል ጊዜ ወሰደ አስተማማኝ በሆኑ ታሪካዊ ምንጮች መሠረት (ቻምበርስ ኢንሳይክሎፒዲያ 1950 ስለመስቀሉ የተጻፈውን አንቀጽ ይመልከቱ) በመስቀል ላይ እንዲሞት የተፈረደበት ሰው ለመሞት ጥቂት ቀናት ይወስዳል፡፡ ታድያ ይህ ድርጊት ጥቂት ቀናትን መጠየቁ የተለመደ ሁኔታ ሆኖ ሳለ በኢየሱስ ሁኔታ ለምን ጥቂት ሰዓታትን ብቻ ወሰደ?
ሙሉ ከሆነ የሮማውያን ስቅለት በሕይወት የተረፈ አንድም ሰው ስለመኖሩ በታሪክ አልተመዘገበም፡፡ ጆሲፈስ ፍላቪየስ (ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን) የተሰኘ ሮማዊ አይሁድ ጸሐፌ ታሪክ በዘገበው ታሪክ ውስጥ በመስቀል ላይ የተሰቀሉ ሦስት ጓደኞቹን ባለ ሥልጣናትን በማግባባት እንዴት ከመስቀል ላይ እንዲወርዱ እንዳደረጋቸው የሰፈረ ታሪክ እናገኛለን፡፡ ሰዎቹ ለአጭር ጊዜ ተሰቅለው ከወረዱ በኋላ በወቅቱ የነበረው ከፍተኛ ኅክምና ቢደረግላቸውም ነገር ግን ከሦስቱ ሁለቱ ወዲያውኑ ሲሞቱ አንዱ ብቻ ነበር በሕይወት መትረፍ የቻለው፡፡[11] ኢየሱስ ግን ለሦስት ሰዓታት ያህል ነበር በመስቀል ላይ የቆየው፡፡ ከመሰቀሉ በፊት በአይሁድ ተገርፏል፤ ብዙዎችን ለሞት ይዳርግ በነበረው የሮማውያን ግርፋት ውስጥ አልፏል፤ የእሾህ አክሊል በመድፋት በመቃ ተቀጥቅጧል፤ መስቀሉን ተሸክሞ ከፕራይቶርዮን እስከ ጎልጎታ ድረስ እንዲሄድ ተደርጓል፡፡ በዚህ ሁሉ ስቃይ ውስጥ አልፎ የሰውነቱን ክብደት በሙሉ በሚስማር በተቸነከሩት እጆቹና እግሮቹ ላይ ተሸክሞ ለሦስት ሰዓታት ያህል ወደ ላይ እና ወደ ታች እያለ መተንፈስ ነበረበት፡፡ በመጨረሻም መሞቱን ያዩት ወታደሮች ጎኑን በጦር ወግተውታል፡፡ እንግዲህ አንድ ሰው ጀርባው እስኪከፈት ድረስ ተገርፎ፣ እጆችና እግሮቹ ተቸንክረው፣ በመስቀል ተሰቅሎ፣ ጎኑ በጦር ተወግቶ፣ ከመስቀል ላይ ወርዶ ደግሞ እንደ ሲሞንቶ በሚያጣብቅ 100 ፓውንድ ቅመም ቢታሸግ – በዚያ ውስጥ አልፎ በሕይወት መኖር መቻል ከትንሳኤ ጋር የሚተካከል ተዓምር የሚጠይቅ ነው!
ሁለቱ ደቀመዛሙርቶች እያሉ እርሱ ለምን ተሰቅሎ “ሞተ”? ምድርን በሙሉ ለሦስት ሰዓት የሸፈነው ጨለማ ጉዳይስ? (ማቴዎስ 27፡45፣ ማርቆስ 15፡33 ሉቃስ፣ 23፡44)፡፡
ጠያቂው “ሁለቱ ደቀ መዛሙርቶች” ሲሉ ምን ለማለት እንደፈለጉ ግልፅ አይደለም፡፡ ምድርን ለሦስት ሰዓታት የሸፈነው ጨለማ ከአዲስ ኪዳን ውጪ በሚገኙት የታሪክ መዛግብት የተረጋገጠ ነው፡፡ ይህን ጉዳይ የሚጠቅስ አስደናቂ የታሪክ መረጃ በ55 ዓ.ም አካባቢ እንደተጻፈ ምሑራን ይናገራሉ፡፡ ታሉስ የተባለ ሮማዊ ጸሐፌ ታሪክ በክርስቶስ ስቅለት ወቅት በምድር ላይ ስለወደቀው ጨለማ ጽፎ የነበረ ሲሆን ነገር ግን በእርሱ የተጻፈው ቀዳሚ ሰነድ በመጥፋቱ የተነሳ ያለን መረጃ ጁሊየስ አፍሪካኑስ የተባለ ክርስቲያን የታሪክ ጸሐፊ (160-240 ዓ.ም) የእርሱን ጽሑፍ በመጥቀስ የጻፈው ነው፡፡ አፍሪካኑስ እንዲህ በማለት ጽፏል፡- “በሦስተኛው የትረካ (መጽሐፉ) ታሉስ ይህንን ጨለማ የፀሐይ ግርዶሽ በማለት ይጠራዋል፤ ይህ ለኔ ስህተት መስሎ ይታየኛል፡፡”
ጁሊየስ አፍሪካኑስ የታሉስን ጽሑፍ የጠቀሰው ክርስቶስ የተሰቀለው ሙሉ ጨረቃ በምትታይበት በፋሲካ ዋዜማ በመሆኑና በሙሉ ጨረቃ ጊዜ ደግሞ የፀሐይ ግርዶሽ የማይከሰት በመሆኑ በክርስቶስ ስቅለት ወቅት በምድር ላይ የወደቀው ጨለማ የፀሐይ ግርዶሽ እንደነበረ ታሉስ በመጽሐፉ ውስጥ ማስፈሩ ትክክል እንዳልሆነ በሚገልጽበት ክፍል ነው፡፡[12]
ተሰቃዩን በሌላ ተሰቃይ የመለወጡ ወይም የመተካቱ አፈጻጸም በጨለማውና በትርምሱ ጊዜ በሐምራዊ መጎናጸፊያ ሽፋን ስር ተፈጽሞ ይሆናል ወይ?
አሕመዲን ሆይ፤ በግምት እና በመሰለኝ መናገር አይበቃዎትም ወይ? የመጎናፀፍያውን ቀለም እንኳ እስከመገመት ያደረስዎትን እስከ ዛሬ ድረስ ዓለም ያላወቀውን እርሶና ጥያቄዎቹን በማስኮረጅ ያገዙዎት ዶ/ር ሐሙዳ አብዱል ዓጢ ብቻ የሚያውቁትን ሚስጥራዊ መረጃ ሊነግሩን ይችላሉ ወይ? ተሰቃዩ በሌላ ተሰቃይ ተተክቷል የሚል ደካማ ግምት ሲያስቀምጡ ኢየሱስ እንዳልተሰቀለ ከሚናገረው የቁርኣን ጥቅስ ጋር እየተጋጩ እንደሆነ አስተውለዋል ወይ? ማስረጃ አልባ ግምትና ጥርጣሬስ አሳማኝ ሙግት ይሆናል ወይ?
- ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሳለ መጸለዩን በተመለከተ ቀደም ሲል የጠየቁትን ጥያቄ በሌላ አባባል ስለደገሙት ታልፏል፡፡
- ከጥያቄ 23 እና 38 ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ታልፏል፡፡
በማስከተል ጸሐፊው የኢየሱስ ስቅለት ከእስልምና አስተምህሮ አኳያ ተቀባይነት ለምን እንደሌለው መጠነኛ ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡ ለኢየሱስ አለመሰቀል ማስረጃ ይሆናሉ ያሏቸውንም ነጥቦች ጠቃቅሰዋል፡፡ በማስከተል ለተነሱት ነጥቦች ሁሉ መልስ እንሰጣለን፤ ኢየሱስ እንዳልተሰቀለ የሚናገረው የቁርኣን ጥቅስ ለምን ተቀባይነት ሊኖረው እንደማይችል በማስረጃ በማስደገፍ እንገልጣለን፡፡
የክርስቶስን ስቅለት በተመለከተ እስላማዊው አስተሳሰብ ከመጽሐፍ ቅዱስ፣ ከቁርኣንም ሆነ ከታሪክ አኳያ ፍጹም ስህተት መሆኑን በማረጋገጥ የአሕመዲንን ቅጥፈቶች የሚያጋልጥ ጽሑፍ እዚህች ጋር ጠቅ በማድረስ ያንብቡ፡፡
ማጣቀሻዎች
[1] መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ሆሴዕ 6፡6 የግርጌ ማጥኛ ገፅ 1324 ይመልከቱ፡፡
[2] Nabil Qureshi: Seeking Allah, Finding Jesus; Zondervan, Grand Rapids, Michigan 2014, pp. 150-151
[3] https://www.wikiislam.net/wiki/seven_sleepers_of_ephesus_in_the_quran
[4] Sahih Muslim, Book 037, Number 6666; number 6665;
[5] Nabil Qureshi: Seeking Allah, p. 150
[6] “Clearly, the weight of historical and medical evidence indicates that Jesus was dead before the wound to his side was inflicted and supports the traditional view that the spear thrust between his right rib, probably perforated not only the right lung but also the pericardium and heart and thereby ensured his death. Accordingly, interpretations basedon the assumption that Jesus did not die on the cross appear to be at odds with modernmedical knowledge.” Journal of the American Medical Association (21 March 1986) [1463]
[7] ‘Martyr’ (ሰማዕት) የሚለው የእንግሊዘኛ ቃል ከዚህ ቃል የተገኘ ነው፡፡
[8] Sahih Muslim, Book 037, Number 6666; number 6665;
[9] Sahih Muslim, Book 037, Number 6668
[10] Philo, on the Embassy of Gauis, Book 40. Available on this website:-
http://www.earlyjewishwritings.com/text/philo/book40.html
[11] The Life of Flavius Josephus; Available on the following website:-
http://www.ccel.net/j/josephus/works/autobiog.htm
[12] Robert E. Van Voorst: Jesus Outside the New Testament, An Introduction to the Ancient Evidence Wm. Β. Eerdmans Publishing, Grand Rapids, Michigan, 2000, p. 20 pdf