ክርስትና፣ እስልምናና ባሕል
በታሪክ አጋጣሚዎች ክርስቲያኖች ክርስትናን የባሕላቸው ማስፋፍያ መሣርያ ለማድረግ የሞከሩባቸው ሁኔታዎች ቢኖሩም የክርስትና ስሪቱ የሕዝቦችን ቋንቋ፣ ባሕልና መለያዎች የሚያጠፋ አይደለም። በበዓለ ሃምሳ ዕለት ቤተክርስቲያን ስትመሠረት መንፈስ ቅዱስ ሐዋርያት የተለያዩ የዓለም ቋንቋዎችን እንዲናገሩ ነበር ያደረጋቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ በአንፆክያ ከተማ አይሁድን ፈርቶ ከአሕዛብ ራሱን ለመለየት የሞከረውን ሐዋርያው ጴጥሮስን እንዲህ ብሎት ነበር፦ “…አንተ አይሁዳዊ ሳለህ በአይሁድ ኑሮ ያይደለ በአሕዛብ ኑሮ ብትኖር፥ አሕዛብ በአይሁድ ኑሮ ሊኖሩ እንዴት ግድ አልሃቸው?…” (ገላትያ 2፥14)።
ጳውሎስና በርናባስ በገላትያ ወንጌልን ከሰበኩ በኋላ ክርስትናን የተቀበሉትን አሕዛብ ወደ ይሁዲ ሥርዓት ለመለወጥ ከኢየሩሳሌም የተንቀሳቀሱ አይሁድ ክርስቲያኖች (Judaizers) ነበሩ። በዚህም ሰበብ የተጠራው የኢየሩሳሌም ጉባኤ ማንም አሕዛብ የአይሁድን ልማዶች የመቀበል ግዴታ እንደሌለበት ደንግጓል። ከዚህ የተነሳ የመጀመርያይቱ ቤተክርስቲያን የአይሁድን ባሕልና ቋንቋ ለማስፋፋት መሣርያ አልሆነችም። በሌላ ቦታ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ብቻ ለእያንዳንዱ እግዚአብሔር እንደ ከፈለለት እያንዳንዱም እግዚአብሔር እንደ ጠራው እንዲሁ ይመላለስ። እንዲሁም በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እደነግጋለሁ። ማንም ተገርዞ ሳለ ተጠርቶ እንደ ሆነ፥ ወደ አለመገረዝ አይመለስ፤ ማንም ሳይገረዝ ተጠርቶ እንደ ሆነ አይገረዝ።” (1ቆሮ. 7:18-19)።
ክርስትና የትኛውንም ባሕል ሆነ ቋንቋ ለማስፋፋት መገልገያ እንዲሆን የእግዚአብሔር ፈቃድ አይደለም። ወንጌል በቋንቋዎችና ባሕሎች ይሰበካል እንጂ ቋንቋዎችና ባሕሎች በወንጌል አይሰበኩም። ክርስቲያኖች ከዚህ የተለየ አካሄድ የተከተሉ እንደሆን ችግሩ የእነርሱ እንጂ የወንጌል አይደለም።
እስልምናስ? እስልምና ሲጀመር ስሪቱ ራሱ አንድን ቋንቋና ባሕል ለማስፋፋት የታለመ ነው። አንድ ሰው ሲሰልም ስሙን ከገዛ ቋንቋው ወደ አረብኛ ይለውጣል። የሃይማኖት ስርዓታቱን ለመከወን የግድ አረብኛ ይማራል። መሠረታዊው የጸሎት ይዘት ትክክል የሚሆነው በአረብኛ ሲሆን ብቻ ነው። የአለባበስ ስርዓት አረባዊ መሆን አለበት። የሰለሙ ሰዎች የፊት ገፅታና አካላዊ እንቅስቃሴ (gusture) ሳይቀር አረብ ወደ መምሰል ይለወጣል። በእስልምና “የነቢዩ ሱና” በሚል ሰበብ የሁሉም ሙስሊም ሁኔታ አረባዊ እንዲሆን ይደረጋል። ከዚያ ሁኔታ ወጣ ያለ ማሕበረሰብም ሆነ ግለሰብ ሃይማኖቱ ፍጹም እንደሆነ አይቆጠርም። ባጠቃላይ እስልምና ፈረንጆቹ “cultural straightjacket” የሚሉት ዓይነት ንፅረተ ዓለም ነው።
እውነተኛው አምላክ ግን ፍጥረትን በብዝሃነት አስውቦ የፈጠረ በመሆኑ ሁሉም ቋንቋዎችና ሁሉም መልካም ባሕሎች ያስደስቱታል። ክርስትና የሰዎችን ቋንቋዎችና ባሕሎች የመለወጥ ጉዳይ ሳይሆን የሰዎችን ልብ የመለወጥ ጉዳይ ነው።