የማርያም እጮኛ የነበረው ዮሴፍ አባቱ ማን ነበር? ያዕቆብ ወይስ ኤሊ?

 


ጥያቄው

«ያዕቆብም ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን የወለደች የማርያምን እጮኛ ዮሴፍን ወለደ።» (ማቴ 1፡16)

በዚህ አንቀጽ እንደተገለጸው የማርያም እጮኛ የነበረው ዮሴፍ የአባቱ ስም ያዕቆብ ነው። ነገር ግን በሌላ ቦታ እንዲህ ይላል፡- «ኢየሱስም ሊያስተምር ሲጀምር ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ያህል ሆኖት ነበር እንደመሰላቸው የዮሴፍ ልጅ ሆኖ፥ የኤሊ ልጅ።» (ሉቃ 3፡23) በዚህ አንቀጽ ደግሞ እንደተገለጸው የዮሴፍ አባት ኤሊ እንደሆነ ነው።

መልስ

ከጥያቄ 44-47 ያለው አንድ አይነትና ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ስለሆኑ በዚህኛው ጥቅልለን መልስ ብንሰጥበት ጥሩ መስሎ ታይቶናል። በማቴዎሱ ላይ የዮሴፍ አባት ያዕቆብ ነው፥ በሉቃሱ ደግሞ ኤሊ ነው። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ይጋጫልን? ነገሩ ጥንቃቄን እና ጥናትን የሚጠይቅ ቢሆንም በእግዚአብሔር እርዳታ ይመለሳል። አንድ በአንድ እንመልከተው፦ በመጀመሪያ ደረጃ የማቴዎሱና የሉቃሱ የዘር ሀረጋት ሊለያዩ የቻሉት ሁለት የተለያዩ የዘር ሀረጋት በመሆናቸው ነው። የትኛው የማን መሆኑን ከማየታችን በፊት በእርግጥም ሁለት የተለያዩ ሀረጋት መሆናቸውን በመረጃ እንመልከት።

እሴይም ንጉሥ ዳዊትን ወለደ። ሰሎሞንም ሮብዓምን ወለደ፤ ሮብዓምም አቢያን ወለደ፤ አቢያም አሣፍን ወለደ፤ __ ማቴ 1፡6-7

በማቴዎሱ የዘር ሀረግ ከዳዊት በኋላ የተጠቀሰው ሰለሞን መሆኑን እንመለከታለን። የሉቃሱን እንመልከት

የዮናን ልጅ፥ የኤልያቄም ልጅ፥ የሜልያ ልጅ፥ የማይናን ልጅ፥ የማጣት ልጅ፥ የናታን ልጅ የዳዊት ልጅ፥ የእሴይ ልጅ፥ የኢዮቤድ ልጅ፥ የቦዔዝ ልጅ፥ የሰልሞን ልጅ፥ __ ሉቃ 3፡31-32

በሉቃሱ ላይ ግን ከዳዊት በኋላ የተጠቀሰው ናታን ነው። ሁለት የተለያዩ የዘር ሀረጋት ስለሆኑ እንዲህ ሊሆን ችሏል። ሰለሞንና ናታን ማናቸው? በ1ሳሙ12 በምናነበው ታሪክ መሠረት ዳዊት ከቤርሳቤህ የወለዳቸው ልጆች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ወንድማማቾች ናቸው ወንድማማቾች በመሆናቸው፥ አንዱ የአንዱ አባት ወይንም አያት ነው ማለት አንችልም። በዘር ሀረግ አያት ወይ የቀደመ ትውልድ እንደ አባት ሊጻፍ ይችላልና በዚህ ላይ ግን ጥያቄ ይነሳል “የተለያዩ የዘር ሀረጋት ከሆኑ

1. የትኛው የማን ነው?

2. ሁለቱም በዮሴፍ ስም ለምን አለቁ? ተራ በተራ እንመልሳቸዋለን፦

1. የዘር ሀረጎቹ የተለያዩ ከሆኑ የማን የማን ናቸው፦ የማቴዎሱ የዘር ሀረግ የዮሴፍ የዘር ሀረግ ሲሆን፥ የሉቃሱ ደግሞ የድንግል ማርያም ነው። ይህንንም በሚቀጥለው መልስ በስፋት እንመለከታለን

2. የሉቃሱ የዘር ሀረግ የማርያም ከሆነ፥ ለምን በዮሴፍ ስም ተጠናቀቀ፦ ይህ ሊሆን የቻለው፥ በዕብራውያኑ ወግ ምክንያት ነው። በአይሁድ ልማድ በአንድ ቤት ወንድ ልጅ ከሌለ፥ የሴቶቹ ባለቤት ወይንም እጮኛ በሴቶቹ አባት ስም ይጠራል። ለዚህም ማስረጃ እናቀርባለን። ከዚያ በፊት ግን በሉቃስ የዘር ሀረግ ጉዳዩ ይህ መሆኑን እናስረግጥ

” ኢየሱስም ሊያስተምር ሲጀምር ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ያህል ሆኖት ነበር እንደመሰላቸው የዮሴፍ ልጅ ሆኖ፥ የኤሊ ልጅ፥” (የሉቃስ ወንጌል 3:23)

በዚህ ስፍራ “እንደመሰላቸው” የሚለው ቃል የትርጉም ድክመት አለበት። የግሪኩ ቃል ἐνομίζετο “ኤኖሚዜቶ” የሚል ሲሆን ትርጉሙም “as reckoned by law or as the custom” የሚል ነው። ወይም በአማርኛ “እንደ ወጉ ወይንም እንደ ስርዓቱ” ማለት ነው።[25] የኢንግሊዝኛውም ትርጓሜ ይህንን ያመላክታል። “As was supposed” ይህ ማለት “as it was intended” ወይንም መሆን እንደነበረበት የሚል ትርጉም ይሰጣል። ታዲያ ወጉ ምንድነው፥ ብሉይ ኪዳናዊ ማስረጃስ አለው ወይ? ቅድም እንዳልነው፥ በአንድ ቤት ውስጥ ወንድ ልጅ ከጠፋ የሴቶቹ ባለቤት ወይንም እጮኛ በአባታቸው ስም ይጠራል ለዚህ ማሳያ ከብሉይ ኪዳን መረጃን እንመልከት፦

“ከካህናቱም ልጆች፤ የኤብያ ልጆች፥ የአቆስ ልጆች፥ ከገለዓዳዊው ከቤርዜሊ ልጆች ሚስት ያገባ፥ በስሙም የተጠራ የቤርዜሊ ልጆች።” (መጽሐፈ ዕዝራ 2:61)

በዚህ ስፍራ እንደምናስተውለው፥ ይህ ሰው ከቤርዜሊ ሴት ልጆች መካከል አግብቷል። ነገር ግን ቤርዜሊ ወንድ ልጅ ስላልነበረው ይህ ሰው በእርሱ ስም ተጠርቷል። በቤርዜሊ ስም የተጠራው በወጉ አማካኘኝነት እንጂ የሆዱ ፍሬ ስለነበር አይደለም ይህንኑ የዘር ሀረግ በነህሚያ 7:63 እናገኘዋለን። በተጨማሪም ተመሳሳይ የዘር ሀረጋት በ1 ዜና 2:34-35 እናገኛለን። በሉቃስ 3:23 ያለው ጉዳይ ከዚህ ጋር አንድ መሆኑን የምናረጋግጥበት ሌላው ማረጋገጫ፥ በሉቃስ የዘር ሀረግ ዘገባ ውስጥ ከዮሴፍ ስም በስተቀር ሌሎች ስሞች definate article ያላቸው መሆኑ ነው። ዮሴፍ እንደ ወጉ የኤሊ ልጅ ተብሎ የተጠራው የማርያም አባት ኤሊ ወንድ ልጆች ስለሌሉት ነበር። ዮሐ 19:25።

አስተውሉ! በማቴዎሱ የዘር ሀረግ ያዕቆብ ዮሴፍን ወለደ ይላል (ማቴ 1:16)። በዚህ ግን እንደ ወጉ ይላል። ይህ የሁለቱን የዘር ሀረጋት የተለያዩ መሆንን ከማሳየት አልፎ፥ የዕብራውያኑን ወግ ያመለክተናል። ያዕቆብ የዮሴፍ እውነተኛ አባቱ ቢሆንም፥ የማርያም እጮኛ ስለነበር የእርሷ ዘር ሀረግ ሲቆጠር በስተመጨረሻው የእርሱ ስም ተጠራ። እንደ ወጉ መደምደሚያ በሁለቱ የዘር ሀረጋት እንዴት ጌታ እንደተሰበከና፥ በአይሁድ ወግ መሠረት የዮሴፍ ልጅ ተብሎ እንደተጠራ አይተናል ምክንያቱም ድንግል ማርያም ከናታን ዘር የተወለደች ስትሆን፥ ዮሴፍ ግን ከሰለሞን ዘር የተወለደ ነው። (ዘኁ 36)

በተጨማሪም እንደማጠቃለያ የክርስቲያን ምሁራኑን ምላሽ ስናስቀምጠው፦

በመጀመሪያ ደረጃ መረዳት ያለብን ነገር የዘር ሐረጉ በማቴዎስ ወንጌል “እሰይ ንጉስ ዳዊትን ወለደ” ይልና የዘረ ሐረጉን በንጉስ ዳዊት ልጅ በንጉሱ ሰለሞን በኩል “ወለደ ወለደ” እያለ ያስኬደዋል። በሉቃስ ግን ከዳዊት በኋላ በንጉስ ሰለሞን ወንድም በናታን በኩል “ልጅ ልጅ ልጅ” እያለ ያስኬደዋል። ይህ ማለት ሁለቱ ጸሐፊዎች ስለ ሁለት የተለያዩ የዘር ሐረጋት እያወሩ ነው ማለት ነው። ይህም የማቴዎስ ወንጌል ስለ ዮሴፍ የዘረ ሐረግ ሲዘረዝር የሉቃስ ወንጌል ደግሞ ስለ ድንግል ማርያም የዘር ሐረግ ይዘረዝራል። በመጀመሪያ “ዮሴፍ የኤሊ ልጅ” በሚለው አነጋገር ውስጥ ልጅ በብዙ ይተረጎማል። ልጅ የአብራክ ክፋይ፣ የማደጎ፣ የጋብቻ ልጅ (son in law) ተብሎ ይከፋፈላል። የሉቃስ ዘገባ የማርያምን ዘር ጠቅሶ ዮሴፍ የተጠራበት ምክንያት በአይሁዳዊያ አውድ አንድ ወንድ አንዲትን ሴት ካጨና ወይም ካገባ የልጅቱ አባት ወንድ ልጆች ባይኖሩት እጮኛዋ ወይም ባሏ የአባቷ ህጋዊ ወራሽ እና ሕጋዊ ልጅ ይሆናል። ይህንንም በዘኁ 36፡1-12 መመልከት ትችላለህ። በታሪክ ደግሞ ማርያም ወንድሞች እንዳልነበሯት ስለሚታመን እጫኛዋ እየነበረው ዮሴፍ የአባቷ ሕጋዊ ልጅ ተደርጎ ይወሰዳል። በዚህም የኤሊ ልጅ ተብሎ ይጠራል።

ሁለተኛ ደግሞ ሁለቱም የዘር ሀረጎች የዮሴፍ እንደሆኑም ይታመናል። ይህም የሆነበት መንገድ የዮሴፍ አባቶች ተብለው የተጠሩት ያዕቆብና ኤሊ በእናት የሚገናኙ ወንድማማች ነበሩ። ኤሊ ልጅ ሳይወልድ ሞተ። በዘዳ 25፡5-6 መሰረት አንድ ወንድ አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ቢሞት ርስቱና ስሙ እንዳይጠፋ ሚስቱን ወንድሙ ይወርሳትና ልጅ ወልዶ ልጁ በሟቹ ስም ይጠራል። በዚህ ህግ መሰረት ኤሊ ልጅ ሳይወልድ ስለሞተ በእናት ወንድሙ የሆነው ያዕቆብ ሚስቱን አግብቶ ዮሴፍን ወለደ። ይህ ማለት የልጁ ወላጅ አባት ያዕቆብ ሲሆን ህጋዊ አባቱ ደግሞ ኤሊ ነው ማለት ነው። ለዚህም ነው ማቴዎስ ያዕቆብ ዮሴፍን “ወለደ” ሲል ሉቃስ ግን ዮሴፍ የኤሊ “ልጅ” ያለው።[26]