ሄሮድስ ኢየሱስ በልጅነቱ ሳለ ነው የሞተው ወይስ ከዚያ በኋላ?
ጥያቄው፦
«ሄሮድስም ከሞተ በኋላ እነሆ የጌታ መልአክ በግብፅ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት ሞተዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑን እናቱንም ይዘህ ወደ እስራኤል አገር ሂድ አለ። እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ያዘና ወደ እስራኤል አገር ገባ። በአባቱም በሄሮድስ ፈንታ አርኬላዎስ በይሁዳ እንደ ነገሠ በሰማ ጊዜ ወደዚያ መሄድን ፈራ፤ በሕልምም ተረድቶ ወደ ገሊላ አገር ሄደ።» (ማቴ 2፡19-22) በዚህ አገላለጽ መሰረት ኢየሱስ ከግብጽ ወደ እየሩሳሌም የሄደው ሄሮድስ ከሞተ በኋላ ነው። ይህም ሄሮድስ የሞተው እንደማቴዎስ አገላለጽ ኢየሱስ ገና ልጅ በነበረበት ጊዜ ነው። ነገር ግን ሉቃስ ሌላ ተቃራኒ ታሪክ ይነግረናል፡- «የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ በሆነ ጊዜ እንደ በዓሉ ሥርዓት ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ።» (ሉቃ 2:42) እንደ ሉቃስ አገላለጽ መሰረት ደግሞ ኢየሱስ ወደ ግብጽ ሄደ የሚለው ታሪክ በሱ ዘንድ ተቀባይየት የለውም። ማርቆስ ይባስ ብሎም ኢየሱስ ከተጠመቀና ደቀመዛሙርት አፍርቶ ሳይቀር በልጅነቱ ሞቷል ተብሎ የነበረው ሄሮድስ በህይወት እንደ ነበር ይገልጻል። ለዛውም መጥመቁ ዮሐንስ ከተገደለ በኋላ ማለት ነው። «ሄሮድስ ግን ሰምቶ እኔ ራሱን ያስቈረጥሁት ዮሐንስ ይህ ነው እርሱ ከሙታን ተነሥቶአል አለ።» (ማር 6:16) በተመሳሳይ ማቴዎስ ላይም ይህንን እናገኛለን፡-«በዚያ ዘመን የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስ የኢየሱስን ዝና ሰማ፥ ለሎሌዎቹም ይህ መጥምቁ ዮሐንስ ነው፤ እርሱ ከሙታን ተነሥቶአል፥ ስለዚህም ኃይል በእርሱ ይደረጋል አለ።» (ማቴ 14፡1-2)
መልስ፦
እንደ ጠያቂያችኝ መሠረት በመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሄሮድስ ያለ መስሎታል። በመጽሐፍ ቅዱስ ሄሮድስ የሚለውን ቃል አፈታት እና ታሪካዊ ዳራ እንመልከት፦
ሄሮድስ የሚለው ከኤዶም ዘር የተገኙ ቤተሰቦች ስም ነው። እነዚህ ቤተሰቦች የአይሁድን ሃይማኖት ተቀብለው ከ47 ዓዓ እስከ 79ዓም በአይሁድ አገር ነገሥታትና ገዥዎች ሲሆኑ የማስተዳደር ችሎታ ነበራቸው። ነገር ግን ከሌላ ዘር በመሆናቸው ብዙ ብልግናም በመሥራታቸው ሥልጣናቸውንም ከሮም መንግስት ስለተቀበሉ በአይሁድ ዘንድ ተወዳጅነት አልነበራቸውም። ሆኖም በአይሁድ መካከል የሚገኝ ‘የሄሮድስ ወገን’ የሚባል ክፍል ግዛታቸውን ደገፈ፤ ማር 3፥6፣ 12፥13- 17።
መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ ቤተሰብ መካከል የሚከተሉትን ዘጠኝ ሰዎች ስም ይጠቅሳል፦
- ታላቁ ሄሮድስ: የአይሁድ ንጉስ ሆኖ በ37 ዓዓ ነገሠ። በእስራኤል አገር ያለውን የቂሣሪያ ከተማ ቆረቆረ፤ የአይሁድንጉስ ሆኖ በ ዓዓ ነገሠ። በእስራኤል አገር ያለውን የቂሣሪያ ከተማ ቆረቆረ፤ ቤተ መቅደሱን ማሳደስና ማስጌጥ ጀመረ፤ ሕፃናትንም አስገደለ፤ ማቴ 2፥1-8። ዐሥር ሚስቶችን አገባ፤ ከቤተሰቡና ከዚያም ውጭ ብዙ ሰዎችን ፈጀ። ከሞተ በኋላ መንግስቱ ለልጆቹ በሦስት ተከፈለ። ታላቁ ሄሮድስ የሞተበትን ዓመት መወሰን አስቸጋሪ ነው።
- አርኬላዎስ፤ የታላቁ ሄሮድስ ልጅ እስከ 6 ዓ.ም. ይሁዳን ገዛ፤ ማቴ 2፥22።
- ሄሮድስ ፊልጶስ፤ የታላቁ ሄሮድስ ልጅ፤ ማቴ 14፥3።
- ሄሮድስ አንቲጳስ፤ የታላቁ ሄሮድስ ልጅ እስከ 39 ዓ.ም. ገሊላን ገዛ። የወንድሙን የሄሮድስ ፊልጶስን ሚስት አገባ። መጥምቁ ዮሐንስ ስለዚህ ቢገሥጸው አሰረው፤ በሰይፍ አስቆርጦም አስገደለው፤ ማቴ 14፥1-12። ኢየሱስ ቀበሮ ብሎ በመጥራቱ ጠባዩን ገለጠ፤ ሉቃ 13፥32። ጲላጦስ ኢየሱስን ሲልክለት ሄሮድስ በመናቅ ዘበተበት፤ ሉቃ 23፥6-12።
- ሄሮድያዳ፤ የአርስቶቡሎስ ልጅ የታላቁ ሄሮድስ የልጅ ልጅ በመጀመሪያ አጎትዋን ሄሮድስ ፊልጶስን ቀጥሎም ሄሮድስ አንቲጳስን አገባች። መጥምቁ ዮሐንስን አስገደለች፤ ማቴ 14፥3-12።
- ፊልጶስ፤ የታላቁ ሄሮድስ ልጅ እስከ 34 ዓ.ም. ኢጡርያስንና ጥራኮኒዶስን ገዛ፤ ሉቃ 3፥1።
- ንጉስ ሄሮድስ ቀዳማዊ አግሪጳ የአርስቶቡሎስ ልጅ የታላቁ ሄሮድስ የልጅ ልጅ ከ41-44 ዓ.ም. ይሁዳን ገዛ። ሐዋሪያው ያዕቆብን ገደለ፤ ጴጥሮስንም አሰረ። የጌታ መልአክ ግን ጴጥሮስን አዳነ፤ ንጉሡም በመልአኩ ተቀስፎ ሞተ፤ ሐ.ሥ. 12።
- ንጉስ ሄሮድስ ዳግማዊ አግሪጳ፤ የሄሮድስ ቀዳማዊ አግሪጳ ልጅ ከ50 ዓ.ም. ጀምሮ ገሊላን ገዛ። ጳውሎስ በፊቱ ተከሶ ቀርቧል፤ ሐ.ሥ. 25፥13 – 26፥32።
- በርኒቄ፤ የንጉስ ሄሮድስ ቀዳማዊ አግሪጳ ልጅ። አጎትዋን ካገባች በኋላ ከወንድምዋ ከሄሮድስ ዳግማዊ አግሪጳ ጋር ዝሙት እየፈጸመች ኖረች፣ ጳውሎስም ሲከሰስ ከወንድምዋ ጋር ተሰየመች፤ ሐ.ሥ. 25፥23፤ 26፥30።
በመጨረሻም፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ተመሳሳይ ስም ያላቸው ሰዎች መኖራቸውን ሀገር ያወቀው ፀሀይ የሞቀው ጉዳይ ነው። ታዲያ ይሄን ካወቅን ይሄኛው ስም ይሄንን ሰው ለመግለጽ ነው ይሄኛው የዚህ ሀገር ተወላጁን ነው የሚገልፀው በማለት የተለያዩ መሆናቸውን በዚህ መልኩ መልሳችንን ማስረዳት እንችላለን። በጥቅሶቹም ላይ ግጭት የለም።
