“አምላክ ነኝና አምልኩኝ” ብሎ መናገር የአምላክነት ማረጋገጫ ነውን?

“አምላክ ነኝና አምልኩኝ” ብሎ መናገር የአምላክነት ማረጋገጫ ነውን?


ኢየሱስ “አምላክ ነኝና አምልኩኝ” ብሎ ከመናገሩ ይልቅ “አምላክ አይደለሁምና አታምልኩኝ” ብሎ አለመናገሩ አምላክነቱን ያረጋግጣል። እንዴት አትሉኝም?

አንድ አካል አምላክ የሚሆነው የአምላክ ባሕርያት ካሉት ብቻ እንጂ አምላክ ነኝ ስላለ አምላክ አይሆንም፡፡ ከግብፅ ፈርዖኖችና ከሮማውያን ነገሥታት ጀምሮ እስከ ዘመናችን ሐሰተኛ ክርስቶሶች ድረስ “አምላክ ነን” ያሉ ብዙ ሰዎች ሊጠቀሱ ይችላሉ ነገር ግን እንደርሱ ማለታቸው አምላክ አላደረጋቸውም፡፡ አምላክ መሆናቸውን በማወጅ ያጭበረበሩ ሰዎች በሰው ልጆች ታሪክ በተደጋጋሚ ከመታየታቸው አንፃር እንዲህ ያለው ንግግር ለአምላክነት መስፈርት ሊውል አይገባውም፡፡ ትክክለኛው መስፈርት አንድ አካል አምላካዊ ባሕርያትን አንጸባርቋል ወይ? የሚል እንጂ አምላክ ነኝ ብሏል ወይ? የሚል አይደለም፡፡

በአንፃሩ ኢየሱስ አምላክ አለመሆኑን አለመናገሩ የአምላክነቱ ማረጋገጫ በመሆኑ አምላክ “አይደለሁምና አታምልኩኝ” ያለበትን ቦታ እንዲያሳዩን ሙስሊም ወገኖቻችንን ብንጠይቃቸው ተገቢ ይሆናል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰዎች ለሰዎች ለአምላክ ብቻ የሚገባውን ክብር ሲሰጡ ሰው እንጂ አምላክ አለመሆናቸውን ሲገልፁ እንመለከታለን (ሐዋ. 14፡11-18)፡፡ ኢየሱስ ግን ሰዎች ሥራውን ተመልክተው “የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብለው ሲሰግዱለት፣ ሲያመሰግኑትና “አምላኬ” ብለው ሲጠሩት ተቃውሞ ከማሰማት ይልቅ ተግባራቸውንና ንግግራቸውን ሲያጸድቅ እንመለከታለን፡፡ ስለዚህ አምላክ አለመሆኑን አለመናገሩ የአምላክነቱ ማረጋገጫ ነው፡፡


መሲሁ ኢየሱስ