ዷዒፍ ቁርኣኖች መኖራቸውን ያውቃሉ?

ዷዒፍ ቁርኣኖች መኖራቸውን ያውቃሉ?


ብዙ ሙስሊሞች ቁርኣን አንድ ዓይነት ብቻ መሆኑን ነው የሚያውቁት፡፡ ሻል ያለ ዕውቀት ያላቸው ቂርኣት በሚል አከፋፈል ሰባት ዓይነት ቁርኣኖች መኖራቸውን ያውቃሉ ነገር ግን ልዩነቶቹ የአጻጻፍ እንጂ የትርጉም እንዳልሆነ ያምናሉ፡፡ ጥሩ ዕውቀት ያላቸው ደግሞ ልዩነቱቹ የአጻጻፍ ብቻ ሳይሆን የትርጉምም መሆኑን ይገነዘባሉ፤ በቂርኣት አከፋፈልም ቁርኣን በሰባት ያልተወሰነና አሥር ዓይነት መሆኑን፤ አሥሩ ደግሞ እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ቁርኣኖችን በውስጣቸው መያዛቸውን፤ ሁለት ሁለት የተባሉትም አንዳንዶች የተለያዩ ዓይነት ቁርኣኖችን በውስጣቸው መያዛቸውን ያውቃሉ፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ በሙስሊም ሊቃውንት ዘንድ “ያልተለመዱ” ተብለው የተገለሉ ብዙም የማይወራላቸው ቁርኣኖች መኖራቸውን የሚያውቁት ጥቂቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ቁርኣኖች በቁጥር አራት ሲሆኑ መጠርያቸውም፡- ኢብን ሙሐይሲን፣ አል-ያዚዲ፣ አል-ሐሰን እና አል-ዓመሽ ይሰኛሉ፡፡ ኢማም አንነወዊ እና ሌሎች ሙስሊም ሊቃውንት “ያልተለመዱ” በተባሉት በነዚህ ንባቦች መሠረት ቁርአንን ማነብነብ የተወገዘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ስለ እነዚህ ቁርኣኖች የተወሰኑ መረጃዎችን ቀጥሎ በተቀመጠው ታዋቂ የፋትዋ ድረ-ገፅ ላይ ማግኘት ይቻላል፡https://islamqa.info/…/the-seven-modes-of-recitation…
ስለ እነዚህ አራት ዓይነት ቁርኣኖች ያለን መረጃ የዘገባ ሰንሰለታቸው (ኢስናድ) በብዙ አስተላላፊዎች የተረጋገጠ (ሙተወቲር) ሳይሆን ባለ አንድ የዘገባ ሰንሰለት (አሓድ) ነው በሚል በሙስሊም ሊቃውንት መወገዛቸውን ነው፡፡ አሥሩ ቂርኣት እርስ በርሳቸው አንደማይስማሙት ሁሉ እነዚህም ቁርኣኖች ከአሥሩ ጋር የሚስማሙ አይደሉም፡፡ ስለዚህ ለሙስሊም ወገኖቻችን ያለን ጥያቄ፡- እነዚህ ቁርኣኖች የተበረዙ ወይም ሰው ሠራሽ ከሆኑ በቁርኣን ጥበቃ ላይ ጥያቄ ለማንሳት አንገደድም ወይ? ምናልባት ከእነዚህ ቁርኣኖች መካከል አንዱ ትክክለኛ ሊሆን የመቻል ዕድል እንደሌውና በጊዜ ብዛት ትክክለኛነቱ አለመደብዘዙን በምን እርግጠኛ መሆን ይቻላል? የሙስሊም ሊቃውንት ሐሳብ ትክክል ከሆነና እነዚህ ቁርአኖች ሰው ሠራሽ ከሆኑ “እርሱን የሚመስል መጽሐፍ ማንም መፍጠር እንደማይችል” የሚናገሩት የቁርአን አናቅፅ ምን ሊሆኑ ነው? የጥንት ሙስሊሞች ከቀርአን(ኖች) ጋር በጣም የሚመሳሰሉ ነገር ግን እውነተኛ ቁርአን(ኖች) ያልሆኑ መጻሕፍትን ጽፈዋልና! ሙስሊም ወገኖች ቁርአናችሁ እንዲህ ያለ ገፅታ ያለው መጽሐፍ የመሆኑ እውነታ ከልጅነታችሁ ሲነገራችሁ ከነበረው የቁርአን ፍፁማዊ አንድነት ትርክት አኳያ እንዴት ታዩታላችሁ?