ሚስተር ዲዳት የእስልምናን ትምህርት ውድቅ አደረጉ

ሚስተር ዲዳት የእስልምናን ትምህርት ውድቅ አደረጉ


ዛሬ እንደ አጋጣሚ ሆኖ የመጽሐፍት ስብስቦቼን ሳስስ “ኢየሱስ እውን ፈጣሪ ነውን?” በሚል ርዕስ በአሕመድ ዲዳት የተጻፈች ግልገል ክታብ አገኘሁኝ። ከዓመታት በፊት ያነበብኳት ቢሆንም ለትውስታ ያህል ከገጽ ገጽ እያገላበጥኩ ይዘቷን ስቃኝ ከዚህ ቀደም አይቼ የተገረምኩበትን ከታች በምስል ያያያዝኩትን አባባል አገኘሁኝ። ሚስተር ዲዳት እንዲህ በማለት በተለመደ መርዘኛ ምላሳቸው ክርስቲያኖችን ይናደፋሉ፦ “በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ የሚገኙ ከአንድ ሺህ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት የክርስትና እምነት ተከታዮች የናዝሬቱ ኢየሱስ «ክርስቶስ» እንደሆነ በጭፍን ይቀበላሉ። ለዚህም አቋማቸው ማጠናከሪያ ይሆኑ ዘንድ «አንድ ሺህ አንድ» ትንቢቶችን ከአይሁዶች መጽሐፍ ቅዱስ (ከብሉይ ኪዳን መጽሐፍ) እየለቃ ቀሙና እያገጣጠሙ፥ ኢየሱስ አዳኛቸው «መሲሐቸው» መሆኑን በመረጃ ለማስደገፍ ይፍጨረጨራሉ።” (ገጽ 18)።

እንዲህ ያለው አነጋገር ከአምላክ የለሽ፣ ከአይሁዳዊ ወይንም ከሌላ እምነት ተከታይ ዘንድ ቢሰማ እምብዛም ላያስገርም ይችላል። ነገር ግን ከአንድ ሙስሊም ነኝ ከሚል ግለሰብ መሰማቱ ለማመን የሚቸግር ነው። የኢየሱስ መሲህነት (ክርስቶስነት) ሙስሊሞችም ሆኑ ክርስቲያኖች በጋራ የሚስማሙበት ጉዳይ ነው። መሲህ በእብራይስጥ፣ ክርስቶስ በፅርዕ ትርጉማቸው አንድ ሲሆን “የተቀባ” ማለት ነው። በቁርአን ውስጥ ወደ 11 ጊዜ ይህ ማዕርግ ለዒሳ ጥቅም ላይ ውሏል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ደግሞ ወደ 529 ጊዜ ኢየሱስ በዚህ ማዕርግ ተጠርቷል። እውነታው ይህ በሆነበት ሁኔታ አንድ በኢየሱስ መሲህነት አምናለሁ የሚል ሙስሊም ክርስቲያኖች ይህንኑ በማመናቸው ጭፍኖች እንደሆኑ በመግለጽ መወረፉ ጉድ የሚያሰኝ ነው። የኢየሱስን መሲህነት ማመን ጭፍን ካሰኘ እንደ ሙስሊም ጭፍን ሊባል የሚችል ፍጥረት አይኖርም። ክርስቲያኖች ቢያንስ ለኢየሱስ መሲህነት የብሉይ ኪዳንን ትንቢቶች እንዲሁም የአዲስ ኪዳንን የሐዋርያት ምስክርነቶች በመነሻነት ጠቅሰው ተቀብለዋል። ሙስሊሞች ግን የአንዱን የሙሐመድን ምስክርነት በማመን ነው የተቀበሉት። ማስረጃ እንዲያቀርቡ ቢጠየቁ ለይስሙላ እንኳ የሚያቀርቡት ማስረጃ የላቸውም።

በቁርአንም ሆነ በእስላማዊ ምንጮች መሲህ ወይም ክርስቶስ የሚለው ቃል ትርጉም አይታወቅም። ሙሐመድ ክርስቲያኖችና አይሁድ ሲናገሩት በመስማቱ ብቻ ትርጉማቸውንና አስፈላጊነታቸውን ሳያውቅ ከወሰዳቸው ቃላት መካከል አንዱ ይህ ቃል ነው። አንድ ሙስሊም “መሲህ ምን ማለት ነው? ኢየሱስ ለምን መሲህ ተባለ?” ተብሎ ቢጠየቅ ከግምት የዘለለ ሁነኛ ምላሽ የለውም። ሙሐመድም ሆነ ተከታዮቹ ትርጉሙን አያውቁም። ይልቅ ደግሞ እንደ ዲዳት ያሉ ስመ ጥር ሙስሊም ሰባኪያን ክርስትናን ለመተቸት ካላቸው ጉጉት የተነሳ የኢየሱስ መሲህነት በቁርአን እንኳ የሚታመን መሆኑን ዘንግተው ክርስቲያኖች ኢየሱስን መሲህ ብለው ማመናቸውን ከጭፍንነት ቆጥረዋል። ይህ ወቀሳ ትክክል አለመሆኑን አስተውሎ ተቃውሞ የሚያቀርብ አንድ ሙስሊም መጥፋቱ ደግሞ አጀብ ያሰኛል። ምናልባት በሁሉም ነጥቦች ላይ ክርስትናን መቃወም አዋጭ መንገድ መስሎ ታይቷቸው ይሆን ሙስሊም ሰባኪያን እንዲህ ያለ የማወናበድ መንገድ የመረጡት? እስልምና ነገሩ ሁሉ ግራ ነው።


ለእስልምና ሙግቶች ምላሽ