የመሲሑ አምላክነት በዕብራይስጥ ቅዱሳት መጻሕፍት [ክፍል አንድ]

የመሲሑ አምላክነት በዕብራይስጥ ቅዱሳት መጻሕፍት [ክፍል አንድ]

ወንድም ሚናስ


በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት ዙርያ የዕብራይስጥ ቅዱሳት መጻሕፍትን ዋቢ በማድረግ  ተከታታይ መጣጥፎች ለመጻፍ ወስኛለሁ። የመጣጥፎቹ ዓላማም መሲሑ  በሥጋ የተገለጠ ያህዌ መሆኑን ማሳየት ነው። መጣጥፎቹ አራት ክፍል የሚኖራቸው ሲሆን፥ አርዮሳውያንና ነጠላውያንን ከመሳሰሉት የኑፋቄ ቡድኖች ወይም ከሙስሊሞች ጋር ስለ እምነታቸው መወያየት የሚፈልጉ ክርስቲያኖችን ለመጥቀም በማለም የተዘጋጁ ናቸው። እርስዎም ይህንን መጣጥፍ በማካፈል ሌሎች ወገኖች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የበኩለዎን ይወጡ ዘንድ እጋብዛለሁ። በቀጥታ ጥቅሶቹን ወደ መመልከት እንሂድ፦

መዝሙር 721፥9-11፦“ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ፍትህን ለንጉሥ፣ ጽድቅህንም ለንጉሥ ልጅ ዐድል፤ … የበረሓ ዘላኖች በፊቱ ይንበረከካሉ (כָּרַע) ፤ ጠላቶቹም ዐፈር ይልሳሉ።  የተርሴስና የደሴቶች ነገሥታት፣ ግብር ያመጡለታል፤ የዐረብና የሳባ ነገሥታት፣ እጅ መንሻ ያቀርባሉ።  ነገሥታት ሁሉ ይሰግዱለታል (שָׁחָה)፤ ሕዝቦችም ሁሉ ይገዙለታል” (አዲሱ መ.ት)

ቁጥር 1 ሲጀምር  ስለ ንጉሡ  ይናገራል፤ ብዙ  አይሁዳውያን ሊቃውንት ይህ መሲሑን እንደሚያመለክት ይናገራሉ። ይህ ማለት በዘመኑ ለሰሎሞን ቢመስልም ፍጹማዊው የትንቢቱ ምልዓት ስለ መሲሑ ነው (ማቴ. 2፥11)።

የአረማይኩ ትርጉም ይህንን ጥቅስ እንዲህ አስቀምጦታል፦ “አቤቱ ጽድቅህን ለንጉሥ መሲህ ጽድቅህንም ለንጉሥ ዳዊት ልጅ ስጥ”[1]

የባቢሎናውያን ታልሙድ ደግሞ እንዲህ በማለት ያብራራዋል፦ “ስለ መሲሑ በሚናገረው ምዕራፍ ላይ “ስሙ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል፤ ስሙም ከፀሐይ በፊት ነበረ” (መዝሙረ ዳዊት 72፡17) ተብሎ እንደ ተጻፈ የመሲሑ ስም ዓለም ሳይፈጠር ነበረ።”[2]

ከ100-165 ዓ.ም የኖረው ቀዳሚ ዐቃቤ እምነት ሰማዕቱ ዮስጦንዮስ፣ ትሪፎ ከተሰኘ አይሁዳዊ ጋር ባደረገው ውይይት ይህ ምዕራፍ ስለ ኢየሱስ የተነገረ ትንቢት መሆኑን ገልጿል።[3] ትንቢቱ መሲሁን የተመለከተ ስለመሆኑ የአይሁድ ሊቃውንትና የቤተክርስቲያን አበው ምስክርነቶች አሉን ማለት ነው። እውነታው ይህ ከሆን እስኪ ቁጥር 9-11 ላይ ትኩረታችንን በማድረግ እንመልከት።

ክፍለ-ንባቡ መሲሑ ፍጥረታት እንደሚንበረኩለት (“ካራ” כָּרַע) እና  እንደሚሰግዱለት (“ሻኻህ” שָׁחָה) ይገልጻል። ሁለቱ ግሦች ማለትም כָּרַע “ካራ” ፣ እንዲሁም שָׁחָה “ሻኻህ” እንዴት አምልኮን እንደሚያመልክቱ እንመረምራለን፤ በሒደቱም  መሲሑ ያህዌ አምላክ መሆኑን እናጸናለን።

“ይንበረከካሉ” (כָּרַע)

የግሱ ትርጓሜ ከታች ባለው የዕብራይስጥ ሙዳየ ቃል ላይ ተቀምጧል፦

ምስል 1

ይህ ቃል በዕብራይስጥ ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለበትን መንገድ እንመልከት፡-

“ሰሎሞንም ይህን ሁሉ ጸሎትና ልመና ለእግዚአብሔር አቅርቦ ከፈጸመ በኋላ፣ እጆቹን ወደ ሰማይ በመዘርጋት፣ በጒልበቱ ተንበርክኮ (כָּרַע) ከነበረበት ከእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ተነሣ።” — 1ኛ ነገሥት 8፥54 (አዲሱ መ.ት)

“ከዚያም፣ የሠርክ መሥዋዕት በሚቀርብበት ጊዜ፣ የተቀደደውን መጐናጸፊያዬንና ካባዬን እንደ ለበስሁ በሐዘን ከተቀመጥሁበት ተነሣሁ፤ በጒልበቴም ተንበርክኬ (כָּרַע)  ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር እጆቼን በመዘርጋት፣”— ዕዝራ 9፥5 (አዲሱ መ.ት)

ከላይ ባሉት ምንባቦች ውስጥ כָּרַע “ካራ” የሚለው ግሥ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ አምልኮን (ወይም ጸሎትን) እንደሚያመለክት ልብ ይሏል። በሌሎች ምንባቦች ውስጥ ደግሞ כָּרַע “ካራ” ከ שָׁחָה “ሻኻህ” ጋር ሲቀርብ ለያህዌ የሚሰጠውን አምልኮ ለማሳየት ጥቅም ላይ ይውላል። አንድ ምሳሌ እናቅርብ፦

“እስራኤላውያንም ሁሉ እሳቱ ሲወርድ፣ የእግዚአብሔርንም ክብር ከቤተ መቅደሱ በላይ ሲያዩ፣ በመተላለፊያው ወለል ላይ ተንበረከኩ (כָּרַע)፤ በግንባራቸውም ወደ መሬት ተደፍተው ሰገዱ (שָׁחָה) ፤ እንዲህ እያሉም ለእግዚአብሔር ምስጋና አቀረቡ፤ “እርሱ ቸር ነውና፤ ፍቅሩም ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።” እያሉም እግዚአብሔርን አመሰገኑ።” — 2ዜና 7፥3 (አዲሱ መ.ት)

“ይሰግዱለታል” (שָׁחָה)

በተመሣሣይ שָׁחָה “ሻኻህ” የሚለው ግሥ አምልኮን እንደሚያሳይ መዝገበ ቃሉ ይነግረናል፤ ግሡ ለያሕዌ ጥቅም ላይ የዋለበት ምንባብ እንይ፡

“አትስገድላቸው (תִשְׁתַּחְוֶ֥ה)፤ አታምልካቸውም፤ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ (ያህዌ ኤሎሂም) የሚጠሉኝን ልጆች ከአባቶቻቸው ኀጢአት የተነሣ እስከ ሦስትና አራት ትውልድ ድረስ የምቀጣ ቀናተኛ አምላክ (ኤሎሂም) ነኝ፤” — ዘጸአት 20፥5 (አዲሱ መ.ት)

“የምድር ዳርቻዎች ሁሉ ያስታውሳሉ፤ ወደ እግዚአብሔርም ይመለሳሉ፤ የሕዝቦች ነገዶች ሁሉ፣ በፊቱ ይሰግዳሉ (וְיִֽשְׁתַּחֲו֥וּ)።” — መዝሙር 22፥27 (አዲሱ መ.ት)

“ጌታ ሆይ፤ አንተ የሠራሃቸው ሕዝቦች ሁሉ፣ መጥተው በፊትህ *ይሰግዳሉ* (וְיִשְׁתַּחֲו֣וּ)፤ ለስምህም ክብር ይሰጣሉ፤” — መዝሙር 86፥9 (አዲሱ መ.ት)

እንግዲህ ከላይ በተመለከትነው መሠረት “ካራ” כָּרַע እና “ሻኻህ” שָׁחָה የሚሉት ግሦች ብዙውን ጊዜ አምልኮን ያመለክታሉ፤ አንድ ላይ ሲመጡ ደግሞ ለያሕዌ ተገቢ የሆነውን አምልኮ ያመለክታሉ፤ እናም እነኚህ ቃላት በመዝሙር 72፡9-11 ላይ ለመሲሑ ግልጋሎት ላይ ውለዋል፤ ይህም የሚያሳየው መሲሑ መለኮት መሆኑን ነው።


ማጣቀሻዎች

[1]Aramaic Targum to Psalms

[2]Babylonian Talmud, Pesachim 54a

[3] Dialogue with Trypho (Chapter 34)

 

መሲሁ ኢየሱስ