የመሲሑ አምላክነት በዕብራይስጥ ቅዱሳት መጻሕፍት[ ክፍል ሁለት]

የመሲሑ አምላክነት በዕብራይስጥ ቅዱሳት መጻሕፍት[ ክፍል ሁለት]

ወንድም ሚናስ


ለመሲሑ አምላክነት አመልካች ምንባባት ከሆኑት አንዱ ኢሳይያስ 9፥6-7 ሲሆን ጌታ ኢየሱስ ከመወለዱ ከስምንት መቶ ዓመታት በፊት የተጻፈ ነው። ነቢዩ ኢሳይያስ በዳዊት ዙፋን ላይ ለዘላለም ሊነግሥ ከሚመጣው ከኃያሉ አምላክ በቀር ሌላ ያልሆነ ሕፃን እንደሚወለድ ተናግሯል!

ኢሳይያስ 9፥6፦“ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል ስሙም ድንቅ መካር፥ *ኃያል አምላክ* ፥ የዘለዓለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል፡፡”

כִּי-יֶלֶד יֻלַּד-לָנוּ, בֵּן נִתַּן-לָנוּ, וַתְּהִי הַמִּשְׂרָה, עַל-שִׁכְמוֹ; וַיִּקְרָא שְׁמוֹ פֶּלֶא יוֹעֵץ, אֵל גִּבּוֹר, אֲבִי-עַד, שַׂר-שָׁלוֹם.

ይህንን የበለጠ ትኩረት እንዲስብ የሚያደርገው ኢሳይያስ ይህንን የማዕረግ ስም ለያሕዌ መጠቀሙ ነው።

“የተረፉት ይመለሳሉ፣ ከያዕቆብ ቤት የተረፉት ወደ ኀያሉ አምላክ ይመለሳሉ።” — ኢሳይያስ 10፥21 (አዲሱ መ.ት)

ይህ ግልጽ የሆነ የመሲሑን አምላክነት አመልካች ምንባብ ለማስተባበል የኑፋቄ ቡድኖች የሚያቀርቡትን ሙግት ደግሞ በቀጣይ እንዳስሳለን።

ሙግት አንድ፦

“ይህ ጥቅስ መሲሑን የሚመለከት ሳይሆን በዘመኑ ለተወለደው ህጻን የተጠቀሰ ምንባብ ነው።” ይህ ሙግት ዐውዱንም ሆነ የጥንታውያን አይሁዳውያን ሊቃውንት መዛግብትን እንዲሁም የአዲስ ኪዳን ማረጋገጫዎችን ካለማጤን የመነጨ ነው። ከዚህ ቀደም በድረ-ገጻችን ላይ በሰፈረ ጽሑፍ ይህ ክፍል እንደተብራራው ዐውዱን ስንመለከት ስለገሊላ በመናገር  ይጀምርና እግዚአብሔር በዮርዳኖስ ማዶ በባሕር መንገድ ያለውን ቀደም ሲል ተዋርዶ የነበረውን የአሕዛብ ገሊላ እንደሚያከብር ይናገራል (ኢሳይያስ 9፡1-7)፡፡ ጌታችን ኢየሱስም በወቅቱ የነበሩት አይሁዳውያን ባልጠበቁት ሁኔታ ከተናቀው የገሊላ ግዛት ነበር የመጣው፡፡ በወቅቱ የነበሩት አንዳንድ አይሁድ መሲሁን ከገሊላ አይጠብቁትም ነበር፡፡ በትንቢቱ መሠረት ግን እግዚአብሔር ገሊላን አከበረ፡፡ (ማቴ. 3፡13፣ 4፡15፣ 4፡25፣ 21፡11፣ ማር. 1፡9፣ ሉቃ. 4፡14፣ ዮሐ. 7፡41-52)። http://www.ewnetlehulu.org/am/el-gibbor/ ይህንን አስተውለው የተረዱ የአይሁድ ሊቃውንትም ስለ መሲሑ የሚናገር ትንቢታዊ ጥቅስ መሆኑን አትተዋል። የተወሰኑትን ለመመልከት ያህል፦

“ረቢ ሆሴዕ ዘገሊላ እንዲህ አለ፦ የመሲሑ ስም ሰላም ይባላል (ኢሳይያስ 9: 6)፣ ‘የዘላለም አባት፣ የሰላም አለቃ’ ተብሎ ተጽፏልና።”[1]

“ልጅ ተወልዶልናል፣ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል። … ስሙም ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ ፣ ለዘላለም የሚኖ (ዘላለማዊ) ተብሎ ይጠራል። በዘመኑም ሰላምን የሚያበዛልን መሲህ ነው”[2]

ሙግት ሁለት፦

“ይጠሩታል ተብሎ የተጠቀሰው የዕብራይስጥ ቃል የኃላፊ ግስ ስለሆነ መጻኢ ትንቢትን የሚያመለክት አይደለም።” ይህ ሙግት ደግሞ የዕብራይስጥን ሰዋስው በወጉ ካለ መረዳት የሚመነጭ ነው። በዕብራይስጥ ትንቢታዊ ንግር በመጻኢ ግሥ የሚገለፅ ነቢያዊ ፍጽምና (Prophetic Perfection) የተሰኘ አነጋገር አለ፤ ይኸውም ወደፊት የሚከሰተውን ነገር ባለፈ ግሥ በመጥራት መግለጽ ማለት ነው። ነቢዩ ክስተቱን በመንፈስ ዓይን እየተመለከተ ስለሚናገር ልክ እንደተፈጸመ አድርጎ ይናገረዋል። ለምሳሌ በዚሁ ትንቢተ ኢሳይያስ ላይ አንድ ማሳያ ላቅርብ፦

“ስለዚህ ሕዝቤ ወደ ምርኮ ሄዱ (גָּלָ֥ה)፥ ጌታን አላወቁትምና፤ ከበርቴዎቻቸውም ተራቡ፥ ሕዝባቸውም ተጠሙ።” — ኢሳይያስ 5፥13

በዐውደ-ምንባቡ ውስጥ እግዚአብሔር እስራኤላውያን በኃጢአታቸው ምክንያት ስለሚደርስባቸው መከራ ይናገራል። ሙሉ ሐሳቡም ወደ ፊት ስለሚከተላቸው ቅጣት የሚናገር ነው (ኢሳ 5፥9)። ነገር ግን በቁ.13 የወደ ፊቱን ቅጣት ጥንት እንደተፈጸመ አድርጎ ተናገረው። ሄዱ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል גָּלָ֥ה “ጋላህ” በኃላፊ ግሥ የተቀመጠ ነው። ነገር ግን ስለ ወደፊት ክስተት የሚናገር ትንቢት መሆኑ ግልጽ ነው። በተመሳሳይ ኢሳይያስ 9፥6 וַיִּקְרָא “ዋዪቄራ” የሚለው “ይጠሩታል”  ተብሎ የተተረጎመው ቃል የኃላፊ ግሥ ቢሆንም ነገር ግን ትንቢታዊ ቃል የሚሆንበት ምክንያት (1) በጥቅሱ ቊጥር 7 ላይ ለዘለዓለም እንደሚነግሥ ይናገራል፤ በብሉይ ኪዳን ደግሞ ለዘለዓለም እንሚነግሥ ከመሲሑ ውጪ የተነገረለት አካል የለም። (2) በሙግት አንድ ላይ እንደዳሰስነው ዐውዱም፣ የአይሁዳውያን ሊቃውንት ሐተታም ሆነ አዲስ ኪዳን ስለ መሲሑ የተነገረ መሆኑን ያመለክታሉ።

ሙግት ስት፦

“በሕዝቅኤል 32፥21 ላይ ፍጥረታት ኃያላን አማልክት ተብለዋል።” ለዚህ ሙግት ምላሽ ከዚህ ቀደም በቂ ምላሽ ስለተሰጠበት እርሱን እደግመዋለሁ። ጥቅሱ የሚናገረው ስለ ግብፃውያን ነገሥታት ነው፡፡ የግብፅ ፈርዖኖች ራሳቸውን አማልክት አድርገው ይቆጥሩ ስለነበር እነዚህ አማልክት የተባሉት ነገሥታት ሲዖል ውስጥ መሆናቸውን እየተናገረ ነው፡፡ እነዚህ ራሳቸውን አማልክት አድርገው ሲመለኩ የኖሩት ኃያላን ሲዖል ውስጥ መሆናቸውን በምፀት የሚናገር ጥቅስ “ኤል-ጊቦር” መለኮታዊ ማዕርግ መሆኑን ለማስተባበል ሊውል አይችልም፡፡ ስለዚህ ሙግቱ ገለባ ነው፡፡  ሲጀመር “ኤል” ወይም “ኤሎሂም” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እውነተኛውን አምላክ ወይንም ሰዎች እንደ አምላክ የሚያመልኳቸውን ጣዖታትና ፍጡራን ለማመልከት ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ “ኤል” ስለተባሉ ብቻ እውነተኛ አማልክት ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ወሳኙ ነጥብ “ኤል” የተባለው አካል እውነተኛውን አምላክ በሚያመለክት መንገድ መጠቀስ አለመጠቀሱ ነው፡፡ ህፃኑ “ኤል-ጊቦር” የተባለው ሰዎች ስላሉት ወይንም ሐሰተኛ አማልክትን በሚያሳይ መንገድ ሳይሆን ያሕዌ እግዚአብሔር ራሱ ነው “ኤል-ጊቦር” ብሎ ለሰዎች ያስተዋወቀው፡፡ “ኤል ሻዳይ” እግዚአብሔርን ለመግለፅ እንደገባው ሁሉ “ኤል ጊቦርም” በተመሳሳይ እግዚአብሔርን ለመግለፅ ጥቅም ላይ ስለዋለ መለኮታዊ ባሕርይን ይገልፃል፡፡


ማጣቀሻዎች

[1] Babylonian Talmud (Tract Derech Erez Zutha), “How to Recognise the Messiah” Pg. 11

[2] Targum Jonathan to the Prophets, https://www.sefaria.org/Targum_Jonathan_on_Isaiah.9.6


መሲሁ ኢየሱስ