ሰማያዊ ሥጋ አስተምህሮ መጽሐፍ ቅዱሳዊ፣ አመክንዮአዊና ሥነ-መለኮታዊ ህጸጾች

የሰማያዊ ሥጋ አስተምህሮ መጽሐፍ ቅዱሳዊ፣ አመክንዮአዊና ሥነ-መለኮታዊ ህጸጾች

አማኑኤል እንዳለ


ውድ አንባቢያን «ሰማያዊ ሥጋ» የሚለውን ቃል ስትሰሙ ምናልባት የመጀመሪያችሁ ሊሆን ስለሚችል “ከፈረሱ ጋሪው” እንዳይሆን አስቀድሜ ነገሩ ምን እንደሆነ ለማሳወቅ ያህል ጥቂት ነገር ልበል። የሰማያዊ ሥጋ አስተምህሮን ምን እንደ ሆነ በኢትዮጵያ የትምህርቱ ጀማሪ ከሆኑት ከቢሾፕ ተክለማርያም ገዛኸኝ «ቃሉ ይናገር» (2012 ዓ.ም.፣ ገጽ 40) ከተሰኘው መጽሐፍ መጠነኛ ማብራሪያዎችን ማግኘት እንችላለን። በእርግጥ ደራሲው ሐሳቡን በስርዓት ከመተንተን ይልቅ አያሌ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ያለ አውዳቸው ሰዳድሮ ስለሚያስቀምጣቸው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሰማያዊ ሥጋን አስተምህሮ ግልጽና ወጥ በሆነ መንገድ ለማግኘት እጅግ አዳጋች ነው።

ሐዋ.20፡28 “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያንን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመበት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።”

አብ በራሱ ከራሱ ቃል ያዘጋጀው ሥጋና ደም በመሆኑም በሰው ቅርጽ የተገለጠ ሰውነት አለው። በዚህም ከመላእክት ይለያል። ዳሩ ግን በሥጋ የተወለደ አማኑኤል (ቃል ሥጋ ሆኖ ተገለጠ) እንጂ አልተፈጠረም። ነገር ግን ከመላእክት አብዝቶ ይበልጣል ይላል።

ሮሜ.1፡22-25 “ጥበበኞች ነን ሲሉ ዶንቆሮ ሆኑ፤ የማይጠፋውንም የእግዚአብሔርን ክብር በሚጠፋ ሰውና በወፎች አራት እግር ባላቸውም በሚንቀሳቀሱትም መልክ መስለው ለወጡ። ስለዚህ እርስ በርሳቸው ሥጋቸውን ሊያዋርዱ እግዚአብሔር በልባቸው ፍትወት ወደ ርኵስነት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ይህም የእግዚአብሔርን እውነት በውሸት ስለ ለወጡ በፈጣሪም ፈንታ የተፈጠረውን ስላመለኩና ስላገለገሉ ነው፤ እርሱም ለዘላለም የተባረከ ነው፤ አሜን።” በማለት የምናመልከው ኢየሱስ ክርስቶስ ከአፈር የተፈጠረ የሚበሰብስ ሰውነት እንደሌለውና አብ ራሱ ሥጋዬና ደሜ ከሰማይ ከአብ ዘንድ የመጣ ነው ብሎ አረጋግጦልናል። ከዚህ ቀጥሎ ያለውን በማስተዋል እንገንዘበው።

ዮሐ.6፡33 “የእግዚአብሔር እንጀራ ከሰማይ የሚወርድ ለዓለምም ሕይወትን የሚሰጥ ነውና አላቸው።” የእግዚአብሔር እንጀራ ሥጋው ነው። ቁጥር 51 “ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል፤ እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው።”

በጥልቀት ወደ ሥነ-መለኮታዊ ሕጸጾቹ ከመግባታችን በፊት፣ ደራሲው ከጥቅሶቹ ቀጥሎ ያስቀመጧቸውን አረፍተ ነገሮች እና የቋንቋ አጠቃቀም ብንመረምር እጅግ በርካታ መሠረታዊ ህጸጾችን እናገኛለን፦

የሰዋሰውና አወቃቀር ህጸጽ፦ ደራሲው «ዳሩ ግን በሥጋ የተወልደ አማኑኤል እንጂ አልተፈጠረም» በማለት የጻፉት አረፍተ ነገር ከሰዋሰው ሕግ አንጻር በትክክል ያልተዋቀረና የተሟላ ትርጉም የሌለው  ነው። መሠረታዊ በሆነ የቋንቋ ሕግ ላይ እንዲህ ያለ ግደፈት መገኘቱ በትምህርቱ የሦስተኛ ድግሪ (Doctorate) ደረጃ ተምሬአለሁ ከሚል ሰው ፈጽሞ የማይጠበቅ ነው። በእርግጥ የቢሾፑ የዶክትሬት ድግሪ ሐሰት መሆኑን የሚያሳይ የምርመራ ዘገባ ከዚህ ቀደም እዚሁ ድረ-ገጽ ላይ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን የኢትዮጵያ ሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን መሪዎችም ሆኑ የቢሾፕ ተክለማርያም ቤተሰብ ምንም ዓይነት ማስተባበያ ሊያቀርቡለት አልቻሉም ነበር። https://ewnetlehulu.net/tekles-fake-doctorate/

የአልቦ ማስረጃና ስነ መለኮታዊ ስህተት፦ ደራሲው «አብ ራሱ ሥጋዬና ደሜ ከሰማይ ከአብ ዘንድ የመጣ ነው ብሎ አረጋግጦልናል» ይላሉ። ይህ አባባል ትልቅ ድፍረትና ስህተት ነው፤

  • አብ «ሥጋዬና ደሜ ከሰማይ ከአብ ዘንድ የመጣ ነው» ብሎ የተናገረበት ምንም ዓይነት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የለም።
  • በአንድ በኩል «አብ» ተናገረ ብሎ መልሶ ደግሞ «ከአብ ዘንድ ሥጋዬ መጣ» ማለት እርስ በእርሱ የሚጋጭና አብንና ወልድን፣ ወይም ደግሞ ተናጋሪውንና ባለቤቱን ያለመለየት ችግር ያለበት አባባል ነው። በሰማይ ያለው አብና ተናጋሪው አብ ሁለት ይሆናሉ። እንግዲህ ቢሾፑ እያሉን ያሉት ይህንን ነው።
  • በተጨማሪም «በአብ ዘንድ ሥጋና ደም ነበረ» የሚለው እሳቤ የአብን ረቂቅነት ወይም መንፈስነት የሚቃወም ነው (ዮሐንስ 4:24)።

ደራሲው ፦ «አብ በራሱ ቃል ያዘጋጀው ሥጋና ደም በመሆኑም በሰው ቅርጽ የተገለጠ ሰውነት አለው» ካሉ በኋላ ይህ ሥጋ ከመላእክት እንደሚለይና «የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ» እንደሆነ ጠቅሰዋል። ከዚያ በመቀጠልም ደግሞ ሮሜ 1:22-25ን በመጥቀስ፦ «ኢየሱስ ክርስቶስ ከአፈር የተፈጠረ የሚበሰብስ ሰውነት እንደሌለውና አብ ራሱ ሥጋዬና ደሜ ከሰማይ ከአብ ዘንድ የመጣ ነው ብሎ አረጋግጦልናል» በማለት ይደመድማሉ።

ይህ ማብራሪያ መሠረታዊ የሰዋሰውና የአመክንዮ ችግር ያለበት ብቻ ሳይሆን በሥነ-መለኮታዊ ሕጸጽ የተሞላ፣ ወጥነት የሌለውና ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር የሚጋጭ መሆኑን የሚያስረዱ አምስት ዋና ዋና ምክንያቶቼን እንደሚከተለው አቀርባለሁ፦

1. የኢየሱስ ክርስቶስን እውነተኛ ሰው መሆን መካዱ

መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ሰው ሆኖ ከድንግል ማርያም በሥጋ እንደተወለደ ያስተምራል። «ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተሞልቶ በእኛ አደረ» (ዮሐንስ 1:14) ። የሰማያዊ ሥጋ አስተምህሮ ግን የክርስቶስ ሥጋ ከሰማይ የወረደ ነው በማለት ከድንግል ማርያም የነሳውን እውነተኛ የሰው ባሕርይና ሥጋ ያቃልላል ወይም ይክዳል። ክርስቶስ የሰው ልጅ የተባለው በምድር ላይ ከሰው ልጅ (ከማርያም) እውነተኛ ሥጋንና ደምን ስለነሳ ነው (ሉቃስ 1:31-35) ። በተለይም <<እውነተኛ ሰው>> የሚለው ሙያዊ ቃል በኬልቄዶን የእምነት መግለጫ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብ ጋር በባሕርይ አንድ እንደሆነ ሁሉ ከእኛም ጋር አንዱን የሰው ባሕርይ መካፈሉን ለመግለጽ ጥቅም ላይ ውሏል። ኢየሱስ ክርስቶስ ከኅጢአት በቀር በነገር ሁሉ እኛን ሊመስል ተግብቶታልና እርሱ እውነተኛ ሰው መሆኑን እናምናለን፤ የሰማያዊ ሥጋ ትምህርት ግን ከዚህ በተጻራሪ የሰው ልጆችን ለማዳን እውነተኛ ሰው የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ከሰው የሰውን ዘር አልተካፈለም በማለት ትምህርተ ሥጋዌን ይቃወማል።

2. ጥቅሶችን ያለ አውዳቸው መጠቀም

ትምህርቱ ለድጋፍ የሚጠቀማቸው እንደ ዮሐንስ 6:33 እና 51 ያሉ «ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ» የሚሉ ጥቅሶች የክርስቶስን መለኮታዊ ምንጭና ለዓለም ሕይወትን ሰጪነቱን እንጂ የቁሳዊ ሥጋውን አመጣጥ የሚያስረዱ አይደሉም። እንዲሁም ሮሜ 1:22-25 የሚያወራው ስለ ፍጥረታትና ምስሎች አምልኮ (ጣዖት አምልኮ) እንጂ ስለ ክርስቶስ ሥጋ አመጣጥ አይደለም። እነዚህን ጥቅሶች ለሰማያዊ ሥጋ ትምህርት ድጋፍ መጥቀስ የጽሑፎቹን አውድ ሙሉ በሙሉ መሳት ነው።

ለምሳሌ በዮሐንስ 6:38 ላይ፦ «ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም እንጂ የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁና» ብሎ የሚናገረው ሰማያዊ ሥጋ ሳይሆን ኢየሱስ ራሱ ነው፤ ይህንን ማንም ሰው ሊያስተውለው የሚችል ቀላል እውነት ነው። ተናጋሪውም አብ አይደለም፤ ምክንያቱም «የላከኝን» በማለት ተናግሯልና። በዚህ ምንባብ ውስጥ የተላከው ወልድ ነው። በድጋሚ በቁጥር 53 ላይ «የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ» በማለት በመናገሩ «ተናጋሪው አብ ነው» የሚለውን የቢሾፑን መላምት ሙሉ በሙሉ ውድቅ ያደርገዋል፤ ምክንያቱም አብ «የሰው ልጅ» አይደለምና። ታዲያ ተናጋሪው ማን ነው? ወልድ ነው! ስለዚህ በቁጥር 51 ላይ «ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው» ብሎ የተናገረው ወልድ ራሱ እንጂ ሥጋው አይደለም። ወልድ ሙሉ ማንነት ያለውና የሥጋውም ባለቤት እንደሆነ ከክፍሉ አውድ በግልጽ እንረዳለን።

3. የመጽሐፍ ቅዱስን የድነት ትምህርት ማፍረሱ

ዕብራውያን 2:14-17 እንደሚናገረው፦ «እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ» ይላል። ክርስቶስ ሰውን ለማዳን የሰውን እውነተኛ ሥጋ መውሰድ ነበረበት። የክርስቶስ ሥጋ «ሰማያዊ» ብቻ ከሆነና ከእኛ የሰው ልጅ ሥጋ ጋር አንድ ካልሆነ ሰውን ሊወክልና የሰውን ኃጢአት በሥጋው ሊሸከም አይችልም። ምክንያቱም የጥንት አበው እንደሚሉት «ያልነሳውን አላደነውና ያዳነው የነሳውን ነው።>> (Unassumed is unhealed)

ለዚህ እውነት ምላሽ ለመስጠት የቤተ-እምነቱ መምህራን የተለዩ መከራከሪያዎችን ያቀርባሉ፦

  • የመጀመሪያው መክራከሪያ፦ አንዳንዶች «በሥጋ» እና «በደም» የሚለው ሥጋና ደምን መካፈሉን ሳይሆን «በሥጋና በደም ሞትን መካፈሉን» ነው የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ። ሆኖም ግን «በ» የሚለው preposition በጽርዕ (የአዲስ ኪዳን የግሪክ ቋንቋ – μετέσχεν αἵματος καὶ σαρκός) ሆነ በሌሎች የታመኑ የኢንግሊዘኛ ትርጉሞች (KJV, NASB, ESV) ውስጥ እነርሱ በሚሉት መልኩ «ሞትን መካፈል» በሚል የተረጎመ አንዳችም የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ የለም። የጽርዑ አወቃቀር የሚያሳየው ክርስቶስ ልጆቹ (ሰዎች) ያላቸውን ተመሳሳይ ሥጋና ደም (sarx and haima) በግልጽ መካፈሉን እንጂ ሞትን ብቻ ማመልከቱን አይደለም።
  • ሁለተኛው መከራከሪያ፦ ሌሎች ደግሞ ኢየሱስ አስቀድሞ «ሰማያዊ ሥጋን» ያካፈለ ሲሆን ከዚያም አማኞች በትንሣኤ የሚካፈሉትን ሰማያዊ ሥጋ መካፈሉን ያሳያል እንጂ «እንደ እነርሱ ዓይነት ሥጋና ደም ተካፈለ» የሚል ሐሳብ የለውም ይላሉ። ይህ መከራከሪያም ቢሆን ከላይ በተብራራው የግሪክ ሥነ-ጽሑፍ አወቃቀርና አውዳዊ ትርጉም መሠረት መሠረተ-ቢስና ስህተት ነው። ክፍሉ የሚናገረው አማኞች ወደፊት ስለሚለብሱት የከበረ አካል ሳይሆን ክርስቶስ እኛን ለመዋጀት አሁን ያለንበትን ምድራዊ ሥጋና ደም መካፈሉን ነው።

4. የሰማያዊ ሥጋ ትምህርት እርስ በርሱ የሚጋጭ ትምህርት ነው

ደራሲው በአንድ በኩል ሥጋው «የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ» እንደሆነ ይናገራሉ። ነገር ግን «ሥጋ» የተባለው   በባሕርዩ ፍጡር ወይም ቁስ ሆኖ ግን ፍጡር ያልሆነ ነው አይባልም። የአብ ቃል አካላዊ ሲሆን በባሕርዩ ደግሞ ያልተፈጠረና ዘለዓለማዊ ነው፤ ሥጋን ግን በጊዜ ሂደት ገንዘቡ ያደረገው ስለሆነ የአብ ቃል የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ገንዘቡ ያደረገው ያ ሥጋ የተፈጠረ ነው። የአብን አካላዊ ቃልና ሥጋን በመቀላቀል ለአካላዊ ቃል የተነገረውን ለቁስ ሥጋው አድርጎ ማቅረብ ምድባዊ ሕጸጽ (Categoricall Fallacy) ነው።

ሥጋው «ያልተፈጠረ ነው» የሚለውን ይዘን ብንነሳ እንኳን ሥጋው ጅማሮ የለውም ማለት ነው። ይህ ማለት ሥጋው በሰማይም ይኖር የነበረ፣ ከዚያም ወደ ድንግል ማርያም ማኅፀን የገባ ነው እንድንል ያደርገናል። ይህ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ስህተት ብቻ ሳይሆን አንድ ሰው ስለ የትኛውም ሃይማኖት ምንም ዓይነት ቅድመ-ግንዛቤ (ቅድመ ልባዌ) ሳይኖረው መጽሐፍ ቅዱስን ከፍቶ ማንበብ ቢጀምር እንኳ ሊደርስበት የማይችል ትርጉም አልባ ድምዳሜ ነው። ፍጹም ከተሳሳተ ቅድመ-ግንዛቤ የተፈጠረ አስተምህሮ መሆኑን ከዚህ መረዳት ይቻላል።

5. በታሪክ ከተኮነኑ ጥንታዊ ኑፋቄዎች (Docetism & Apollinarianism) ጋር መመሳሰሉ

ይህ አስተምህሮ በአዲስ መልክ የቀረበ ቢሆንም በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ከተኮነኑት ከ«ዶሴቲዝም» (ክርስቶስ እውነተኛ ሥጋ አልነበረውም፣ ሥጋ ያለው ይመስል ነበር እንጂ የሚል) እና ከ«አፖሊናሪዝም» ትምህርቶች ጋር ሙሉ በሙሉ ተመሳሳይነት አለው። ጥንታዊት ቤተክርስቲያን ክርስቶስ «ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው» እንደሆነና ከድንግል ማርያም የነሳው ሥጋ እውነተኛ የሰው ሥጋ መሆኑን አረጋግጣለች።

ይህንን «የሰማያዊ ሥጋ» ትምህርት በድፍረት «ኑፋቄ» ልንል የምንችልበት ዋናው ምክንያት ደግሞ፣ የጌታ ሐዋርያት እንድንጠነቀቅ ያሳሰቡት ትምህርት በመሆኑ ነው።

«ብዙ አሳቾች ወደ ዓለም ገብተዋልና እነርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የማያምኑ ናቸው፤ ይህ አሳቹና የክርስቶስ ተቃዋሚው ነው።» (2ኛ ዮሐንስ ቁ. 7)

«ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደ መጣ የማይታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ ነው፤ ይህም እንዲመጣ ሰምታችኋል፥ አሁንም እንኳ በዓለም አለ።» (1ኛ ዮሐንስ 4:3)

ሐዋርያት ያስጠነቀቁት መሠረታዊ ስህተት ኢየሱስ «ከድንግል ማርያም እውነተኛ የሰው ሥጋ አልነሳም» የሚሉትን በመሆኑ ቢሾፕ ተክለማርያምም ሆኑ የኢትዮጵያ ሐዋርያት ቤተክርስቲያን በዚህ ትምህርታቸው ምክንያት ኑፋቄን ታቅፈዋል የሚል ድምዳሜ ላይ እንድንደርስ ያደርገናል።

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ ሲታይ የሰማያዊ ሥጋ አስተምህሮ በቋንቋ ሰዋሰው፣ በአመክንዮአዊ ፍሰት፣ በጽሑፋዊ አውድና በሥነ-መለኮታዊ መሠረት ላይ ትልቅ ህጸጽ ያለበት ትምህርት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እንደሚያስተምረው ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውን ለማዳን ሲል እውነተኛ የሰው ሥጋን ከድንግል ማርያም ነስቶ ሰው ሆኗል (ዮሐ 1:14፤ ዕብ 2:14)። የክርስቶስን እውነተኛ የሰውነት ባሕርይ የሚያቃልል ወይም «ሥጋው ከሰማይ የመጣ ነው» የሚል ማንኛውም ትምህርት በሐዋርያት የተኮነነና የክርስቶስን የማዳን ሥራ የሚያፈርስ በመሆኑ በጽኑ ሊወገዝ የሚገባው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ አስተምህሮ ነው።


መልስ ለሰባልዮሳውያን