የእስላማዊ ስነ-ፅንስ ተረክ በዘመናዊ ሳይንስ መነፅር [ክፍል አንድ]

የእስላማዊ ስነ-ፅንስ ተረክ በዘመናዊ ሳይንስ መነፅር [ክፍል አንድ]

ዶ/ር ሻሎም መኮንን


ሙስሊም ሰባክያን እስልምና መለኮታዊ ሃይማኖት ስለመሆኑ አስረጂያችን ብለው ከሚያነሷቸው ግንባር ቀደም ሙግቶች መካከል አንዱ ፅንስን በተመለከተ በቁርአን ውስጥ የተነገረው ነው። “በሰባተኛው ክፍለዘመን እስላማዊ መዛግብት ላይ የሰፈረውን የፅንስ አስተዳደግ ተረክ አሁን በ21ው ክፍለዘመን ሳይንስ በረቀቁ ቴክሎጂዎች ታግዞ እውነት መሆኑን አረጋግጧል፤ ይህም እስልምና መለኮታዊ ሃይማኖት መሆኑን ያረጋግጣል” የሚል ስብከት የሳዑዲ ንጉሣዊ ቤተሰብ የግል ኃኪም ከነበረው ከመውሪስ ቡካይሌ መነሳት ወዲህ ከእስልምና ሰባክያን አንደበት የማይጠፋ የተለመደ ስብከት ሆኗል። ነገር ግን ይህ ሙግት እንደ ማስረጃ ከመቅረቡ በፊት በፊት “እውን በቁርአን ላይ የሰፈሩት የፅንስ አስተዳደግ ተረኮች ከእስልምና በፊት እንዲሁም በእስልምና ምሥረታ ወቅት አይታወቁም ነበርን?” የሚል ጥያቄ ቀዳሚ መሆን ነበረበት። እስላማዊ መዛግብት ላይ የሰፈሩት የፅንስ አስተዳደግ ተረኮች በወቅቱ የሚታወቁ ከነበሩ የሙስሊም ሰባኪያን ሙግት ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም። ለዚህ ጥያቄ ግልፅ እና አጭር መልስ “አዎን በሚገባ ነበሩ” የሚል ነው።

እነዚህ ተረኮች የትም ያልነበሩ ናቸው ብንል እንኳን የኢስልምና መዛግብት ያቀረቡት የፅንስ እድገት ሀተታ ፈፅሞ ስህተት ሆኖ ስለምናገኘው የኢስልምና መለኮታዊነት ማስረጃ ሳይሆን ኢስልምናን መለኮታዊ ሃይማኖት ላለመሆኑ አስረጅ ይሆናል። ቁርአን እንዲህ ይላል:-

የፈጠረ አምላክ እርሱ ዕውቀት ረቂቁ ውስጥ አዋቂው ሲሆን (ሚስጥርን ሁሉ) አያውቅምን? (ሱራ 67:14)።

ይህ የቁርአን ሐሳብ ሁላችንንም ያስማማል። አላህ እውነት ፍጥረታቱን ፈጥሮ ከሆነ በዚህ በዚህ መልኩ ፈጠርኩኝ የሚለው ንግግሩ ስህተት መሆን የለበትም። ስህተት ከሆነ ያሉን ሁለት አማራጮች ብቻ ናቸው እነርሱም “አላህ አልፈጠረም” ወይንም “በእሱ ስም በሀሰት የተነገረ ንግግር ነው” ማለት ነው።

ለሙስሊም ሰባኪያን በጣም ቀሎ ቢታይም ሙያው ውስጥ ላለ ሰው ዘመናዊ ስነ-ፅንስን (modern embryology) ከእስላማዊ የፅንስ አስተዳደግ ትረካ ጋር ለማዛመድ ቀርቶ ጎን ለጎን እያደረጉ ለመተቸት እራሱ በእጅጉ አዳጋች ነው። ለዚህም ዋና ምክንያቱ ከዘመናዊ ስነ-ፅንስ ጥናት ግኝት  ጋር እስላማዊ የስነ-ፅንስ ትረካዎች ሊመሳሰሉ ቀርቶ ጭራሽ ተዛማጅነት እንኳን የሌላቸው በመሆኑ ነው።

በዚህ ፅሁፍ ላይ “ሁለቱንም ትረካዎች ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ ከመሆናቸው የተነሳ በአንድ ላይ አያይዞ ለማቅረብ አዳጋች ስለሆነ” እስላማዊ የስነ-ፅንስ ትረካዎችን በዘመናዊው የስነ-ፅንስ ሳይንስ መነፅር በጥንቃቄ መመርመሩን መርጫለው። እስላማዊ ምላሾችንም ጎን ለጎን እያየን እስላማዊ ድርሳናት ላይ የቀረቡት ትንታኔዎች ከየት ከየት ተቀድተው ሊሆን እንደሚችል አብረን እንመለከታለን። 

እስላማዊ ድርሳናት ስለ ስነ-ፅንስ ጥናት (embryology) ምን ይላሉ?

እንደ እስላማዊ ምንጮች ዘገባ ከሆነ በሆድ ውስጥ የሚደረገውን የፅንስ አስተዳደግ ሂደት ከአላህ ውጪ ማንም ሊያውቀው አይችልም። የዚህ ዕውቀት ብቸኛ ባለቤት የሆነው አላህ በሙሐመድ በኩል ለተከታዮቹ “እውቀቱን” ገልጧል።  ስለዚህ እንደ አላህ ዕውቀት ብቻ ተደርጎ የቀረበውን እስላማዊ የስነ-ፅንስ ተረክን በአንድ “እጃችን” ዘመናዊውን የስነ-ፅንስ ጥናት ግኝትን ደግሞ በሌላኛው “እጃችን” በመያዝ ንፅፅር ለማድረግ እስላማዊ መዛግብት በራቸው የተዘጋ ነው።

ኢብን ዑመር እንደተረከው፦ ነቢዩም እንዲህ አሉ፦ ከአላህ በቀር ማንም የማያውቃቸው የሩቅ ነገር መክፈቻዎች አምስት ናቸው። በማህፀን ውስጥ ምን እንዳለ ከአላህ በቀር ማንም አያውቅም(1)፣ ነገ ምን እንደሚከሰት ከአላህ በቀር ማንም አያውቅም(2)፣ ዝናብ መቼ እንደሚመጣ ከአላህ በቀር ማንም አያውቅም(3)፣ ማንኛይቱም ነፍስ በየትኛው ምድር እንደሞትሞት ከአላህ በቀር ማንም አያውቅም(4)፣ ሰአቲቱ መቼ እንደምትቆም ከአላህ በቀር ማንም አያውቅም።(5)  (ሳሂህ አል-ቡክኻሪ መጽሐፍ 97፣ ሐዲስ 9)

በዚህ እስላማዊ ሐዲስ ላይ በግልፅ እንደሰፈረው ሙሐመድ “ከአላህ በቀር ማንም አያውቃቸውም “የሚላቸውን አምስት የሩቅ ነገር መክፈቻዎች ግልፅ አድርጓል።  በክፍሉ ሙሐመድ የሩቅ ነገር መክፈቻዎች ሲል ከሰዎች የራቁ፣ ሰዎች ሊደርሱባቸው የማይችሏቸው ግን አላህ ብቻ የሚደርስባቸው ምስጢራት እያለ ነው። ከዘረዘራቸው ከአምስቱ ሩቅ መክፈቻዎች (ምስጢራት) ውስጥ በማህፀን ውስጥ ያለው ነገር (የፅንስ እድገት) አንዱ ነው።

በዚህ እስላማዊ መዝገብ ላይ የቀረበው የሙሐመድ ንግግር ማስተባበያ የማይፈልግ ግልፅ ንግግር ነው። ነገር ግን ሙስሊም ወገኖቻችን ከዚህ ስህተት ለመዳን “ስለ-ፅንስ የታወቀው በጥናት እንጂ አላህ ባወቀበት መልኩ አይደለም” የሚል ነጥብ ማንሳታቸው የማይቀር ነው። እኛም “ታድያ ሰዓቲቱ የምትቆምበትን ቀንስ በጥናት ሰዎች ሊደርሱበት ይችላሉ ማለት ነው?” ብለን እንጠይቃቸዋለን። ምክንያቱም የእነዚህ አምስት ነገሮች ዕውቀት ባለቤትነት ለአላህ ብቻ የተሰጠ ሲሆን በተጠቀሰው ዝርዝር ውስጥ የሰዓቲቱ መቆሚያ እና የፅንስ ዕድገት በአንድ ዝርዝር ውስጥ በመካተታቸው ሙስሊም ወገኖቻችን ዝርዝሮቹን ነጣጥለው እንዲመለከቱዋቸው የሚፈቅድ መንገድ የለም። ከሰው ልጅ የራቁ ሚስጥሮች (የሩቅ ነገር መክፈቻዎች) ውስጥ በተጨማሪም የሰው ልጅ የሚሞትበት ስፍራ፣ ነገ ምን እንደሚከሰት፣ ዝናብ መች እንደሚዘንብ አለመታወቃቸው ተካተዋል። ከላይ የሚገኘው ሐዲስ በቁርአን የተደገፈ ነው፦

አላህ የሰዓቲቱ ዕውቀት እርሱ ዘንድ ብቻ ነው፡፡ ዝናብንም ያወርዳል፡፡ በማህጸኖችም ውስጥ ያለን ሁሉ ያውቃል፡፡ ማንኛይቱ ነፍስም ነገ የምትሰራውን አታውቅም፡፡ ማንኛይቱ ነፍስም በየትኛው ምድር እንደምትሞት አታውቅም፡፡ አላህ አዋቂ ፣ ውስጠ አዋቂ ነው። (ሱራ 31፥34 )

ተፍሲር ኢብን ከቲር ይህንን ክፍል እንደሚከተለው ያብራራዋል፡

የሰዓቲቱ ዕውቀት፣ መቼ እንደሚዘንብ እና በማህፀን ውስጥ ያለው ምን መሆኑ አላህ ዘንድ ነው የሚታወቀው። ነገ ምን እንደሚገጥመው፣ የት አገር እንደሚሞት ማንም ሰው አያውቅም። አላህ ውስጠ አዋቂው ነውና። የሩቅ ነገር አዋቂው አላህ ነው። እነዚህ ነገሮች የሩቅ ምስጢሮች ናቸው። አላህ ካላሳወቀው በቀር እነዚህን የሚያውቅ ማንም የለም። “ቀኒቱ መቼ እንደምትቆም” በየትኛውም ነብይ ሆነ ለአላህ ቅርብ በሆነ መልአክ አይታወቅም።

ኢብን ከቲርም ተመሳሳይ ነገር ነው የሚለን። በቁርአን የተጠቀሱትን አምስት ነገሮች ከራሱ ከአላህ እና አላህ ካላሳወቀው በቀር የሚያውቀው የለም።

ሙስሊም ወገኖቻችን “አላህ ካሳወቀው በቀር” የሚለውን ሐርግ በመያዝ  “ለተመራማሪዎች የቁርአንን ልከኝነት ለማረጋገጥ አሳወቃቸው” የሚል መውጫ ቀዳዳ ማዘጋጀታቸው አይቀርም።

ይሁን እንጂ ኢብን ከቲርን በጥንቃቄ ስንመለከተው እንዲህ ይለናል።

መቼ እንደሚዘንብ ከአላህ ውጭ ማንም አያውቅም። ነገር ግን አላህ ትእዛዝን ሲሰጥ ዝናብን የሚያዘንቡ መላእክት መቼ እንደሚዘንብ ያውቃሉ። በዚህም መልኩ በፍጥረቱ ውስጥ ያሉ እርሱ ሲፈቅድ ያውቃሉ። እርሱ ብበቸኝነት በማህፀን ውስጥ የሚፈጥረውን ያውቃል። ነገር ግን ወንድ ይሁን ሴት የተባረከ ይሁን የተረገመ እርሱ ሲያዝ ይህን የሚፅፉ መላእክት ያውቃሉ። እንዲሁም ከፍጥረቱ እርሱ የሚፈቅድላቸው ያውቃሉ። ነገ ምን እንደሚገጥመው ይሁን በዚህ ዓለም ከሞትም በኋላ ምን እንደሚገጥመው ማንም አያውቅም።

ክፍሉን በሚገባ ካስተዋልን ፍጡራን ሊያውቁ ይችላሉ ሲባል በተፈለገው ሥራ ላይ ስለተሳተፉ መላእክት እንጂ በእራሳቸው መንገድ ተመራምረው ስላወቁ ተመራማሪዎች አይደለም። በእስልምና እምነት ዝናብን የሚያዘንቡት መላእክት በመሆናቸው አላህ ” ዝናብ አዝንቡ” ሲል ሥራቸው ስለሆነ ሲዘንብ በአላህ ፍቃድ ማወቃቸው አይቀርም። ይህም በራሱ ሌላ ስህተት ነው። የሰው ልጆች በሚትዮሮሎጂ ዕውቀት ዝናብ መች እንደሚዘንብ ከማወቅ አልፈው ቴክኖሎጂን ተጠቅመው ዝናብ ማዝነብና ማቆም መቻላቸውን እናስታውስ። በዚህ ሐዲስ ላይ የሚነሱ መሰል ጥያቄዎች ቢኖሩም ከርዕሳችን አንፃር እናልፋቸዋለን።

አላህ ለመልእክተኛ እንጂ በእራሱ መንገድ ለሚመራመር ሰው “በብቸኝነት ያውቃል የተባለውን የሩቅ ነገር ሚስጥር “አይገልጥም። ቁርአን እንዲህ ይላል፦

እርሱ ሩቁን ሚስጥር አዋቂ ነው። በሚስጥሩም ላይ አንድንም አያሳውቅም ከመልእክተኛ ለወደደው ቢሆን እንጂ ( ለሌላ አይገልፅም ) እርሱም ከበስተፊቱም ከበስተኋላውም ጠባቂ ያደርግለታል።( ሱራ 72:25-27)

እንደ እስልምና መዛግብት ከቁርአን ውጪ ያለ፣ ከአላህ ግልጠተ መለኮት ውጪ የሆነ የስነ-ፅንስ ጥናት በእስልምና ተቀባይነት የላቸውም። እንግዲህ የሙስሊም አቃቤያውያን በፅንስ እድገት ዙርያ ሁለት ከባድ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል። የመጀመሪያው መዛግብቶቻቸውን አክብረው “የስነ-ፅንስን ዕውቀት የአላህ ብቻ ዕውቀት ነው” እንዳይሉ በተጨባጭ መልኩ መታወቁ፤ ሌላው በእስልምና መዛግብት የቀረበው ተረክ በዘመን አመጣሽ መሳርያዎች ከተደረሰበት ተጨባጭ የስነ-ፅንስ ጥናት ዕውቀት ጋር በተቃርኖ መቆማቸው የማይወጧቸው ሁለት አጣብቂኞች ሆነዋል።

 እንግዲህ የሙስሊም አቃቤያን እነዚህን አጣብቂኞች እንወጣበታለን ያሉት መውጫ መንገድ የቁርአንን ቃላት “ቀደም ባልነበሩ በአዳዲስ ትርጉሞች መተካት” እንዲሁም በተኳቸው አዳዲስ ትርጉሞች ሳይንስ አስቀመጣቸው ከሚባሉት ቅደም ተከተሎች ውስጥ በመግባት” እዚህ እና እዚያ” በመርገጥ በቂ ዕውቀት የሌላቸውን ሰዎች ማወናበድ ነው።

ለዚህም አገልግሎት ይውልላቸው ዘንድ አዲስ እስላማዊ የስነ-ፅንስ አቀራረብ መፈልሰፍ አስፈልጓቸዋል። የኑጥፋህ ደረጃ ፣ የአምሻጅ ደረጃ፣ የአለቃህ ደረጃ ፣ የሙድጋህ ደረጃ፣ …ወዘተ.።

ይቀጥላል…

ቁርኣን