1ዮሐንስ 5፡20 ላይ ኢየሱስ “እውነተኛ አምላክ” አልተባለምን? የዳንኤል ዋላስ ማብራርያ

1ዮሐንስ 5፡20 ላይ ኢየሱስ “እውነተኛ አምላክ” አልተባለምን?


ይህ አጭር ጽሑፍ በዶ/ር ዳንኤል ቢ. ዋላስ (Dr. Daniel B. Wallace) ከተጻፈውና እ.ኤ.አ. በ1996 ከታተመው Greek Grammar Beyond the Basics: An Exegetical Syntax of the New Testament ገጽ 326-327 የተወሰደ ነው።

1 ዮሐንስ 5:20 “የእግዚአብሔርም ልጅ እንደ መጣ፥ እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እውነተኛም በሆነው በእርሱ አለን፥ እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው።

ግሪክ፡- “ሁቶስ ኤስቲን ሆ አሌቲኖስ ቴዎስ ካይ ዞዌ አዮንዮስ”

ይህ ጥቅስ በተለያዩ ምክንያቶች ከሥነ-አተረጓጎም አንጻር አከራካሪ ሆኗል። እዚህ ላይ አሳሳቢው ነገር “እርሱ” (ሁቶስ) የሚለው ተውላጠ ስም የሚያመለክተው ማንን ነው የሚለው ነው። ምንም እንኳን “ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ” የሚለው ለተውላጠ ስሙ የቀረበ ቢሆንም፣ ብዙ ሊቃውንት ግን “እግዚአብሔር አብን” ሊያመለክት ይችላል ይላሉ። ለምሳሌ ዊነር (Winer) የተሰኘ ምሑር ሲሞግት፦ “በመጀመሪያ ደረጃ፣ ‘እውነተኛ አምላክ’ የሚለው መጠሪያ ዘወትር በብቸኝነት አብን ለመግለጥ ጥቅም ላይ የሚውል ነው፤ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፣ ጥቅሱን ተከትሎ ከጣዖት አምልኮ የሚያስጠነቅቅ ማሳሰቢያ ይገኛል፣ ‘እውነተኛ አምላክ’ ደግሞ ሁልጊዜ ከጣዖታት ጋር የሚነጻጸር ነው” ይላል።

ነገር ግን “ክርስቶስ” የተውላጠ ስሙ መነሻ (antecedent) ነው የሚለውን አቋም ለመደገፍ የሚቀርቡት መከራከሪያዎች የሚከተሉት ናቸው፦

  1. እውነተኛ አምላክ የሚለው መጠሪያ በሌላ ስፍራ ለክርስቶስ ጥቅም ላይ ባይውልም “እውነት” (አሌቲያ) የሚለው ግን በዮሐንስ ጽሑፎች ውስጥ ተሰጥቶታል (ዮሐ 14:6)። በተጨማሪም፣ ዊነር እንደሚለው “እውነተኛ አምላክ” የሚለው ሐረግ የተደጋገመ መጠሪያ አይደለም፤ ምክንያቱም የሚገኘው በዮሐንስ 17:3 እና በ1ዮሐንስ 5:20 ላይ ብቻ ነውና!
  2. በዮሐንስ ጽሑፎች ውስጥ ክርስቶስ ሕይወት (ዞዌ) ተብሎም ተጠርቷል (ዮሐ 11:25፤ 14:6፤ 1 ዮሐ 1:1-2)፤ ይህ መጠሪያ ደግሞ በአንድም ስፍራ ለአብ አልተሰጠም።
  3. “እርሱ” (ሁቶስ) የሚለው አመልካች ተውላጠ ስም በዮሐንስ ወንጌልና መልእክታት ውስጥ ጥልቅ የሆነ ሥነ-መለኮታዊ ትርጉም ያዘለ ይመስላል። በተለይም ሁቶስ” ሰውን ለማመልከት ከገባባቸው ወደ 70 ከሚጠጉ አጋጣሚዎች መካከል እስከ 44 የሚደርሱቱ (ወደ ሁለት ሦስተኛው የሚጠጋ) የሚያመለክቱት ወልድን ነው። ከተቀሩት ውስጥ አብዛኞቹ ከወልድ ጋር የሆነ ዓይነት ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ናቸው። ከሁሉ በላይ ትኩረት የሚስበው ደግሞ ተውላጠ ስሙ በምንም ዓይነት ሁኔታ አብን ለማመልከት አለመግባቱ ነው። ይህ መረጃ በ1ዮሐንስ 5:20 ላይ “እርሱ” ተብሎ የተጠቀሰው  “ኢየሱስ ክርስቶስ” የመሆኑን ዕድል በእጅጉ ይጨምረዋል።

ጉዳዩ በሰዋስው ብቻ የሚወሰን ባይሆንም፣ “እውነተኛ አምላክ” የሚለው ገለጻ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመግለጥ መግባቱን የሚያግድ ምንም ዓይነት የሰዋስው ምክንያት እንደሌለ መናገሩ እዚህ ላይ በቂ ነው።


መሲሁ ኢየሱስ