እውን የወንጌላት ጸሐፊያን አይታወቁምን?
በወንድም በረከት ጌትነት
የወንጌላት ጸሐፊያን በውል እንደማይታወቁና መጻሕፍቱ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች (Anonymous) እንደተጻፉ ከሙስሊም አቃብያነ እምነት ዘንድ ደጋግሞ መስማት የተለመደ ነው። ይህ ግምት ላይ የተመሰረተ ሙግት ከምዕራባውያን ለዘብተኛ ሊቃውንት (Liberal Scholars) የመነጨ ሲሆን[1] ከማስረጃ አልባነቱም በላይ የወንጌላትን ታሪካዊና የጽሑፍ አመጣጥ (Textual History) ፍጹም የሚቃረን ነው። በአንጻሩ አራቱ ወንጌላት በማቴዎስ፣ በማርቆስ፣ በሉቃስና በዮሐንስ ለመጻፋቸው አያሌ ታሪካዊና ምክንያታዊ ማስረጃዎች አሉ።
ወንጌላቱ በትውፊት በተጠቀሱት ጸሐፊያን አልተጻፉም የሚለውን መላምት ውድቅ የሚያደርጉትን ዋና ዋና ነጥቦች እንደሚከተለው መመልከት ይቻላል፦
- የጥንታውያን እደ–ክታባት (Manuscripts) ምስክርነት
ለዘብተኛ ምሁራን ለሚያነሱት “የማንነት መደበቅ” (Anonymity) መላምት ትልቁና ዋነኛው ፈተና የጸሐፊ ስም የሌለበት አንድም የወንጌል ቅጂ አለመገኘቱ ነው። የአዲስ ኪዳን ምሁሩ ብራንት ፒትሪ ይህንን ሲያስረዱ እንዲህ ይላሉ፦
“የወንጌላት ጸሐፊያን ማንነታቸው አይታወቅም ለሚለው መላምት የመጀመሪያውና ምናልባትም ትልቁ ችግር ይህ ነው፦ የማቴዎስ፣ የማርቆስ፣ የሉቃስ ወይም የዮሐንስ ወንጌል ሆኖ ስም የሌለበት አንድም ቅጂ እስካሁን አልተገኘም። የሉም፤ እስከምናውቀው ድረስ ደግሞ ኖረውም አያውቁም።”[2]
በ1ኛው ክፍለ ዘመን የጸሐፊ ስም ሳይኖርበት የሚዘዋወር ጽሑፍ ያልተለመደ ከመሆኑም በላይ ከመጀመሪያው ጸሐፊው ሳይታወቅ የተሰራጨን አንድ ጽሑፍ ከዓመታት በኋላ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ሰዎች በተመሳሳይ ስም ሊሰይሙት አይችሉም። ሌሎች ደራሲያቸው እንደማይታወቅ ከሚነገርላቸው ጥንታውያን መጻሕፍት በተለየ በአራቱ ወንጌላት እደ-ክታባት ላይ ምንም ዓይነት የስም መለዋወጥ ልዩነት አይታይም። ይህ የሚያሳየው ወንጌላት ከመነሻቸው የጸሐፊዎቻቸውን ስም ይዘው እንደነበር ነው። የታወቁት የአዲስ ኪዳን ሊቃውንት ዲ.ኤ. ካርሰን፣ ዳግላስ ሙ እና ሊዮን ሞሪስ የታላቁን የጀርመን አዲስ ኪዳን ምሁር የማርቲን ሄንገልን (Martin Hengel) ሙግት በመጥቀስ ይህንን ሐሳብ ያጸናሉ።[3] ጽሑፎቹ ቁርጥራጭ ከመሆናቸው የተነሳ የመጀመሪያው ገጽ ካልጠፋ በስተቀር በጥንታውያን ቅጂዎች ላይ ስማቸው በግልጽ ሰፍሯል። ለአብነት ያህል፦
- ፓፒረስ 4 (P4) እና ፓፒረስ 62 (P62) [2ኛው ክፍለ ዘመን]፦ “የማቴዎስ ወንጌል” (The Gospel according to Matthew) የሚል ስያሜ አላቸው።
- ኮዴክስ ሲናይቲከስ እና ቫቲካነስ (Codex Sinaiticus & Vaticanus) [4ኛው ክፍለ ዘመን]፦ “በማቴዎስ”፣ “በማርቆስ” የሚሉትን ስሞች ይዘዋል።
- ፓፒረስ 75 (P75) [ከ2ኛው-3ኛው ክፍለ ዘመን]፦ “የሉቃስ ወንጌል” (The Gospel according to Luke) የሚል ስያሜ ይዟል።
- ፓፒረስ 66 (P66) [2ኛው ክፍለ ዘመን]፦ “የዮሐንስ ወንጌል” የሚል ርዕስ አለው።[4]
- የቤተክርስቲያን አባቶች አንድ ወጥ ስምምነት
የጥንት የቤተክርስቲያን አባቶች የወንጌላቱ ጸሐፊዎች ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ እንደሆኑ በአንድ ድምፅ መስክረዋል። ለምሳሌ ያህል፦
- የሂራፖሊሱ ፓፒያስ (የሐዋርያው ዮሐንስ ደቀመዝሙር የነበረ)[5]
- የሊዮኑ ኢራኒየስ (Irenaeus)[6]
- የእስክንድርያው ቀሌምንጦስ (Clement of Alexandria)[7]
- የቂሳሪያው አውሳቢዮስ (Eusebius)[8]
እነዚህና ሌሎችም ያልተጠቀሱ አባቶች ያለ ምንም ልዩነትና ክርክር የወንጌላቱን ባለቤቶች ለይተው አስቀምጠዋል።
- የውጭ ወገኖችና የተቃዋሚዎች ምስክርነት
የቤተክርስቲያን አባቶች ብቻ ሳይሆኑ በአስገራሚ ሁኔታ የቤተክርስቲያን ተቃዋሚዎችና መናፍቃን ሳይቀሩ የወንጌላቱን ጸሐፊያን ማንነት ይቀበሉ ነበር። ይህንን የሊዮኑ ኢራኒየስ በስፋት ዘግቦታል።[9] በተለይም በ2ኛው ክፍለ ዘመን ክርስትና ላይ በሰነዘረው የትችት ጽሑፍ የሚታወቀው አረማዊው ፈላስፋ ሴልሰስ (Celsus) ሲሞግት፦ “የኢየሱስ ደቀመዛሙርት የእርሱን እውነተኛነት ለማሳየት ኢየሱስ የወደፊቱን ነገር አስቀድሞ እንደሚያውቅ አድርገው ጻፉ“ በማለት ይከራከራል።[10] ሴልሰስ እዚህ ላይ የጽሑፎቹን ባለቤትነት ከማጣጣል ይልቅ ራሳቸውን ጸሐፊዎቹን (ደቀመዛሙርቱን) ነው ለመንቀፍ የሞከረው። ይህ የሚያሳየው የጥንት የክርስትና ተቃዋሚዎች እንኳ ወንጌላት በደቀመዛሙርቱና በባልደረቦቻቸው እንደተጻፉ ያውቁ እንደነበር እንጂ ጸሐፊያቸው እንደማይታወቅ አድርገው አያስቡም ነበር። መጻሕፍቱ ማንነቱ ባልታወቀ ሰው የተጻፉ ቢሆን ኖሮ ይህ ተቺ ፈላስፋ ቀድሞ የሚያጠቃውና የሚያጣጥለው የወንጌላቱን ባለቤትነት እንጂ ራሳቸውን ደቀመዛሙርቱን ባልሆነ ነበር።
- የስርጭት አመክንዮ
ነገሩ ለዘብተኛ ሊቃውንት እንደሚሉት ቢሆንና ወንጌላት መጀመሪያ ሲጻፉ የጸሐፊያቸውን ስም ሳይዙ በነጻነት ተሰራጭተው ቢሆን ኖሮ የሚከተለው ክስተት መፈጠሩ ፍጹም የማይቀርና ምክንያታዊ ነበር፦
ወንጌላቱ ከተጻፉ በኋላ ወደ ተለያዩ የሮም ግዛት አካባቢዎች (ለምሳሌ፦ ወደ ሮም፣ ኢየሩሳሌም፣ አንጾኪያ፣ እስክንድርያ፣ ቀጰዶቅያ፣ ኤፌሶን) ለአገልግሎት ይሰራጫሉ፤ በዚያም አንዱ ከሌላው እየገለበጠ ያባዛዋል። መጻሕፍቱ መጀመሪያ ላይ ስም የሌላቸው ቢሆን ኖሮ እያንዳንዱ አካባቢ ያለው ማኅበረሰብ እንደየራሱ ግምት የተለያየ ስም ይሰጣቸው ነበር። በዚህም ምክንያት አንዱ “የጴጥሮስ ወንጌል” ሲለው፣ ሌላው “የበርናባስ”፣ ሌላው ደግሞ “የበርተሎሜዎስ” ወይም “የይሁዳ” እያለ የተደበላለቀና የተጻረረ የስም ዝርዝር ሊኖረን ይገባ ነበር።
ለዚህ ግልጽ ምሳሌ የሚሆነን የዕብራውያን መልእክት ነው። ጸሐፊው በጽሑፉ ላይ ስሙን ስላልጠቀሰ በጥንታውያን እደ-ክታባት ላይ አንዱ የጳውሎስ ዝርዝር ውስጥ ሲያስገባው ሌላው ደግሞ ሲያስወጣው የቤተክርስቲያን አባቶችም በጸሐፊው ማንነት ዙሪያ ሲከራከሩና የተለያየ ግምት ሲሰጡ እንሰማቸዋለን። ይህ ጸሐፊው ሳይጠቀስ ለቀረ ጽሑፍ የሚሆን ፍጹም ተፈጥሯዊና ምክንያታዊ መደምደሚያ ነው።
በአንጻሩ ግን በአራቱም ወንጌላት ላይ እንዲህ ዓይነት ግራ መጋባት ፈጽሞ አልተከሰተም። ሁሉም ጥንታውያን እደ-ክታባትና ቁርጥራጮች አንድ ወጥ በሆነ መልኩ የማቴዎስን፣ የማርቆስን፣ የሉቃስንና የዮሐንስን ስም ይዘዋል። አባቶችም ያለ ምንም ክርክርና ውዝግብ እነዚህን ጸሐፊያን ተቀብለዋል። ይህም ወንጌላት ገና ከመነሻቸው ጸሐፊዎቻቸው ታውቀው የተሰራጩ መሆናቸውን የማይናወጥ ታሪካዊ እውነት ያደርገዋል።
ማጣቀሻዎች
[1] Bart D. Ehrman, Jesus, Interrupted: Revealing the Hidden Contradictions in the Bible (New York: HarperOne, 2009), p. 103.
[2] Brant Pitre, The Case for Jesus: The Biblical and Historical Evidence for Christ (New York: Image Books, 2016), p. 19.
[3] D. A. Carson, Douglas J. Moo, and Leon Morris, An Introduction to the New Testament (Grand Rapids, MI: Zondervan, 1992), p. 60. (See also Martin Hengel, “Studies in the Gospel of Mark”).
[4] Bruce M. Metzger and Bart D. Ehrman, The Text of the New Testament: Its Transmission, Corruption, and Restoration, 4th ed. (New York: Oxford University Press, 2005), pp. 56–92; see also Pitre, The Case for Jesus, p. 20.
[5] Eusebius, Church History, 3.39.16.
[6] Eusebius, Church History, 5.8.3; see also Irenaeus, Against Heresies, Book III, Chapter 1, Section 1.
[7] Eusebius, Church History, 6.14.5–7 (Note: 3.39.16 is specifically for Papias, Clement’s account on the Gospels’ order is preserved in Book 6).
[8] Eusebius, Church History, 2.15.1–2.
[9] Irenaeus, Against Heresies, Book III, Chapter 11, Section 7.
[10] Origen, Contra Celsum (Against Celsus), Book II, Section 15.
