ኢሳይያስ 9፥6 እና የኦንሊ ጂሰስ (Oneness) አስተምህሮ
የኦንሊ ጂሰስ ትምህርት አራማጆች ትንቢተ ኢሳይያስ 9፥6ን እንደ ዋነኛ መከራከሪያ በመጠቀም “ወልድ ራሱ አብ ነው” የሚል ድምዳሜ ላይ ይደርሳሉ። ሆኖም ይህ ትርጓሜ የቅዱሳት መጻሕፍትን አውድ፣ የዕብራይስጥን ሥነ-ልሳን ዘይቤንና የነገረ-መለኮትን መሠረታዊ መርሆች የሳተ ነው።
1. የ“አቢ–አድ” (Abi-ad) ሥነ–ልሳናዊ ትንታኔ
በዕብራይስጥ “የዘላለም አባት” የሚለው ሐረግ አቢ–አድ (אֲבִיעַד) ተብሎ ይነበባል። በሴማዊ ቋንቋዎች ጥናት (Semitic Philology) “አባት” (Ab) የሚለው ቃል መጠሪያነት የግዴታ ወላጅነትን (Paternity) አይገልጽም። ይልቁንም የአንድ ነገር “ምንጭ”፣ “ባለቤት” ወይም “አምራች” ለሆነ አካል የሚሰጥ የክብር ስም ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “አብ” (Ab/Abi) የሚለው ቅጥያ ከሌሎች ቃላት ጋር ተጫፍሮ ሲመጣ የግድ ወላጅነትን ወይም አካላዊ ማንነትን (Ontological Identity) አይወክልም። ይልቁንም የስሙ ባለቤት ያለውን ባሕርይ ወይም ምንጭነት የሚያመለክት ዘይቤያዊ አገላለጽ ነው።
ለዚህም የሚከተሉት ስሞች በቂ ማስረጃዎች ናቸው፦
- አቤሴሎም/አቢሳሎም (Absalom): “የሰላም አባት” ማለት ሲሆን፣ ትርጉሙም “የሰላም ባለቤት” ወይም “ሰላማዊ” ማለት እንጂ እርሱ ራሱ የሰላም ወላጅ ነው ማለት አይደለም።
- አበኔር/አቢኔር (Abner): “የብርሃን አባት”፤ ይህም ብርሃን ያለው ወይም የብርሃን ምንጭ ማለት ነው።
- አቤሜሌክ/አቢሜሌክ (Abimelech): “አባቴ ንጉሥ ነው” ወይም “የንጉሥ አባት”፤ ይህም የሥልጣንና የክብር መገለጫ ነው።
- አቢግያ/አቢጋኤል (Abigail): “የደስታ አባት” ወይም “የደስታ ምንጭ” ማለት ነው።
በኢሳይያስ 9፥6 ላይ ክርስቶስ “የዘላለም አባት” (Abi-ad) መባሉ፣ ከላይ ከተጠቀሱት የመጽሐፍ ቅዱስ ስሞች አወቃቀር ጋር ፍጹም የተጣጣመ ነው። ከላይ እንደሚታየው አቢ የሚለው “አባት” ተብሎ የሚተረጎመው ቃል ከሌሎች ቃላት ጋር ተያይዞ ሲመጣ አባት መሆንን በጭራሽ አያሳይም። አቢጋኤል የሚለው ስም የሴት መጠርያ ቢሆንም አባት የሚለውን ቃል በውስጡ ይዟል። ይህ ማለት ተጠሪዋ አባት ናት ማለ ግን አይደለም። አቤሴሎም “የሰላም ባለቤት” እንደሚባለው ሁሉ፣ ክርስቶስም “የዘላለም ባለቤት/ምንጭ” በመሆኑ “የዘላለም አባት” ተባለ እንጂ የኢየሱስ አባት ራሱ ኢየሱስ ነው ለማለት ተፈልጎ አይደለም። እንዲህ ያለ መረዳት መጽሐፍ ቅዱስን አንብቦ ከሚያውቅ ሰው የሚጠበቅ አይደለም። እግዚአብሔር የሰጠንን ማስተዋል ካለመጠቀም የሚመነጭ ስሁት ድምዳሜ ነው።
ይህ ሥነ-ልሳናዊ እውነታ “አባት” የሚለው ቃል በትንቢቱ ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለው የክርስቶስን የዘላለም ባለቤትነት (Mastery over Eternity) ለመግለጥ እንጂ እርሱ “አብ” የተባለው አካል ነው ለማለት እንዳልሆነ በቂና የማያዳግም ማስረጃ ይሆናል።
2. በስሞቹ መካከል ያለው ትይዩነት (Parallelism)
በዚያው ጥቅስ ላይ “ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የሰላም አለቃ” የሚሉ ሌሎች መጠሪያዎችም ይገኛሉ። “የሰላም አለቃ” የሚለው ቃል ክርስቶስን የሰላም ምንጭ እንደሚያደርገው ሁሉ፣ “የዘላለም አባት” የሚለውም የዘላለም ምንጭ እንደሆነ ያመለክታል። “ኃያል አምላክ” የሚለው መጠሪያ ክርስቶስ ከአብ ጋር በባሕርይ (Essence/Ousia) አንድ መሆኑን ሲያረጋግጥ፣ “የዘላለም አባት” የሚለው ደግሞ በሥራው (Functional role) የጊዜ ፈጣሪና ባለቤት መሆኑን ያሳያል።
3. የአብና የወልድ የማንነት ልዩነት በትምህርተ ድኂን (Soteriology) ውስጥ አስፈላጊ ነው
የኦንሊ ጂሰስ ትምህርት “አብ ራሱ ሥጋ ለብሶ መጣ” የሚል ከሆነ የክርስቶስ የቤዝዎት ሥራ ትርጉም ያጣል። በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መሠረት ወልድ ራሱን ለአብ መሥዋዕት አድርጎ አቅርቧል (ዕብ 9፥14)። አቅራቢው (ወልድ) እና ተቀባዩ (አብ) አንድ ማንነት ከሆኑ፣ መሥዋዕትነቱ በራሱ ላይ የተከናወነ ድራማ ይሆናል። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ “ወልድን የላከው አብ ነው” በማለት በላኪና በተላኪ መካከል ያለውን አካላዊ ልዩነት (Hypostatic Distinction) በግልጽ ያስቀምጣል። ኢሳይያስ 9፥6 ላይ “ሕፃን ተወልዶልናል” ሲል የሥጋዌን ምስጢር (the mystery of incarnation)፣ “ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል” ሲል ደግሞ ከአብ ዘንድ መሰጠቱን ያሳያል። ተሰጪው (ወልድ) እና ሰጪው (አብ) የተለያዩ አካላት መሆናቸው የተገለጠ ነው።
በልደት ወደዚህ ዓለም የገባው አብ ራሱ ነው ከተባለ እንግዲያውስ በሥጋ የሞተልንም አብ ነው ልንል ነው። ነገር ግን በመስቀል ላይ የሞተው አብ ሳይሆን በሥጋ የተገለጠው ወልድ ነው። አብ ሞቷል የሚለው ትምህርት “ፓትሪፓሺያኒዝም” (Patripassianism) በሚል የሚታወቅ ሲሆን በጥንቷ ቤተክርስቲያን የተወገዘ ስህተት ነው። መዳን የተገኘው ወልድ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ለአብ በማቅረቡ ነው። ከዚህ በተጻራሪ የሚያስተምር ትምህርት በቃለ እግዚአብሔርም በታሪክም ውድቅ የሆነ ስሁት አስተምህሮ ነው።
ማጠቃለያ
ትንቢተ ኢሳይያስ 9፥6 የክርስቶስን ፍጹም መለኮታዊነት (Ontological Deity) የሚያረጋግጥ እንጂ፣ አካላዊ ማንነቱን ከአብ ጋር የሚቀላቅል አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ የአብ “ልጅ” እንጂ “አብ” አይደለም። እርሱ የዘላለም ባለቤት በመሆኑ “የዘላለም አባት” ተባለ፤ ነገር ግን በአሓዱ ሥሉስ ውስጥ ለዘላለም “ወልድ” ሆኖ ይኖራል። የኦንሊ ጂሰስ ትምህርት ይህንን ምስጢር ባለመረዳት የአምላክን አካላዊ ህልውና ወደ ነጠላነት በመጠቅለል የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የሚጻረር የሐሰት ትምህርት ነው።
