አብያታር ወይስ አቢሜሌክ? በማርቆስ 2፡26 ላይ ለሚነሳው ጥያቄ ምላሽ
መጽሐፍ ቅዱስን ለማጣጣል የሚተጉ ወገኖችና ለዘብተኛ ምሑራን በማርቆስ 2፡26 ላይ የሚገኘውን አገላለጽ እንደ ትልቅ “የታሪክ ስህተት” እና “የታሪክ ዘመን መሳከር” (Anachronism) በመጥቀስ ትችት ሲሰነዝሩ እንሰማለን። 1ሳሙኤል 21 ላይ ዳዊት ወደ ኖብ ሄዶ የተቀደሰውን ኅብስት የተቀበለው ከካህኑ አቢሜሌክ እጅ እንደሆነ በግልጽ ተጽፎ ሳለ ማርቆስ ግን ታሪኩን ሲጠቅስ “አብያታር ሊቀ ካህናት በነበረ ጊዜ” ማለቱ የታሪክ ግጭት ነው ይላሉ። ሒሱን የሚያቀርቡት ወገኖች “ማርቆስ አባትና ልጅ የሆኑትን አቢሜሌክና አብያታርን አውቆ ይሁን ተሳስቶ ቀያይሯቸዋል” በማለት የወንጌላዊውንና የጌታን ቃል ተዓማኒነት ለመሸርሸር ይሞክራሉ። ሆኖም ይህ ዓይነቱ ክስ በጥልቀት ላልመረመረው ሰው አሳማኝ ቢመስልም በጥንት የታሪክ አጻጻፍ ልማድ፣ በጽርእ ቋንቋ ሰዋስው አጠቃቀምና በወቅቱ በነበረው የአይሁድ የትርጓሜ ስልት (Hermeneutics) ሚዛን ሲመዘን መሠረት ቢስ መሆኑን እንረዳለን።
- የ“ኤፒ” (ἐπὶ) እና የባለቤት ቅጥያ (Genitive Case) ትስስር
በግሪክ ቋንቋ ἐπὶ የሚለው መስተዋድድ ከባለቤት ቅጥያ (Genitive) ጋር ሲመጣ ትርጉሙ “በ… ዘመን” ወይም “በ… ጊዜ” የሚል ሰፊ የጊዜ አውድን ይይዛል። ለዚህ ነው የአዲሱ መደበኛ ትርጉም አዘጋጆች “በሊቀ ካህናቱ በአብያታር ዘመን” በማለት የተረጎሙት። ዳንኤል ዋላስ የተሰኙ የታወቁ የግሪክ ሰዋስው ምሑር እንደገለጹት ይህ አወቃቀር የግድ አንድ ድርጊት የተፈጸመበትን ትክክለኛ ሰዓት ወይም ግለሰቡ በሥልጣን ላይ የነበረበትን ወቅት ብቻ አያመለክትም። እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦
“…አምስተኛውን አመለካከት በተመለከተ፣ በአሁኑ ወቅት የእኔ ምርጫ በመስተዋድድ ላይ የተመሠረተውን ሐረግ ‘በሊቀ ካህናቱ በአብያታር ዘመን‘ የሚል ትርጉም እንዲኖረው አድርጎ መውሰድ ነው። ምንም እንኳ ማርቆስ ይህንን መስተዋድድ (ἐπὶ) ሌላ ቦታ ላይ ለጊዜ አመላካችነት ሲጠቀምበት ባይታይም፣ በዚህ ጥቅስ ላይ ግን በዚህ መንገድ መጠቀሙ ወደ ሙሉ እርግጠኛነት የቀረበ ነው፤ ምክንያቱም ‘አብያታር ሊቀ ካህናት በነበረበት ጊዜ‘ እና ‘በሊቀ ካህናቱ በአብያታር ዘመን‘ የሚሉት ሁለቱም አገላለጾች የጊዜ መግለጫዎች (temporal expressions) ናቸውና። በተጨማሪም፣ ἐπὶ + ባለቤት አመላካች ስም (genitive noun) የሆነው ሰዋሰዋዊ አወቃቀር ከማርቆስ ወንጌል ውጭ በሰፊው ለጊዜ አመላካችነት ያገለግላል፤ ትርጉሙም ‘በ… ዘመን‘ ከሚለው ጋር ተመሳሳይ ነው። የባወር መዝገበ ቃላት (BDAG) ይህንኑ የἐπὶ እና የባለቤት ቅጥያ ጥምረት ለጊዜ አመላካችነት (‘በ… ዘመን’ ወይም ‘በ… የግዛት ዘመን’) በሚል አገባብ ጥቅም ላይ የዋለባቸውን በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስና የጥንት አባቶች (patristic) ጥቅሶችን ዘርዝሯል። ለምሳሌ፦ ሉቃስ 4፡27 (‘በነቢዩ በኤልሳዕ ዘመን‘)፣ ሉቃስ 3፡2 (‘በሊቀ ካህናቱ በሐናና በቀያፋ ዘመን‘) እና ማርቆስ 2፡26ን (‘በሊቀ ካህናቱ በአብያታር ዘመን‘) መጥቀስ ይቻላል…” (Daniel B. Wallace, “Mark 2:26 and the Problem of Abiathar,” accessed March 23, 2026, https://bible.org/article/mark-226-and-problem-abiathar)
ከላይ ከቀረቡት ናሙናዎች መካከል ሉቃስ 3፡2ን ብንወስድ “ሐናና ቀያፋም ሊቃነ ካህናት ሳሉ” (ἐπὶ ἀρχιερέως Ἅννα καὶ Καϊάφα) የሚል አገላለጽ እናገኛለን። ይህ አገላለጽ ከሰዋሰዋዊ አወቃቀር አኳያ in the time of the high priest, Annas and Caiaphas “በሊቀ ካህናቱ በሐናና በቀያፋ ዘመን” ተብሎ መተርጎም አለበት። በወቅቱ ይፋዊው ሊቀ ካህናት ቀያፋ ቢሆንም ሐና ግን ቀድሞ የነበረና ተሰሚነት ያለው በመሆኑ ከሊቀ ክህነት ቢሻርም ስሙ በጋራ ተጠቅሷል። ማርቆስም የተጠቀመው ይህንኑ የጊዜ አገላለጽ ዘይቤ ነው።
ይህ አገላለጽ በታሪክ ውስጥ እጅግ ታዋቂ በነበረው ሰው ስም ዘመኑን የመሰየም (Eponymous dating) ልማድን የተከተለ ነው። ለምሳሌ ያህል “ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ልጅ ሳሉ፣ ‘ነቢዩ’ ሙሐመድ በተወለዱበት ዓመት፣ ጠቅላይ ምኒስትር አብይ የኢንሳ ኃላፊ ሳሉ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ማትያስ የኢየሩሳሌም ገዳም አስተዳዳሪ ሳሉ፣ ወዘተ.” ቢባል እነዚህ ወገኖች በተጠቀሱበት ማዕርግ በወቅቱ ይታወቁ ነበር ማለት አይደለም። በተመሳሳይ፣ አብያታር ከካህኑ አቢሜሌክ ይልቅ በታሪክ ውስጥ እጅግ የታወቀና ከዳዊት ጋር የረዥም ዘመን ግንኙነት የነበረው ሊቀ ካህናት ነው። ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ ይህን ታሪክ ሲጠቅስ፣ ሰዎቹ በቀላሉ እንዲረዱት በታዋቂውና በዳዊት ዘመን ዋና በነበረው ሊቀ ካህናት (አብያታር) ስም ጠቅሶታል። አቢሜሌክ (የአብያታር አባት) በሳኦል እጅ ከተገደለ በኋላ ብቸኛው በሕይወት የተረፈ ልጅ ነበረ። አብያታር ኤፉዱን ይዞ ወደ ዳዊት በመኮብለል በዳዊት የስደት ዘመን ሁሉ አብሮት የነበረና የዳዊት መንግሥት ዋና ሊቀ ካህናት የሆነ ሰው ነው። አቢሜሌክ በታሪክ ውስጥ የሚታወቀው ለጥቂት ጊዜና ዳዊትን በመርዳቱ ሳብያ ሲገደል ብቻ ነው። አብያታር ግን ለ40 ዓመታት ያህል በሊቀ ካህንነት ያገለገለና በዳዊት ዘመን ለነበረው የክህነት አገልግሎት ዋናው ተወካይ ነበር። ስለዚህ ታሪኩ “በሊቀ ካህናቱ በአብያታር ዘመን” ተብሎ መጠቀሱ ስህተት ሳይሆን የታሪክ አገላለጽ ዘዴ ነው።
- የአንቀጽ (Article) አለመኖር ፋይዳ (Anarthrous Construction)
በማርቆስ 2፡26 ላይ ውሱን መስተአምር (τοῦ) በአብያታርና በሊቀ ካህናት መካከል አልገባም። ጥቅሱ የሚለው ἐπὶ Ἀβιάθαρ ἀρχιερέως (In the time of Abiathar high priest) እንጂ ἐπὶ Ἀβιάθαρ τοῦ ἀρχιερέως (In the time of Abiathar the high priest) አይደለም። ውሱን መስተአምር (τοῦ) ቢኖር ኖሮ አብያታር በዚያች ቅጽበት በሥልጣን ላይ የነበረ መሆኑን ያጠነክረው ነበር። አንቀጹ ባለመኖሩ ግን አገላለጹ ይበልጥ “ገላጭ” (Predicate) ይሆናል። ይህም ማለት “አብያታር በነበረበት በዚያ የታሪክ ምዕራፍ” እንደማለት ነው።
- “ኤፒ” (ἐπὶ) እንደ ምንባብ አመላካች (Locative Sense)
ሌላውና አሳማኝ የሆነው ሰዋሰዋዊ ትንታኔ ἐπὶ የሚለውን ቃል “በ… ክፍል” (In the section of) ብሎ መተርጎም ነው። ማርቆስ በምዕራፍ 12፡26 ላይ ስለ ሙሴና ስለሚነድደው ቁጥቋጦ ሲናገር ἐπὶ τοῦ βάτου (በሙሴ መጽሐፍ በቍጥቋጦው ዘንድ የተጻፈውን አላነበባችሁምን?) የሚል አገላለጽ ተጠቅሟል። ይህንን የአዲሱ መደበኛ ትርጉም አዘጋጆች “በሙሴ መጽሐፍ ይኸውም ስለ ቍጥቋጦው በተነገረው ክፍል” በማለት አስቀምጠውታል። ይህ ማለት ሙሴ ቁጥቋጦው ውስጥ ነበረ ማለት ሳይሆን “ስለ ቁጥቋጦው በሚናገረው የኦሪት ክፍል” ማለት ነው።
በተመሳሳይ ማርቆስ 2፡26 ላይ ἐπὶ Ἀβιάθαρ ἀρχιερέως “በሊቀ ካህናቱ በአብያታር ዘመን” ከማለት ይልቅ “በሊቀ ካህናቱ በአብያታር ክፍል” ማለት ይቻላል። ስለ አብያታር በሰፊው በሚተረከውና እርሱም ዋና ገጸ-ባሕርይ በሆነበት በ1ሳሙኤል 21-22 የታሪክ ክፍል ውስጥ ማለቱ ነው። ይህም በጥንቱ ዘመን ምዕራፍና ቁጥር ባልነበረበት ወቅት አንድን ጥቅስ ለመጠቆም የሚጠቀሙበት ትክክለኛ ሰዋሰዋዊ መንገድ ነው።
- የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን የቃል አጠቃቀም ልማድ
ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ሌላው ጉዳይ በአንደኛው ክፍለ ዘመን የነበረው “ሊቀ ካህናት” የሚለው አባባል አጠቃቀም ነው። በአይሁዳዊው ጸሐፌ ታሪክ ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን ጽሑፎች ውስጥ እንደሚታየው “ሊቀ ካህናት” የሚለው ስም ለዋናው ካህን ብቻ ሳይሆን ለሊቀ ካህናቱ ቤተሰቦች ወይም ከፍተኛ ማዕርግ ላላቸው ካህናት ሁሉ በጋራ ጥቅም ላይ ይውል ነበር። አብያታር የሊቀ ካህኑ የአቢሜሌክ ልጅ እንደመሆኑ በአንደኛው ክፍለ ዘመን የቃላት አጠቃቀም መሠረት “ሊቀ ካህናት” በሚለው የቤተሰብ ማዕረግ ውስጥ ይካተታል (Antiquities 20.6 180-81; Wars 4.160, 238)። ለዚህ የቃላት አጠቃቀም መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ምስክርነቱን ይሰጣል። ለምሳሌ ያህል በአዲስ ኪዳናችን ውስጥ በብዙ ቦታዎች ላይ “የካህናት አለቆች” ἀρχιερεῖς (አርኬሬይስ) የሚሉ ቃላትን የምናገኝ ሲሆን በነጠላ ἀρχιερέως (አርኬሪዎስ) ይሰኛል። ስለዚህ የዮሴፍ ወልደ ኮርዮን ዘገባ በአዲስ ኪዳንም የተደገፈ ሲሆን ሊቀ ካህን የሚለው አባባል በአንድ ግለሰብ ብቻ የተገደበ ሳይሆን በዙርያው የሚገኙ አስፈላጊ አካላትን የሚያጠቃልል እንደ ሆነ እንገነዘባለን። ጌታችንም አብያታርን በዚህ ማዕርግ ሲገልጽ በዘመኑ በነበረው የቃል አጠቃቀም እየገለጸው ብቻ ሊሆን ይችላል።
ማጠቃለያ
በማርቆስ 2፡26 ላይ የሚሰነዘረው ክስ ቅዱሳት መጻሕፍትን ከታሪካዊና ሰዋሰዋዊ አውዳቸው ነጥሎ ለማጥቃት የሚደረግ ያልተገራ ሙከራ ነው። ተቺዎች በአንድ ታዋቂ ግለሰብ ስምና በዚያ የታሪክ ምዕራፍ መካከል ያለውን ትስስር ለማስተዋል ከመጣር ይልቅ በግርድፉ በመውሰድ “ተጣርሶ አገኘን” ብለው ለድምዳሜ መቸኮላቸው ጥንታዊ የታሪክ አጻጻፍ ስልትን (Historiography) ካለመገንዘብ የመነጨ መሆኑን እንረዳለን። ወንጌላዊው ማርቆስ የተጠቀመበት “ኤፒ” የሚለው ቃል ድርጊቱ የተፈጸመበትን ትክክለኛ “ቅጽበት” ሳይሆን ድርጊቱ የተከናወነበትን ሰፊ “የታሪክ ምዕራፍ” ለመጠቆም የገባ ነው። አብያታር በንጉሥ ዳዊት ዘመን የነበረው ገናናነትና ያበረከተው የረጅም ዓመታት የክህነት አገልግሎት ያንን የታሪክ ምዕራፍ በእርሱ ስም ለመሰየም በቂ ምክንያት ነው። ይህ ደግሞ በወቅቱ ለነበሩት አንባቢያንም ሆነ ዛሬ በጥልቀት ለሚመረምሩ ምሑራን ግልጽ የሆነ የታሪክ አገላለጽ ዘይቤ ነው።
ይህንንና መሰል ጥቅሶችን ስናነብ ትኩረታችን እንከን ፍለጋ ላይ ሊሆን አይገባውም። መጽሐፍ ቅዱስን ለነቀፋና ለትችት ብቻ የሚመረምሩ ሰዎች በቃሉ ውስጥ ያለውን ሕይወት ሰጪ መልእክትና የእግዚአብሔርን የማዳን ታሪክ ሳይገነዘቡ ይቀራሉ። ቅዱሳት መጻሕፍትን የምናነበው በውስጣቸው የዘላለም ሕይወት እንዳለ ስለምናምንና ክርስቶስን ስለምናገኝባቸው ነው። እንዲህ ያሉ ውጫዊ የሚመስሉ ነጥቦች በጥንቃቄ ሲገመገሙ በዚህ ጽሑፍ እንዳረጋገጥነው የቃሉን መለኮታዊ ምንጭነትና የታሪካዊ ዘገባውን ተዓማኒነት የሚያጸኑ እንጂ የሚሸረሽሩ አይደሉም። ቅዱስ ቃሉን ለትችት ሳይሆን ለሕይወት ማንበብ እንድንችል እግዚአብሔር አምላካችን ይርዳን። አሜን።
