የትንሣኤ ዘገባዎች ስብጥር

የትንሣኤ ዘገባዎች ስብጥር


የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ የክርስትና እምነት መሠረትና ዋልታ ነው። ሆኖም አራቱ ወንጌላት (ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ) ይህንን ታላቅ ክስተት የዘገቡት ከተለያየ አቅጣጫና ለተለያዩ ተደራሲያን በመሆኑ በመጀመሪያ ሲታዩ “የሚጋጩ” የሚመስሉ ጥቃቅን ልዩነቶች ይስተዋላሉ። ለምሳሌ፦ “መቃብሩ ጋ መጀመሪያ የደረሰው ማን ነው? መላእክቱ ስንት ነበሩ? መቼ ነው የሄዱት?” የሚሉ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ። ይህንን ሁኔታ በአንድ የአደጋ ቦታ ላይ እንደነበሩ አራት ምስክሮች አድርገን ልንወስደው እንችላለን፤ አንዱ ያየውን ሌላኛው ባያየውም አራቱም የሚናገሩት ግን ስለ አንዱ እውነት ነው። ዘገባዎቹ የሚጋጩ ቢመስሉም በጥንቃቄ ስንመረምራቸው ተሰባጣሪ ሆነው እናገኛቸዋለን። ዘገባዎቹን አቀናጅቶ ማንበብ አራቱ ወንጌላት አንዳቸው ሌላቸውን እንደማይጻረሩ፣ ይልቁንም እንደ አንጸባራቂ አልማዝ ከተለያየ አቅጣጫ ሆነው ስለ አንዱ ታላቅ እውነት እንደሚመሰክሩ እንድንገነዘብ ያስችለናል። ቀጥሎ የሚገኘው ስብጥሮሽ Murray J. Harris በተሰኙ ምሑር የተዘጋጀ ነው።

  1. ኢየሱስ ከሙታን ከተነሳ በኋላ ገና ጎህ ሳይቀድ ድንገት የምድር መንቀጥቀጥ ሆነ። በዚያን ጊዜ መልአክ መጥቶ ከመቃብሩ ደጃፍ ላይ ድንጋዩን አንከባለለው፤ ጠባቂዎቹም ከመፍራታቸው የተነሳ ተንቀጠቀጡ፣ ጥለውም ሸሹ (ማቴ. 28፡2-4)።

  2. እሁድ ማለዳ ፀሐይ ከመውጣቷ በፊት፣ መግደላዊት ማርያም፣ የያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያም እንዲሁም ሰሎሜ ወደ መቃብሩ መጡ። ዓላማቸውም በኋላ ከሚመጡት ሌሎች ሴቶች ጋር (ቁጥር 7ን ይመልከቱ) በመሆን የኢየሱስን ሥጋ በሽቱ ለመቀባት ነበር። ሲደርሱ ግን የሚገርም ነገር ገጠማቸው፤ ድንጋዩ ከመቃብሩ አፍ ተንከባሎ ነበር (ማቴ. 28፡1፤ ማር. 16፡1-4፤ ዮሐ. 20፡1)።

  3. ከሴቶቹ መካከል አንዷ ወይም ከዚያ በላይ የሆኑት ወደ መቃብሩ ዘልቀው ገቡ፤ ሥጋው በዚያ አለመኖሩንም ተረዱ (ይህም በዮሐንስ 20፡2 ላይ መግደላዊት ማርያም “ድንጋዩ ተነስቷል” ብቻ ሳይሆን ሥጋው እንደጠፋ መናገሯን መሠረት ያደረገ ነው)።

  4. መግደላዊት ማርያምም የኢየሱስ ሥጋ ከመቃብር መወሰዱን ለጴጥሮስና ለዮሐንስ ለመንገር ወዲያውኑ በፍጥነት ተመለሰች (ዮሐ. 20፡2)።

  5. ማርያም (የያዕቆብና የዮሳ እናት) እና ሰሎሜ በመቃብሩ ውስጥ አንድ መልአክ (በማርቆስ ወንጌል “ጎልማሳ” የተባለውን) አዩ። መልአኩም ኢየሱስ መነሣቱን አበሰረላቸው፤ እንዲሁም “ኢየሱስ በገሊላ ይገናኛችኋል” ብለው ለደቀ መዛሙርቱ እንዲነግሩ አዘዛቸው (ማቴ. 28፡5-7፤ ማር. 16፡5-7)።

  6. እነዚህ ሁለት ሴቶች በታላቅ ፍርሃትና መደነቅ ውስጥ ስለነበሩ፣ በመንገድ ላይ ለማንም ምንም ሳይናገሩ ወዲያውኑ ወደ ከተማው ተመለሱ (ማቴ. 28፡8፤ ማር. 16፡8)።

  7. ከገሊላ የመጡ ሌሎች ሴቶችና ዮሐና (ሉቃ. 8፡3) የኢየሱስን ሥጋ ለመቀባት ያዘጋጁትን ሽቱ ይዘው መቃብሩ ላይ ደረሱ። እነርሱም ሁለት “ሰዎችን” (መላእክት፤ ሉቃ. 24፡4፣ 23) አገኙ። ከዚያም መላእክቱ የነገሯቸውን የትንሣኤ የምስራች አሁን በአንድነት ተሰብስበው ለነበሩት “ለአሥራ አንዱና ለሌሎች ደቀ መዛሙርት” ለማብሰር ተመለሱ (ሉቃ. 24፡19፣ 22-23፤ ማቴ. 26፡56)።

  8. በሌላ በኩል፣ በመግደላዊት ማርያም ወሬ የሰሙት ጴጥሮስና ዮሐንስ (ምናልባትም ሌሎችም፤ ሉቃ. 24፡24) ወደ መቃብሩ ሮጡ። በመንገድ ላይ ከማርያምና ከሰሎሜ ጋር አልተገናኙም ነበር። መቃብሩ ደርሰውም የተልባ እግር ልብሶቹን ብቻ አዩና ወደ ቤታቸው ተመለሱ (ዮሐ. 20፡3-10፤ ሉቃ. 24፡12)።

  9. መግደላዊት ማርያም ጴጥሮስንና ዮሐንስን ተከትላ እንደገና ወደ መቃብሩ መጣች። በዚያም በመቃብሩ ውስጥ ሁለት መላእክትን ካየች በኋላ፣ ራሱን ኢየሱስን አገኘችው (ዮሐ. 20፡11-17፤ ማር. 16፡9)።

  10. መግደላዊት ማርያም ኢየሱስን ማየቷንና መነሣቱን ለደቀ መዛሙርቱ ለመንገር ተመልሳ ሄደች (ዮሐ. 20፡18፤ ማር. 16፡10-11)።

  11. ማርያም (የያዕቆብና የዮሳ እናት) እና ሰሎሜም ኢየሱስን በመንገድ ላይ አገኙት። እርሱም “ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ንገሩአቸው” ብሎ አዘዛቸው (ማቴ. 28፡9-10)።

  12. ደቀ መዛሙርቱ አሁን መቃብሩ ባዶ መሆኑንና የትንሣኤውን ዜና ከሦስት የተለያዩ ወገኖች (ማለትም ከመግደላዊት ማርያም፣ ከዮሐናና ከገሊላ ሴቶች፣ እንዲሁም ከማርያምና ከሰሎሜ) ሰምተዋል፤ ሆኖም ወሬውን እንደ ተራ ተረት ቆጥረው ሊያምኑአቸው አልቻሉም (ሉቃ. 24፡10-11፤ ማር. 16፡11)።

  13. በዚያው ቀን ከሰዓት በኋላ ኢየሱስ ወደ ኤማሁስ በሚጓዙ ሁለት ደቀ መዛሙርት መካከል ተገለጠ። እነርሱም ወዲያውኑ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ለአሥራ አንዱና ለሌሎቹ የሆነውን ሁሉ ነገሯቸው (ሉቃ. 24፡13-35፤ ማር. 16፡12-13)።

  14. ኢየሱስ ለጴጥሮስ (ለኬፋ) ተገለጠ (ሉቃ. 24፡34፤ 1 ቆሮ. 15፡5)።

  15. በዚያው እሁድ ምሽት ቶማስ በሌለበት፣ ኢየሱስ ለአሥራ አንዱና አብረዋቸው ለነበሩት ሁሉ ተገለጠላቸው (ሉቃ. 24፡33፣ 36-43፤ ዮሐ. 20፡19-23፤ 1 ቆሮ. 15፡5፤ ማር. 16፡14)።

  16. ከአንድ ሳምንት በኋላ ደግሞ ቶማስ ባለበት ኢየሱስ እንደገና ለአሥራ አንዱ ተገለጠላቸው (ዮሐ. 20፡26-29)።

  17. በገሊላ በሚገኘው በጥብርያዶስ ባሕር አጠገብ ኢየሱስ ለሰባት ደቀ መዛሙርት ተገለጠላቸው (ዮሐ. 21፡1-22)።

  18. አሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት በገሊላ ባለ ተራራ ላይ ከኢየሱስ ጋር ተገናኙ (ማቴ. 28፡16-20፤ ማር. 16፡15-18)።

  19. ኢየሱስ በአንድ ጊዜ ከአምስት መቶ ለሚበልጡ ሰዎች ተገለጠ (ሉቃ. 24፡44-49፤ 1 ቆሮ. 15፡6)።

  20. ለያዕቆብም ተገለጠ (1 ቆሮ. 15፡7)።

  21. በመጨረሻም ወደ ሰማይ ከመድረጉ በፊት፣ በቢታንያ አቅራቢያ ለአሥራ አንዱ ተገለጠላቸው (ሉቃ. 24፡50-52፤ ሐዋ. 1፡6-11፤ 1 ቆሮ. 15፡7፤ ማር. 16፡19-20)።


“Three Crucial Questions about Jesus” by Murray J. Harris, Baker Books, 1994, ISBN 0-8010-4388-3; from the appendix, pages 107-109.

የእንግሊዝኛው ቅጂ A Suggested Harmonization of the Resurrection Narratives በሚል ርዕስ ይገኛል።


መሲሁ ኢየሱስ