“አብ በራሱ ሕይወት እንደለው እንዲሁ ደግሞ ለወልድ በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታል” የሚለው ከኢየሱስ አምላክነት አኳያ እንዴት ይታያል?

“አብ በራሱ ሕይወት እንደለው እንዲሁ ደግሞ ለወልድ በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታል” የሚለው ከኢየሱስ አምላክነት አኳያ እንዴት ይታያል?

የአምላክ ሕልውና በማንም ላይ ጥገኛ አይደለም፤ አይኾንምም፡፡ በዮሐንስ ወንጌል 5፡26 ላይ መጽሐፍ ቅዱስ “አብ በራሱ ሕይወት እንደለው እንዲሁ ደግሞ ለወልድ በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታል” ይላል፡፡ ነገር ግን እንደዚህኛው ጥቅስ ገለጻ የኢየሱስ ሕልውና በአብ (አምላክ) ላይ ጥገኛ ነው፡፡ “ለወልድ በራሱ ሕይወት አንዲኖረው ሰጥቶታል” ይላል፡፡ ወልድ ሕልውና (ሕይወት) ያገኘው አብ ስለሰጠው ነው፡፡ የኢየሱስ ሕልውና በአብ ላይ ጥገኛ ነው፡፡ ኢየሱስ ያለ አብ በራሱ ሕልውና ሊኖረው ካልቻለ እንዴት አምላክ ሊሰኝ ይችላል?

ይህ የኢየሱስን ዘለዓለማዊ መገኘት (Eternal Generation) የሚያመለክት በመኾኑ የሥላሴን አስተምሕሮ የሚደግፍ ነው፡፡ በሥላሴ አስተምሕሮ መሠረት ኢየሱስ በዘለዓለማዊ መገኘት ከአብ የተገኘ ነው፡፡ ለዚህ ነው የኒቅያ የሃይማኖት መግለጫ “ከአምላክ በተገኘው አምላክ፣ ከብርሃን በተገኘ ብርሃን፣ ከእውነትኛ አምላክ በተገኘ እውነተኛ አምላክ፣ በተፈጠረ ሳይኾን በተወለደ…” የሚሉ አንቀፆችን ያካተተው፡፡ የኢየሱስ ሕይወት ከአብ የተገኘ ነው፡፡ ይህ መገኘት ዘለዓለማዊና በጊዜ ያልተገደበ ሲሆን የኢየሱስን መለኮታዊ ባሕርይ ከአብ አያሳንስም፡፡ አብ ያሉት ባሕርየ መለኮታት ኹሉ ወልድም አሉት፡፡በሌላ አባባል ለመኖር በማንም ላይ ጥገኛ ያልሆነው የአብ ሕይወት የወልድም ሕይወት ነው ማለት ነው፡-

“እግዚአብሔርም የዘለዓለምን ሕይወት እንደ ሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው፡፡ ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም፡፡” (1ዮሐንስ 5፡11-12)፡፡

እግዚአብሔርን በትክክል መግለፅ የሚችል ምሳሌ ባይኖርም የወልድን ዘለዓለማዊ መገኘት ለመረዳት ተከታዩ ምሳሌ ይረዳል፡፡ እስኪ በጊዜ ያልተገደበ ከዘለዓለም ዘመናት በፊት ሲያበራ የነበረ አንድ ኮከብ አስቡ፡፡ ብርሃኑ ኮከቡ በነበረበት ጊዜ ኹሉ አብሮት ነበር፡፡ ነገር ግን የኮከቡ ብርሃን ከኮከቡ የተገኘ ነው፡፡ ብርሃኑ ከሌለ ኮከብነቱ ይቀራል፡፡ ኮከቡ ከሌለ ብርሃኑም ሊኖር አይችልም፡፡ የአብና የኢየሱስንም ቁርኝት በዚህ መንገድ መረዳት ይቻላል፡፡ ለዚህ ነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱና አብ አንድ መሆናቸውን፤ እርሱን ያየ አብን ማየቱን እዲሁም እርሱ በአብ አብም ደግሞ በእርሱ እንዳለ የተናገረው (ዮሐ. 14፡9-11)፡፡ “አብ” እና “ወልድ” የሚሉት መጠርያዎች ይህንን ዘለዓለማዊ አንድነት የሚገልፁ ናቸው፡፡

 

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች የተሰጠ መልስ ማውጫ

እግዚአብሔር ማነዉ?

መሲሁ ኢየሱስ

ለእስልምና ሙግቶች ምላሽ