በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለቀረቡ ግብረ ገባዊ ትችቶች የተሰጠ መልስ
በዚህ ጽሑፍ ሙስሊም ወገኖቻችን በማሕበራዊ ትስስር ገፆች ከሚቀባበሏቸው ጥያቄዎች መካከል የተወሰኑትን እንመለከታለን፡፡ ጥያቄዎቹን ያዘጋጀው ሰው ለውይይት በሚጋብዝ መንገድ ሳይሆን ሰላማዊ ውይይትን በሚያደፈርስ ጨዋነት በጎደለው መንገድ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ በማሕበራዊ ሚድያ ኡስታዞች ዘንድ የተለመደ አቀራረብ የሚመጥን ባይሆንም እነኚህን በመሳሰሉት ሙግቶች ግራ ሊጋቡ የሚችሉትን ወገኖች ታሳቢ በማድረግ መልስ ለመስጠት ወስነናል፡፡ ጠያቂው እንዲህ ሲል ይጀምራል፡-
ከመጽሐፍ ቅዱስ አስገራሚ ይዘቶች መካከል
በዚህ ክፍል የምንመለከታቸው አንቀፆች ብዙውን ጊዜ ስናነባቸው ፈገግ የሚያደርጉን፣ አንዳንዶቹ ደግሞ አሳዛኝ የሆኑ አልፎም አስደንጋጭ የሆኑ የባይብል አንቀፆችን ነው፡፡ እነዚህ አንቀፆች ቅዱስ በተሰኘ መጽሐፍ ውስጥ ሊኖሩ የማይገቡና ፈጽሞ የመለኮታዊ ቃልነትን ካባ ያልተላበሱ ናቸው።
የቁርአንና የሐዲስ ተረቶችን እንደ መለኮታዊ መገለጥ ከተቀበለ ሰው እንዲህ ያለ ንግግር መስማት በእጅጉ አስገራሚ ነው፡፡ ሙስሊም የዳዕዋ አስፋፊዎች መጽሐፍ ቅዱስን ሲጠቅሱ የትችት አጉሊ መነፅር በማጥለቅ፤ ቁርአናቸውን ሲጠቅሱ ደግሞ የኅሊና መነፅራቸውን በማውለቅ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡
- ታላቁ ገዳይ
እንደ መጽሐፍ ቅዱስ መሠረት አምላክ በሆነ ወቅት ደስ ካላለው “ለምን ይሄን አያችሁ?” ብሎ ሳይቀር ህዝብ በመደዳ ጨፍጭፎ ሊያስለቅስ ይችላል፡፡
“ወደ እግዚአብሔርም ታቦት ውስጥ ተመልክተዋልና የቤትሳሚስን ሰዎች መታ፤ በሕዝቡም ከአምስት ሺህ ሰው ሰባ ሰዎችን መታ፤ እግዚአብሔርም ሕዝቡን በታላቅ ግዳይ ስለ መታ ሕዝቡ አለቀሰ።” (መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 6፡19)
የእግዚአብሔር ታቦት የክብሩ መገኛ እንጂ ተራ ቁስ ባለመሆኑ የተመረጡ ካህናት ካልሆኑ በስተቀር ማንም በዘፈቀደ እንዲመለከተው አልተፈቀደም፤ ስለዚህ እግዚአብሔርን በመዳፈር ባልተቀደሰ ማንነት የተመለከቱት ሰዎች መቀሠፋቸው አያስገርምም (ዘኁ. 4፡20)፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ የሰው ልጆች ፈጣሪና በነፍሳቸው ላይ ፍፁማዊ ሥልጣን ያለው አምላክ ነው፡፡ ስለዚህ የማንንም ነፍስ በወደደው ሰዓት በወደደው መንገድ ቢወስድ ጠያቂ የለውም፡፡
- ብልት መንካት እጅ ያስቆርጣል
እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ መሠረት የአንድን ወንድ ብልት አንዲት ሴት በጠብ መሀል ከጨበጠች እጇ ይቆረጣል። ይህ አስቂኝ ብቻ ሳይሆን ከቅዱሳን መጽሐፍት ውስጥ ሊገኝ የማይገባው ቁምነገር አልባ ተራ ዝባዝንኬ ነው።
“ሁለት ሰዎች እርስ በርሳቸው ቢጣሉ፥ የአንደኛውም ሚስት ባልዋን ከሚመታው ሰው እጅ ታድነው ዘንድ ብትቀርብ፥ እጅዋንም ዘርግታ ብልቱን ብትይዝ፥ እጅዋን ቍረጥ፥ ዓይንህም አትራራላት። ” (ኦሪት ዘዳግም ምዕ. 25፥11-12)
በጸብ መሃል የወንድ ብልት መያዝ ትርጉሙ ምን እንደሆነ የገባህ አትመስልም፡፡ ወገኔ ወንድ ከሆንክ ከመግደል ሙከራ ያልተናነሰ ጥቃት መሆኑን ትረዳለህ፡፡ አንድን ሰው ሕይወቱን ሊያሳጣው ወይንም ደግሞ ዘር እንዳይተካ ሊያደርገው የሚችለውን አደጋ ሆነ ብሎ ያደረሰ ሰው እንዲህ ያለ ፍርድ አይገባውም እያልከን ነው? ለመሆኑ በእስልምና ሲሰርቅ የተያዘ ሰው ቅጣቱ ምንድነው? እጅ መቁረጥ! ሱራ 5:38፡- “ሰራቂውንና ሰራቂይቱንም በሠሩት ነገር ለቅጣት፣ ከአላህ የሆነን መቀጣጫ፣ እጆቻቸውን ቁረጡ፡፡” ሊተካ የሚችለውን ንብረት የሰረቀ ሰው እጁ ተቆርጦ ሊተካ የማይችለውን ዘር ያጠፋ ሰው በዚህ ሁኔታ መቀጣቱ ኢ-ፍትሃዊ የሚሆነው በምን ሒሳብ ነው? ይልቁኑ “…ቁምነገር አልባ ተራ ዝባዝንኬ…” የሚለው አገላለፅህ የመረዳት አቅምህን የሚያስገመግም ተራ ንግግር ነው፡፡ የዘዳግም መጽሐፍ የሕግ መጽሐፍ ነው፡፡ የሕግ መጽሐፍ ደግሞ በማሕበረሰቡ ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉ ወንጀሎችን በሙሉ በተቻለ መጠን ይጠቅሳሉ፡፡ ዋናው ጉዳይ በዚህ ዘመን ላለነው ለኛ አእምሮ መመቸት አለመመቸቱ ሳይሆን ሕጉ ለተሰጣቸው በዚያን ዘመን ለነበሩት ሰዎች መጥቀም አለመጥቀሙ ነው፡፡ ደግሞ የገዛ ነቢይህና ቁርአንህ ያከበሩትን መጽሐፍ እንዲህ ማብጠልጠልህ የገዛ ሃይማኖትህን አለማወቅህን ወይንም የሃይማኖትህን አስተምሕሮ አለመቀበልህን ያሳያል፡፡ ለበለጠ መረጃ፡-
እስላማዊ አጣብቂኝ ፡- መጽሐፍ ቅዱስ ከተበረዘ ቁርኣን ዋሽቷል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ካልተበረዘ ቁርኣን የፈጣሪ መጽሐፍ አይደለም!
መጽሐፍ ቅዱስ በሚለው ማውጫ ስር ተጨማሪ ጽሑፎችን ታገኛላችሁ፡፡
- ባርነትን አሜን ብለህ መቀበል አለብህ
መጽሐፍ ቅዱስ ባርነትን አስመልክቶ ያለው አስተምህሮ እጅግ ኃላቀር ነው። የባርነትን አስከፊ ስርአት ለማስወገድ ያስቀመጣቸው ቆራጥም ሆነ ሒደታዊ መፍትሔዎች የሉም። በተቃራኒው ግን ባሪያ ለሎሌው ተገዥ እንዲሆንና እድሜ ልኩን በባርነት ቀንበር እንዲማቅቅ በግልጽ ይመክራል።
“ሎሌዎች ሆይ፥ ለበጎዎችና ለገሮች ጌቶቻችሁ ብቻ ሳይሆን ለጠማሞች ደግሞ በፍርሃት ሁሉ ተገዙ።” (1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 2፡18)
ይህ ትችት ባርያ አሳዳሪና ባሪያ ነጋዴ የነበረውን ሙሐመድን እንደ እውነተኛ ነቢይ ከተቀበለ ሰው መሰንዘሩ በእጅጉ አስገራሚ ነው፡፡ እስላማዊ ሐዲሳት እንዲህ ይላሉ፡-
“ጃቢር ኢብን አብዱላህ እንዳስተላለፈው፡- አንድ ባርያ ወደ አላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) በመምጣት ቃል ኪዳን ያዘ፡፡ ነቢዩም ባርያ መሆኑን አላወቁም ነበር፡፡ አሳዳሪው በመምጣት ባርያው እንዲመለስለት በጠየቀ ጊዜ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ‹‹ሽጥልኝ›› አሉት? በሁለት ጥቁር ባርያዎችም ገዙት፡፡” Sahih Muslim, Book 10, Number 3901
የክርስትናው ዓለም በባርነት ውስጥ የተሳተፈበት ዘመን ነበር፡፡ ይህ በአትላንቲክ ላይ ሲደረግ በነበረው የባርያ ንግድ ሊገለፅ ይችላል፡፡ ይሁንና የባርያ ንግድ እንዲቀር የተንቀሳቀሱትና በብዙ ፍልሚያ እንዲቀር ያደረጉት በመጽሐፍ ቅዱስ አጥብቀው የሚያምኑ ክርስቲያኖች ነበሩ፡፡ የሙስሊሙ ዓለም ግን ባርነት እንዲቀጥል ትግል ሲያደርግ እንደነበረና አሁንም ድረስ ባርነት ከተስፋፋባቸው የዓለም ክፍሎች ቀዳሚውን ስፍራ መያዙ ሊታበል የማይችል ሃቅ ነው፡፡ ባርነት አብሶም የጥቁር ባርነት በእስልምና ዋና ተቋማት ተቀባይነት ያለውና በተማሩ ሙስሊሞችና የሕግ ሊቃውንት እንዲሁም መልካም በተባሉት አማኞች ዘንድ ዕውቅና የተቸረው ነው፡፡ ግብፅ በአረቦች ከተወረረች በኋላ በ639 እና 642 ዓ.ም. ቢላድ አል-ሱዳን ወይም “የጥቁሮች ምድር” ለሙስሊሙ ዓለም የባርያ ምንጭ ሆኖ ነበር፡፡ የባርያ ፈንጋዮች ዋና ዋና ምንጮች ጦርነት (ጂሃድ)፣ ድንገተኛ ጥቃት፣ ገባርነት፣ ግዢ እና ጠለፋ ነበሩ፡፡ (John Alembillah Azumah, The Legacy of Arab-Islam in Africa, Oxford, England፡ One World, 2001, p. 141.) እስልምናን በተቀበለው አብዛኛው የአፍሪካ ክፍል አውሮፓውያን ከመምጣታቸው ከብዙ ክፍለ ዘመናት በፊት የባርያ ንግድ የተቀናጀና ተቋማዊ ይዘት ነበረው፡፡ (Azumah, p. 117) የእስልምና ቅድስት ከተማ የሆነችው መካ “የዓለም የባርያ ንግድ ማዕከል” ሆና እስከ ሃያኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ያገለገለች ሲሆን ከምስራቅ አፍሪካና ከሱዳን የመጡ ባርያዎች ወደ መላው አረብያና የሙስሊም ዓለም ይሰራጩ ነበር፡፡ (Azumah, p. 146) የእስልምናው ዓለም ድል የነሳቸውንና በግዛቱ ወሰን ላይ የሚገኙትን ብዙ ሕዝቦች ለ1000 ዓመታት ያህል ባርያ አድርጓል፡፡ (Hugh Kennedy, The Great Arab Conquests, U.S.A፡ Da Capo Press, 2007, pp. 222- 223, 323, 367; Bernard Lewis, What Went Wrong? Western Impact and Middle Eastern Response, England: Oxford University Press, 2002, pp. 11, 26, 85-89)፡፡
ወደ ጥቅሱ ሐሳብ ስንመለስ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ባርነትን ለማበረታታት የታለመ ሳይሆን ክርስትናን የተቀበሉ በዘመኑ የነበሩ ባርያዎች እንዴት መኖር እንዳለባቸው የሚያስተምር ነው፡፡ ክርስትናን የተቀበሉ ባርያዎች በዘመኑ የነበረውን ጥብቅ የባርነት ሥርዓት መቃወም ሕይወታቸውን ሊያሳጣቸው በሚችልበት ሁኔታ አመፅ ውስጥ ከመግባት ይልቅ ለጌቶቻቸው በትህትና እየተገዙ በመልካም ሥነ ምግባር እንዲያሸንፏቸው ከመምከር የተሻለ መልካም ምክር አልነበረም፡፡ ቀጣዩ ክፍል እንዲህ ይላል፡- “በግፍ መከራን የሚቀበል ሰው እግዚአብሔርን እያሰበ ኃዘንን ቢታገሥ ምስጋና ይገባዋልና።” (ቁ. 18)
ይህ ምክር ከአእምሮ ባርነት ነፃ በማውጣት ትእግስትን የሚያላብስ ዘመኑን ያገናዘበ ምክር ነው፡፡ የዚህ ትችት አቅራቢ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ቢኖር ኖሮ ባርያዎችን ምን ብሎ ይመክራቸው ይሆን? ጥብቅ በነበረው የሮማውያን ሥርዓት ላይ በማመፅ ዘግናኝ አሟሟት እንዲሞቱ ወይንስ በትህትና እየተገዙ ጌቶቻቸውን በመልካም ሥነ ምግባር እንዲያሸንፉ? ካላዋቂ መካሪ ይጠብቀን!
በዘመነ ብሉይ እግዚአብሔር ባርነትን ቢታገስም ባርያዎች በየ 7 ዓመቱ ነፃ እንዲወጡ አዟል፤ ባርያ ፈንጋዮችም በሞት እንዲቀጡ አዟል (ዘጸ. 21፡2፣ 21፡16)፡፡ አዲስ ኪዳን በዘመኑ ጥብቅ በነበረው የሮማውያን የባርነት ሥርዓት ሥር የነበሩትን አማኞች በትዕግሥት እንዲገዙ ቢመክርም የባርነት መሠረት የሆነውን የዘር ብልጫን አፍርሷል፡- “አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና” (ገላ. 3፡28)፤ ባርያ የሚያሳድሩ አማኞች እንደ ባርያ ሳይሆን እንደ ወንድሞች እንዲቆጥሯቸው ያሳስባቸዋል፡- “ከእንግዲህ ወዲህ እንደ ባሪያ አይሆንም፥ ነገር ግን ለእኔ በተለየ የተወደደ ወንድም ከሆነ፥ ለአንተማ ይልቅ በስጋውም በጌታም ዘንድ ከባሪያ የሚሻል የተወደደ ወንድም እንዴት አይሆንም። እንግዲህ እንደ ባልንጀራ ብትቈጥረኝ፥ እንደ እኔ አድርገህ ተቀበለው” (ፊልሞና 17)፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ባርነትን በሒደት የሚያስወግድ አስተምሕሮና መርህ በውስጡ ይዟል፡፡ በመጨረሻም ባርነት እንዲቀር የታገሉትና ስኬትን ያስመዘገቡት በመጽሐፍ ቅዱስ አጥብቀው የሚያምኑት የክርስቶስ ተከታዮች ነበሩ፡፡
- የወሲብ ባርነት ይበረታታል ካስፈለገህ ሴት ልጅህንም መሸጥ እንደምትችል ይገልፃል፡፡
ሰውም ሴት ልጁን ለባርነት ቢሸጥ ባሪያዎች እንደሚወጡ እርስዋ አትውጣ። ጌታዋን ደስ ባታሰኘው በዎጆ ይስደዳት፤ ስለ ናቃት ለሌላ ወገን ሰዎች ይሸጣት ዘንድ አይገባውም። (ኦሪት ዘጸአት ምዕ. 21፥7-8)
ይህንን አይነት መመሪያ “የፍቅር አምላክ” የተባለ አካል በአንድ ወቅት ህግ አድርጎት ነበር ብሎ ማሰብ ህሊና ይቀበለዋልን?
ሲጀመር “የወሲብ ባርነት” የሚል ቃልም ሆነ ሐሳብ በዚህ ቦታ የለም፡፡ የወሲብ ባርነት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለማወቅ ቁርአንና የሙሐመድን ታሪክ ማጥናት ጠቃሚ ነው (ሱራ23፡5-6፣ 4፡24፣ Sahih Muslim, vol. 2, No. 3371)፡፡ በጥንት ዘመን ድኻ የሆኑ ቤተሰቦች ለተሻለ ኑሮ ሴት ልጆቻቸውን ለባለጠጎች በአገልጋይነት “ይሸጡ” ነበር፡፡ በዚህ መንገድ ልጆቹ የተሻለ ኑሮ ያገኛሉ፤ ወላጆቻቸውም ከሥቃይ ይተርፋሉ፡፡ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ለባለ ጠጋ የተሰጠች ሴት እንደ ማንኛውም ባርያ አትታይም፡፡ በአገልጋይነት ቢያኖራትና ግዴታዋን ባትወጣ በወጆ ነፃ የመውጣት መብት አላት፤ እንደ ተራ ባርያ ለሌላ ወገን አትሸጥም፡፡ ለልጁ ቢድራት ለሴቶች የሚደረገው ሁሉ ይደረግላታል፡፡ ልጁ ሌላ ሴት ቢያገባ ለኑሮዋ አስፈላጊ የሆነ ነገር ሁሉ ሳይጎድልባት ትኖራለች፡፡ ይህንን ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኛ ካልሆነ ቀደም ሲል ገንዘብ ከፍዬባታለሁ ብሎ የወደደውን የማድረግ መብት የለውም፤ በነፃ የማሰናበት ግዴታ አለበት፡፡ ሙሉ ክፍሉ እንዲህ ይነበባል፡-
“ሰውም ሴት ልጁን ለባርነት ቢሸጥ ባሪያዎች እንደሚወጡ እርስዋ አትውጣ። ጌታዋን ደስ ባታሰኘው በዎጆ ይስደዳት፤ ስለ ናቃት ለሌላ ወገን ሰዎች ይሸጣት ዘንድ አይገባውም። ለልጁም ቢድራት፥ ለሴት ልጆች የሚገባውን ያድርግላት። ከእርስዋ ሌላም ቢያጋባው፥ መኖዋን ልብስዋንም ለምንጣፍዋም ተገቢውን አያጕድልባት። ይህንም ሦስት ነገር ባያደርግላት ያለ ገንዘብ በከንቱ ትውጣ።” (ዘጸአት 21፡7-11)
ከጌታዋ ልጅ ጋር ያላት ግንኙነት እንደ ማንኛውም ጋብቻ መሆኑን በተሻለ ግልፅነት ለመረዳት በእንግሊዘኛ ትርጉም እናንብበው፡-
“… If he marries another woman, he must not deprive the first one of her food, clothing and marital rights. If he does not provide her with these three things, she is to go free, without any payment of money.” Exodus 21፡7-11
ይህ ሕግ በድኽነት ለሚማቅቁ ቤተሰቦች የሚበጅ ነው፡፡ ድኻ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ባለጠጎች በማስጠጋት ገንዘብ ያገኛሉ፣ ልጆቻቸውም መብቶቻቸውን እንደ ባርያ ሳይገፈፉ በመልካም ሁኔታ ይኖራሉ፡፡ ለጋብቻም ከተፈለጉ እንደ ማንኛዋም ሚስት መብታቸው ተከብሮ ይኖራሉ፡፡ ይህ በዘመነ ብሉይ ድኾችን ለመጥቀም የተሰጠ ሕግ ነው፡፡ ለመሆኑ እስልምና ለሴት ልጅ ከዚህ የተሻለ ምን መብት ሰጥቶ ይሆን?
- ሰው በሊታ ስለሆኑ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ፡)
መጽሐፍ ቅዱስ ከያዛቸው ቁምነገር አልባ ትርክቶች መካከል አንዱ ስለሰው በሊታ ሰዎች ተዘግቦ የምናገኘው ታሪክ አንዱ ነው። እንደሚከተለው ይነበባል፦
ንጉሡም። ምን ሆነሻል? አላት፤ እርስዋም። ይህች ሴት። ዛሬ እንድንበላው ልጅሽን አምጪ፤ ነገም ልጄን እንበላለን አለችኝ። ልጄንም ቀቅለን በላነው፤ በማግሥቱም። እንድንበላው ልጅሽን አምጪ አልኋት፤ ልጅዋንም ሸሸገችው ብላ መለሰችለት። (መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ ምዕ. 6፥28-29)
አምላክ በዚህ ተረት በመሠለ ታሪክ ውስጥ ለአማኙ ምን ሊያስተላልፍ እንዳሰበ ግልጽ አይደለም። ትርክቱስ ምን ሊፈይድ ነው በቅዱሳን መጽሐፍ ውስጥ የተቀመጠው?
በላዔ ሰብዕነትን (Cannibalism) ከተረት መፈረጁ ጠያቂው ምን ያህል ከመረጃ የራቀና ዕውቀት አጠር እንደሆነ ያሳያል፡፡ እንዲህ ያለ ዘግናኝ ልማድ በረሃብ ዘመን በብዙ ሀገራት ውስጥ የታየ ክስተት መሆኑን የዓለም ታሪክ እማኝነቱን ይሰጣል፡፡ ለምሳሌ ያህል ይህ የዘጋርዲያን ዘገባ በርካታ እንዲህ ያሉ ክስተቶችን ይዘረዝራል https፡//www.theguardian.com/commentisfree/2013/may/05/cannibalism-history-europe-famine-shipwreck
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተዘገበው ይህ ታሪክ በረሃብ ዘመን የተከሰተ አሳዛኝ ታሪክ ነው፡፡ የሰማርያ ከተማ በሦርያውያን ወታደሮች በመከበቧ ምክንያት ረሃብ እጅግ ሲጠና እንመለከታለን፡፡ ዘመኑ ነቢዩ ኤልሳዕ የነበረበት ዘመን ነበርና ንጉሡ ይህንን ታሪክ ሲሰማ እጅግ በመቆጣት የኤልሳን ራስ ለመቁረጥ ተነሳ፡፡ ኤልሳዕ በሃያ አራት ሰዓታት ውስጥ ይህ የረሃብ ታሪክ ተለውጦ በሰማርያ ከተማ ጥጋብ እንደሚሆን ትንቢት ተናገረ፤ እንደተናገረውም ሆነ (1ነገሥት 6፡24-7፡20)፡፡ የታሪኩ ሙሉ ምስል እንዲህ ሆኖ ሳለ ይህ ሙስሊም ፕሮፓጋንዲስት ግን መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው በሊታ” ስለሆኑ ሰዎች ተረት የተናገረ ለማስመሰል ሞክሯል፡፡ በእንዲህ ያለ የችግር ዘመን እግዚአብሔር ነቢዩን እንዴት ከሞት እንደታደገውና ተዓምራዊ በሆነ ሁኔታ ሕዝቡን እንዴት ከችግር እንዳወጣ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ጠያቂው ባቀረበው መንገድ በማጣመም ማቅረብ የጠያቂውን አላዋቂነት የሚገልጥ ነው፡፡
- የአካል ጉዳተኞችን ስብዕና ዝቅ ያደረገ
አካል ጉዳተኛ የሆነ ግለሰብ እኩል መብት እንደሌለው መጽሐፍ ቅዱስ በማያሻማ መልኩ ይነግረናል። አካል ጉዳተኞችንም በግልፅ ቋንቋ “ነውረኛ” ሲል ይገልፃቸዋል።
“ዕውር፥ ወይም አንካሳ፥ ወይም አፍንጫ ደፍጣጣ፥ ወይም ትርፍ አካል ያለው፥ወይም እግረ ሰባራ፥ ወይም እጀ ሰባራ፥ ወይም ጐባጣ፥ ወይም ድንክ፥ ወይም ዓይነ መጭማጫ፥ ወይም እከካም፥ ወይም ቋቍቻም፥ ወይም ጃንደረባ፥ ነውረኛ ሁሉ አይቅረብ። ከካህኑ ከአሮን ዘር ነውር ያለበት ሰው የእግዚአብሔርን የእሳት ቍርባን ያቀርብ ዘንድ አይቅረብ፤ ነውረኛ ነው፤ የአምላኩን እንጀራ ያቀርብ ዘንድ አይቅረብ።” (ዘሌዋውያን 21፥18-21)
እንኳንስ የእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት ይቅርና ውትድርና፣ ፓይለትነት፣ ሆስተስነት፣ የሆቴል ቤት አስተናጋጅነትና የመሳሰሉት ሙያዎች የራሳቸው የሆነ አካላዊ መስፈርት አላቸው፡፡ እዚህ ጋ ምናልባት ጥያቄ ሊፈጥር የሚችለው እነዚህ አካላዊ ጉዳቶች ያሉበት ሰው “ነውረኛ” በሚል ቃል መገለፁ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በ1954 ዓ.ም. ቃሉን ከእብራይስጥ ወደ አማርኛ የተረጎሙ ሰዎች የመረጡት ጥሩ ያልሆነ ምርጫ ነው፡፡ “ሙም” የሚለው የእብራይስጥ ቃል ግን “እንከን ያለበት” ተብሎ ቢተረጎም ይበልጥ ትክክል ይሆናል፡፡ ስለዚህ ለቤተ መቅደሱ አገልግሎት የተሟላ አካልና ጤንነት እንደ መስፈርት መቀመጡ ጥያቄን የሚያስነሳ አይደለም፡፡ አካል ጉዳተኛን ዝቅ አድርጎ መመልከትም ሆነ ጎጂ ተግባር መፈፀም በመጽሐፍ ቅዱስ በጥብቅ የተከለከለ ጉዳይ ነው፡- “ደንቆሮውን አትስደብ፥ በዕውርም ፊት ዕንቅፋት አታድርግ፥ ነገር ግን አምላክህን ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።” (ዘሌ. 19፡14)
በተመሳሳይ ብልትህ ወይንም የመራቢያ አካልህ የተጎዳ ከሆነ ሲያምርህ ይቀራል እንጅ የእግዚአብሔር ጉባኤ ውስጥ አትገባትም..!
“ቍላው የተቀጠቀጠ ብልቱም የተቈረጠ ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባ። ” (ኦሪት ዘዳግም 23፡1)
በጥንት ዘመን ሰዎች በፈቃደኝነትም ሆነ ያለ ውዴታቸው ለአምልኮተ ጣዖትና ለታማኝ አገልጋይነት ሲባል የመራቢያ አካላቸው ጥቅም እንዳይሰጥ እንደሚደረግ ይታወቃል፡፡ እንዲህ ያሉ ወገኖችን ከቤተ መቅደሱ የሚያግደው ሕግ በሒደት ይህንን ጎጂ ልማድ ለማስቀረት እንደሚረዳ እሙን ነው፡፡ አንዳንድ አላዋቂዎች ይህ ጥቅስ የወንድን የዘር ፍሬ በግልፅ ቃል በመጥቀሱ ምክንያት አማኞችን ለማሳፈር ሲሞክሩ ይታያሉ፡፡ የሕግ መጻሕፍት አሻሚ ትርጉሞችን ለመከላከል አንዳንዴ የማሕበረሰቡን ባሕል ችላ በማለት መሰል ግልፅ ቃላትን እንደሚጠቀሙ ይታወቃል፡፡ የሥነ ሕይወት መማርያ መጻሕፍትንም ከተመለከትን ተመሳሳይ የቃላት አጠቃቀም እናገኛለን፡፡ አንድን የአካል ክፍል አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በትክክለኛ ስሙ መጥራት ኃጢአት አይደለም፡፡ ዳሩ ግን በ1954 ዓ.ም. የትርጉም ሥራውን የሠሩ ወገኖች የመረጡት ባሕላችንን ያላገናዘበ የቃል ምርጫ ከመሆንም አልፎ በእብራይስጡ ንባብ ውስጥ “የቆሰለ ወይም የተቀጠቀጠ” ተብለው ሊተረጎሙ የሚችሉ “ደካህ” እና “ፓትሳ” የሚሉ ቃላት እንጂ “ቍ#” የሚል ቃል የለም፡፡ ስለዚህ የወንድ የዘር ፍሬ በውስጠ አዋቂነት የተጠቀሰ እንጂ ቃል በቃል እንደርሱ ተብሎ ሊተረጎም የሚችል ቃል በቦታው ላይ አለመኖሩ መታወቅ አለበት፡፡ שָׁפְכָ֖ה (ሸፈኻህ) የሚል ቃል በቦታው ላይ የሚገኝ ሲሆን “ብልቱ” ተብሎ ነው መተርጎም ያለበት፡፡ ይህንን የተገነዘቡት “የአዲሱ መደበኛ ትርጉም” ተርጓሚዎች “ብልቱ የተቀጠቀጠ ወይም የተቆረጠ…” በማለት ተርጉመውታል፡፡ ትርጉም የሰው ሥራ በመሆኑ እንከን እንደማያጣው የታወቀ ነው፡፡
ጠያቂው ከተናገረው በተጻራሪ ያለ ውዴታቸው በብልታቸው ላይ አደጋ የደረሰባቸው ጃንደረቦች ሕገ እግዚአብሔርን የሚጠብቁ ከሆነ ታላቅ በረከት እንደሚጠብቃቸው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ይናገራል፡-
“እግዚአብሔር ሰንበቴን ስለሚጠብቁ ደስ የሚያሰኘኝንም ነገር ስለሚመርጡ ቃል ኪዳኔንም ስለሚይዙ ጃንደረቦች እንዲህ ይላልና፦ በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋም የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ።” (ኢሳ. 56፡4-5)
በአዲስ ኪዳን ደግሞ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ወንጌልን ለመስማት ከአሕዛብ ወገን ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚያሰልፈውን ዕድል አግኝቷል (ሐ.ሥ. 8፡26-39)፡፡
- እግዚአብሄር እዝነተ ቢስ ከመሆኑ አንፃር ሴቶች ህፃናት ከብቶች ሳይቀሩ በጅምላ ቢጨፈጨፉ ግድ አይሰጠውም እንዴውም ትዕዛዝ አስተላልፎ ሳይቀር ያስጨፈጭፋል፡፡
“አሁንም ሄደህ አማሌቅን ምታ፥ ያላቸውንም ሁሉ ፈጽመህ አጥፋ፥ አትማራቸውም፤ ወንዱንና ሴቱን ብላቴናውንና ሕፃኑን በሬውንና በጉን ግመሉንና አህያውን ግደል። ” (መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 15፡3)
በምድረ ከነዓን የነበሩትን ሕዝቦች ታሪክ ስናጠና እነዚህ ሕዝቦች እግዚአብሔር ለክፍለ ዘመናት የታገሳቸው ነገር ግን ህፃናትን ለጣዖታት መሠዋት፣ ከቤተሰብ አባላትና ከእንስሳት ጋር ወሲብ መፈፀምን የመሳሰሉ ጸያፍ ተግባራትን ባሕል ያደረጉ ፍፁም ሰይጣናዊ ሥልጣኔዎች እንደነበሩ እንገነዘባለን፡፡ እንዲህ ያለውን ተግባር በመፈፀም ምድሪቱን ስላረከሱና እግዚአብሔርን ስላስቆጡ ከምድሪቱ ይወገዱ ዘንድ የእግዚአብሔር ፍርድ ተላለፈባቸው፡፡ እግዚአብሔር እነዚህን ኃጢአተኛ ሥልጣኔዎች ምን ያህል እንደታገሳቸው ለመረዳት የፍርድ ፅዋቸው እስኪሞላ ድረስ እስራኤላውያን በግብፅ ባርነት ለአራት ክፍለ ዘመናት መሠቃየታቸውን ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ነው፡-
“አብራምንም አለው፦ ዘርህ ለእርሱ ባልሆነች ምድር ስደተኞች እንዲሆኑ በእርግጥ እወቅ፤ ባሪያዎች አድርገውም አራት መቶ ዓመት ያስጨንቋቸዋል። ደግሞም በባርነት በሚገዙአቸው ሕዝብ ላይ እኔ እፈርዳለሁ፤ ከዚያም በኋላ በብዙ ከብት ይወጣሉ። አንተ ግን ወደ አባቶችህ በሰላም ትሄዳለህ፤ በመልካም ሽምግልና ትቀበራለህ። በአራተኛው ትውልድ ግን ወደዚህ ይመለሳሉ፤ የአሞራውያን ኃጢአት ገና አልተፈጸመምና።” (ዘፍ. 15፡13-16)
እግዚአብሔር በኖኅና በሎጥ ዘመናት ተመሳሳይ ፍርድ በኃጢአተኞች ላይ አስተላልፏል (ዘፍ. 8፣ 19)፡፡ በነዚያ ዘመናት ሕፃናትና እንስሳትም አብረው ጠፍተዋል፡፡ እነዚህ ታሪኮች በቁርአንም ሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተዘገቡ ሙስሊሞች ለይተው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥያቄ የሚያነሱበት ምክንያት የለም (ሱራ 7፡64፣ 10፡73፣ 11፡40-44፣ 25፡37፣ 29፡14፣ 120፣ 54፡9፣ 11-12፣ 54፡34)፡፡ በተጨማሪም ቁርአን ኣድ እና ሠሙድ የተባሉ ሕዝቦች የጅምላ ጥፋት እንደደረሰባቸው ይናገራል (ሱራ 69፡6፣ 54፡18-21፣ 51፡41፣ 41፡13፣ 7፡78፣ 11፡67፣ 26፡158፣ 41፡17፣ 54፡31፣ 91፡14)፡፡ በነዚህ ታሪኮች መካከል ያለው ልዩነት በኖኅና በሎጥ ዘመናት እግዚአብሔር ተፈጥሮን መጠቀሙና በኋለኞቹ ዘመናት ደግሞ እስራኤላውያንን መጠቀሙ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለእስራኤላውያን ማስጠንቀቂያም ጭምር ሲሆን ተመሳሳይ ተግባር ከፈፀሙ ተመሳሳይ ዕጣ እንደሚገጥማቸው ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል (ዘሌ. 26፡14-46፣ ዘዳ. 28፡15-68፣ ዘዳ. 9፡4-5)፡፡ ነገር ግን እስራኤላውያን በማስጠንቀቂያው ባለመፅናት የነዚያኑ ሕዝቦች መጥፎ ተግባራት መድገም በመጀመራቸው ጌታ እግዚአብሔር በዙርያው የነበሩ መንግሥታትን በመጠቀም ከምድሪቱ ላይ እንዳስወገዳቸው ቅዱስ ቃሉ ይናገራል (2ነገ. 17፣ 25)፡፡ በዚህ ፍርድ ወቅት የህፃናት አብሮ መጥፋት ለሰው አእምሮ የሚከብድ መሆኑ አይካድም፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሥልጣኔዎች ለክፍለ ዘመናት በዚህ መንገድ የኖሩና የመስተካከል ተስፋ ያልነበራቸው መሆናቸው ለዚህ ጥፋት እንዲዳረጉ ሰበብ ሆኗል፡፡ ትዕዛዙ ለአንድ ሕዝብ፣ በአንድ ወቅትና በአንድ ቦታ ከእግዚአብሔር ዘንድ በቀጥታ የተሰጠ እንጂ የሁል ጊዜ አለመሆኑ ሊሰመርበት የሚገባው ሌላው ነጥብ ነው፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ የህፃናቱን የወደፊት ሁኔታ የሚያውቅና በሕይወታቸው ላይ ፍፁማዊ የሆነ ሥልጣን ያለው መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ መሞታቸው አሳዛኝ ቢሆንም በነዚያ ሰይጣናዊ ሥልጣኔዎች ውስጥ አድገው ለዘላለም ከመጥፋት ይተርፋሉ፤ እግዚአብሔርም ደግሞ በወዲያኛው ዓለም የዘላለምን ሕይወት በማጎናፀፍ ሊክሳቸው ይችላል፡፡ በቁርአንና በእስላማዊ ሐዲሳት ውስጥ በስፋት የተጻፈ አንድ ታሪክ ይህንን ጉዳይ ለመረዳት ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ በታሪኩ መሠረት አል-ኸዲር የተባለ የአላህ መልእክተኛ አንድን ህፃን እንዴት እንደገደለና ህፃኑ ወደ ፊት አመፀኛ ሆኖ የሚያድግ መሆኑን በማወቁ ምክንያት ያንን እንዳደረገ ተነግሯል፡፡ በዚህም ሁኔታ ለሙሴ ትምሕርት መስጠቱም ተጽፏል (ሱራ 18፡60-82፣ Sahih Al-Bukhari, Volume 1, Book 3, Number 124)፡፡ ስለዚህ ሙስሊም ወገኖቻችን የገዛ መጻሕፍታቸውን ቢያጠኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ እዚያው ተጽፎላቸዋል፡፡