የምሥራቹን ለሙስሊሞች ለማድረስ ጠቃሚ መረጃዎች

የምሥራቹን ለሙስሊሞች ለማድረስ ጠቃሚ መረጃዎች

 

ማውጫ

መግቢያ  

  1. የእስልምና ታሪክ

1.1.        አረብያ ቅድመ እስልምና  

1.2.        የእስልምና አጀማመር  

1.3.        የነቢዩ ሙሐመድ የመጀመርያው መገለጥ    

1.4.        የነቢዩ ሙሐመድ ስብከት (ጥሪ)  

1.5.        የእስልምና እንቅስቃሴ ከነቢዩ ሙሐመድ ሞት በኋላ  

1.6.        የእስልምና ክፍሎች  

1.7.        የእስልምና መሠረቶች  

1.8.        አምስቱ የእስልምና አዕማዶች  

1.9.        ስድስቱ የእምነት አንቀፆች      

1.9.        የእስልምና መጻሕፍት  

ቁርኣን    

ሐዲስ (ትውፊቶች)  

  1. የእስልምናና የክርስትና ልዩነቶች

2.1.        እግዚአብሔርን በተመለከተ  

2.2.        ኢየሱስን በተመለከተ  

2.3.        መንፈስ ቅዱስ  

2.4.        መጽሐፍ ቅዱስን በተመለከተ  

2.5.        ደህንነትን በተመለከተ  

2.6.        የሰው ልጆችን በተመለከተ  

2.7.        ኃጢኣትን በተመለከተ  

2.8.        ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ሕብረት  

  1. ለሙስሊሞች ወንጌልን ማድረስ

3.1.        ለምንድነው ወንጌልን መስበክ ያለብን?  

3.2.        እንዴት ነው ወንጌልን የምንሰብከው?  

ወንጌልን የምንሰብከው ለ 3 ዓይነት ሰዎች ነው      

3.2.1.         የወንጌል አሰባበክ ዓይነቶች  

3.2.2.         ወንጌልን ለመስበክ የሚያስፈልጉን ነገሮች  

ተጨማሪ ንባቦች  


መግቢያ

እስልምና በዓለማችን ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ከተስፋፉ ሃይማኖቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ወደ 1.6 ቢሊየን የሚሆኑ ሙስሊሞች በዓለም ላይ እንደሚገኙ የሚገመት ሲሆን አብዛኞቹ በመካከለኛው ምስራቅና በሰሜን አፍሪካ ይኖራሉ፡፡

ሙስሊሞች ፈጣሪን በጣም የሚፈሩና መልካም ነገሮችን ለሌሎች በማድረግ የሚያምኑ ሕዝቦች ናቸው፡፡ ልክ እንደ ክርስቲያኖች በፈጣሪ አንድነት፣ በነቢያት፣ በቅዱሳት መጻሕፍት፣ በመላእክት መኖር፣ በሙታን ትንሣኤና በመጨረሻው ፍርድ ያምናሉ፡፡ በፍቅርና በአክብሮት በመቅረብ በእነዚህ ርዕሶች ዙርያ ከነርሱ ጋር ለመወያየት የሚፈልጉትንም ክርስቲያኖች ለመስማት ፍቃደኞች ናቸው፡፡ ስለዚህ ከሙስሊሞች ጋር ያለን ግንኙነት በፍርሃት ወይም በጥርጣሬ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን በፍቅርና በአክብሮት ላይ የተመሠረተ መሆን ይገባዋል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ እንድንወድና የእርሱን የምሥራች መልእክት እንድናደርስላቸው አዞናል፡፡ እርሱ ደግሞ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእኛ ጋር እንደሚሆንና ኃይልን እንደሚሰጠን ቃል ገብቶልናል፡፡ በእርሱ በመታመን የተሰጠንን ይህንን ታላቅ ተልዕኮ ልንወጣ ይገባናል፡፡

ሙስሊሞች ምን እንደሚያምኑና ስለ ፈጣሪ ያላቸው ግንዛቤ ምን እንደሆነ ማወቅ ከእነርሱ ጋር መልካም የሆነ ግንኙነት እንዲኖረንና ሊረዱት በሚችሉት መንገድ ወንጌልን እንድናደርስ ያስችለናል፡፡ ይህ ጽሑፍ ስለ እስልምና እንዲሁም ስለ ሙስሊሞች መሠረታዊ የሆኑ ግንዛቤዎችን ያስጨብጣችኋል፤ ስለ እስልምናም የበለጠ ጥናት ማድረግ እንድትችሉ ያነሳሳችኋል፡፡ ከሙስሊሞች ጋር በፍቅርና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ስለ ክርስትና እንዴት መወያየት እንደምትችሉም አቅጣጫዎችን ይጠቁማችኋል። ውድ አንባቢያን፤ እግዚአብሔር ይህንን ጽሑፍ ተጠቅሞ የምሥራቹን ለሙስሊም ባልንጀሮቻችሁ ታደርሱ ዘንድ እንዲያስታጥቃችሁ ምኞታችንና ጸሎታችን ነው፡፡


1.       የእስልምና ታሪክ

1.1.              አረብያ ቅድመ እስልምና

እስልምና ከመጀመሩ በፊት በአረብ ምድር በጥቂቱ አራት ዓይነት የእምነት ቡድኖች ነበሩ፡

  1. ጣዖታውያን (የጣዖት አምላኪዎች)
  2. ክርስቲያኖች (አብዛኞቹ ከትክክለኛው የክርስትና አስተምሕሮ ያፈነገጡ ነበሩ)
  3. አይሁድ
  4. ሐኒፋ[ዎች] (በአንድ አምላክ መኖር የሚያምኑ በቁጥር አናሳ የነበሩ አረቦች ሲሆኑ በእስላማዊ ምንጮች ውስጥ ተጠቅሰዋል)

ከእስልምና በፊት የነበረው ዘመን በሙስሊሞች ግንዛቤ ጀሐሊያ (የድንቁርና ዘመን) በመባል ይታወቃል (ሱራ 28፡46)፡፡ በጀሐሊያ ዘመን መካ የጣዖት አምልኮ ማዕከል የነበረች ስትሆን 360 ጣዖታት የሚገኙበት ካዕባ የተሰኘ የአምልኮ ቦታ ነበራት፡፡ እያንዳንዱ የአረብ ጎሣ የየራሱን ጣዖት በካዕባ ያመልክ የነበር፡፡ በዚያ ዘመን በአረብያ ይኖሩ የነበሩት ሕዝቦች ከብት በማርባትና በንግድ ነበር ይተዳደሩ የነበሩት፡፡

1.2.              የእስልምና አጀማመር

“ኢስላም” የሚለው የአረብኛ ቃል “መገዛት” (Submission) የሚል ትርጓሜ አለው፡፡ ሙስሊም ሊቃውንት ሲያብራሩት “ለአላህ ፍቃድ መገዛት” ማለት ነው ይላሉ፡፡ በአንፃሩ ደግሞ የሃይማኖቱ ተከታይ መጠርያ የሆነው “ሙስሊም” የሚለው ቃል ቀጥተኛ ትርጉም “የተገዛ” ማለት ሲሆን፤ ሙስሊም ሊቃውንት ሲያብራሩት “ለአላህ ፍቃድ የተገዛ” ማለት ነው ይላሉ፡፡

እስልምና መቼ በማንና እንዴት ተጀመረ? ለሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ ስንሰጥ፡- ይህ ሃይማኖት የተጀመረው በ610 ዓ.ም እ.ኤ.አ ሲሆን ጀማሪው ሙሐመድ አብደላ አብዱልሙጠሊብ የተባሉ መካ በመባል የምትታወቅ ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ የምትገኝ ከተማ ነዋሪ የነበሩ የአረብ ሰው ነበሩ፡፡

ቀደም ሲል እንደገለጽነው መካ በወቅቱ በ360 ጣኦታት የተሞላ ካዕባ የተባለ የማምለኪያ ስፍራ የነበራት ለአካባቢው አረቦች እንደ አምልኮ ማዕከል የምታገለግል ከተማ ነበረች፡፡ በዚያን ዘመን አረብ ጣዖታውያን ከዲንጋይ፣ ከእንጨትና ከብረት የተሠሩ ጣዖቶቻቸውን ወደዚያ ስፍራ በማምጣት ያመልኳቸው ነበር፡፡ ነቢዩ ሙሐመድ ሕይወታቸው ካለፈ ቢያንስ 200 ዓመታት ያህል ዘግይተው በሙስሊሞች የተጻፉት ታሪኮቻቸው እንደሚናገሩት ከሆነ በተፀነሱ በሁለተኛው ወር ወላጅ አባታቸው አብደላ  ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ ህፃኑ ሙሐመድን የማሳደግ ኃላፊነት በትከሻቸው ላይ የወደቀው እናታቸው አሚና ቢንት ወሒብ ገጠር ሐሊማ የተባለች ሴት ዘንድ በማደጎ እንዲቆዩ በመስጠታቸው ሳብያ እስከ አራት ዓመታቸው ድረስ እዚያው ኖሩ፡፡ ከዚህ በኋላ እናታቸው ዘንድ ተመልሰው ጥቂት እንደኖሩ ገና የስድስት ዓመት ህፃን ሳሉ እናታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ ከዚህም የተነሳ በአያታቸው በአብዱልሙጠሊብ (ሸይባህ ኢብን ሐሺም) ዘንድ ለመኖር ተገደዱ፡፡ በቁራይሽ ጎሳ ዘንድ የተከበሩት አያታቸው ሙሐመድን በጣም ይወዷቸውና ይንከባከቧቸው እንደ ነበር በሙስሊሞች የተጻፉት እነዚህ ድርሳናት ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ገና የስምንት ዓመት ህፃን በነበሩ ጊዜ አያታቸው አብዱልሙጠሊብ ሕይወታቸው በማለፉ ሙሐመድ ከአያታቸው ጋር ከሁለት ዓመት በላይ ለመቆየት አልታደሉም፡፡ ቤተሰባዊ እንክብካቤ ሊያደርጉላቸው የሚችሉትን ሰዎች በሞት የተነጠቁት ሙሐመድ እስከ አስራ ሁለት ዓመታቸው ድረስ ሰዎች ዘንድ ተቀጥረው ግመልና ፍየል በመጠበቅ በሚያገኙት ገንዘብ አጎታቸው አቡጧሊብን እየረዱ አብረዋቸው ይኖሩ ነበር፡፡ እድሜያቸው አስራ ሁለት ዓመት ከሞላ በኋላ ከአጎታቸው ጋር ለንግድ ወደሦርያ እንደተጓዙ ከታሪካቸው እንረዳለን፡፡

የነቢዩ ሙሐመድ ሕይወት መቃናት የጀመረው ከቁረይሽ ጎሣ ለነበረች ከድጃ ለተባለች ኃብታም መበለት በውክልና የንግድ እንቅስቃሴ መምራት በጀመሩበት ወቅት ነበር፡፡ በሙስሊሞች የተጻፉት ግለ ታሪኮቻቸው እንደሚናገሩት በታማኝነታቸው የተማረከችው የ40 ዓመቷ ከዲጃ በወቅቱ እድሜያቸው 25 ዓመት ለነበሩት ለሙሐመድ የጋብቻ ጥያቄ በማቅረቧ ሳቢያ በመካከላቸው የነበረው የ15 ዓመታት ልዩነት ሳያግዳቸው ትዳር መሥርተው የከዲጃ ሕይወት እስካለፈበት ዕለት ድረስ ለ25 ዓመታት ያህል አብረው ለመኖር ችለዋል፡፡ ከዚህም ጋብቻ ሙሐመድ ስድስት ልጆችን ያፈሩ ቢሆንም ከሴት ልጃቸው ከፋጢማ በስተቀር ሁሉም እድሜያቸው ከፍ ሳይል በሞት ተቀጭተዋል፡፡

ሙሐመድ ከአጎታቸው ጋርም ሆነ የከድጃን የንግድ እንቅስቃሴ እየመሩ ወደ ተለያዩ ስፍራዎች መጓዛቸው የክርስትና፣ የአይሁድና የዞራስትሪያኒዝም እምነት ተከታዮች ከሆኑ ሰዎች ጋር እንዲገናኙና ስለ እምነታቸው እንዲሰሙ ሰፊ እድል እንደሰጣቸው መገንዘበ እንችላለን፡፡ የነዚህም እምነቶች ተፅዕኖ በእስልምና ሥነ መለኮትና ባሕል ውስጥ በሰፊው ተንጸባርቆ እንመለከታለን።

1.3.              የነቢዩ ሙሐመድ የመጀመርያው መገለጥ

ከከዲጃ ጋር ትዳር ከመሠረቱ በኋላ እንደ ቀድሞው ለንግድ ረጃጅም ጉዞዎችን ማድረግ ያላስፈለጋቸው ሙሐመድ የተረጋጋ ሕይወት መምራት ስለቻሉ መንፈሳዊ ጉዳዮችን በማሰላሰል ጊዜያቸውን ያሳልፉ ነበር፡፡ ይህንን ለማድረግ አመቺ ሆኖ ያገኙት ሒራ የተባለ እዚያው መካ አካባቢ የሚገኝ ዋሻ በመሆኑ ለስድስት ወራት ያህል ወደዚያ ዋሻ በመመላለስ በፆምና በጸሎት ይቆዩ ነበር፡፡ በቀደምት ሙስሊሞች የተጻፉት ግለ ታሪኮቻቸው እንደሚያስረዱት በሒራ ዋሻ ውስጥ ሳሉ ከዕለታት በአንዱ ቀን መልአኩ ጂብሪል (ገብርኤል) ወደ እሳቸው በመምጣት በሱራ 96፡1-5 ላይ የተጻፈውን ቃል “ገለጠላቸው”፡፡ ሙሐመድ በሒራ ዋሻ ውስጥ መጀመሪያ እንደተገለጠላቸው የተናገሩት ቃል እንዲህ የሚል ነበር፡-

አንብብ በዚያ ሁሉን በፈጠረው ጌታህ ስም፡፡ ሰውን ከረጋ ደም በፈጠረው ጌታህ ስም፡፡ አንብብ ጌታህ በጣም ቸር ሲሆን በብዕር ያስተማረ ሰውን ያላወቀውን ሁሉ ያሳወቀ ሲሆን፡፡

ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ለ23 ዓመታት ያህል ጂብሪል “እየተገለጠላቸው” የተለያዩ መገለጦችን ሲያስተምራቸው እንደቆየና እሳቸውም የተገለጠላቸውን ነገር ለተከታዮቻቸው ያስተምሩ እንደነበር ከእስላማዊ ምንጮች እንረዳለን፡፡

1.4.              የነቢዩ ሙሐመድ ስብከት (ጥሪ)

ነቢዩ ሙሐመድ “የተገለጠላቸውን” መልእክት ቀስ በቀስ ለመካ ነዋሪዎች ማስተማር ጀመሩ፡፡ በአገልግሎታቸው የመጀመርያዎቹ ዓመታት ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ የተለያዩ የቅርብ ሰዎቻቸው እስልምናን ተቀበሉ፡፡ የሙሐመድ አስተምህሮ ያተኮረው፡-

  • ስለ ተውሂድ (በፈጣሪ አንድነት ማመን)
  • በዮም አል ቂያማ (የመጨረሻው ፍርድ) ማመን
  • ስለ ሽርክ (የጣዖት አምልኮ ከንቱነት)
  • ስለ ኢባዳ (ለአምላክ ስለሚገባው አምልኮና ክብር)
  • ስለ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ፍትህ
  • አላህ ስለሠራቸው ተዓምራዊ ታሪኮች

ነቢዩ ሙሐመድ እምነታቸውን በግልፅ ማስተማር በጀመሩበት ወቅት በእሳቸውና በመካ ጣዖታውያን መካከል ከፍተኛ አለመግባባት ተፈጠረ፡፡ ከዚህም የተነሳ በሙሐመድና በተከታዮቻቸው ላይ ስደት ተነሳ፡፡ በታሪኮቻቸው መሠረት ሙሐመድ ሚስታቸው ከዲጃና አጎታቸው አቡ-ጧሊብ በመሞታቸው እንዲሁም በቁረይሾች ጥላቻ አዝነው ባሉበት ጊዜ በሌሊት ተዓምራዊ በሆነ ሁኔታ ቡራቅ በተባለ በቅሎ መሳይ እንስሳ ላይ ሆነው ወደ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ እንደሄዱና ከዚያም ወደ ሰማይ ተወስደው ነቢያትን እንዳገኙ፤ በአል አቅሳ መስጊድም በእሳቸው መሪነት ሶላት እንደሰገዱ፤ በቀን አምስት ጊዜ መስገድ የመጣውም ከዚያን ወዲህ እንደሆነ ይነገራል፡፡

ከቁረይሾች ዘንድ ስደት እየበረታባቸው ስለመጣ ነቢዩ ሙሐመድ ከተከታዮቻቸው መካከል የተወሰኑትን ወደ አክሱም የላኩ ሲሆን በወቅቱ ክርስቲያን የነበረው የአክሱም ንጉሥም ጥሩ አቀባበል አድርጎላቸው ከለላ ሰጥቷቸዋል፡፡ ይህ ስደት በሙስሊሞች ዘንድ “የመጀመርያው ሂጅራ” በመባል ይታወቃል፡፡ ወደ አክሱም ከመጡት የመጀመርያዎቹ ሙስሊሞች መካከል ኡቤይዱላህ ኢብን ጃሽ የተባለ የመሐመድ የአክስታቸ ልጅ ወደ ክርስትና እንደተለወጠና እስከ እድሜው መጨረሻ ድረስ እዚሁ ኢትዮጵያ ውስት እንደኖረ የእስልምና ምንጮች ይናገራሉ፡፡

ነቢዩ ሙሐመድ በመካ በነበሩባቸው ጊዜያት አንዳንድ ከቁረይሽ ወገን የነበሩ ሰዎች እስልምናን ስለተቀበሉ ቁረይሾች በጣም ተናደው ነቢዩን ሊገድሏቸው ስለወሰኑ በ622 ዓ.ም. ከመጀመሪያዎቹ ሙስሊሞች ጋር በወቅቱ ያስሪብ ተብላ ወደምትታወቀው ወደ መዲና ተሰደዱ፡፡ ይህም በጊዜው ለከተማዋ መረጋጋትን ስለፈጠረ የሙሐመድን መምጣት የመዲና ሰዎች በአዎንታዊ መልኩ ነበር የተቀበሉት፡፡ የተከታዮቻቸውም ቁጥር ከቀድሞው ከፍ አለ፡፡ ይህ ስደት “ሂጅራ” በመባል የሚታወቅ ሲሆን ኋላ ላይ 622 ዓ.ም የእስልምና ካላንደር መጀመሪያ ለመሆን በቅቷል፡፡

1.5.              የእስልምና እንቅስቃሴ ከነቢዩ ሙሐመድ ሞት በኋላ

ከነቢዩ ሞት በኋላ እስልምና በአረብያ ምድርና በዙርያው ባሉት አገራት በፍጥነት ተስፋፋ፡፡ ለዚህ ደግሞ ከእሳቸው በኋላ የተነሱ ኻሊፎች (የሙሐመድ ተተኪ መሪዎች) አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር፡፡ ከሙሐመድ ሞት በኋላ አራት ኸሊፎች ተነስተዋል፡-

አቡበከር ሲዲቅ (632-634)

የእስልምና መሥራች የሆኑት መሐመድ በ632 ባልተጠበቀ ሁኔታ የህልፈታቸው ዜና እንደተሰማ ከመጀመርያዎቹ ሙስሊሞች መካከል አንዱ የሆኑት አማቻቸው አቡ በከር የሙስሊሙን ኡማ የማረጋጋት ኃላፊነት በትከሻቸው ላይ ወደቀ፡፡ አቡ በከር ከመካ የስደት ዘመን ጀምሮ በታማኝነት መሐመድን የተከተሉ የልብ ወዳጃቸው ነበሩ፡፡ የመሐመድ ጨቅላ ሚስት የአይሻ አባትም ነበሩ፡፡ የመሐመድ ሞት ድንገተኛ ስለነበረና የእሳቸውን ቦታ ሊረከብ የሚችል ሰው ስላልተዘጋጀ በሕዝበ ሙስሊሙ ዘንድ ካላቸው ተሰሚነት የተነሳ አዛውንቱ አቡበከር የመጀመርያውን የኸሊፋነት ሥልጣን ተረከቡ፡፡

በሥልጣን ዘመናቸው የሚከተሉትን ጂሃዳዊ ተልዕኮዎች ፈፅመዋል፡-

  • በመሐመድ የጂሃድ ሠራዊት ተገደው የሰለሙ ብዙ ሕዝቦች ከህልፈታቸው በኋላ እስልምናን በመተው ወደ ኋላ ተመልሰው ነበር፡፡ ሌሎች ደግሞ ያለፍቃዳቸው እንዲከፍሉ የተጫነባቸውን ዘካት አቋርጠው ነበር፡፡ አቡበከር እስልምናን የተውትን እነዚህን ሕዝቦች ጂሃድን በማወጅ ወደ እስልምና እንዲመለሱ አድርገዋል፡፡ ዘካትንም እንዲከፍሉ አስገድደዋቸዋል፡፡
  • የእስላም ጦር ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ውጪ አገራት በመዝመት ጂሃዳዊ ወረራዎችን የፈፀመውም በአቡ በከር ዘመን ነበር፡፡ በውጤቱም ከሞላ ጎደል የክርስቲያን ግዛቶች የነበሩት ኢራቅና ሦርያ ሰልመዋል፡፡

ዑመር ኢብኑል ኸጧብ (634-644)

ዑመር የመሐመድ አማካሪና የቅርብ ወዳጅ የነበሩ ሲሆን የመሐመድ ሚስት የሐፍሳ አባትም ነበሩ፡፡ በአገዛዝ ዘመናቸው የሚከተሉትን ጂሃዳዊ ተግባራት ፈፅመዋል፡-

  • ሠራዊት በማደራጀት በአቡበከር የተጀመረውን የጂሃድ ወረራ አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ በዚህም መሠረት ኢራቅ፣ ኢራን፣ ሦርያና ፍልስጥኤም ጠንካራ የእስላም ይዞታዎች እንዲሆኑ አድርገዋል፡፡
  • በእስልምና አስተዳደር ስር የወደቁትን አገራት እስልምና ብሔራዊ ኃይማኖት እንዲሆንና በሸሪኣ እንዲተዳደሩ አድርገዋል፡፡
  • ደቡባዊ ሕንድን በመዝለቅ እንዲሁም በምዕራብ በኩል ኑብያን (ሱዳንን) በእስልምና ቁጥጥር ስር አድርገዋል፡፡
  • ሰሜን አፍሪቃን ሙሉ በሙሉ በእስልምና ቁጥጥር ስር አድርገዋል፡፡ በየአገራቱ የሸሪኣ ፍርድ ቤቶችን በማቋቋም ዳኞችን ሾመዋል፡፡
  • የፖሊስ ኃይልና ወህኒ ቤቶችን አቋቁመዋል፤ ባልሰለሙት ሕዝቦች ላይ (በክርስቲያኖችና በአይሁድ ላይ) ከፍተኛ ግብር ጥለዋል፡፡
  • ክርስቲያኖችና አይሁዶች ከአረብያ እንዲባረሩ አድርገዋል፡፡
  • እስላማዊ የመንግሥት አስተዳደርን በየአገራቱ በመዘርጋት ከአስር ሺህ በላይ መስጊዶችንና እስላማዊ ትምህርት ቤቶችን አቋቁመዋል፡፡
  • በኢየሩሳሌም መስጊድ አስገንብተዋል፡፡
  • በመጨረሻም በአንድ ባርያ ተገድለዋል፡፡ ቀጣዩን ኸሊፋ እንዲመርጡ ኮሚቴ አቋቁመው የነበረ በመሆኑ በኮሚቴው ምርጫ መሠረት በኡሥማን ተተኩ፡፡

ኡሥማን ኢብኑ አፋን (644-656)

ኡሥማን ወደ ኢትዮጵያ ከመጡት ሙስሊም ስደተኞች መካከል አንዱ የነበሩ ሲሆን የመሐመድን ልጅ ሩቂያን አግብተው ነበር፡፡ ቁርአንንም መልክ ለማስያዝ ባደረጉት ጥረት ይታወቃሉ፡፡ የኡሥማን ሥልጣን ላይ መውጣት የመሐመድ አማችና የአጎታቸው ልጅ በነበሩት በአሊ ደጋፊዎች ዘንድ ቁጣን ቀስቅሶ ነበር፡፡ በዚህም ሳብያ የሥልጣን ዘመናቸውን ያሳለፉት በተቃውሞ ቢሆንም የተለያዩ ጂሃዳዊ ተግባራትን ፈፅመዋል፡-

  • ባህር ኃይል በማቋቋም ብዙ አገራትን ተዋግቷል (ኢራን፣ ትንሹ ኢስያ፣ አፍጋኒስታን፣ የሶቭዬት ህብረትን የተወሰነ ክፍል፣ ሩቅ ምስራቅ አገራትን፣ እስፔንን በከፊል፣ ሰሜን አፍሪቃን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር አውለዋል)፡፡
  • ቢዛንታይኖች የተነጠቋቸውን ግዛቶች ለማስመለስ ያደረጉትንም ጥረት አምክነዋል፡፡
  • በመጨረሻም ኡሥማን በቤታቸው ሳሉ በተቃዋሚዎቻቸው ተገድለዋል፡፡

አሊ ኢብኑ አቡጧሊብ (656-661)

አሊ የመሐመድ የአጎት ልጅና የልጃቸው የፋጢማ ባል ነበሩ፡፡ “በትክክል የተመሩ” ከሚባሉት የሱኒ ኸሊፋዎች መካከል የመጨረሻው ሲሆኑ በሺኣ ሙስሊሞች ዘንድ ደግሞ የመጀመርያው ኸሊፋ ተደርገው ይታሰባሉ፡፡ የአሊ ዘመነ ሥልጣን በእርስ በርስ ጦርነትና በአመፅ የሚታወቅ ቢሆንም ሊጠቀሱ የሚችሉ ጂሃዳዊ እንቅስቃሴዎች ነበሩ፡፡

  • አሊ ከተቡክ ጦርነት በስተቀር በመሐመድ ሕይወት ዘመን በተደረጉት ጂሃዶች ሁሉ ላይ ተሳትፈዋል፡፡
  • የባሕር ኃይላቸውን በመጠቀም ሕንድ ድረስ በመዝለቅ ተዋግቷል፡፡
  • የተወሰኑ የአፍጋኒስታን ክልሎችንም አስልመዋል፡፡

የሺኣ ሙስሊሞች ለሁሴን መታሰብያ ራሳቸውን ሲገርፉ የሚያሳይ ፎቶግራፍ

  • በግዛት ዘመናቸውም በመዲና የነበሩትን አይሁዶች በማጥቃትና ንብረታቸውን በመውረስ ከአገር አባረዋል፡፡
  • ኋላም የማስተዳደር ብቃታቸው ደካማ ስለነበር በሙስሊሙ ሕብረተሰብ መካከል ክፍፍልና አለመረጋጋት ተፈጠረ፡፡ በዚህም ሳብያ ሌሎች ሃገራትን ለመውረር ይደረግ የነበረው ጦርነት ተቋረጠ፡፡
  • አሊ በተቃዋሚዎቻቸው በመገደላቸው ምክንያት እስከዚህ ዘመን ድረስ የቀጠለው የሺኣ እና የሱኒ መለያየት ተጀመረ፡፡

አሊን የሚደግፉ ሙስሊሞች ሺኣ በመባል የሚታወቁ ሲሆኑ የአሊና የፋጡማ ዝርያ የሆነ ወንድ ልጅ ብቻ የሙስሊሞች መሪ መሆን እንዳለበት ያምናሉ፡፡ ከአሊ ልጆች መካከል አንዱ የሆነው ሁሴን በጦርነት የሞተ ሲሆን ሺአዎች በግፍ የተገደለ ሰማዕት እንደሆነ ያምናሉ፡፡ በየዓመቱም ወደ እርሱ መቃብር በመሄድ በማልቀስና ራሳቸውን በመግረፍ መታሰብያ ያደርጉለታል፡፡

1.6.              የእስልምና ክፍሎች

እንደ ማንኛውም ሃይማኖት እስልምናም የተለያዩ ቤተ እምነቶች አሉት፡፡ ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡-

  1. ሱኒ – አሊና ዘሮቹን የማይከተሉ ሙስሊሞች ሱኒ በመባል የሚታወቁ ሲሆን ካለው አጠቃላይ የሙስሊም ሕዝብ ቁጥር 90 ከመቶ የሚሆነውን ይይዛሉ፡፡ የሙስሊሞች መሪ ከሙሐመድ ወገን (ከቁረይሽ ጎሳ) መሆን እንዳለበት የሚያምኑ ሲሆኑ በቀጥታ ውልደት የግድ ከሙሐመድ የዘር ሐረግ መሆን እንዳለበት አያምኑም፡፡ ሱኒዎች የሸሪኣ ህግ ፈጽሞ መለወጥ እንደማይችል ያምናሉ፡፡
  2. ሺኣ – የሺኣ ሙስሊሞች የአሊ ተከታዮች ናቸው፡፡ ከአሊና ከፋጢማ የዘር ሐረግ የሆነ ወንድ ልጅ ብቻ የዓለም ሙስሊሞች መሪ መሆን እንዳለበት ያምናሉ፡፡ ሺኣዎች በብዛት የሚኖሩት በኢራቅ፣ ኢራን፣ ባህሬን እና አዘርባጃን ውስጥ ሲሆን በተጨማሪም ቱርክ፣ የመን፣ ፓኪስታን፣ ሊባኖስ፣ ህንድ እና አፍጋኒስታን ውስጥ በትንሽ መጠን ይገኛሉ፡፡ ሺኣዎች በ832 ዓ.ም. የጠፋውን የካሊፋ አስተዳደር እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡ የሸሪኣ ህግም ሊለወጥ እንደሚችል ወይንም ደግሞ እንደየአካባቢው አውድ ሊስተካከል እንደሚችል ያምናሉ፡፡
  3. ሱፊ – ሱፊዎች ተመስጦን (Misticism) የሚለማመዱ ሙስሊሞች ሲሆኑ ሱኒ እና ሺኣን ከመሳሰሉ የተለያዩ የእስልምና ክፍሎች የመጡ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከፈጣሪያቸው ጋር የግል ሕብረት እንዲኖራቸው ስለሚፈልጉ የተለያዩ መንፈሳዊ ልምምዶችን ይጠቀማሉ፡፡ ሱፊዎች ብዙ ጊዜ ዋሊ በመባል የሚታወቁ መንፈሳዊ መሪዎችን ይከተላሉ፡፡ መንፈሳዊ በረከቶችንም ለማግኘት ቅዱሳን እንደሆኑ ወደሚያምኗቸው ሰዎች መቃብሮች ይሄዳሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች አብዛኞቹ ሱፊዎች ናቸው፡፡
  4. አሕመዲያሚርዛ ጉለም አሕመድ (1835-1908 ዓ.ም.) በተባለ ሰው በፓኪስታን አገር ውስጥ የተጀመረ ሲሆን አሕመዲያዎች ይህንን ሰው የእስልምና አዳሽና ነቢይ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ በአሕመዲያዎች እምነት መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የተሰቀለ ሲሆን ነገር ግን ሳይሞት ተቀብሮ ደቀ መዛሙርቱ ባደረጉለት የህክምና እርዳታ አገግሞ በሕንድና በፓኪስታን ድንበር አካባቢ ወደሚገኙ አይሁዶች ዘንድ በመሄድ ከኖረ በኋላ እንደ ማንኛውም ሰው ተፈጥሯዊ ሞት ሞቷል፡፡ እነዚህ የእምነት ቡድኖች የተለያዩ ጽሑፎችን እና ሚድያዎችን በመጠቀም በዓለም ላይ እስልምናን ለማስፋፋት በሚደረግ እንቅስቃሴ ግንባር ቀደሙን ሚና ይጫወታሉ፡፡ ባለፉት ሃምሳና ስድሳ ዓመታት ውስጥ በሙስሊሞች ስለክርስትና የተጻፉ አብዛኞቹ ጽሑፎች በነዚህ ቡድኖች የተዘጋጁ ናቸው፡፡ በዘመናችን የሚገኙ ብዙ ሙስሊም ምሁራን የኢየሱስን ስቅለት በተመለከተ “ስውን ቲዎሪ” በመባል የሚታወቀውን ይህንን የአሕመዲያዎች መላ ምት ያስተጋባሉ፡፡
  5. ባሕላዊ እስልምና (Folk Islam) – ይህ የእስልምና ክፍል የእስልምናና የባሕላዊ ሃይማኖቶች ቅይጥ ሲሆን ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ባላቸው አንዳንድ የአፍሪካ ማህበረሰቦች ውስጥ የተስፋፋ ነው፡፡ እነዚህ ሙስሊሞች መንፈሳዊ ኃይላትን የሚፈሩ ሲሆኑ ጥንቆላ፣ ድግምት፣ መተት፣ እርግማንና በመሳሰሉት ነገሮች ያምናሉ፡፡ በሕይወታቸው ውስጥም ችግሮች ሲገጥሟቸው ወደ ጠንቋዮችና ወደ ባሕላዊ ኃኪሞች ዘንድ ይሄዳሉ፡፡
  6. ተራማጅ (ለዘብተኛ) እስልምና (Modernist or Liberal Islam) – እነዚህ እስልምና ከዘመናዊው ዓለም ጋር መሄድ እንዲችል ለውጥ ያስፈልገዋል በማለት የሚያምኑ ሙስሊሞች ናቸው፡፡ እስልምና ከየትኛውም ፖለቲካ የፀዳ መሆን እንዳለበትና የማንኛውም ሰው መብት በእኩል ሁኔታ የተከበረ መሆን እንዳለበት ያምናሉ፡፡ ማንኛውም ሰው የፈለገውን ሃይማኖት የመምረጥ መብቱም የተከበረ መሆን እንዳለበት ይናገራሉ፡፡ ብዙዎቹ ተራማጅ አስተሳሰብ ያላቸው ሙስሊሞች በምዕራባውያን አገራት ውስጥ በስደት የሚኖሩ ናቸው፡፡
  7. አክራሪ እስልምና (Radical Islam) – እነዚህ ከጠቅላላው ሕዝበ ሙስሊም አኳያ በቁጥር አነስተኛ ሲሆኑ እስልምና በጂሃድ ጦርነት መስፋፋት እንዳለበት የሚያምኑ ናቸው፡፡ እውነተኛ ሙስሊሞች አይደሉም ብለው በሚፈርጇቸው ሙስሊም መንግሥታትም ላይ አመፅን ይቀሰቅሉ፡፡ ባሕላዊ ሙስሊሞችን ጨምሮ ሌሎች የሃይማኖት ቡድኖች በሙሉ መወገድ እንዳለባቸው ያምናሉ፡፡

1.7.              የእስልምና መሠረቶች

እስልምና የሥራ ኃይማኖት ነው፡፡ ሙስሊሞች ሲሞቱ መልካም ሥራቸው ከክፉ ሥራቸው ጋር ሚዛን ላይ እንደሚቀመጥና መልካም ሥራቸው በልጦ ከተገኘ ወደ ገነት እንደሚገቡ ነገር ግን መጥፎ ሥራቸው በልጦ ከተገኘ ወደ ዘላለም እሳት እንደሚሄዱ ያምናሉ፡፡ ከዚህ የተነሳ ሙስሊሞች ገነት መግባት አለመግባታቸውን እርግጠኞች ሆነው ማወቅ አይችሉም፡፡

1.8.              አምስቱ የእስልምና አዕማዶች

ወደ ገነት ለመግባት ሙስሊሞች አምስት ነገሮችን ማድረግ እንዳለባቸው ያምናሉ፡-

  1. ሸሃዳ ሸሃዳ ማለት የእምነት መግለጫ ማለት ነው፡፡ አንድ ሰው ሙስሊም ለመሆን “ላኢላ ሀኢለላ ሙሐመደን ረሱልአላህ” (ከአላህ በስተቀር አምላክ የለም ሙሐመድም ደግሞ መልእክተኛው ናቸው) ብሎ መናገርና የተናገረውን ደግሞ በፍጹም ልቡ ማመን አለበት፡፡

  1. ሰላት ሰላት ማለት ጸሎት ማለት ነው፡፡ አንድ ሙስሊም በቀን አምስት ጊዜ ወደ መካ ዞሮ መጸለይ ይጠበቅበታል፡፡ የስግደት አቅጣጫውም ቂብላ ይሰኛል፡፡ ሙስሊሞች ከመጸለያቸው በፊት የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቻቸውን መታጠብ አለባቸው፡፡
  2. ፆም ሙስሊሞች በእስልምና ካሌንደር መሠረት ዘጠነኛውን ወር በፆም ያሳልፋሉ፡፡ ይህንንም ወር ረመዳን በማለት ይጠሩታል፡፡ መልአኩ ጂብሪል በዚህ ወር ውስጥ ለነቢዩ ሙሐመድ እንደተገለጠላቸው ያምናሉ፡፡ በፆም ወቅትም ፀሐይ ወጥታ እስክትጠልቅ ድረስ ምግብ መብላት፣ ውሃ መጠታትም ሆነ የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈፀም ክልክል ነው፡፡
  3. ዘካት ዘካት ግዴታ ምፅዋት ነው፡፡ ሙስሊሞች እስልምናን ለመደገፍና የተቸገሩ ሙስሊሞችን ለመርዳት ምፅዋት የመስጠት ግዴታ አለባቸው፡፡ የሱኒ ሙስሊሞች ካላቸው አመታዊ ገቢ ከመቶ5 እጅ መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡

    ለሐጅ የሄዱ ሙስሊሞች በካዕባ ዙርያ

  1. ሐጅ ሐጅ ወደ መካ የሚደረግ ሃይማኖታዊ ጉዞ ሲሆን በእልምና ካሌንደር መሠረት በአስራ ሁለተኛው ወር ላይ የሚደረግ ነው፡፡ በሐጅ መቅት ሙስሊሞች በመካ የሚገኘውን የኪዩብ ቅርፅ ያለውን ጥቁር ዲንጋይ ሰባት ጊዜ ይዞራሉ፡፡ ወደ መካ የሐጅ ጉዞ ያደረገ ሰው በሙስሊም ሕብረተሰብ መካከል ከበሬታ ይሰጠዋል፤ “ሐጂ” በሚል ማዕረግም ይጠራል፡፡

1.9.              ስድስቱ የእምነት አንቀፆች

አንድ ሙስሊም ተከታዮቹን ስድስት ነጥቦች ማመን ይኖርበታል፦

  1. በአላህ አንድነት – ይህ እምነት “ተውሂድ” ይሰኛል፡፡
  2. በመላዕክት
  3. በቅዱሳት መጻሕፍት
  4. በነቢያት
  5. በመጨረሻው የፍርድ ቀን
  6. ሁሉ ነገር አስቀድሞ የተወሰነ መሆኑን (Predestination)

1.9.              የእስልምና መጻሕፍት

ቁርኣን

በሙስሊሞች እምነት መሠረት ቁርኣን ፍፁም የሰው እጅ ያልገባበት ከአላህ ዘንድ በቀጥታ የወረደ መገለጥ ነው፡፡ ይህንንም መገለጥ ናዚል ወይም ተንዚል በማለት ይጠሩታል፡፡ ይህ መጽሐፍ ነቢዩ ሙሐመድ በ23 ዓመታት የአገልግሎት ዘመናቸው በመልአኩ ጂብሪል በኩል ከአላህ ዘንድ እየወረደላቸው ያስተማሯቸው ቀጥተኛ የአላህ ንግግሮች ስብስብ እንደሆነ በሙስሊሞች ዘንድ ይታመናል፡፡ የመጽሐፉ እናት የተባለ ያልተፈጠረ ገነር ግን አላህ በነበረበት ጊዜ ሁሉ ከርሱ ጋር የነበረ በወርቅ ሰሌዳ ላይ የተጻፈ ጽሑፍ እንዳለና ቁርኣን ደግሞ የዚያ ግልባጭ እንደሆነም ያምናሉ፡፡ በእርግጥ ቁርኣን ስለመጽሐፉ እናት ጥቆማ ይስጥ እንጂ ስለምንነቱ በደንብ አያብራራም (ሱራ 13፡39)፡፡ ነገር ግን ይህንን በተመለከተ ያለው የአብዛኞቹ ሙስሊሞች እምነት ከላይ የተቀመጠው ነው፡፡

የቁርኣንን አሰባሰብ በተመለከተ በአማርኛ ቁርኣን መቅድም ላይ ተጽፎ የሚገኝ ሐሳብ እንዲህ ይላል፡-

ቁርኣን በብራናም በሰሌዳም በአጥንትም በሰሌንም በስስ ድንጋዎችም ላይ የአያቶቹ ተራ ተጠብቆ ተጽፎ በነቢዩ ቤት ይቀመጥ ነበር፡፡ ብዙዎቹ ምዕመኖች በቃላቸው አጥንተውት ሲኖሩ ከነቢዩ እረፍት በኋላ 12 ዓመተ ስደት በየማማህ በተደረገው ጦርነት በቃላቸው ካጠኑት ብዙዎቹ ስለአለቁ በመስጋት በዑመር አልኸጣብ  አስታዋሽነት አቡበክር አልሲዲቅ ዘይድ ሣቢትን አዘው ጽሑፎቹንና በቃል ያጠኑትን እያመሣከረ የአያቶቹን ተራ ጠብቆ ከአንድ ዓመት በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ በአንድ ጥራዝ ሰበሰበው። ስም አውጡለት ተብሎ ገሚሶቹ ሲፍር ይባል ሲሉ ይህ የአይሁድ አጠራር መሆኑን ጠልተው የሐበሻ (ኢትዮጵያ) ሰዎች መሰሉን መጽሐፍ ይሉታል በማለት መጽሐፍ ብለው ጠሩት ማለትን ኢትቃን 189 ገፅ ላይ ያስረዳል፡፡

ዳግመኛ ኸሊፋ ኡስማን 25 ዓመት ስደት ባነባበቡ ግጭት ስለተገኘ በአራት የቁርኣን ሊቃውንት በተከናወነ ጉባኤ የቃላቱን አጻጻፍ ያለነጥብ ለየንባቡ ተስማሚ አድርገው በመጀመርያው አወራረድ መሠረት የሱራዎቹን ተራ ጠብቀው ሰበሰቡት፡፡ ኸሊፋውም በአምስት ኮፒዎች አጽፎ አንዱን ለራሱ አስቀርቶ አራቱን ለመካና ለደማስቆ ለባስራ ለኩፋ ከተሞች ልኮ ማንኛው ሰው ከነዚ ብቻ እንዲገለብጥ አድርጎ የቀረውን ስላቃጠለው ቁርኣን አንድነቱን ጠብቆ ይኖራል እስከ አሁንም ምንም መለዋወጥ አልደረሰበትም፡፡

ቁርኣን 114 ሱራዎች (ምዕራፎች) ያሉት ሲሆን የአንቀፆቹ (የቁጥሮቹ) ብዛት ደግሞ 6236 ናቸው፡፡ በየጊዜው ለማንበብ እንዲያመች በሰላሳ ክፍሎች ተከፍሏል፡፡ እነዚህም ክፍሎች ጁዝዕ ይባላሉ፡፡ 79 የሚያህሉ ምዕራፎች በመክፈቻቸው ላይ በሚገኙ ቃላት የተሰየሙ ሲሆኑ 35 የሚሆኑት ደግሞ በውስጣቸው በሚገኙ ቃላት ተሰይመዋል፡፡

የቁርኣንን ምዕራፎች አቀማመጥ ስንመለከት በጊዜ ቅዳም ተከተል (chronological sequence) የተቀመጡ ሳይሆኑ ከሞላ ጎደል ከረጅሙ ወደ አጭሩ ምዕራፍ የተደረደሩ ናቸው፡፡ ከመጀመሪያው “አልፈቲሃ” (የመክፈቻይቱ ምዕራፍ) ውጪ ያሉት ምዕራፎች ሁሉ አቀማመጣቸው በዚሁ መልኩ እንዲሆን የታሰበ ይመስላል፡፡

ሙስሊሞች ለቁርኣን ያላቸው ከበሬታ እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡ ባልነጻ እጅ ሊነኩት አይደፍሩም፡፡ በብዙ ሙስሊሞች ቤት ለቁርኣን የተለየ ማስቀመጫ ይገኛል፡፡ ከሌሎች ቁሳቁሶች በላይም ከፍ አድርገው ያስቀምጡታል፡፡ በእጆቻቸው ሲይዙትም ከወገባቸው በታች አያደርጉትም፡፡

ሐዲስ (ትውፊቶች)

ከነቢዩ ሙሐመድ ሞት በኋላ የተለያዩ የቁርኣን አንቀፆችን አውድ ለመረዳት ነቢዩ የተናገሯቸውንና ያደረጓቸውን ነገሮች ማወቅ እጅግ አስፈልጎ ነበር፡፡ ከዚህ የተነሳ በአፈ ታሪኮች ተጠብቀው የቆዩትን የነቢዩን ንግግሮችና ታሪኮች አንድ ላይ ለመሰብሰብና ለመጻፍ ሙስሊም ሊቃውንት ጥረቶችን አደረጉ፡፡ የተሰበሰቡ ወጎችና ታሪኮች “ሐዲስ” በመባል ይታወቃሉ፡፡ እነዚህን ወጎችና ታሪኮች የማሰባሰብ ሥራ የተደረገው ነቢዩ ካረፉ ከ250-300 ዓመታት በኋላ ነበር፡፡ ይህንን ኃላፊነት ከተወጡ ሰዎች መካከል በይበልጥ ታዋቂ የሆኑት አል-ቡኻሪ በመባ የሚታወቁ ሰው 600,000 ያህል ሐዲስ ሰብስበዋል፡፡ በጥንቃቄ መርምረው ከመረጧቸው በኋላም 7200ዎቹን በማጽደቅ ሌሎቹን ተአማኒነት የሌላቸው በመሆናቸው በመጽሐፋቸው ውስጥ ሳያካትቷቸው አለፉ፡፡

የሐዲስ ተዓማኒነት የተመሠረተው ትውፊቱን ያስተላለፉ ሰዎችን የዘር ሐረግ በማረጋገጥ ነው፡፡ መረጃውን ያስተላለፉ ሰዎች ምን ያህል የሚታመኑ ናቸው? በመጀመርያ ለነርሱ የ

ተናገሩ ሰዎች ከሙሐመድ ተባባሪዎች (ሰሃባዎች) የሚመደቡ ነበሩን? በመጨረሻም እስከ ተመዘገበበት ጊዜ ድረስ እነዚህን ትውፊቶች ያስተላለፉ ሰዎች እነ ማን ነበሩ? የሚሉ ጥያቄዎች የአንድን ሐዲስተ ዓማኒነት ለማረጋገጥ ወሳኞች ነበሩ፡፡

በሱኒ ሙስሊሞች ዘንድ ይበልጥ አስተማማኝ እንደሆኑ የሚታመንባቸው የሐዲስ ስብስቦች 6 ሲሆኑ እነርሱም፡-

  1. ሳሂህ አል-ቡኻሪ
  2. ሳሂህ ሙስሊም
  3. ሱናን አቡ ዳውድ
  4. ሱናን ኢብን ማጃህ
  5. ሱና አን-ናሳዒ
  6. አሚያት ቲርሚዝ ናቸው።

2.     የእስልምናና የክርስትና ልዩነቶች

እስልምናና ክርስትና ብዙ የሚያመሳስሏቸው ነገሮች ቢኖራቸውም ነገር ግን በዚያው መጠን ልዩነታቸው የሰፋ ነው፡፡ ክርስቲያኖችና ሙስሊሞች በአንድ አምላክ፣ በመላእክት፣ በነቢያት፣ በቅዱሳት መጻሕፍት፣ በሙታን ትንሣኤ፣ በመጨረሻው ፍርድና በመሳሰሉት ነገሮች ያምናሉ፡፡ ነገር ግን ወደ ዝርዝር ሁኔታዎች ሲገባ በነዚህ ነገሮች ሁሉ ላይ የማይስማሙባቸው የተለያዩ ነጥቦች ይከሰታሉ፡፡

2.1.              እግዚአብሔርን በተመለከተ

የክርስቲያኖች እምነት

በክርስቲያኖች እምነት መሠረት እግዚአብሔር ሥላሴ ነው፡፡ ሥላሴ ማለት አንድነት በሦስትነት ማለት ነው፡፡ በሌላ አባባል እግዚአብሔር በሦስት አካል ያለ አንድ መለኮት ነው ማለት ነው፡፡ እነዚህ የእግዚአብሔር አካላት አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ ናቸው፡፡ ይህ ነገር ለመረዳት እጅግ ያዳግታል ሆኖም በእምነት እንቀበለዋለን፡፡ ይህንን በጥሩ ሁኔታ ከሚደግፉልን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች መካከል ማቴዎስ 28፡19 እና 2 ቆሮንቶስ 13፡14 ሲሆኑ በርካታ የብሉይና የአዲስ ኪዳን ጥቅሶችም አሉ፡፡

 ሙስሊሞች የሚያምኑት

ሙስሊሞችም አንድ አምላክ ብቻ እንዳለ ያምናሉ፡፡ ይህም የሃይማኖታቸው እጅግ ወሳኙ የእምነት ክፍል ነው፡፡ እምነታቸውን ሲያውጁም “ከአላህ በቀር አምላክ የለም . . . ” በማለት ነው፡፡ ነገር ግን አንድ አምላክ በሦስት አካላት ሊሆን እንደሚችል አያምኑም፡፡ እንዲያ ማሰብ ለእነርሱ እጅግ በጣም የሚያስደነግጥና የኃጢአት አስተሳሰብ ነው፡፡ አብዛኞቹ ሙስሊሞች ክርስቲያኖች ስለ ሥላሴ ምን እንደሚያምኑ አስበው ግራ ይጋባሉ፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ እግዚአብሔር አባት፣ ማሪያም እናት እና ኢየሱስ ደግሞ የእነርሱ ልጅ እንደሆነ ይመስላቸዋል፡፡

በተጨማሪም እግዚአብሔርን ፈፅመው አባት ብለው አይጠሩትም፡፡ ቁርኣን አላህ የማንም አባት እንዳልሆነ ይናገራል፡፡ አንድ ሰው ከአላህ ጋር የቀረበ ግንኙነት ከማድረጉ የተነሳ አባት ብሎ ሊጠራው መቻሉ እንኳንስ ሊታሰብ ሊታለም የማይችል ነገር ነው፡፡

2.2.              ኢየሱስን በተመለከተ

የክርስቲያኖች እምነት

እንደ ክርስቲያኖች እምነት ኢየሱስ ክርስቶስ የሥላሴ ሁለተኛው አካል ነው፡፡ ሁልጊዜም ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ነበር፡፡ ወደ ምድር መጣ፣ ከድንግል ማሪያም ተወለደ እናም እንደ ሰው ኃጢአት የሌለበትን ሕይወት ኖረ፡፡ ለሰው ልጆች የኃጢዓት ሥርየት ለመሆን ሲል በመስቀል ላይ ሞተ፡፡ ከዚያ በኋላ ከሙታን ተነስቶ ወደ ሰማይ አረገ፡፡ በሰው ልጆች ሁሉ ላይ ለመፍረድም ወደምድር ተመልሶ ይመጣል፡፡

የሙስሊሞች እምነት

ሙስሊሞች ኢየሱስን አምላክ ወይም የእግዚአብሔር ልጅ ብለው አይጠሩትም፡፡ ነገር ግን ኢየሱስን እንደ ትልቅ ነቢይ ያከብሩታል፤ ኢየሱስ በማለት ፋንታም ዒሳ ብለው ይጠሩታል፡፡ ወደ ምድር የመጣውም ወደ ሙሐመድ ለማመላከት ብቻ ነው ይላሉ፡፡ ከድንግል ማሪያም መወለዱ ላይ ከክርስቲያኖች ጋር ይስማማሉ ነገር ግን በመስቀል ሞት መሞቱን እና በሶስተኛውም ቀን ከሙታን መነሳቱን አያምኑም፡፡ ሙስሊሞች ኢሳ ሙስሊም ሆኖ እንደሚመለስና ክርስቲያኖችን ሁሉ አስልሞ መስቀሎችን ሁሉ እንደሚሰባብር ያምናሉ፡፡

2.3.              መንፈስ ቅዱስ

ክርስቲያኖች እምነት

መንፈስ ቅዱስ የሥላሴ ሦስተኛው አካል ሲሆን እግዚአብሔር ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ወደ ምድር የተላከው ክርስቶስ በምድር ሳለ የጀመረውን ሥራ ለመቀጠል ነው፡፡ ዓላማውም እኛን መምራትና ወደ ኢየሱስ ማመላከት ነው፡፡

በ1 ቆሮንቶስ 12 እንደተፃፈልን ደግሞ መንፈሳዊ ስጦታዎችንም ይሰጠናል፡፡ በገላቲያ 5 እንደተፃፈው በአስተሳሰባችንና በአኗኗራችን የበለጠ ኢየሱስን እንድንመስል ያግዘናል፡፡

የሙስሊሞች እምነት

ቁርአን አንዳንዴም “ቅዱስ መንፈስ” ብሎ ስለሚጠራው “መንፈስ” ይናገራል፡፡ ነገር ግን አብዛኞቹ ሙስሊሞች ይህ የሚያመለክተው መልአኩ ገብርኤልን እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ሙስሊሞች ለነቢዩ ሙሐመድ የተገለጠውና የቁርአንን መልዕክቶች የሰጣቸው መልአኩ ገብርኤል ነው ብለው ያምናሉ፡፡

2.4.              መጽሐፍ ቅዱስን በተመለከተ

የክርስቲያኖች እምነት

መጽሐፍ ቅዱስ ለሰዎች የመጣ የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ እግዚአብሔር ብሉይ ኪዳንንም ሆነ አዲስ ኪዳንን ለመጻፍ ብዙ የሰው ጸሐፊዎችን ተጠቅሟል፤ ነገር ግን ሁላቸውም በጻፉበት ጊዜ በእግዚአብሔር መንፈስ ተመርተው ነበር፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የማይሻርና የማይለወጥ ተብሎ ተጠርቷል፡፡ እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሙሉ በሙሉ እውነትና ያለስህተት ነው ማለት ነው፡፡ አንዳች ነገር በላዩ መጨመር ወይም ከላዩ መቀነስ አይቻልም፡፡

ሙስሊሞች እምነት

ሙስሊሞች አላህ ለእስራኤል ልጆች ቶራህን (አምስቱን የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት)፣ መዝሙርንና ወንጌልን እንደሰጠ ያምናሉ፡፡ የመጀመሪያዎቹ ቅዱሳት መጽሐፍትም እነርሱ ናቸው፡፡ ነገር ግን አይሁዳውያንና ክርስያቲኖች ሆነ ብለው መጽሐፍ ቅዱስን እንደቀየሩት ያምናሉ፡፡ በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ፈፅሞ መታመን እንደሌለበት ያስባሉ፡፡

ሙስሊሞች እጅግ በጣም የተቀደሰ የሆነው ቁርአናቸው ለሰው ልጆች ከአላህ የተላከ የመጨረሻ መመሪያና ትዕዛዝ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ቁርአን የአላህ ቃላት በቀጥታ በመልአኩ ገብርኤል በኩል አልፈው በነቢዩ ሙሐመድ ትውስታ ውስጥ የተከተቡበት እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ቁርአን መጽሐፍ ቅዱስን እንደተካውም ያምናሉ፡፡  

2.5.              ደህንነትን በተመለከተ

የክርስቲያኖች እምነት

ደህንነት ማለት ከኃጢአታችን የተነሳ ከሚደርስብን ዘለዓለማዊ ቅጣት መትረፍ ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለወደደን አንዳችንም የማይገባን ብንሆንም እንኳ የመዳንን ነፃ ስጦታ ሰጠን፡፡ ይህም በፀጋ መዳን ተብሎ ይታወቃል፡፡ ይህንን የመዳን ፀጋ ማግኘት የሚቻለውም የሥላሴ ሁለተኛ አካል በሆነውና ይቅርታን እናገኝ ዘንድ ስለበደላችን በሞተው በክርስቶስ ኢየሱስ አማካይነት ብቻ ነው፡፡ መዳን እንደክፍያ የሚሰጥ ነገር ስላልሆነ ሥራ ሰርተን አናገኘውም፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ስናምን ኃጢአታችን ይቅር ተብሏል የዘላለም ህይወትንም ተቀብለናል፡፡

ሙስሊሞች እምነት

ሙስሊሞች ኢየሱስ ለኃጢአታችን ስርየት እንደሞተ አያምኑም፡፡ የሚያምኑት አላህ መሀሪ እንደሆነና ሁሉንም ኃጢአቶች በፈለገ ጊዜ ብቻ ይቅር እንደሚል ነው፡፡ በእስልምና ደህንነት በሥራ የሚገኝ ነገር ነው፡፡ ሙስሊሞች ወደ ገነት ለመግባት መልካም ነገር በማድረግ እና የአላህን ህግጋት በመታዘዝ ይገባቸዋል፡፡ የአንድ ሙስሊም ሕይወት በምታበቃበት ጊዜ መልካም ሥራው ከክፉ ሥራው በልጦ ከተገኘ በቀጥታ ወደገነት ይገባል፡፡ ነገር ግን አብዛኛዎቹ ሙስሊሞች ወደገነት ከመግባታቸው በፊት ስለክፉ ሥራቸው ወደሚቀጡበት አንዳች ስፍራ እንደሚሄዱ ያምናሉ፡፡

2.6.              የሰው ልጆችን በተመለከተ

ክርስቲያኖች እምነት

ሰዎች በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጥረዋል፡፡ ሁላችንም በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት እኩል ነን፡፡ አዳም እግዚአብሔርን ባለመታዘዙ ምክንያት ኃጢአት ወደምድር ስለገባ (ሮሜ 5፡12) ሁላችንም ኃጢአተኞች ሆንን፡፡ ኃጢአት ከእግዚአብሔር ይነጥለናል፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ለማደስና የኃጢአት ስርየት ለማግኘት የምንችልበት መንገድ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የሠራውን ሥራ ኃይል በማመን ብቻ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር በግላችን ህያው የሆነ ሕብረትን ማድረግ እንችላለን፡፡

ሙስሊሞች እምነት

ሙስሊሞች በእግዚአብሔር አምሳል እንደተፈጠርን አያምኑም፡፡ ሰዎች ኃጢአተኛ ሆነው እንደሚወለዱ አያምኑም፡፡ መልካም ሥራን መሥራት ኃጢአትን እንደሚያጣፋ ያምናሉ፡፡ በተጨማሪም ሙስሊሞች አላህ እጅግ ቅዱስና ሊቀረብ የማይችል እንደሆነ ያምናሉ፡፡

2.7.              ኃጢኣትን በተመለከተ

ክርስቲያኖች የሚያምኑት

ኃጢኣት በእግዚአብሔር ቅዱሳን ሕግጋት ላይ ማመጽ ነው ስለዚህ እግዚአብሔር ኃጢኣትን ሳይቀጣ አያልፍም፡፡ የኃጢኣት ደመወዝም የዘላለም ሞት ነው፡፡ የመጀመርዎቹ ሰዎች ከገነት የተባረሩት ኃጢኣት በመሥራታቸው ምክንያት ነበር፤ ስለዚህ የሰው ዘሮች ሁሉ በኃጢኣት የተበከለ ማንነት አላቸው፡፡ የሰው ልጆች የእግዚአብሔርን የቅድስና መስፈርት በማሟላት ራሳቸውን ከዘለዓለም ፍርድ ማዳን ስለማይችሉ ቤዛ (ምትክ) ያስፈልጋቸዋል፡፡ እግዚአብሔር የኃጢኣታችንን እዳ በመክፈል ይዋጀን ዘንድ አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ልኳል፡፡ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የእርሱን ጽድቅ ስለሚለብስ ከኃጢኣት ዕዳ ነጻ ነው፡፡ በእርሱ የማያምን ግን የራሱን የኃጢኣት እዳ እንዲከፍል ስለሚጠበቅበት ወደ ዘለዓለም ሞት ይሄዳል፡፡

ሙስሊሞች የሚያምኑት

ሙስሊሞች ኃጢኣትን ለዘለዓለም ከእግዚአብሔር እንደሚለይ ነገር ሳይሆን እንደ ስህተት ነው የሚቆጥሩት ስለዚህ ሰዎች መልካም ሥራዎችን በመስራት የራሳቸውን የኃጢኣት ዕዳ መክፈል እንደሚችሉ ያምናሉ፡፡ እያንዳንዱ ሰው የራሱን የኃጢኣት እዳዎች መልካም ሥራዎችን በመሥራት የመፋቅ ግዴታ አለበት፡፡ በመጨረሻው የፍርድ ቀን የእንዳንዱ ሰው መልካም ሥራዎችና ክፉ ሥራዎች በሚዛን ላይ ይቀመጣሉ፡፡ አላህ ለሰው ልጆች ምንም ዓይነት ቤዛ አላዘጋጀም፡፡ የሰው ልጆች ከገነት ለመባረራቸው ኃጢኣት ምክንያት ቢሆንም ነገር ግን ሰዎች ወደ ምድር የመጡት ለፈተና ነው፡፡ በዚህች ምድር ላይ ያለውን ፈተና ማለፍ የቻሉ ሰዎች ወደ ገነት ይገባሉ፡፡

2.8.              ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ሕብረት

ክርስቲያኖች የሚያምኑት

በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑ ክርስቲያኖች ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው፡፡ ይህ የልጅነት መብት የሚገኘው በእግዚአብሔር አንድያ ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ዳግመኛ በመወለድ ነው፡፡

ሙስሊሞች የሚያምኑት

ሙስሊሞች የአላህ ልጆች እንደሆኑ አያምኑም፡፡ ከዘጠና ዘጠኙ የአላህ መልካም ስሞች መካከል አባት የሚል የለበትም፡፡ ስለዚህ ሙስሊሞች ከአላህ ጋር ያላቸው ሕብረት የጌታ እና የባር እንጂ የአባት እና የልጅ አይደለም፡፡ አላህን አባት ብሎመጥራት ከባድ ኃጢኣት እንደሆነም ይሰማቸዋል፡፡

3.     ለሙስሊሞች ወንጌልን ማድረስ

ወንጌል የሚለው ቃል ኢዋንጌሊዮን ከሚል የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጓሜውም የምሥራች ወይም መልካም ዜና ማለት ነው፡፡ የምሥራቹ ደግሞ የክርስቶስ አዳኝነት ነው፡፡ ወንጌልን ማዳረስ ማስጠንቀቅ፣ ማብራራት እና ጥሪን ያጠቃልላል፡፡

  • ሰዎችን ስለ ኃጢዓትና ስለ ውጤቱ ማስጠንቀቅ (ዮሃ. 16፡8፣ ሐዋ. 24፡25፣ ራዕ. 20፡11-15)
  • እግዚአብሔር ለሰዎች ያዘጋጀውን የቤዛነት መንገድ ማብራራት (ሐዋ. 8፡29-35፣ ሮሜ 3፡21-26፣ 2ቆሮ. 5፡21)
  • ሰዎች በንስሐ እንዲመለሱና በወንጌል እንዲያምኑ ጥሪ ማድረግ (ማር. 1፡15፣ ሉቃ. 13፡1-5፣ ሮሜ 1፡17፣ ሮሜ 10፡9-13)

3.1.              ለምንድነው ወንጌልን መስበክ ያለብን?

ሙስሊሞች በፍቅር እና በአክብሮት ከሚቀርቧቸው ሰዎች ጋር ስለ ፈጣሪያቸው ለመወያት ፍቃደኞች ናቸው!

  • የጌታ ትዕዛዝ ስለሆነ በማቴዎስ 28፡18-20 ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ታላቁን ተልዕኮ ሲሰጣቸው እንመለከታለን፡- ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ። እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።

ደግሞም በሕዝቅኤል 3፡18 ላይ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ በማለት ያስጠነቅቀናል፡- እኔ ኃጢአተኛውን፦ በእርግጥ ትሞታለህ ባልሁት ጊዜ፥ አንተም ባታስጠነቅቀው ነፍሱም እንድትድን ከክፉ መንገዱ ይመለስ ዘንድ ለኃጢአተኛው አስጠንቅቀህ ባትነግረው፥ ኃጢአተኛ በኃጢአት ይሞታል ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ። ነገር ግን አንተ ኃጢአተኛውን ብታስጠነቅቅ እርሱም ከኃጢአቱና ከክፉ መንገዱ ባይመለስ፥ በኃጢአቱ ይሞታል፥ አንተ ግን ነፍስህን አድነሃል።

  • ሰዎችን ከሲኦል ለማዳን ወደ ሞት የሚነዱትን ታደግ ሊታረዱ የተወሰኑትን አድን።ምሳሌ 241
  • ክርስቶስ የሞተለት ዓላማ ስለሆነበእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።ዮሃ. 316
  • ጠቢባን ስለሚያደርገን የጻድቅ ፍሬ የሕይወት ዛፍ ናት፥ ነፍሶችንም የሚሰበስብ እርሱ ጠቢብ ነው።ምሳ. 1130
  • ከጌታ ዘንድ ሽልማትን ስለሚያስገኝልን መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤ ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፥ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፥ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም።(2ጢሞ. 4፡7-8)
  • ድል ነሺዎች ስለሚያደርገን እነርሱም ከበጉ ደም የተነሣ ከምስክራቸውም ቃል የተነሣ ድል ነሡት፥ ነፍሳቸውንም እስከ ሞት ድረስ አልወደዱም።ራዕ. 1211 

3.2.              እንዴት ነው ወንጌልን የምንሰብከው?

ለስብከተ ወንጌል ከመውጣታችን በፊት ወይንም ደግሞ ስለ ወንጌል ከሰዎች ጋር ስንነጋገር አድማጮቻችን ምን ዓይነት ሰዎች እንደሆኑ ልናውቅ ይገባናል፡፡ ሐዋርው ቅዱስ ጳውሎስ ለተለያዩ ሰዎች ወንጌልን ሲሰብክ የተለያዩ አቀራረቦችና ንግግሮችን ይጠቀም እንደነበር እናያለን፡፡ ለአይሁዶች (ሐዋ 13፡13-43)፣ ላልተማሩ አሕዛቦች (ሐዋ 14፡15-17) እና ለተማሩ አሕዛቦች (ሐዋ 17፡18-34) ምን ዓይነት አቀራረቦችና የንግግር ዓይነቶችን ይጠቀም እንደነበር ማየት እንችላለን፡፡ ወንጌልን ስንሰብክ አድማጮቻችን ምን ዓይነት ሰዎች እንደሆኑ በመለየት ምን ዓይነት አቀራረብና ንግግር መጠቀም እንዳለብን መወሰን በጣም አስፈላጊ ነው፡፡

ወንጌልን የምንሰብከው ለ 3 ዓይነት ሰዎች ነው

  1. የጠፉቱ (The Lost) – እነዚህ ክርስቶስን የማያውቁ ስለሆኑ ስለ ክርስቶስ ማንነትና ሥራ ልናብራራላቸው ያስፈልገናል፡፡ ሐዋ 8፡9-13 ሐዋ 17፡16-34
  2. በክርስትና የሃይማኖት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ (Inistitutionalised by Tradition and Religion) – እነዚህ የክርስቶስን ማንነትና ሥራ ያውቃሉ ነገር ግን በሥራቸው እንደሚድኑና ለመዳን የቅዱሳን ሰዎች ምልጃ እንደሚያስፈልጋቸው የሚያምኑ ናቸው፡፡ ክርስትና ለእነርሱ ሕይወት ሳይሆን ውርስና ባሕል ነው፡፡
  3. ወደ ኋላ የተመለሱ (Broken or Displaced) – ክርስቶስን የሚያውቁትና በአንድ ወቅት አማኞች የነበሩ ናቸው፡፡ እነዚህን ሰዎች ለመመለስ የተሰናከሉበትን ምክንያት መጠየቅና መረዳት አስፈላጊ ነው፡፡

ሙስሊሞች ስለ ክርስቶስ ብዙ ነገሮችን የሚያምኑ ቢሆኑም ነገር ግን ትክክለኛውን የእርሱን ማንነት አያውቁም፡፡ ቁርኣን ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን፣ አምላክ መሆኑን፣ ስለ ኃጢዓታችን መሞቱን፣ ደህንነት የሚገኘው እርሱ በመስቀል ላይ የሰራውን ስራ በማመን መሆን እና የመሳሰሉትን ወሳኝ እውነቶች ስለሚክድ የቁርኣኑ ዒሳ እና የመጽሐፍ ቅዱሱ ኢየሱስ አንድ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ስለዚህ ሙስሊሞች ከመጀመርዎቹ ሰዎች ወገን የሚመደቡ ስለሆኑ የክርስቶስን ማንነትና ሥራ ልናብራራላቸው ያስፈልገናል፡፡ ለሙስሊሞች ወንጌልን ስንሰብክ የመወያያ ነጥቦቻችን በደህንነት፣ የክርስቶስ ማንነትና ቅዱሳት መጻሕፍት ዙርያ ያጠነጠኑ መሆን ይገባቸዋል፡፡ ስለ ክርስቶስም ስንነግራቸው፡- ሥጋን ለብሶ የመጣው ኢየሱስ (ዮሃ 1፡1-14) ሕግን በሙሉ መጠበቁን (1ጴጥ 2፡22) በሰማይ ያለውን አባቱን ደስ ማሰኘቱን (1ዮሃ 2፡2) የራሱን ጽድቅ ለኛ መስጠቱን (ፊል 3፡9) ከሚመጣውም ፍርድ እኛን ማዳኑን (ሮሜ 14፡10፣ ዕብ 9፡27) መንገር ያስፈልገናል፡፡ ይህንን ስናደርግ ደግሞ ንግግራችን በፀጋ የተሞላ መሆን አለበት (ቆላስይስ 4፡5-6)፡፡

የኢየሱስን ስቅለት በተመለከተ ቁርኣን የሚከተለውን ይናገራል፡-

እኛ የአላህን መልክተኛ የመርየምን ልጅ አልመሲህ ዒሳን ገደልን በማለታቸው /ረገምናቸው/ አልገደሉትም አልሰቀሉትምም ነገር ግን ለነሱ /የተሰቀለው ሰው በዒሳ/ ተመሰለ፡፡ እነዝያ በሱ ነገር የተለያዩት ከርሱ /መገደል/ በመጠራጠር ውስጥ ናቸው፡፡ ጥርጣሬን ከመከተል በስተቀር በሱ ነገር ምንም እውቀት የላቸውም፡፡ በእርግጥም አልገደሉትም፡፡ ይልቁንስ አላህ ወደርሱ አነሳው፡፡ አላህም አሸናፊ ጥበበኛ ነው፡፡ ሱራ 4፡157-158

የዚህን ጥቅስ መሠረታዊ ችግሮች ለማስረዳት የሚከተሉትን ጥያቄዎች ልንጠይቃቸው እንችላለን፡-

  1. ይህ እምነት ከታሪካዊ ዘገባዎች ጋር ይጋጫል፡፡ በየትኛውም የታሪክ ዘገባ ድጋፍ የለውም፡፡ የታሪክ መዛግብትን በአንድ ሰው “መገለጥ” መሻር ጭፍን እምነት አይሆንምን?
  2. አላህ ዒሳ ምንም ሳይሆን ዝም ብሎ ወደራሱ መውሰድ ከቻለ በእርሱ ፈንታ ሌላ ሰው እንዲገደል ማድረጉ ጥቅሙ ምንድነው? በዚህ ድርጊቱስ አላህ ፍትሃዊ ውሳኔ ወስኗል ማለት ይቻላል?
  3. በዒሳ ፈንታ ሌላ ሰው እንዲሰቀል አላህ ሁኔታዎችን ባያመቻችና የሰውየውን መልክ ከዒሳ መልክ ጋር ባያመሳስል ኖሮ ዒሳ ተሰቅሏል የሚል ትምህርት ባልተስፋፋ ነበር፡፡ ታዲያ አላህ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ሕይወት አያሳዝነውምን? ስለምን ይህን ሁሉ የማስመሰል ሥራ በመሥራት ክርስትና እንዲፈጠር አደረገ?
  4. የዒሳ መልክ የተመሳሰለው ለጠላቶቹ ብቻ ወይንስ ለወዳጆቹም ጭምር? ለሁለቱም ወገኖች ከሆነ አላህ የዒሳ ተከታዮች የነበሩትን አማኞች በማታለል ማሳሳት ለምን አስፈለገው? ለጠላቶቹ ብቻ ከሆነ ከወዳጆቹ መካከል አንዱ እንኳ አለመሰቀሉን ስለምን አልዘገበም?
  5. በዒሳ ፈንታ ተሰቀለ የተባለው ሰው በመስቀል ላይ በነበረበት ጊዜ ሲመለከቱ የነበሩ የዓይን ምስክሮች መኖራቸው አይካድም፡፡ ታዲያ እነዚህ ከዒሳ ጠላቶች ወገን ያልነበሩ ሰዎች የተሰቀለውን ሰው ሲመለከቱ የሚታያቸው የዒሳ መልክ ወይንስ የሰውዬው መልክ? የዒሳ መልክ ከሆነ ስለ ስቅለቱ ትዕይንት ሊመሰክሩ የሚችሉት ዒሳ መሰቀሉን ነው፡፡ ነገር ግን የተሰቀለው ሌላ ሰው ስለሆነ ምስክርነታቸው ሀሰት ነው የሚሆነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በማያውቁት ሁኔታ ሀሰትን በመመስከር ለራሳቸውም ተሳስተው ሌሎችንም በምስክርነታቸው እንዲያሳስቱ ያደረገውን ይህንን የማታለል መንገድ ለመጠቀም አላህ ስለምን መረጠ? አላህ ሁሉን ቻይ አይደልምን? ስለምን ለብዙዎች መጥፋት ምክንያት የሆነውን ይህንን መንገድ ተጠቀመ? ማንንም ሳያታልልና ሳያሳስት ዒሳ እንደይሰቀል ማድረግ አይችልም ነበርን?
  6. ነቢዩ ሙሐመድ ይህንን “መገለጥ” ይዘው የመጡት ነገሩ ከተከሰተ ከ600 ዓመታት በኋላ ነው፡፡ ከዚያ በፊት የነበሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህዝቦች የኢየሱስን መሰቀል በማመን አልፈዋል፡፡ በዚሁም ሳብያ ብዙዎች እስከ ህይወት መስዋዕትነት ድረስ ዋጋ ከፍለዋል፡፡ ታዲያ አላህ ይህን ያህል አመታት በመዘግየት “መገለጡን” ከሚልክ ወዲያውኑ በወቅቱ ቢልክ ኖሮ ብዙዎችን ከጥፋት ለማዳን የተሻለ መንገድ አይሆንም ነበርን? ለነዚያ ለጠፉ ህዝቦች ህይወትስ ተጠያቂው ዒሳ የተሰቀለ በማስመሰል ያታለላቸውና ያሳሳታቸው ራሱ አላህ አይሆንምን?

እነዚህንና የመሳሰሉ ጥያቄዎችን ብንጠይቅ ሙስሊሞች እምነታቸውን ቆም ብለው እንዲመረምሩ ልንረዳቸው እንችላለን፡፡

3.2.1.     የወንጌል አሰባበክ ዓይነቶች

የተለያዩ የወንጌል አሰባበክ ዓይነቶች አሉ፡፡ እነዚህን አቀራረቦች እንደየ አካባቢው ሁኔታና እንደ አድማጮቻችን ዓይነት መርጠን ልንጠቀም ያስፈልገናል፡፡ የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል፡-

  • ፊት ለፊት (Confrontational)
  • ቀጥተኛ የሆነ ጥያቄ በመጠየቅ ከሰዎቹ ምላሽ በመነሳት ወንጌልን መናገር፡፡
  • በቀጥታ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወንጌልን መናገር፡፡
    • የአደባባይና የመንገድ ዳር ስብከቶች ይህንን መንገድ የተከተሉ ናቸው፡፡
    • በግልም ይህንን ዘዴ መጠቀም እንችላለን ነገር ግን ከሙስሊሞች አንጻር ብዙም ውጤታማ ላይሆን ይችላል፡፡
  • ምሁራዊ አቀራረብ (Intellectual aproach)
  • አመክንዮአዊ በሆነ መንገድ ወንጌልን ማስረዳት ነው፡፡ ሐዋርው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ዘዴ ይጠቀም ነበር (ሐዋ 17፡16-31)፡፡ ሙስሊሞች አንድ ሰው አመክንዮን በመጠቀም ፈጣሪውን ወደ ማወቅ ሊመጣ እንደሚችል ስለሚያምኑ በምክንያትና በማስረጃ የተደገፉ ነገሮችን ስንነግራቸው በደንብ ሊሰሙን ይችላሉ፡፡
  • ምስክርነታዊ (Testimonial)
  • እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ ያደረገው አንድ መልካም ነገር ካለ እርሱን ማካፈል ማለት ነው፡፡
  • በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ እንደተዘገበው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ዘዴ ተጠቅሟል፡፡
  • ከሌሎች የአሰባበክ ዘዴዎች ጋር በማጣመር ልንጠቀመው እንችላለን፡፡ ውጤታማነቱም ከፍተኛ ነው፡፡
  • ግብዣ (Invitational)
  • በቤተ ክርስቲያናችን ወይንም ደግሞ በቤታችን የተዘጋጀ ልዩ ፕሮግራም ካለ ወደዚያ ሰዎችን በመጋበዝ ወንጌልን እንዲሰሙ እድል መፍጠር በጣም ውጤታማ ነው፡፡
  • ሰዎችን በማገልገል (Service) (ሐዋ 9፡36)
  • ጌታችን ኢየሱስ ሰዎች መልካሙን ሥራችንን አይተው የሰማዩ አባታችንን እንዲያከብሩ ብርሃናችን በሰዎች ፊት ሊበራ እንደሚገባ ነግሮናል (ማቴ 5፡15)፡፡
  • ሰዎችን ስንረዳ እርዳታችን መቀጠል ያለበት ክርስቶስን እስከተቀበሉ ድረስ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ቢቀበሉም ባይቀበሉም ሰዎችን መርዳት ክርስቲያናዊ ግዴታችን ነው።
  • በጓደኝነት (Friendship)
  • ከሙስሊሞች አንጻር ይህ በጣም ውጤታማ የሆነ ወንጌልን የማድረስ አቀራረብ ነው፡፡
  • ለሙስሊሞች ስለ ክርስቶስ ከመናገራችን በፊት ስለ ክርስቲያኖችና ስለ ክርስትና ያላቸውን የተሳሳቱ አመለካከቶች በመቅረፍ መተማመን በመካከላችን እንዲኖር ጥረት ብናደርግ ውጤታማ እንሆናለን፡፡ ለዚህ ደግሞ ወሳኙ መንገድ ጥሩና ትክክለኛ የሆነ ጓደኝነት መመሥረት ነው፡፡

3.2.2.     ወንጌልን ለመስበክ የሚያስፈልጉን ነገሮች

  • መንፈስ ቅዱስን መቀበልወንጌል የሚሰበከው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነው፡፡ ያለ መንፈስ ቅዱስ እርዳታ ወንጌልን መስበክ አይቻልም። እርሱም፦ አብ በገዛ ሥልጣኑ ያደረገውን ወራትንና ዘመናትን ታውቁ ዘንድ ለእናንተ አልተሰጣችሁም፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ።ሐዋ 18
  • በቂ ዝግጅት ማድረግ

ይህ በሁለት መንገዶች ሊገለጽ ይችላል፡-

  • መጸለይወንጌልን በማዳረስ ተልዕኮ ውስጥ ጸሎት ወሳኙን ስፍራ ይይዛል፡፡ ያለጸሎት ዝግጅት የሚደረግ ወንጌልን የማዳረስ እንቅስቃሴ ውጤታማ ሊሆን አይችልም፡፡ እግዚአብሔር ቅዱሱን መንፈስ እንዲሰጠን፣ ጥበቃ እንድያደርግልንና የሰዎችን ልብ የሚይዘውን ክፉ ተቃዋሚ እንዲያስር መጸለይ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን አስቀድሞ ኃይለኛውን ሳያስር ወደ ኃይለኛው ቤት ገብቶ ዕቃውን ሊበዘብዝ የሚችል የለም፥ ከዚያም ወዲያ ቤቱን ይበዘብዛል።ማር 327
  • ስለ ክርስትናና ስለ እስልምና በቂ ዕውቀት መያዝ፡ከመናገራችን በፊት የምንናገረውን ካላወቅን ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን ወደ ግራ መጋባት ነው የምንመራው፡፡ በተለይ ከሙስሊሞች ጋር የሚደረግ ውይይት በግዴለሽነትና ያለ በቂ ዝግጅት የሚሆን ከሆነ ውጤቱ የከፋ ነው የሚሆነው፡፡ በዚህ ዘመን ያሉ ብዙ ሙስሊሞች አንዳንድ የተመረጡ የመጽሐፍ ቅዱስን ጥቅሶችን ያጠናሉ፡፡ በቂ ዝግጅት የሌለውን ክርስቲያን ካገኙ በሰላ ክርክር ሊያጣድፉት ይችላሉ፡፡
  • ወንጌል የእግዚአብሔር ኃይል መሆኑን ማወቅይህንን ስናደርግ በእግዚአብሔር መታመን እንችላለን፡፡ በቀላሉም ተስፋ የምንቆርጥ አንሆንም፡፡ የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና። የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ ተብሎ ተጽፎአልና። ጥበበኛ የት አለ? ጻፊስ የት አለ? የዚች ዓለም መርማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገምን? በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች፥ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአልና። መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፥ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው፥ ለተጠሩት ግን፥ አይሁድ ቢሆኑ የግሪክ ሰዎችም ቢሆኑ፥ የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ክርስቶስ ነው። ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና፥ የእግዚአብሔርም ድካም ከሰው ይልቅ ይበረታልና።” 1ቆሮ 18-25
  • ፍቅርና አክብሮትን ማሳየትሙስሊሞች እንደ ማንኛውም ሰው ፍቅርና አክብሮትን ይሻሉ፡፡ እኛ ደግሞ እንደ ክርስቲኖች ሰዎችን ሁሉ መውደድና ማክበር ይገባናል፡፡ ይህንን የክርስቶስ ኢየሱስን የፍቅርና ለሌሎች የመጠንቀቅ ባሕርይ በእኛ ዘንድ ሲያዩ ሙስሊሞች በጣሙን ይደነቃሉ፤ የምንናገረውንም ነገር በደስታ ይሰማሉ፡፡
  • መመስከር እንጂ ያለመከራከርጌታ ኢየሱስ ስለ ስሙ እንድንመሰክር እንጂ እንድንከራከር አልላከንም፡፡ ስለዚህ ከሙስሊሞች ጋር ስንነጋገር በተቻለ መጠን ክርክርን ማስወገድ ያስፈልገናል፡፡
  • አንድ ለአንድ ሆኖ መመስከርከሙስሊሞች ጋር በቡድን የሚደረግ ውይይት ብዙ ጊዜ ውጤታማ አይደለም፡፡
  • እነርሱ ሊረዷቸው የሚችሏቸውን አነጋገሮችና ቃላት መጠቀምለምሳሌ ያህል በወንጌል ፈንታ እንጂል፣ በኢየሱስ ፈንታ አል መሢህ ዒሳ፣ ወዘተ. ብንል የበለጠ ሊሰሙን ይችላሉ፡፡
  • የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን መጠቀምሙስሊሞች የነቢያትና የጥንት አባቶችን ታሪኮች ለማወቅ በጣም ይፈልጋሉ፡፡ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ያሉ ብዙ ታሪኮች ስለ ክርስቶስ ማንነትና ሥራ ለማብራራት ስለሚያስችሉን እነርሱን መጠቀም በጣም ይረዳናል፡፡ ለምሳሌ ያህል ክርስቶስ በእኛ ፈንታ በመስቀል ላይ መሞቱን ለማስረዳት የአብርሃምና የይስሃቅን ታሪክ መጠቀም እንችላለን፡፡ (የመሥዋዕቱ ልጅ ይስሐቅ ወይንስ እስማኤል? የሚለው ክርክር ማስተላለፍ በምንፈልገው መልዕክት ላይ የጎላ ተፅዕኖ ስለሌለው ማንሳቱ አስፈላጊ አይደለም።)
  • ከመስጊድ ቢያነስ 100 ሜትር ራቅ ማለትበዚያ ክልል ውስጥ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎችን ብናደርግ የምንጠየቅበት ሁኔታ ሊኖር ስለሚችል ከሙስሊሞች ጋር የሚነጋገሩ ክርስቲያኖች ሁሉ ይህንን ማወቅ ይገባቸዋል፡፡
  • የሚከብዷቸውን ነጥቦች ቶሎ አለማንሳትሙስሊሞች ቶሎ ሊረዷቸው የማይችሏቸውን ሥላሴን የመሳሰሉ ርዕሶችን በሌሎች ጉዳዮች ላይ ከተወያየንና መንገድ ከጠረግን በኋላ ብናነሳ የበለጠ እንዲገነዘቡ ልናቀልላቸው እንችላለን፡፡
  • የነቢዩ ሙሐመድን ስም አለማጥላላትለሙስሊሞች ነቢዩ ሙሐመድ ታላቅ ነቢይና የተከበሩ ሰው ናቸው ስለዚህ በእሳቸው ላይ ለሚሰነዘር ለማንኛውም ትችት ትዕግስት የላቸውም፡፡ እኛም ደግሞ ይህንን በማድረግ ስሜታቸውን በመጉዳት ከእነርሱ ጋር ያለንን ግንኙነት ማበላሸት የለብንም፡፡
  • ቁርኣንን በጥንቃቄ መያዝሙስሊሞች ለቁርኣን ልዩ የሆነ አክብሮት ስላላቸው በጥሩ ሁኔታ ያልተያዘ ወይንም ደግሞ የተሰመረበትና ምልክት የተደረገበት ቁርኣን ሲያዩ ቅሬታ ሊሰማቸው ይችላል፡፡
  • ለአለባበስ ጥንቃቄ ማድረግሙስሊሞች ለሜዳዊ ሥርኣቶች ትኩረት ስለሚሰጡ አለባበሳችንና የጸጉር አቆራረጣችን እንዳያሰናክላቸው ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባናል፡፡
  • እንዲናገሩና እንዲጠይቁ ዕድል መስጠትሙስሊሞች ስለ ክርስትና የተነገራቸው ብዙ የተሳሳቱ ነገሮች ስላሉ ብዙ ጊዜ ለመናገር እንጂ ለመስማት ፍቃደኞች አይደሉም፡፡ ሰዎችን ማዳመጥና የራሳቸውን ሐሳብ እንዲገልጹ ዕድል መስጠት ትኩረታቸውን ለማግኘት ይረዳል፡፡
  • ከዕውቀታችን በላይ የሆኑ ጥያቄዎን ከጠየቁን እንዳልተዘጋጀንበትና ሌላ ጊዜ በዝግጅት እንደምንመልስላቸው በትህትና መንገርሙስሊሞች ፊት ስንቀርብ ለሚጠይቁን ጥያቄዎች ሁሉ መልስ እንዳለን ራሳችንን በመቁጠር መሆን የለበትም፡፡ ሰዎች እንደ መሆናችን መጠን ሁሉን አዋቂዎች አይደለንም፡፡ ያልተዘጋጀንባቸውን ጥያቄዎች የሚጠይቁን ከሆነ የማናውቃቸውን ነገሮች በመናገር ግራ ከመጋባት ይልቅ ጊዜ እንዲሰጡን በመጠየቅ ልንመልስላቸው እንደምንችል መንገር አስተዋይነት ነው፡፡
  • ጌታን ለመቀበል የሚወስኑ ካሉ ለአደጋ እንዳይጋለጡ በሚስጥር ክትትል በማድረግ ማስተማርበወንጌላውያን ክርስቲያኖች ዘንድ የሚታይ አንድ ትልቅ ችግር ቢኖር ሰዎች መለወጣቸውን በአደባባይ እንዲናገሩ ማጣደፍ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ዓይነቱ አካሄድ በእምነታቸው ያልጸኑ አዳዲስ አማኞችን ለአደጋ ስለሚያጋልጥና ወደ ኋላ እንዲመለሱ ምክንት ስለሚሆን ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባናል፡፡

 


 

ተጨማሪ ንባቦች

  • እንድረስላቸው፡ በጌርሃርድ ኔልስ እና ዋልተር ኤሪክ፡ 2000 ዓ.ም.
  • አል ኪታብ፡ በጌርሃርድ ኔልስ፡ 1985 ዓ.ም.
  • የክርስቲያን ሙስሊም ውይት፡ በዶ/ር ዕውነቱ ከበደ፡ 1991 ዓ.ም.
  • የነቢ ዒሳ መልዕክት፡ በጌርሃርድ ኔልስ፡ 1992 ዓ.ም.
  • የእግዚአብሔርን ፍቅር ለሙስሊሞች ማካፈል፡ በቢል ዴኔት
  • ወንጌልን ለሙስሊሞች፡ በጌርሃርድ ኔልስ፡ 1992 ዓ.ም.
  • ውድ ዐብደላ፡ በጌርሃርድ ኔልስ፡ 1986
  • ለሙስሊሞች ጥያቄዎች የክርስቲያኖች መልሶች፡ በጌርሃርድ ኔልስ
  • እውነቱ ይህ ነው፡ በመጋቢ ዲንሰን መንዲድ፡ 2000 ዓ.ም.
  • ገሃድ፡ የእስልምና ጥናት መምርያ ለክርስቲያኖ፡ በበርናባስ ፈንድ የተዘጋጀ
  • መሳተፍ፡ ክርስቲያናዊ ምላሾች ለእስልምና፡ በበርናባስ ፈንድ የተዘጋጀ
  • እስልምናና የታላቁ ነቢይ የሙሐመድ ታሪክ፡ በሐጂ ሙሐመድ ሳኒ ሐቢብ

ለክርስቲያኖች