እንፍጠር! የእግዚአብሔርን ሥሉስ አሓዳዊነት የሚያረጋግጥ ማስረጃ

እንፍጠር!

የእግዚአብሔርን ሥሉስ አሓዳዊነት የሚያረጋግጥ ማስረጃ

በወንድም ሚናስ


“እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ።”
— ዘፍጥረት 1፥26

የእግዚአብሔርን ሥሉስ አሓዳዊነት ከሚያመለክቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መካከል አንዱ ይህ ጥቅስ ነው። እግዚአብሔር አብ ዓለማትን በልጁ መፍጠሩን (ዕብ1፥2፤ ዮሐ1፥3፤ ቆላ1፥16-17) እንዲሁም ደግሞ ፍጥረትን በማስገኘት ሒደት መንፈስ ቅዱስ ጉልሕ አስተዋጽኦ እንዳለው ቅዱሳት መጻሕፍት አበክረው ይነግሩናል (ዘፍ 1፥3 ፤ ኢዮ33፥4)። በዘፍጥረት 1፥26 ላይ በብዙ ቁጥር ግስ “እንፍጠር” (נַעֲשֶׂה “ናዓሳህ”) በብዙ ቁጥር ስሞች “በመልካችን” (בְּצַלְמֵ֖נוּ ቦጼሌሜኑ) እንዲሁም “ምሳሌአችን” ( כִּדְמוּתֵנוּ ” ኪዴሙቴኑ”) ማለቱ አሐዱ ሥሉስን እንደሚያመለክት ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን የሚስማሙበት እውነታ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይህንን እውነታ የተቃወሙ የእምነት ቡድኖችም ሆኑ ግለሰቦች አልታጡም። በዚህ ጽሑፍ ወሒድ ዑመር የተሰኘ የእስልምና “ዐቃቤ እምነት” “የሥላሴ እሳቤ” በሚለው መጽሐፉ ውስጥ ያነሳውን ሙግት እንመለከታለን። ጸሐፊው እንዲህ ይላል፦

“ከአንድ አይሁዳዊ ምሁር ጋር እየተጨዋወትን ቀበል አርጌ፦ “ኤሎሂም እነማንን ነው እንፍጠር ያለው? ብዬ ጠየኩት፥ እርሱ፦ “በዚህ አንቀጽ ላይ በአይሁድ ጥንታዊ ምሁራን እና ዘመናዊ ምሁራን ዘንድ የተለያየ መልስ ተሰቶበታል” አለኝ። ከተሰጡት መልሶች መካከል፦
1. ኤሎሂም ከመላእክት ጋር እየተነጋገረ ነው፣
2. ከምድር ጋር እየተነጋገረ ነው፣
3. እራሱ ለግነት የብዜት ግስ እየተጠቀመ ነው፣
4. እራሱ ከራሱ ባሕርያት ጋር በዘይቤያዊ አነጋገር እየተናገረ ነው” የሚል ነው። ”[1]

ከላይ የተጠቀሱት አራቱም ነጥቦች ከጥንት ጀምሮ የሥላሴ አስተምህሮን መቀበል በማይፈልጉ ሰዎች የሚቀርቡ መላምቶች እንጂ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ ያላቸው ነጥቦች አይደሉም። ጽሑፌን ላለማርዘም አራቱንም ነጥቦች በጨረፍታ ለመዳሰስ ልሞክር፦

1መላምት፦ “ከመላዕክት ጋር እየተነጋገረ ነው።” እንዲህ ዓይነቱ ትርጓሜ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አምሳል ብቻ ሳይሆን በመላእክትም ጭምር  ተፈጥሯል የሚል አንድምታ ይኖረዋል፡፡ ነገር ግን በቁ. 27 ላይ “እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤” በማለት ከመላዕክት ጋር ተነጋገረ የሚለውን ሙግት ፉርሽ ያደርገዋል፡፡ የዘፍጥረት ጸሐፊ ሙሴ 5፥1 ላይ “እግዚአብሔር አዳምን በፈጠረ ቀን በእግዚአብሔር ምሳሌ አደረገው” በማለት የሰው ልጅ በእግዚአብሔር መልክ ብቻ የተፈጠረ መሆኑን በግልጽ አመልክቷል፡፡ በተጨማሪም በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ አንድም ቦታ ላይ እግዚአብሔር ከየትኛውም ፍጥረታት ጋር በመተባበር ፈጠረ አልተባለም፡፡ ይልቅ እግዚአብሔር አምላካችን በነቢዩ በኢሳይያስ አንደበት እንዲህ በማለት “ከመላእክት ጋር ተማከረ” የሚሉትን ወገኖች ይቃወማቸዋል፦

“የእግዚአብሔርን መንፈስ ያዘዘ፥ ወይስ አማካሪ ሆኖ ያስተማረው ማን ነው? ወይስ ከማን ጋር ተመካከረ? ወይስ ማን መከረው? የፍርድንም መንገድ ማን አስተማረው? እውቀትንስ ማን አስተማረው? የማስተዋልንስ መንገድ ማን አሳየው?” (ኢሳይያስ 40፡13-14)

“ከማኅፀን የሠራህ፥ የሚቤዥህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሁሉን የፈጠርሁ፥ ሰማያትን ለብቻዬ የዘረጋሁ ምድርንም ያጸናሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ ከእኔ ጋር ማን ነበረ?” (ኢሳይያስ 44:24)

2መላምት፦ “ከምድር ጋር እየተነጋገረ ነው።” በዘፍጥረት አውድ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ትርጓሜ የሚሰጥ ምንም ነገር የለም። ይህንን ግምት ጥሩ አማራጭ ነው ብሎ የሚያስብ ማንም ሰው በብሉይ ኪዳን ውስጥ ለዚህ የሚሆን ምንም ዓይነት ማሳያ ማቅረብ እንደማይችል ግልጽ ነው። እግዚአብሔር አምላክ ግዑዟን ምድር “ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር” ብሎ አማከራት ማለት ለማሰብ እንኳ የማይመጥን የስላቅ ንግግር ነው። 

3 መላምት፦ “ራሱን ለግነት የብዜት ግስ እየተጠቀመ ነው።” ይህ መላምት ውድቅ የሚሆንበት ምክንያት ራስን ለማክበር በብዙ ቁጥር መናገር በጥንቱ እብራይስጥ ውስጥ ቅዱሳት መጻሕፍት በተጻፉበት ዘመን አለመታወቁ ነው። አንዳንዶች ዳንኤል 2፥36ን ይህንን ምልከታ ለማፅናት ይጠቀሙበታል። ነገር ግን ነቢዩ ዳንኤል እየተናገረ የነበረው ሦስቱን ጓደኞቹን (አናንያ፣ አዛርያ እና ሚሳኤልን) በመወከል መሆኑን ከአውዱ መገንዘብ እንችላለን። እዚሁ ገጽ ላይ በሌላ ጽሑፍ እንደተብራራው የሕልሙ ትርጓሜ የዳንኤልና የጓደኞቹ የጸሎት መልስ እንጂ የዳንኤል ብቻ አይደለም (ዳን. 2፡17-18)፡፡ ስዚህ ዳንኤል ብዙ ቁጥር  መጠቀሙ ጓደኞቹንም ጭምር በመወከል በንጉሡ ፊት መቅረቡን የሚያሳይ እንጂ አንዳንዶች አንደሚሉት ራሱን በማክበር ነገሥታት “እኛ” እንደሚሉት (pluralis majestatis) እየተናገረ አይደለም፡፡ በባቢሎን ምድር ምርኮኛ የነበረው ዳንኤል በንጉሥ ፊት ቀርቦ ልክ እንደ ንጉሥ በእኛነት ራሱን ሊገልፅ ይችላል ተብሎ ማሰብ በራሱ የማይመስል ነው፤ በዘመኑም የሚታወቅ ልማድ ስለመሆኑ ማስረጃ የለም፡፡ ሌላ የሚጠቅሱት ዕዝራ 4፥18 ነው እርሱም ቢሆን ንጉሡ በዙርያው ያሉትን አማካሪዎቹንና የመንግሥቱን ባለሥልጣናት ሁሉ በመወከል “እኛ” ብሎ መናገር ይችላል፡፡ ንጉሡ “እኛ”ብሎ የተናገረው ራሱን ለማክበር ነው እንዳይባል እንዲህ ያለው አገላለፅ በዚያ ዘመን በፋርስ ምድር የተለመደ ስለመሆኑ ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም፡፡ ይሁን እንኳ ቢባል በዳንኤልና በዕዝራ ውስጥ የሚገኙት ንግግሮች በአረማይክ ቋንቋ የተጻፉ በመሆናቸውና የዘፍጥረት መጽሐፍ በእብራይስጥ ቋንቋ የተጻፈ በመሆኑ በእብራይስጥ ለተነገረ ንግግር ማስረጃ ሊሆኑ አይችሉም። በአጭሩ ራስን በግነት ብዜት መጥራት በጥንት እብራውያን ዘንድ እንደማይታወቅ የአይሁድ የቋንቋ መድበለ ዕውቀቶች መስክረዋል[2]።

4 መላምት፦ “ራሱን በዘይቤያዊ አገላለጽ እየተናገረ ነው።” ይህም ማለት ልክ ዳዊት በዘይቤያዊ አገላለጽ ነፍሱን እና አጥንቱን እየጠራ እንደተናገረው (መዝ 42፥5፤ መዝ 103፥1) እግዚአብሔርም ራሱ በዚህ ዓይነት ዘይቤ እየገለፀ ነው የሚል ነው። ሆኖም ግን ይህ ሙግት ድኩም የሚሆንባቸው ሁለት መሠረታዊ ምክንያቶች አሉ (1) ዳዊት የገዛ ማንነቱን ክፍሎች “ነፍሴ ሆይ”፣ “አጥንቶቼም” እያለ ሲጠራ ስለምናነብ ራሱን በዘይቤያዊ አገላለጽ እየጠቀሰ መሆኑን ግልጽ ሲሆን በዘፍጥረት 1፥26 ላይ ግን እግዚአብሔር ልክ እንደ ዳዊት የገዛ ማንነቱን ክፍሎች ሲጠቅስ ባለማንበባችን ራሱን በዘይቤ እየገለጠ ነው ለማለት አያስደፍርም። (2) ራስን በራስ ማናገር ስሙር ሙግት ቢሆን ኖሮ በጥንት ዘመን የነበሩት አይሁዳውያን ለክርስቲያኖች በሚሰጡት ምላሽ ይህንን መላምት ባካተቱ ነበር፤ የጥንቶቹ የአይሁድ ክርስቲያኖች ዘፍ 1፥26 አምላክ ከአንድ በላይ አመልካች መሆኑን በጥብቅ ያምኑ ነበርና።

ተከታዩ የአይሁድ ምንጭ አይሁድ ሊቃውንት ይህንን ጥቅስ ለማብራራት ምን ያህል ተቸግረው እንደነበርና ጥቅሱ ለነጠላ አሓዳዊነት እሳቤ ምን ያህል እንቅፋት እንደሆነ ያሳያል፦

❝ረቢው ሳሙኤል ባር ሀንማን በረቢ ዮናታን ስም እንዳሉት ሙሴ ኦሪትን በየቀኑ እየጻፈ ወደዚህ ጥቅስ መጣ “ኤሎሂምም አለ ሰውን በአምሳላችን እንፍጠር፡፡” ሙሴም በመገረም የአጽናፈ ዓለሙ ጌታ ሆይ ለምን ለኑፋቄዎች (አምላክ ከአንድ በላይ መሆኑን ለሚያምኑ) ምክንያት ትሰጣለህ?” አለ። እግዚአብሔርም ለሙሴ መለሰለት “አንተ ጻፍ ሊሳሳት የሚፈልግ ሁሉ ይሳሳት ፡፡”[3]

ክርስቲያን ያልሆኑ የጥንት የአይሁድ ሊቃውንት አሁን ያለውን የሥላሴ እሳቤ ለመቀበል ዳር ዳር እያሉ እንደነበር በሌላ የአይሁድ ምንጭ ውስጥ እንዲህ ተጽፎ እናገኛለን፦

“የእግዚአብሔርም ሜምራ አለ፦ የሰውን ልጅ እንደ እኛ በአርአያች እንፍጠር በፍጥረትም ሁሉ ላይ ይግዛ”[4]

“ሜምራ” የሎጎስ/ቃል አቻ ሲሆን በዕብራውያን መረዳት መሠረት ከእግዚአብሔር የተለየ አካል ነበር። ለምሳሌ በታርጉማቸው ውስጥ ስለ ኦሪት ዘዳግም 26፡17-18 ሲጽፉ “ሜምራን (ሎጎስን) በራስህ ላይ ንጉሥ አድርገህ ሹመሃል፤ ይህም አምላክ እንዲሆንህ ነው” ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ ዘፍጥረት 28፡20-21 ላይ በአረማይክ ታርጉም ያዕቆብ እግዚአብሔር አምላኩ እንደሚሆን ከመናገር ይልቅ የእግዚአብሔር ሜምራ አምላኩ እንደሚሆን ስዕለትን ሲሳል ይታያል፡፡ በዚሁ የአረማይክ ታርጉም ውስጥ ዘዳግም 4፡7 ሲብራራ የእግዚአብሔር ቃል ሜምራ በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ የሰዎችን ጸሎት እንደሚቀበል ተገልጿል፡፡

ከላይ የተዘረዘሩትን ማስረጃዎች በትኩረትና በማስተዋል ካገናዘብን የሥላሴ አስተምህሮን ለመቀበል በቂ ሆኖ እናገኘዋለን።

በአሚነ ሥላሴ ያጽናን!


1. የሥላሴ እሣቤ ገጽ 39

2 .Khan, Geoffrey Ed., Encyclopedia of Hebrew Language and Linguistics, (Boston: Brill, 2013), 146.

[3] Genesis Rabbah, VIII.8, p. 59.

[4] Fragmentary Targum, Exodus 12:42

[5] Gieschen, Charles A., Angelomorphic Christology: Antecedents & Early Evidence, (Boston: Brill, 1998), 113.

 

ለእስልምና ሙግቶች ምላሽ