እውን የዕብራውያን ጸሓፊ ተሳስቷልን?
ወንድም ሚናስ
ሐዲስ ኪዳን አፊዎተ መለኮት መኾኑን የማይቀበሉ ወገኖች ብዙውን ጊዜ ከሚያነሷቸው የመከራከሪያ ክሶች መኻከል የሐዲስ ኪዳን ጸሓፊያን የብሉይ ኪዳንን ምንባባት በሚጠቅሱበት ጊዜ መልእክቱን በትኽክል ስለማያስቀምጡ በእግዚአብሔር መንፈስ የተጻፈ ነው ለማለት እንቸገራለን፤ የሚል ነው። ለዚህም እማኝ ብለው ከሚያነሷቸው የመከራከሪያ ጥቅሶች ውስጥ የዕብራውያን ጸሓፊ መዝሙረ ዳዊት 40፥6 በሚጠቅስበት ጊዜ ምንባቡን ቀይሮ በራሱ መንገድ ጽፎታል የሚል ነው። እኛም ጥቅሶቹን በማስቀደም ወደ ምላሻችን እንዘልቃለን።
Διὸ εἰσερχόμενος εἰς τὸν κόσμον λέγει,Θυσίαν καὶ προσφορὰν οὐκ ἠθέλησας, σῶμα δὲ κατηρτίσω μοι·
“ስለዚህ ፥ወደ ዓለም ሲገባ፦ መሥዋዕትንና መባን አልወደድኽም ሥጋን ግን አዘጋጀኽልኝ፤” ዕብ 10፥5
የዕብራውያን ጸሓፊ ይህንን ምንባብ የወሰደው ከመዝሙር 40፥6 ሲኾን ዕብራይስጡ ከላይ ከሰፈረው የዕብራውያን መልእክት ለየት ባለ መልኩ እንዲህ ይነበባል፦
זֶ֚בַח וּמִנְחָ֨ה | לֹֽא־חָפַ֗צְתָּ אָ֖זְנַיִם כָּרִ֣יתָ לִּ֑י עוֹלָ֥ה וַֽ֜חֲטָאָ֗ה לֹ֣א שָׁאָֽלְתָּ
“መሥዋዕትንና ቊርባንን አልፈለግህም፤ ጆሮቼን ግን ከፈትክ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትን፣ የኀጢአትንም መሥዋዕት አልሻህም።” (መዝ.40፥6) [ትርጉም በአዘጋጁ]
እዚህ ጋር መታወቅ ያለበት መሠረታዊ ነገር የዕብራውያን ጸሓፊ፣ በሌሎች ስፍራዎች እንደሚያደርገው፣ መዝሙረ ዳዊት 40፥6ን የወሰደው ከጥንታዊው የሰብዓ ሊቃናት ትርጒም መሆኑ ነው። እንዲህ ይነበባል፦
θυσίαν καὶ προσφορὰν οὐκ ἠθέλησας, σῶμα δὲ κατηρτίσω μοι· ὁλοκαύτωμα καὶ περὶ ἁμαρτίας οὐκ ᾔτησας.
“መሥዋዕትንና ቍርባንን አልወደድህም፤ ሥጋን ግን አዘጋጀኽልኝ፤ የሚቃጠለውንና ስለ ኀጢአት የሚቀርበውን መሥዋዕት አልሻህም።”
የሰብዓ ሊቃናት ትርጒም የዕብራይስጡ ዋና ንባብ የጽርእ ትርጒም ሲኾን በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን በስፋት ጥቅም ላይ ይውል ነበር። በዘመኑም የነበሩት አይሁዳውያን ዘንድ በቀዳሚነት ተቀባይነት የነበረው ከመኾኑም በላይ ትርጒሙ የተጻፈበት ኮይኔ ጽርእ በጊዜው የመግባቢያ ቋንቋ (Lingua Franca) በመሆኑ ምክንያት በሕዝቡ ዘንድ ተደራሽነት አግኝቷል። ስለኾነም የጸሓፊው ተደራሲያን አብዛኛዎቹ የሚናገሩት ጽርእ ስለነበረ፣ ሐዲስ ኪዳንን በአረማይክ ወይም በዕብራይስጥ መጻፉ ተደራሽነቱ ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል። በርግጥ አንዳንድ የጥንት ክርስቲያኖች አረማይክና ዕብራይስጥ እንደሚችሉ እሙን ቢኾንም፣ ነገር ግን በዕለት ተዕለት ኑሯቸው ከሌሎች ጋር ያላቸው ግንኙነት የሚከውነው በጽርእ ቋንቋ ነበር። በተለይም ዕብራይስጥ በወቅቱ የሰፊው ሕዝብ የመግባቢያ ቋንቋ አልነበረም። የዕብራውያን መልእክት ደግሞ አሕዛብንም የሚያጠቃልል ስለኾነ ከዕብራይስጥም ኾነ ከአረማይክ ይልቅ ጽርእ ለተደራሲያን ትክክለኛ ቋንቋ ይኾናል። ስለዚህ፣ የዕብራውያን ጸሓፊ አንባቢያኑ ይበልጥ ከሚያውቁት ትርጕም ከኾነው ጥንታዊው የጽርእ ቅጂ ከመጥቀሱ አንጻር፣ የብሉይን ምንባብ አዛብቷል ተብሎ የመልእክቱ ተዓማኒነት በጥርጥር ሊታይ የሚችልበት አግባብ አይኖርም። በዚህ ዘመንም ትርጉሞች ውሱንነቶች እንዳሉባቸው እያወቅን እንጠቅሳቸዋለን። በምናቀርበው ሙግት ወይም ትምህርት ላይ የጎላ ተጽዕኖ እንዳለው ካልተሰማን በስተቀር ምሑራን ያዘጋጁትን ትርጒም እንዳለ እንወስዳለን እንጂ ቃላት ላይ ማሻሻያ አናደርግም። የዕብራውያን ጸሐፊም ከዚህ የተለየ ተግባር አልፈጸመም።
ኾኖም የሰብዓ ሊቃናት ተርጓሚዎች “ሥጋን አዘጋጀኽልኝ” ወደ ሚለው አተረጓጐም እንዴት ሊመጡ ቻሉ? የሚለውን ለመረዳት ዕብራይስጡን መገንዘብ ያስፈጋል፤ ዕብራይስጡ אָ֖זְנַיִם כָּרִ֣יתָ “አዝናይም ካሪይታ” የሚል ሲኾን በቁሙ ሲተረጐም “ጆሮዬን ቈፈርክ” የሚል ነው። ይህ ቁማዊ አተረጓጐም እንደ ኤን.ኤስ.ቢ፣ ኢ.ኤስ.ቪ፣ እንዲሁም በ1611 ዓ.ም በተዘጋጀው ኬ.ጄ.ቪ. ወዘተ፣ ባሉ አንዳንድ ቅጆች በኅዳግ መዘክር ላይ በአማራጭነት ተቀምጧል። ታዲያ “ጆሮዬን ቈፈርክ” ማለት ምንድር ነው? ምንስ ማለት ነው? የተለያዩ የእንግሊዝኛ ቅጂዎች በሚከተሉት መንገዶች ተርጒመውታል፦
“…thou madest perfectly ears to me…” (Wycliffe Bible)
“…my ears you have pierced…” (NIV የ 1984 ትርጒም)
“…you gave me to understand…” (Jewish NJPS Translation)
“…You make that quite clear to me…” (NET)
እንግዲህ ከላይ ያየናቸው ቅጂዎች ይህንን ለመረዳት አስቸጋሪ የኾነውን ሐረግ ዋናው ጸሓፊ ሊናገር የፈለገውን ዐሳብ በተቻላቸው መጠን ግልጽ ለማድረግ እየሞከሩ ነው። የሰብዓ ሊቃናት ተርጓሚያንም ተግባር ከዚህ የተለየ አይደለም፤ ልክ እንደ ዊክሊፍ ባሉ ትርጒሞች “ፍጹም ጆሮን ፈጠርክልኝ” እንደተባለው፣ የሰብዓ ሊቃናት ተርጓሚያንም እግዚአብሔር የመዝሙረኛውን ጆሮዎች መፍጠሩን ለማመልከት እንደኾነ ተገንዝበዋል፤ ስለኾነም ዕብራይስጡን አንብበው መገንዘብ ለማይችሉ ተደራሲያን ጕዳዩን ግልጽ ለማድረግ ሞክረዋል፤ ይኸውም ስለ ጆሮ አፈጣጠር ብቻ እግዚአብሔርን ከማመስገን ይልቅ መላ አካላቱን ጠቅለል ባደረገ መልኩ “ሥጋን አዘጋጀኽልኝ” ብለውታል። ከእኛ ይልቅ እነርሱ ዋናው ጽሑፍ ለተዘጋጀበት ዘመን የቀረቡ ስለነበሩ በእነርሱ ዘመን አባባሉ የነበረውን ትርጓሜ እርግጠኛ ሆነን በማናውቅበት ሁኔታ ተሳስተዋል ማለት ትክክል አይሆንም።
በሌላ ወገን ደግሞ ከተመለከትን በዘመነ ብሉይ አንድ ባርያ ነጻ መውጣት ካልፈለገና እስከ መጨረሻው ጌታውን ለማገልገል ከመረጠ ጆሮን የመበሳት ሥርዓት ይፈጽማል፦
“ባሪያውም፦ ጌታዬን ሚስቴን ልጆቼንም እወድዳለሁ፥ አርነት አልወጣም ብሎ ቢናገር፥ ጌታው ወደ ፈራጆች ይውሰደው፥ ወደ ደጁም ወደ መቃኑ አቅርቦ ጆሮውን በወስፌ ይብሳው፤ ለዘላለምም ባሪያው ይሁን።” (ዘጸ. 21፥5-6)
ይህ ሥርዓት የሚከወነው ባርያው ለጌታው እስከ መጨረሻው በፍጹማዊ መታዘዝ ቃሉን እየሰማ ለመኖር መምረጡን ለማመልከት ነው። መዝሙረኛው אָ֖זְנַיִם כָּרִ֣יתָ “አዝናይም ካሪይታ” (ጆሮዬን ከፈትክ) ሲል ይህንን ትዕምርታዊ ተግባር በመጠቆም የመታዘዝን አስፈላጊነት ለመግለጽ ነው የሚሉ ሊቃውንት አሉ። ይህንን አባባል፣ እግዚአብሔርን መታዘዝና መስማት ከመሥዋዕት እንደሚበልጥ ነቢዩ ሳሙኤል ከተናገረው ቃል ጋር አያይዞ መረዳት ይቻላል፦
“ሳሙኤልም፦ በውኑ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ደስ እንደሚለው እግዚአብሔር በሚቃጠልና በሚታረድ መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ፥ መታዘዝ ከመሥዋዕት፥ ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል።” (1ሳሙ. 15፥22)
የዕብራውያን ጸሓፊ ጥቅሱን ከጠቀሰ በኋላ በማስከተል የሚገኘውንም ዐሳብ መጥቀሱ የሰብዓ ሊቃናቱን ትርጉም ብቻ ሳይሆን የዕብራይስጡንም ትርጉም ከግምት ውስጥ ማስገባቱን ያስገነዝበናል፦
“በዚያን ጊዜ፦ እነሆ፥ በመጽሐፍ ጥቅልል ስለ እኔ እንደ ተጻፈ፥ አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ አልሁ ይላል። በዚህ ላይ፦ መሥዋዕትንና መባን በሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕትንም ስለ ኃጢአትም የሚሰዋ መሥዋዕትን አልወደድህም በእርሱም ደስ አላለህም ብሎ፥ እነዚህም እንደ ሕግ የሚቀርቡት ናቸው፥ ቀጥሎ፦ እነሆ፥ አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ ብሎአል። ሁለተኛውንም ሊያቆም የፊተኛውን ይሽራል። በዚህም ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ አንድ ጊዜ ፈጽሞ በማቅረብ ተቀድሰናል።” (ዕብ. 10:7-10)
በአውዱ መሠረት እግዚአብሔር አምላክ ከመሥዋዕት ይልቅ ለፈቃዱ በመታዘዝ ደስ ይሰኛል፤ ስለዚህ ክርስቶስ ፈቃዱን ለመፈጸም ወደ ምድር መጥቷል፤ ይህንንም ፈቃዱን የገዛ ሥጋውን መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ ፈጽሞታል። ፍጽምና ከጎደለው የዘመነ ብሉይ መሥዋዕት ይልቅ እውነተኛ መታዘዝ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ነው። ክርስቶስ ደግሞ በፍጹማዊ መታዘዝ ፍጹማዊ መሥዋዕት የሆነውን የገዛ ሥጋውን በማቅረብ የእግዚአብሔርን የልብ ፈቃድ አርኪ በሆነ መንገድ ፈጸመ። በዚህ ግንዛቤ መሠረት የዕብራውያን ጸሐፊ የዕብራይስጡን እማሬያዊ ትርጒም የሰብዓ ሊቃናት ከተረጎሙበት ፍካሬያዊ ትርጒም ጋር በማጣመር ያቀረበበትን መንገድ አስደናቂ ሆኖ እናገኘዋለን።
ጽሑፋችንን ስናጠቃልል የሰብዓ ሊቃናት ተርጓሚያንም ኾኑ (አዘጋጁ እንደሚያምነው የዕብራውያን ጸሓፊ የሆነው) ነዋየ ኅሩይ ቅዱስ ጳውሎስ የዕብራይስጡን መልእክት በማዛባት ሊፈረጁ የሚችሉበት አሳማኝ ምክንያት የለም።