“ከመሥዋዕት ይልቅ ምህረትን እወዳለሁ” – ታድያ የኢየሱስ መሠዋት ለምን አስፈለገ?
በማቴዎስ 9:13 ላይ “ከመሥዋዕት ይልቅ ምህረትን እወዳለሁ” ይላል፡፡ አምላክ “ከመስዋዕት ይልቅ ምህረትን እወዳለሁ” እያለ እንዴት ዓለም በሠራው ኃጢአት ምህረት ማድረግ ሲችል ኢየሱስን በማሠቃየት መሥዋዕት አደረገው?
ጠያቂው የጠቀሱት ክፍል ስለ እግዚአብሔር ምህረት ሳይሆን ሰዎች ለባለንጀሮቻቸው የሚያደርጉትን ምህረትና ለእግዚአብሔር ያላቸውን ታማኝነት የተመለከተ ነው፡፡ ጌታችን ቃሉን የጠቀሰው ከትንቢተ ሆሴዕ 6፡6 ላይ ሲሆን በዕብራይስጥ “ኼሲድ” የሚለው “ምህረት” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ሰው ለባለንጀራው የሚያሳየውን ቀና ባሕርይ ወይም ለእግዚአብሔር ያለውን ሎሌነት እንዲሁም እግዚአብሔር ከአገልጋዮቹ የሚጠብቀውን ሁሉ በጥቅሉ የሚያመለክት ነው፡፡ ሆሴዕ 6፡4 ላይ ይኸው ቃል “ፍቅር” ተብሎ ተተርጉሞአል፡፡ ለእግዚአብሔር ፈቃድ ታማኝ ሳይሆኑ መሥዋዕት ማቅረብ በእርሱ ዘንድ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም (1ሳሙኤል 15፡22-23፣ ኢሳይያስ 1፡11-20፣ ኤርምያስ 7፡21-22፣ አሞፅ 5፡21-24፣ ሚክያስ 6፡6-8፣ ማቴዎስ 9፡13፣ 12፡7)፡፡[1] ስለዚህ የክፍሉ መልዕክት እግዚአብሔር ከሰው ለእርሱ ከሚቀርብ መስዋዕት ይልቅ ሰው ለባለንጀራው የሚያሳየው ምህረት እና ለእርሱ ያለው ታማኝነት ያስደስተዋል የሚል እንጂ ያለ ክርስቶስ መስዋዕትነት የሰው ልጆች ከኃጢአታቸው ይድናሉ የሚል አይደለም፡፡
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ጠያቂው ክፍሉን የተረዱበት መንገድ ትክክል ቢሆን እንኳ (ስህተት መሆኑ ይሰመርበት) ድምዳሜያቸው ትክክል ሊሆን አይችልም፡፡
እግዚአብሔር ሰዎችን ወደ ገሃነም ከመላክ ይልቅ ምህረትን ቢያደርግ ደስ ይለዋል ነገር ግን ምህረትን መውደዱ ሰዎችን ሁሉ ወደ ገነት እንዲያገባ እንደማያደርገው ሁሉ ከመስዋዕት ይልቅ ምህረትን መውደዱ ያለ መሥዋዕት ኃጢአትን ይቅር እንዲል ያስችለዋል ወደሚል ድምዳሜ አይመራም፡፡ እግዚአብሔር አፍቃሪ አባት የሆነውን ያህል ፍትሃዊ አምላክም በመሆኑ ምክንያት በኃጢአተኞች ላይ እንዲፈርድ ፍትሃዊ ባሕርዩ ግድ ይለዋል፡፡ ነገር ግን ከሥላሴ አካላት መካከል አንዱ የሆነው ወልድ የኃጢአት ዕዳችንን በመክፈል ከእግዚአብሔር ፍትሃዊ ፍርድ ነፃ አውጥቶናል፡፡ የእግዚአብሔር ፍትህና የእግዚአብሔር ፍቅር በእኩል ሁኔታ የተገለጡበት ብቸኛ ቦታ ቢኖር የክርስቶስ መስቀል ነው፡፡
ለእስልምና ሙግቶች ምላሽ