ለምን ሒጃብ?

ለምን ሒጃብ?

ዶ/ር ሻሎም መኮንን


ከዚህ ቀደም በዚህ ድረገፅ ያቀረብኳቸውን ጽሑፎቼን ትከታተል የነበረች እህት እርሷ አንዲት ያለቻት ግን ክርስትናን እንዳትቀበል የጋረዳትን ጻፈችልኝ። ይኸውም የክርስቲያን ሴቶች አለባበስ መልካም እንዳልሆነ እስላማዊ አለባበሶች ግን ልከኛ መሆናቸውን ነው። ከዚች እህት ጋር በተለዋወጥነው መልዕክት ርዕሱ ላይ ተግባብተን ብንጨርስም የሌሎች ክርስቲያኖችም ሆነ የሙስሊም እህቶቻችን ምልከታ በመሆኑ መረጃውን ይፋ ማድረግ የተሻለ ኾኖ አግኝቼዋለው። እንደ ወትሮው ኹሉ ከጽሑፉ ጠንከር ያለ እና የማይናወጥ ሐሳብ እንደምታገኙ ተስፋ እያደረኩ ወደ ዝርዝር ሐሳቡ ልግባ።

ሰዎች እስከሆንን፣ የሚያስብ አእምሮ እስካለን ድረስ “አንድን ነገር አድርጉ፣ ወይንም አታድርጉ” ስንባል የምናስከተለው ጥያቄ “ለምን?” የሚል ነው። ጤነኛ የአስተሳሰብ መንገድ ተከትለን ሙስሊም ሴቶች ስለምን ሒጃብ ግዴታ ተደረገባቸው ብለን ብንጠይቅ ከእሥልምና መዛግብት እንዲሁም ከሙስሊም መምህራን የምናገኘው ምላሽ አጥጋቢ ኾኖ አናገኘውም። ሙስሊም ሴቶች ለምን ሒጃብ ያደርጋሉ? ቁርኣን ለዚህ ጥያቄ “አጭር እና ግልጽ” መልስ እንዲህ በማለት ያስቀምጣል፦

“ነቢዩ ሆይ! ለሚስቶችህ፣ ለሴቶች ልጆችህም፣ ለምእምናን ሚስቶችም ከመከናነቢያዎቻቸው በላያቸው ላይ እንዲለቁ ንገራቸው፡፡ ይህ እንዲታወቁና (በባለጌዎች) እንዳይደፈሩ ለመኾን በጣም የቀረበ ነው፡፡ አላህም መሓሪ አዛኝ ነው፡፡” የአሕዛብ ምዕራፍ 59 (ሱራ 33)

US school demands 'letter from clergy' to allow students in hijab

በዚህ የቁርኣን ክፍል ላይ እንደተመለከትነው ሙስሊም ሴቶች ሒጃብ የሚለብሱበት ዋናው ምክንያታቸው እራሳቸውን “ከደፋሪዎች” ለመከላከል ነው። ምክንያቱ ትንሽ አስቂኝ ይመስላል። <ሒጃብ ጨርቅ እንጂ ብረት አይደል> በሚል እዚህ ጋር ርእሱን ማብቃት ይቻላል። ነገር ግን በጉዳዩ ላይ “ደጋፊም ኾነ ነቃፊ” ባለመሆን እንቀጥል። እንደተባለው ሒጃብ የማድረግ ዋና ምክንያቱ ይህ ከሆነ “የመደፈር አደጋ ያለባቸው” ላይ ብቻ እንጂ ሁሉም ሴቶች ላይ ግዴታ መደረግ አልነበረበትም። የመደፈር አደጋ የማይደርስባት ሴት፣ እድሜዋ የተቃራኒ ፆታን የወሲብ ስሜት ቀስቃሽ ካልሆነ፣ ጥቃቱ እንዳይደርስባት የሚከላከሉ ጠባቂዎች ካሏት እንዲሁም በተለያየ ምክንያት ልትደፈር ፈጽሞ የማትችልን ሴት ሒጃብ እንድታደርግ ማስገደድ “ሒጃብ ከታዘዘበት” ዋና ምክንያት ጋር በእጅጉ ይጣረሳል። ሒጃብ ለሴት ልጅ ግዴታ የሆነባት “እንዳትደፈር ነው” ከተባለ “የማትደፈር ሴትን” በግድ ሒጃብ አድርጊ በሚል ማስገደድ ከአመክንዮ በእጅጉ የራቀ ጅምላ ፈራጅ ትእዛዝ ነው። የዘጠና አመት ሴት፣ የሁለት አመት ህፃን፣ አካል ጉዳተኛ ሴት፣ እንደው ጠቅልሎ ሴቶች ሁሉ ላይ ግዴታ ጥሎ “እራስን ከመደፈር ለመከላከል ሒጃብ ማድረግ” በሚል እንደ መፍትሄ ማስቀመጥ ትክክል አይደለም። ይህ ማለት በሌላ ቋንቋ በሽታ ለሌለበት ሰው ይህ ጥሩ “መድኃኒት” ነው ብሎ እንደማዘዝ ነው። ይህ የሁሉን ቻይ አምላክ ትዕዛዝ ሊሆን ቀርቶ የሚያገናዝብ፣ መዝኖ ትእዛዝ የሚያስተላልፍ አእምሮ ያለው ሰው ውሳኔ ፈፅሞ ሊሆን አይችልም።

ከዚህ በመቀጠል የሚመጣው ጥያቄ አንዲት ሴት ሒጃብ ማድረጓ ከደፋሪዎች ያስጥላታል ወይ? የሚል ነው። ለዚህም ቀላል እና አጭር መልሱ “በጭራሽ!” የሚል ነው። እንዲያውም በተቃራኒው አንድ ወንድ የሚስቱና የሌላ ሴት አለባበስ እንዲሁም አቋቋም ከተመሳሰለ ትኩረቱን ወደዚያች ሴት የማድረግ እድሉ እንደሚጨምር ባለሙያዎች ይናገራሉ። በዚህ ስሜት ካየነው ለሁሉም ሴቶች ተመሳሳይ ዓይነት ልብስ ማዘዝ ደፋሪዎችን ምናልባት የሚገፋፋ ቢሆን እንጂ አይከላከልም። በሙስሊም ሰባክያን ዘንድ “ያረጀ፣ ያፈጀ” በጥናት ያልተደገፈ የመንደር ወሬን እንደ ትልቅ ግኝት በፕሮፌሽናል ደረጃ ሲያቀርቡልን መስማቱ የተለመደ ነው። እስካሁን አስገድደው በሚደፍሩ ሰዎች ዙርያ በርካታ ጥናቶች ተካሂደዋል። በዘርፉ ምሁራን ዘንድ ሴት ልጅ የመረጠችው የአለባበስ ዓይነት ለመደፈር ምክንያት ይሆናል የሚል ምልከታ የለም። የአስገድዶ ደፋሪዎች ምክንያት የማሕበራዊ ተግባቦት ችግር፣ ብስጭት፣ መከፋት፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ከተደፋሪዋ ጋር መጋጨት፣ የባሕርይ ብልሹነት፣ ፀረ-ማህበረሰብ የስብዕና እክል፣ ሴት ልጅ በእራሷ የመወሰን አቅም የላትም የሚል አመለካከት እና የመሳሰሉት ናቸው። እንደ እውነቱ ከሆነ እስልምና የሴትን ልጅ መደፈር የሚያበረታታ እንጂ የሚከላከል አለመሆኑ እስልምናን ላጠኑ ሰዎች ሁሉ ግልፅ ነው። ሴት ልጅ ባሏን መፍታት አትችልም፣ ሴት ልጅ እርሻ ስለሆነች ገብታችሁ እረሱ፣ ሴት ልጅ በየትኛውም ቦታ ባሏ ለወሲብ ከጠየቃት ያለመፍቀድ መብት የላትም። ብዙ ማንሳት ይቻላል። (ለበለጠ መረጃ ሴቶች በቁርኣን በሐዲስና በመጽሐፍ ቅዱስ በሚል ርዕስ የተዘጋጀውን መጣጥፍ ይመልከቱ።) እንደዚህ ዓይነት አመለካከቶችን የያዘ ኃይማኖት ወደኋላ ተመልሶ ሴት ልጅ እንዳትደፈር መፍትሄ “ሒጃብ ማድረግን” ማቅረቡ አስገራሚ ነው። ሙስሊም ሰባክያን ከልባቸው ለሴት ልጅ መደፈር የሚቆሮቆሩ ከሆነ አስገድዶ መድፈርን የሚያበረታቱ እስላማዊ አመለካከቶችን እንደ ሌሎች ኋላ-ቀር እስላማዊ ዕይታዎች ሁሉ ለማደስ መጣር ይኖርባቸዋል። ሳይንሳዊ የሆኑ አመለካከቶችን እስልምና ውስጥ ለማስገባት በሚጥሩበት ልክ፣ የአኢሻን ዕድሜ ወደ አቅመ ሄዋን ለማድረስ የሚታገሉትን አቅም ወደዚህ ማዞር ይገባቸዋል።

በርግጥ እንደ ክርስቲያንነቴ ከአካባቢው ባሕል፣ ከተለመደው አለባበስ ያፈነገጠ ዓይነት እንዲሁም እጅግ የተገላለጠ አለባበስን አልደፍግም። ቢሆንም በቁርአን የቀረበው የሒጃብ አድርጉ አመክንዮ አእምሮውን ለማሰብ ለሚጠቀምበት፣ በየትኛውም ዓይነት አካባቢ ባሕል ላደገ ሰው አይዋሓድም። አንድ ወንድ ሴትን ልጅ የሚደፍረው በውስጣዊ ችግሩ እንጂ በአለባበሷ ምክንያት ፈፅሞ አይደለም። ለሴት ልጅ ያለፈቃዷ መደፈር በየትኛውም መንገድ ተጠያቂው “ደፋሪው” ብቻ ነው። ምሳሌ ላቅርብ፦ ባንክ ገብቼ ገንዘባቸውን ፊት ለፊት ስላስቀመጡ ነጠኳቸው፣ ወይንም ዘረፍኩ የሚባል ምላሽ በየትኛውም መንገድ ከተጠያቂነት አያድንም። ነገር ግን ቁርአንም ሆነ እስልምና የተደፈረችን እንስት በዚህ ምክንያት “ስለመደፈሯ ተጠያቂ ” በማድረግ ስሜታቸው በሽታ ለሆነባቸው ወንጀለኞች ተባባሪ እየሆኑ እንዳለ መገንዘብ ያስፈልጋል። ሒጃብ ግዴታ የሚደረግበት ምክንያቱ ሴት ልጅ እራሷን ከደፋሪ ለመከላከል ከሆነ ምክንያቱ ፈፅሞ አያስኬድም።

ሒጃብን አምርረን ለምን እንቃወማለን?

የሙስሊም ሰባኪዎች “ሒጃብን የሀያ አንደኛው ክፍለዘመን አእምሮ” ሊቀበለው ስላልቻለ እጅ ቢሰጡም እኛን ለማሳጣት የሚሄዱበት ረጅም መንገድ አለ። እርሱም “መጽሐፍ ቅዱስም ቢኾን እኮ ያዛል፣ የካቶሊክ እና የኦርቶዶክስ መነኮሳትም እንደሙስሊም ሴቶች ይሸፋፈናሉ! ነገር ግን እስልምና ላይ ሲሆን ብቻ ጭቆና ትላላችሁ” የሚል ማምለጫ ነው። እርግጥ ነው! የካቶሊክ እና የኦርቶዶክስ መነኮሳት ይሸፈናሉ። ነገር ግን ሰባክያኑ ሒጃብን የምንቃወንበትን ምክንያት ለመረዳት የፈለጉ አይመስልም። አንዲት የካቶሊክ ወይንም የኦርቶዶክስ መነኩሴ መሸፈኛዋን ካወለቀች እንደ እስልምናው አለም የሚገርፋት፣ ከቤቷ የሚያባርራት አካል የለም። መሸፋፈኗን ወዳ እና ፈቅዳ ነው የምታደርገው። አንዲት ሙስሊም ሴት “ሒጃብ ምርጫዬ ነው” ብትልም ሒጃቧን አውልቃ ብትጥል የሚደርስባትን መከራ አሳምራ ታውቀዋለች። እኛ ሒጃብን ከሌሎች ዓይነት ሃይማኖታዊ አለባበሶች በመነጠል ስንቃወም “ግዴታ አይሁን” በሚል እንጂ ሒጃብ ምርጫቸው ቢሆን እንኳ እንዳይለብሱ የሚል አመለካከት የለንም። በእርግጥ በሒጃብ ስር የሚፈጸሙ በርካታ የሽብር ጥቃቶችና ወንጀሎች ቢኖሩም ሒጃብን ጠቅልሎ የመከልከልና ያለመከልከል ድርሻ የመንግሥት ባለስልጣናት እና የፀጥታ ኃይላት ነው።

ሒጃብና የጤና ጉዳቱ

በባለሙያተኞች ሰፈር ቀርቶ የትኛውም ሰው በአጋጣሚ እንኳን “ልጆቻችሁን ፀሐይ አሙቁ፣ የፀሐይ ሙቀት ቫይታሚን አለው” እየተባለ በመገናኛ ብዙኅን ሲለፈፍ መስማቱ የማይቀር ነው። የፀሐይ ሙቀት በቆዳችን የሚገኘውን ዲሀይድሮኮሌስትሮል ሰባት የተባለን ንጥረ ነገርን ወደ ቫይታሚን ዲ’ ነት እንዲቀየር ያደርጋል። ስለዚህ የፀሐይ ሙቀት ረብ የለሽ ሳይሆን አስፈላጊ ነው። በቂ የፀሐይ ሙቀት አለማግኘት የቫይታሚን ዲ እጥረት ችግር (vitamin D deficiency) ዋነኛ መንስኤ ነው። የቫይታሚን እጥረት ከሚያስከትላቸው የጤና መዘዞች ውስጥ የተወሰኑትን እንበል። የአሜሪካ ብሄራዊ ካንሰር ተቋም የቫይታሚን ዲ እጥረት የጡት ካንሰርን ጨምሮ የተለያዩ ዓይነት ካንሰሮች እንደሚያመጣ ይጠቁማል። https://www.cancer.gov/news-events/cancer-currents-blog/2016/vitamin-d-metastasis

በቂ ፀሐይ አለማግኘት ተፈጥሮአዊውን የሰውነት በሽታ የመከላከል አቅም ያዳክማል። ሰውነታችን በሽታን የሚከላከልበት በኹለት ዓይነት መንገዶች ነው። አንደኛው ከተፈጥሮ የወሰድነው የመከላከል አቅም ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በክትባቶች እንዲሁም በመድኃኒቶች የምናገኘው ነው። ቫይታሚን ዲ የበሽታ ተከላከይ ህዋሶች ማለትም ኒትሮፊሎች ማክሮፌጆች በሽታ ተዋጊ ሕዋሶች በመለጠፍ ከውጪ የመጣ ባእድ ነገርን (በሽታን) እንዲዋጉ የሚያግዛቸውን ንጥረ ነገሮች እንዲያዘጋጁ ያደርጋል። በቂ የቫይታሚን አቅርቦት በሰውነታችን ከሌለ ሰውነታችን በሽታ የመከላከል አቅሙ ይጎዳል። ቫይታሚን ዲ “የስኳር ሕመም፣ የአጥንት መሳሳት፣ ጭንቀት፣ ካንሰር፣ የመርሳት ችግር (አልዛይመር)” ወዘተ. ከ53 በላይ በሽታዎች ጋር ቀጥታ ግንኙነት እንዳለው የተሠሩ ጥናቶች ያሳያሉ። እኛ ሰዎች ካሉን ጠቅላላ ጂኖም 3% የሚያህሉት በቫይታሚን ዲ የሚዘወሩ በመሆኑ የዚህ ንጥረ ነገር እጥረት በሰውነታችን ከተከሰተ ከ1000 በላይ ጂኖች መጎዳታቸው አይቀሬ ነው።  https://www.ed.ac.uk/vet/news-events/news-and-archive/2019-news/how-vitamin-d-affects-the-immune-system

በቅርቡ በኮቪድ ህመምተኞች ዙርያ በተሠራ ጥናት በቂ ቫይታሚን ዲ በሰውነታቸው ያላቸው ሰዎች የኮቪድ ህመም አይበረታባቸውም። በተቃራኒው በቂ የቫይታሚንድ ዲ በሰውነታቸው የሌላቸቸው ሰዎች ሲማቅቁ እና ሲሞቱ ታይቷል። https://journals.plos.org/plosone/article?id=10.1371/journal.pone.0239799

የቫይታሚን እጥረትን በተመለከተ የእንግሊዝ ብሔራዊ ጤናት ያስነበበውን ጽሑፍ በዚህ አድራሻ ታገኛላችሁ https://www.nhs.uk/conditions/vitamins-and-minerals/vitamin-d/

ከቫይታሚኑ መለስ ስንል ፀጉርን ሁሌ መሸፈን በቂ ኦክስጅን ወደ ፀጉር እንዳይደርስ ስለሚያደርግ ለፎሮፎርና ለፀጉር ድርቀት ያጋልጣል። ከፀሐይ የምናገኘው ቫይታሚን ዲ በቆዳችን ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውለው በኬራቲኖሳይት አማካኝነት ነው። እነዚህ ኬራቲንን፣ በፀጉር፣ በጥፍር እና በቆዳ ውስጥ ያለ ፕሮቲን የሚያቀነባብሩ የቆዳ ሴሎች ናቸው። በቂ የፀሐይ ሙቀት ካላገኘን በፀጉር ከረጢቶች ውስጥ ያሉት ኬራቲኖሳይቶች እክል ስለሚገጥማቸው የፀጉር መነቃቀልን፣ መመለጥ፣ የጥፍር በሽታ ወዘተ ያጋጠመናል። ከጊዜ አንፃር እንጂ ብዙ ማለት ይቻላል። ለማንኛውም የተወደድሽው ሙስሊሟ እህቴ መረጃዎችን የማታገላብጪ ከሆንሽ አንድ ጥያቄ በውስጥሽ መመላለሱ አይቀርም። እንዴት ስንት ሚልየን ሴቶች ሒጃብ እያደረጉ ምንም አልሆኑም? እንደምትይ እገምታለው። እኔም በደንብ ሆነዋል እልሻለሁ። በቢልየኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በዓለም ላይ የቫይታሚን ዲ እጥረት አለባቸው። የሌላው ዓለም ተጠቂዎች የፀሐይ ሙቀት ስለማይደርሳቸው ቢባል የዐረቡ ዓለም ግን በቂ ከበቂም በላይ የፀሐይ ሙቀት እየደረሳቸው (15°- 36°N) የዚህ እክል ተጠቂዎች መሆናቸው አስገራሚ ነው። [Michael F Holick and Tai C Chen. Vitamin D deficiency: a worldwide problem with health consequences. Am J ClinNutr 2008; 87(4): 1080S– 6S]

የቫይታሚን ዲ እጥረት በዐረቡ ዓለም ወረርሽኝ የሆነው በሒጃብ ምክንያት ብቻ ላይሆን ይችላል። የሙስሊም ባለሙያዎች የዐረቡ ዓለም ነዋሪዎች በዚህ እጥረት መጠቃታቸው የአኗኗር ሁኔታቸው፣ እራስን ለፀሐይ አለማጋለጥ ተለምዶአዊ በመሆኑ እንደሚሆን ይገምታሉ። በየትኛውም መንገድ ቢባል ግን ሒጃብን ማስመለጥ አይቻልም። አንድ በሩቅ ምስራቋ የሙስሊም ሀገር በባንግላዴሽ ተሠራ በተባለ ጥናት ሒጃብ በሚያደርጉ እና በማያደርጉ ሴቶች ጉልህ ልዩነት አልታየም ይለናል። [Islam MZ, Akhtaruzzaman M. Hypovitaminosis D is common in both veild and nonveild Bangladeshi women. Asia Pac Clin Nut. 2006; 15: 81-87] የሙስሊሙ ዓለም አድሎ ለሌለበት ሃቀኛ ምርመራ ብዙ ጊዜ ዝግ ከመሆኑ አንጻር እንዲህ ያሉ መረጃዎችን ማመን ቢቸግርም ሒጃብ ከፀሐይ ብርሃን በቂ ቫይታሚን ዲ እንዳናገኝ እንደሚያደርግ ፊደል ከቆጠረ ሰው ሁሉ የሚሰወር አይደለም። አንድ በኢራን ሀገር በሚኖሩ ተሸፋፋኝ ሙስሊም ሴቶች ላይ የተሠራ ጥናት ሴቶቹ የዚህ ንጥረ ነገር እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚታይባቸው አረጋግጧል። [Shahla, Charehsaz S, Talebi R, Omrani M. Vitamin DDeficiency in Young Females with Musculoskeletal Complaints in Urmia, Northwest of Iran. IJMS. 2005; 30 (2)] ይህ ከሆነ ደግሞ ቫይታሚን ዲ እጥረት ለበርካታ በሽታዎች ስለሚዳርግ መሸፋፈን በጤንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል።

ምክር ለሙስሊም እህቶች

የተወደድሽ ሙስሊሟ እህቴ፤ ከላይ በአጭሩ የዘረዘርኩልሽ እውነት መሆኑን የጤና ባለሙያዎችን በመጠየቅ፣ የኅክምና ነክ መጣጥፎችን በማንበብ፣ እንዲሁም ከራስሽ ሕይወት በመነሳት ጉዳቱን ማረጋገጥ ትችያለሽ። ፀጉርሽ በመሸፈኑ ጤነኛ ነው? የፀጉርሽ ዘለላዎች አይነቃቀሉም? ፎሮፎር፣ የፀጉር ድርቀት ወዘተስ የለብሽም? የእኔ እህት እዚህ ጋር ልብ እንድትይ የምፈልገው ነገር አለ። ክረምት በሽታዎች የሚበዙት አንዱ ምክንያት በቂ የፀሐይ አቅርቦት ባለመኖሩ ሰውነታችን ቫይታሚን ዲ ባለማግኘቱ ነው። ሙስሊም ወንዶች ሴቶች ሒጃብ እንዲያደርጉ አጥብቀው ቢናገሩም ተከትሎ የሚመጣብሽን ነገር ያንቺን ያህል አያስተውሉም። ሒጃብ ለምን ታደርጊያለሽ? እንዳትገረፊ፣ ስቃይ እንዳይገጥምሽ መሆኑ ይገባኛል። ነገር ግን ሒጃብ የምታደርጊው እንዳትደፈሪ ከሆነ ሒጃብ የብረት ልብስ አይደለም፤ ሊከለክልልሽ ፈፅሞ አይችልም። ሙስሊም ወንዶችን ላለማሰናከል ከሆነም ሌሎች ሴቶች እንደልባቸው እየለበሱ የአንቺ ተጀባቡኖ መውጣት ሙስሊም ወንዶችን ከመሰናከል ለማስጣል ምንም ጥቅም የለውም። መጽሐፍ ቅዱስ ባህሉንና ዘመኑን የዋጀ ልከኛ አለባበስ እንድንለብስ ያዛል። እንድትገላለጪ እየነገርኩሽ አይደለም። የአለባበስ ምርጫሽ የእራስሽ ሆኖ ሳለ ልከኛ፣ አካላዊ ጤናሽንም ሆነ መንፈሳዊ ሕይወትሽን የማይጎዳ አለባበስ እንድትለብሺ እመክራለሁ፦

“እንዲሁም ደግሞ ሴቶች በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራሳቸውን ከመግዛት ጋር ሰውነታቸውን ይሸልሙ፤ እግዚአብሔርን እንፈራለን ለሚሉት ሴቶች እንደሚገባ፥ መልካም በማድረግ እንጂ በሽሩባና በወርቅ ወይም በዕንቍ ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ አይሸለሙ።” (1ኛ ጢሞቴዎስ 2፥9-10)

“ለእናንተም ጠጕርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጎናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ።” (1ኛ ጴጥሮስ 3:3-4)


ሴቶች በእስልምና