አላህ አታላይ ነውን?

አላህ አታላይ ነውን?


አንዲት ሙስሊም ወገናችን አላህ “አታላይ” መባሉን በተመለከተ በማሕበራዊ ሚድያ ላይ ለለጠፍኩት አንድ አስተያየት ምላሽ በሚል መጠነኛ ሐተታ ይዛ ብቅ ብላለች፡፡

ሙስሊሟ ወገናችን ይህ ስም ከ 99ኙ የአላህ ስሞች መካከል አይደለም በማለት በከረረ ንግግር ትችት ሰንዝራለች፡፡ ቁርአን ለአላህ በሰጠው በዚህ መጠርያ አላህን መጥራት እንደማይቻልም ትነግረናለች፡፡ ይህ የልጅቱን የመረጃ እጥረት የሚያሳይ ነው፡፡ በሳሒሕ ሐዲሳት አላህ 99 ስሞች እንዳሉት ቢገለፅም የስሞቹን ዝርዝር በተመለከተ ከሙሐመድ የተላለፈ ግልፅ መረጃ ባለመኖሩ ሙስሊም ሊቃውንት የተለያየ ዝርዝር አዘጋጅተዋል፡፡ ስሞቹ አንድ ላይ ሲደመሩ በአጠቃላይ ወደ 276 ይመጣሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል خير الماكرين (ኸይር አል-መክሪን) “Best of deceivers” “ከአታላዮች ሁሉ የበለጠ አታላይ” የሚለው አንዱ ነው፡፡ የአረብኛው የዊኪፒድያ ገፅ በተለያዩ ሙስሊም ሊቃውንት የተጠቀሱ 10 ዝርዝሮችን ያካተተ ሲሆን የአላህን አታላይነት የሚገልፀው ስም አንዱ ነው፡፡ https://ar.wikipedia.org/…/%D8%A3%D8%B3%D9%85%D8%A7%D8… ስለዚህ ሙስሊም ሊቃውንት በዝርዝሩ ባልተስማሙበት ሁኔታ የሚመቻትን ብቻ መርጣ አታላይ የሚለው በዝርዝሩ ውስጥ የለም የሚለው አባባሏ ተቀባይነት የለውም፡፡

በዚህ ዘመን በብዙ ሙስሊሞች ዘንድ የታወቀው ዝርዝር በጃሚ አት-ቲርሚዚ ቅፅ 6፣ መጽሐፍ 45፣ ሐዲስ ቁጥር 3507 ላይ የሚገኝ ሲሆን ደኢፍ (ደካማ) ሐዲስ ነው፡፡ ተከታዩ የሐዲስ ገፅ ላይ ገብቶ ማየት ይቻላል፤ ከስር “ደኢፍ” የሚል ማሳሰብያ ተጽፎበታል፡- https://sunnah.com/tirmidhi/48/138

በብዙ ሙስሊሞች ዘንድ የተለመደው ይህ ዝርዝር “አላህ” የሚለውን ጨምሮ በቁርአን ውስጥ የሚገኙ ብዙ የአላህ መጠርያዎችን ያላካተተ ሲሆን በቁርአን ውስጥ ይገኛሉ ተብለው ጥቅስ የተጠቀሰላቸው ብዙዎቹ ስሞች በአረብኛው ቁርአን ውስጥ ተጠቅሰው አናገኛቸውም፡፡

ሙስሊም ወገኖቻችን የስሞቹ ዝርዝር ላይ ስምምነት በሌለበት ሁኔታ ከደኢፍ ሐዲስ በተገኘ ዝርዝር ላይ ተመስርተው እነዚህን 99 ስሞች የሸመደደና ያነበነበ ሰው ገነት እንደሚገባ ማመናቸው ሌላው አስገራሚ ነገር ነው፡፡ በርግጥ ይህንን የሚለው ሐዲስ የተላለፈው ከሙሐመድ ነው (ሳሂህ አል-ቡኻሪ ቅፅ 9፣ መጽሐፍ 93፣ ሐዲስ ቁጥር 489)፡፡

እነዚህን ስሞች በተመለከተ ብዙ የምንለው ነገር ስላለን ወደ ፊት እግዚአብሔር ቢፈቅድ በሌላ ጽሑፍ እንመለሳለን፡፡ (ለምሳሌ ያህል ብዙዎቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት የክርስቶስ ማዕረጋት የተቀዱ ስለመሆናቸው፣ አንዳንዶቹ ለእውነተኛው አምላክ ተገቢ አለመሆናቸው፣ ወዘተ.)፡፡ የሆነው ሆኖ ሙስሊሟ ወገናችን የገዛ ሃይማኖቷን በትክክል እንድታጠናና ከአጉል ትችት እንድትቆጠብ እንመክራታለን፡፡


እዚህ ልጥፍ ስር በሙስሊም እህታችን የተሰጠ ምላሽና የኔ ምላሽ ይህንን ይመስላል፦

ሙስሊም፦ ከየት አመጣህው 276 ፖስቴን አንብበህዋል?? አላህ በቁርኣን ከጠቀሳቸው ማለትም እኛ እንድናውቃቸው ከተገለጡት 99 ስሞዎች ውስጥ አል መከር የሚባል የለም ። በቁርኣን የተጠቀሠው ቃላት ሁሉ የአላህ ስም ነው ከሆነ 276 ብቻ ሆነብህ

የኔ ምላሽ፦ ከላይ የተባለው ያልገባው ብቸኛ ሰው እዚህ ገፅ ላይ አንቺ ብቻ ነሽ። በሌላ ኮሜንት ነሲኽ ወልመንሱኽ በቁርአን ውስጥ የለም ብለሽ ስትከራከሪ ያየሽ ሰው ይህ ጉዳይ እንዲገባሽ አይጠብቅም። ገና ብዙ ይቀርሻል። ለማንኛውም ከላይ ባለው ጽሑፍ ውስጥ የሚከተሉት ነጥቦች ተገልፀዋል።

  1. 99ኙ የአላህ ስሞች የትኞቹ ናቸው በሚለው ጉዳይ ዙርያ ሙስሊም ሊቃውንት አልተስማሙም።
  2. አላህ በቁርአን ውስጥ خير الماكرين (ኸይር አልመክሪን) ተብሎ ተጠርቷል (3:54)።
  3. ዛሬ ብዙ ሙስሊሞች የተቀበሉት خير الماكرين የሚለውን የአላህ ቁርአናዊ መጠርያ ያላካተተው የ99ኙ ስሞች ዝርዝር ሐዲሱ ደዒፍ ነው። የአላህ ስሞች የተባሉት ብዙዎቹም በቁርአን ውስጥ አይገኙም። ማስረጃውን ከላይ ተመልከቺ።
  4. 99ኙ የአላህ ስሞች ተብለው በሙስሊም ሊቃውንት የተዘጋጁ ከ10 በላይ ዝርዝሮች የሚገኙ ሲሆን በመካከላቸው የጋራ የሆኑት አንድ ጊዜ ብቻ ተቆጥረው ልዩነቶቹ ሲደመሩ 276 ናቸው። አሁንም ከላይ ሊንኩን ተመልከቺ።
  5. ሊንኩ ውስጥ እንደተመለከተው ኢብን አል-ዐረቢና ኢብን አል-ወዚሪን የመሳሰሉት ሊቃውንት خير الماكرين የሚለውን ከ99ኙ የአላህ ስሞች መካከል አስገብተው ቆጥረዋል። ስለዚህ 99ኙ የአላህ ስሞች ተብሎ የሚታወቀው ዝርዝር አንቺ የተቀበልሽው የደኢፍ ሐዲስ ዝርዝር ብቻ እንዳልሆነ ማወቁ ይጠቅምሻል።

ስለዚህ የአንድ ግለሰብ ኮፒ ይዘሽ በየቦታው እየዞርሽ ሰው ከምትዘልፊ ክርክሩ ይቅርብሽና ሰከን ብለሽ ተማሪ።

ሙስሊም፦ ዘለፋው ብሽሽቁ ይቆይህና በሙቀት ሳይሆን በእውቀት ተናገር በሙቀት ሳይሆን በስሌት ስራ በቁርኣን የተጠቀሱት የአላህ ስሞች 99 ብቻ ናቸው ። ከተጠቀሱት 99 የአላህ ስሞዎች ውስጥ መከረ የሚል የለም።ያ ማለት የአላህ ስም 99 ብቻ ናቸው ማለቴ አይዴለም እኛ የማናውቃቸው ተቆጥረው የማያልቁ አላህ ብቻ የማውቃቸው አሉ ። ለእኛ ግን 99 ዎቹ ብቻ ነው የእንድናውቅ የተገለፀልን! አላህ መከረ አልተባለም ። የተባለውም “ማኪሪን” ማለትም ከአድመኞች ሁሉ ፣ መረሓግብር ከሚያወጡት ሁሉ በላጭ ነው ማለት ነው።

3፥54 *አይሁዶችም አደሙ አላህም አድማቸውን መለሰባቸው፡፡ አላህም ከአድመኞች ሁሉ በላጭ ነው*፡፡ وَمَكَرُوا۟ وَمَكَرَ ٱللَّهُ ۖ وَٱللَّهُ خَيْرُ ٱلْمَٰكِرِينَ

“መከረ” مَكَرَ ማለት “አቀደ” “አሴረ” ማለት ነው፤ “ማኪሪን” مَٰكِرِين ማለት “ሴረኞች” አቃጂዎች” እና “አድመኞች” ማለት ነው፤ አላህ ከማኪሪን ሁሉ በላጭ ነው አለ እንጂ “ማኪር” مَٰكِرِ አልተባለም። ልዩነቱ ለተመልካች ይቀመጥ ቁርኣን ባይብል አይዴለም እንደፈለክ አትፈስር የቁርኣን ማዕና ለመረዳት አልታደልክም ። የሌለ ነገር ምህር ምህር አያጫውትህ

የኔ ምላሽ፦ እህት ከሌላ ሰው የወሰድሽውን ኮፒ ይዘሽ ስትዛለፊ የነበርሽው አንቺ ነሽ፡፡ እኔ የሚጠቅምሽን ነገር ነው የመከርኩሽ፡፡ ስለ እስልምና ለመሟገት መሠረታዊ አስተምህሮውን ማወቅ ይኖርብሻል፡፡ አልመከርም ካልሽ እኔ ምን ገዶኝ፡፡

በቁርአን የተጠቀሱት የአላህ ስሞች 99 ብቻ ናቸው የሚል ከየት አመጣሽ? ስሞቹ 99 መሙላታቸውን ወይም ከ 99 አለመብለጣቸውን በምን አወቅሽ? በጃሚ አት-ቲርሚዚ ውስጥ የሚገኘው ደኢፍ ሐዲስ በቁርአን ውስጥ የሚገኙ የተወሰኑ ስሞችን ያላካተተና በቁርአን ውስጥ የማይገኙ ብዙ ስሞችን ያካተተ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ፈጣሪነቱን የሚያሳየውን “አልፋጢር” እንዲሁም ጌትነቱን የሚያሳየውን “አርረብ” የሚሉ ወሳኝ ስሞችን አላካተተም፡፡ ሐዲሱ ያካተታውን ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል الخافض አልኻፊድ፣ الرافع አልራፊ፣ الواجد አልዋጅድ፣ المقدم አልሙቀዲም፣ ወዘተ. የሚሉ ስሞች በቁርአን ውስጥ የአላህ ስሞች ሆነው አልመጡም፡፡ አላህ በነዚህ ስሞች የተጠራባቸውን ቦታዎች ከቁርአን ውስጥ ካሳየሽኝ አንቺ በጣም ጎበዝ ነሽ፡፡ በስም ደረጃ የሌሉ በግሥ መደብ የተቀመጡ ሌሎች ብዙ ቃላት አሉ፡፡ ስለዚህ በስም ደረጃ ያልተቀመጡ የተወሰኑ ቃላትን ብቻ መርጠን ከ99ኙ ስሞች መካከል የምንቆጥርበትና ሌሎችን የምንተውበት ምክንያት ምንድነው? ለዚህ ነው ሊቃውንቶቻችሁ እርስ በርሳቸው የማይስማሙ የተለያዩ ዝርዝሮችን ያዘጋጁት፡፡

“ኸይር አልመክሪነ” ማለት የአማርኛ ተርጓሚዎች እንደተረጎሙት ሳይሆን Best of the Deceivers (ከአታላዮች/አጭበርባሪዎች/ተንኮለኞች/አድመኞች ሁሉ የበለጠ አታላይ/አጭበርባሪ/ተንኮለኛ/አድመኛ) ማለት ነው፡፡ አላህ ከአታላዮች ጋር ተቆጥሯል ነገር ግን ከእነርሱ የሚለየው ከእነርሱ በላይ አታላይ በመሆኑ ነው፡፡ የተለያዩ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የተዘጋጁ የአረብኛ መዝገበ ቃላት ቃሉን deceit, evasion, elusion, plot እያሉ ነው የተረጎሙት፡፡ አንድ የእንግሊዘኛ ተርጓሚ እንዴት ብሎ እንደተረጎመ ተመልከቺ፡-

“And they cheated/deceived and God cheated/deceived, and God (is) the best (of) the cheaters/deceivers.” (Sura 3:54) Muhammad Ahmed-Samira Translation

ሱራ 7፡99 ላይ ሁለት ጊዜ “መክረ አላሂ” ተብሏል፡፡ ሱራ 13፡42 የአታላይነት ሁሉ ምንጭ አላህ መሆኑ ተነግሯል፤ “ፊሊላሂ አል-መክሩ” ይላል፡፡ ሱራ 68፡45 ላይ አላህ ብርቱ ተንኮለኛ መሆኑ “ከይዲ” በሚል ቃል ተገልጿል፡፡ ተርጓሚዎቻችሁ ስለሚያድበሰብሱ እንጂ አላህ ከአታላዮች ሁሉ የላቀ አታላይ መሆኑ በብዙ ቦታዎች ተነግሯል፡፡ ለዚህ ነው ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ ኢብን አል-ዐረቢና ኢብን አል-ወዚሪን የመሳሰሉት ሙስሊም ሊቃውንት “ኸይሩ አልመክሪነ” (Best of the Deceivers) “ከአታላዮች ሁሉ የበለጠ አታላይ” የሚለውን ስም ከ99ኙ የአላህ ስሞች መካከል የሚያካትቱ ዝርዝሮችን ያዘጋጁት፡፡


ልዩ ልዩ