አሕመዲን ጀበልና የሙሐመድ መድብለ ጋብቻ
ሐሰተኛ ነቢይ ለመታደግ የተደረገ ከንቱ ጥረት
በማስከተል የሚገኘው ጽሑፍ አቶ አሕመዲን ጀበል የሙሐመድን የጋብቻ ሕይወት ከትችት ለመከላከል በፌስቡክ ላይ ለጻፏቸው ተከታታይ ጽሑፎች የሰጠኋቸው ምላሾች ስብስቦች ናቸው።
ጋብቻ ከኸዲጃ ጋር
አሕመዲን ጀበል ሙሐመድ ለ25 ዓመታት ከኸዲጃ ጋር በአንድ ለአንድ ጋብቻ ተወስኖ መኖሩን ከህልፈቷ በኋላ ለኖረበት መድብለ ጋብቻ እንደ ማፅደቂያ አድርገው አቅርበዋል። ሙሐመድ የሴሰኝነት ችግር ቢኖርበት ኖሮ እስከ 25 ዓመቱ ለምን ሳያገባ ኖረ? ከ25-50 ዓመቱ እንዴት በኸዲጃ ብቻ ተወስኖ ኖረ? የሚሉትን የመሳሰሉ አስቂኝ ጥያቄዎችን ይጠይቃሉ። መልሱ ግልፅና ቀላል ነው።
ሙሐመድ ከኸዲጃ ጋር በጋብቻ እስከ ተጣመረበት ጊዜ ድረስ በድኽነት ይኖር የነበረ ተንከራታች ወጣት ነበር። በዚያ የችግር ዘመን ደርሳ ከድኽነት ያስጣለችው ኸዲጃ ናት። እርሷ በሕይወት በነበረችበት ዘመን በአንድ ለአንድ ጋብቻ ተወስኖ የመኖሩም ምስጢር ይኸው ነው። በእርሷ ንብረት ከድኽነት ወጥቶ በቤቷ እየኖረ በእርሷ ላይ ደርቦ ማግባት የማይታሰብ ነው። ከእርሷ ህልፈት በኋላ በአንድ ለአንድ ጋብቻ ተወስኖ ቢኖር ኖሮ ከኸዲጃ ጋር በዚያ መንገድ የኖረው በፈቃዱ እንጂ ተገድዶ እንዳልሆነ መደምደም በቻልን ነበር። ከእርሷ ህልፈት በኋላ ደስ ያሰኘችውን ሴት ሁሉ (ዘመዶቹን ጨምሮ) እንዲያገባ አላህ እንደ ፈቀደለት በመናገር የቻለውን ያህል ሴት አግብቶ ኖሯል። ለምሳሌ ተከታዩን ጥቅስ እስኪ እንመልከት:-

በሀገራችን አክራሪ ወሓቢዝምን በማስፋፋት የሚታወቁት አቶ አሕመዲን ጀበል
ሱራ 33:50 “አንተ ነቢዩ ሆይ! እኛ እነዚያን መህሮቻቸውን የሰጠሃቸውን ሚስቶችህን፣ አላህ ባንተ ላይ ከመለሰልህም እነዚያን እጅህ የጨበጠቻቸውን ምርኮኞች፣ እነዚያንም ከአንተ ጋር፣ የተሰደዱትን የአንጎትህን ሴቶች ልጆች፣ የአክስቶችህንም ልጆች፣ የየሹማህንም ሴቶች ልጆች ፣ የየሹሜዎችሕንም ሴቶች ልጆች (ማግባትን) ለአንተ ፈቅደንልሃል፤ የአመነችንም ሴት ነፍሷን (ራሷን) ለነቢዩ ብትሰጥ ነቢዩ ሊያገባት የፈለገ እንደ ሆነ፣ ከምእምናን ሌላ ላንተ ብቻ የጠራች ስትሆን፣ (ፈቀድንልህ)፤ በነርሱ (በምእምናን) ላይ በሚስቶቻቸውና እጆቻቸውም በጨበጧቸው (ባሮች ነገር) ግዴታ ያደረግንባቸው በእርግጥ አውቀናል፤ ባንተ ላይ ችግር እንዳይኖር፣ (ያለፉትን ፈቀድንልህ)፤ አላህም መሐሪ አዛኝ ነው።”
በዚህ የአላህ ፈቃድ መሠረት ሙሐመድ የአክስቱ ልጅ የነበረችውን ለማደጎ ልጁ ተድራ የነበረችውን ዘይነብን ጭምር ከባሏ ነጥቆ አግብቷል። እነ አሕመዲን መልስ የሌለውን ጉዳይ አንስተው ራሳቸውን ከሚያስጨንቁ ዝም ቢሉ ይሻላቸው ነበር። ለበለጠ መረጃ ይህንን ጽሑፍ ያንብቡ https://ewnetlehulu.net/zaynab/
ጋብቻ ከሰውዳ ቢንት ዘምዓ ጋር
አቶ አሕመዲን ጀበል የሙሐመድን የመድብለ ጋብቻ ሕይወት ለማጽደቅ መናኛ ሙግቶችን ማቅረባቸውን ቀጥለዋል። በባለፈው ጽሑፋቸው በኸዲጃ ላይ ደርቦ ስላላገባ ሙሐመድ ሴሰኛ አልነበረም በማለት የተከራከሩ ሲሆን ለዚህ ግልጽ የሆነው ምክንያት በችግር ዘመኑ ደርሳ ከድኽነት ባወጣችው ከበርቴ ሴት ላይ ደርቦ ሊያገባ የሚችልበት ዕድል አልነበረውም የሚል ነው። ኸዲጃ ከመካ ቱጃሮች መካከል ቀዳሚዋ ናት። በኃብቷ የተገዛው ሙሐመድ በእርሷ ላይ ደርቦ ሊያገባ ቢሞክር የሚደርስበትን አበሳ ማሰብ አያዳግትም። በመሆኑም ከኸዲጃ ጋር የኖረባቸው ዘመናት ትክክለኛ ማንነቱን ለማወቅ የሚያስችሉ አይደሉም። አሕመዲን ይህንን ሃቅ ችላ በማለት የሙሐመድን መልካምነት ሊያሳምኑን መታገላቸው አስገራሚ ነው።
በአዲሱ ጽሑፋቸው ደግሞ ያቀረቡት ሙግት ሙሐመድ ሴሰኛ ቢሆን ኖሮ ሰውዳ ቢንት ዘምዓ የተሰኘችውን የ55 ዓመት መበለት አያገባም ነበር የሚል ነው። ይህቺን ሴት እንዲያገባ ኸውላ ቢንት አል ሐኪም የተሰኘች ሴት ምክር የለገሰችው ሲሆን ከአቡበክር ልጅ ከአኢሻ እና ከሰውዳ መርጦ እንዲያገባ አማራጭ ጥቆማ ተሰጥቶት ነበር። ነገር ግን ሙሐመድ ሰውዳን መረጠ፤ ይህ ደግሞ መልካም ሰው መሆኑን ያሳያል – እንደ አሕመዲን።
ይህ ሙግት ብዙ ችግሮች አሉበት፦
1ኛ. ማንኛውም ወንድ የቀድሞ የትዳር አጋሩ በሞት ከተለየችውና እንክብካቤ የሚያሻቸው ልጆችና ኃብት ካሉት በዕድሜ በሳል ሴት እንደሚመርጥ የታወቀ ነው። ስለዚህ ሙሐመድ ሰውዳን መምረጡ ያን ያህል የሚያስገርም አይደለም።
2ኛ. ሙሐመድ ቤቱን ማስተዳደር የማትችለውን በወቅቱ የ6 ዓመት ህፃን የነበረችዋን አኢሻን ከማግባት ይልቅ ሰውዳን ካገባ በኋላ በማስከተል ደግሞ አኢሻን ማግባቱ ትርፍና ኪሳራውን እያሰላ የሚነቀሳቀስ ሰው እንደ ነበረ እንጂ ህፃናትን ጨምሮ ለሴቶች ጤናማ ያልሆነ ፍላጎት የነበረው ሰው አለመሆኑን አያሳይም።
3ኛ. አቶ አሕመዲን እያሉን እንዳሉት ሙሐመድ ፍትሃዊና ጻድቅ ሰው ቢሆን ኖሮ ሰውዳን ከተጠቀመባት በኋላ ሌሎች አማራጮችን ሲያገኝ ባልጣላት ነበር። በእስላማዊ ምንጮች መሠረት ሙሐመድ ኋላ ላይ ሰውዳን ችላ ያላት ሲሆን እርሷም እንዳይፈታት ስለለመነችው የዕለት ጉርሷን ብቻ እየሰፈረላት የእርሷን ቀን ከአኢሻ ጋር እንዲያሳልፍ ተስማምታለች። ድንቄም ጻድቅ ሰው! (ለበለጠ መረጃ ይህንን ጽሑፍ ያንብቡ https://www.answering-islam.org/Shamoun/sauda.htm
4ኛ. የአንድ ሰው ስብዕና የሚለካው በችግር ዘመን ሳይሆን በስኬት ዘመን ነው። ሙሐመድ ከኸዲጃ ጋር በኖረበት ዘመንም ሆነ ከእርሷ ህልፈት በኋላ በነበሩት ጥቂት ዓመታት በነበረው ሕይወቱ ትክክለኛ ማንነቱ ሊለካ አይችልም። ወደ መዲና ገብቶ ፈላጭ ቆራጭ የጦር አበጋዝ ከሆነ በኋላ የነበረው ሕይወት የትክክለኛ ማንነቱ ማሳያ ነው። በነዚያ ዘመናት ለሴቶች የነበረውን አቀራረብ ተመልክተን አሕመዲን እያሉን እንዳሉት ሕይወቱ ምሳሌያዊ ይሆን እንደሆን ማየት ያስፈልገናል። ሙሐመድ የአክስቱ ልጅ የነበረችውን የማደጎ ልጁን ሚስት ዘይነብን ጨምሮ መልከ መልካም መስለው የታዩትን ሴቶች ሁሉ ማግበስበስ የጀመረው ወደ መዲና ከገባ በኋላ ነበር።
አቶ አሕመዲን የትኛውን የማጣመም ክህሎታቸውን ተጠቅመው በስኬት ዘመን የነበረውን የሙሐመድን ስነ ምግባር እንደሚያጸድቁ ወደፊት የምናየው ይሆናል። እስከ አሁን ድረስ ግን አልተሳካላቸውም።
ስለ ሙሐመድ ማንነት ለማወቅ ይህንን ገጽ ይጎብኙ፤ ብዙ ጽሑፎችን ያገኛሉ https://ewnetlehulu.net/muhammad/
ጋብቻ ከአኢሻ ጋር
አሕመዲን ጀበል እንደ ተለመደው የሙሐመድን የጋብቻ ሕይወት ትክክል አድርጎ ለመሳል እንደ ገለባ ክምር የተኮፈሰ ነገር ግን ፍሬ የሌለው ሐተታ ለንባብ አብቅተዋል። ሙሐመድ የ6 ዓመት ህፃን አጭቶ በ9 ዓመቷ አብሯት መተኛቱ ትክክል እንደሆነ ሊያሳምኑን ይህንን ያህል መድከማቸው አሳዛኝ ነው። ጽሑፎቻቸው ብዙ ስህተቶችን የሸከፉ ቢሆኑም የተወሰኑትን ብቻ ላንሳ።
- የጌታን እናት ቅድስት ድንግል ማርያምንና አኢሻን ለጌታ እናት አክብሮት በጎደለው መንገድ ማነጻጸራቸው እጅ በጣም ስህተት ነው። ሁለቱንም “ድንግል” በሚል ቃል የጠቀሱ ሲሆን የጌታን እናት ወደ አኢሻ ደረጃ ዝቅ ለማድረግ አልመው የተናገሩት ነው። የጌታ እናት “ድንግል” በሚል መጠርያ የምትጠራበት ምክንያት በድንግልና ጌታን ስለወለደች ነው። አንዲት ሴት በድንግልና ስላገባች “ድንግል” የሚል ማዕርግ ለሕይወት ዘመኗ ሁሉ መስጠት የተለመደ ካለመሆኑም በላይ በጋብቻ ኖራ ሕይወቷ ያለፈን ሴት በዚህ አጠራር መጥቀስ ትርጉም አይሰጥም። ይህንን ልዩ ዓላማ ያለው አጠራር ተገቢ ባልሆነ ቦታ አስገብተዋል። አቶ አሕመዲን አንዲትን በጋብቻ እየኖረች ያለችን ሴት በድንግልና ስላገባች ብቻ “ድንግል እገሊት” ብሎ መጥራት ተቀባይነት ያለው ጉዳይ እንደ ሆነ የሚያስቡ ከሆነ በአካባቢያቸው በሚኖሩት ባለ ትዳር እናቶች ላይ ይህንን አጠራር በመሞከር ግብረ መልሳቸውን ቢያዩ ጥሩ ትምህርት የሚያገኙበት ይመስለኛል። የገዛ ባለቤታቸውንም “ድንግል እገሊት” እያሉ በሰዎች ፊት መጥራትን ቢያዘወትሩና ለሌሎች ምሳሌ ቢሆኑ ምን ይላቸዋል?
- የጌታን እናት በተመለከተ በምንጭነት የጠቀሱት “የያዕቆብ ወንጌል” በክርስቲያኑ ማሕበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው የፈጠራ ጽሑፍ፤ መስመ ወንጌል (Pseudo Gospel) እንጂ በያዕቆብ የተጻፈ አይደለም። ሙስሊም ሊቃውንት እስላማዊ ምንጮችን ጠንካራ፣ ደህና፣ ደካማ እና ቅጥፈት ብለው በመከፋፈል ለሚቀበሉትና ለማይቀበሉት ምንጭ ጥብቅ መስፈርት ባወጡበት ሁኔታ ምሑራን የፈጠራ ጽሑፍ መሆኑን በአንድ ድምፅ የሚስማሙበትን በያዕቆብ ስም ባልታወቀ ግለሰብ የተጻፈን ጽሑፍ ተአማኒ ማስረጃ አድርጎ ማቅረብ አስቂኝ ነው። የእርሳቸው ጊዜ ሲሆን መረጃ ከተአማኒ ምንጮች ብቻ እየጠየቁ ለክርስትና ሲሆን የፈጠራ ጽሑፍ መጥቀሳቸው ትዝብት ላይ ይጥላቸዋል።
- የጠቀሱት የያዕቆብ ወንጌል ዮሴፍ የጌታን እናት እንዲጠብቃት እንደ ወሰዳት እንጂ ለጋብቻ እንደ ወሰዳት አይናገርም። የዮሴፍንም ዕድሜ ከፍ አድርጎ የጠቀሰበት ምክንያት የእጮኝነቱ ዓላማ ጋብቻ ሳይሆን ጥበቃ መሆኑን ለማሳየት ነው። እንዲያውም ዮሴፍ ከእርሷ ጋር ወሲብ የመፈጸም ፍላጎት እንደሌለው ምዕራፍ 15፡4 ላይ ይገልጻል። አቶ አሕመዲን የጠቀሱትን ተዓማኒነት የሌለው ምንጭ ራሱ በማጣመም የማይለውን ለማስባል ሲጣጣሩ ታይተዋል። ምን ያህል ተስፋ ቢቆርጡ ይሆን?
- መጽሐፍ ቅዱስ ወላዲተ አምላክ ብፅእት ማርያምን ንቁ፣ በሳልና ጥበበኛ ሴት አድርጎ ቢያቀርብም ትክክለኛ ዕድሜዋን አይገልጽም። አቶ አሕመዲን በጠቀሱት በያዕቆብ ወንጌል መሠረት ግን ማርያም ለዮሴፍ የታጨችው በ12 ዓመቷ ቢሆንም ተዓምራዊ በሆነ ሁኔታ የፀነሰችው በ16 ዓመቷ ነበር። መጽሐፉ በምዕራፍ 12፡3 ላይ በግልጽ “She was sixteen years old when these mysteries happened to her” (እነዚህ ምስጢራት (ድንቃድንቆች) በእርሷ ላይ ሲከሰቱ አሥራ ስድስት ዓመቷ ነበር) ይላል። አቶ አሕመዲን ግን እንዲህ ሲሉ በገዛ ፈጠራቸው ላይ የተመሠረተ ጥያቄ ይጠይቃሉ፦ “እኛ እንደ አንዳንድ ጋጠወጦችና ተሳዳቢዎች ብንሆን ኖሮ “ማርያም በለጋ ዕድሜዋ በማርገዟ ለሥነ ልቦናና አካላዊ ጥቃት ተዳርጋለች” ወዘተ ባልን ነበር፡፡ … እኛ በእነሱ አካሄድ ብንጓዝ ኖሮ “እንዴት የዓለሙ ፈጣሪ የሚባለው ኢየሱስ በ12 ዓመት ህፃን ማህፀን ለመረገዝ ፈቀደ?” ስንል በጠየቅን ነበር።”
ክርስቲያኖች ዕድሜው በ50ዎቹ ውስጥ የነበረው ሙሐመድ የ6 ዓመት ህፃን አጭቶ በ9 ዓመቷ አብሯት መተኛቱ ትክክል እንዳልሆነ መናገራቸው ከጨዋነት የጎደለ ነገር እንደሌለው ለመረዳት ሚዛኑን ያልሳተ ኅሊና ያለው ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው። እንደ አሕመዲን ግን ተአማኒነት ከሌለው ምንጭ ከጠቀሱ በኋላ ይህ አልበቃ ብሎ በምንጩ ውስጥ ያልተባለን ቅጥፈት ከኪስ አውጥቶ መጻፍ ኅሊና ቢስነትን ይጠይቃል። እኛ እርሳቸው የተጠቀሟቸውን “ጋጣወጦች፣ ተሳዳቢዎች” የሚሉ ቃላትን ልንጠቀም አንሻም፤ ነገር ግን እርሳቸውን ከሚያክል ሙስሊሙን ማሕበረሰብ ወክሎ ሊናገር ከሚችል ሰው እንዲህ ያለ ቅጥፈት እንደማይጠበቅ መግለጽ በቂ ነው። ሌላውን ጋጣወጥና ተሳዳቢ አድርገው የሳሉት አሕመዲን ይህንን ስህተታቸውን ለማረምና ይቅርታ ለመጠየቅ የሚበቃ ህሊና ያላቸው እንደሆን በቀጣይ የምናይ ይሆናል።
- በመጀመርያው ጽሑፋቸው ከተዛባ ምንጭ በመጥቀስ፣ የጠቀሱትን ምንጭ ደግሞ በማስዋሸት የጀመሩት አቶ አሕመዲን በሁለተኛው ጽሑፋቸው ርዕሱን ከአኢሻ የጨቅላ ዕድሜ ጋብቻ “ዮሴፍና ማርያም ባልና ሚስት ነበሩ” ወደሚል ርዕስ በማዞር ሐሳብ ለማስቀየር ሲታገሉ ታይተዋል። ይህ ግልጽ Red Herring Fallacy ነው። የማርያምን ዕድሜ በተመለከተ መነሻ ያደረጉት የማይታመን ምንጭና የገዛ ፈጠራቸውን ሆኖ ሳለ ገና ከመሠረቱ የተበላሸውን መረጃቸውን እንደ እውነት በመቁጠር ሌላ ክርክር መጀመራቸው ለአኢሻ ጉዳይ መልስ እንዳጠራቸው ማሳያ ነው።
- አቶ አሕመዲን ይህንን ሁሉ እያወሩ ያሉት የሙሐመድንና የአኢሻን ጋብቻ በዘመኑ በነበረው ባሕል መመዘን ተገቢ መሆኑን ለማሳመን እንደሆነ ግልጽ ነው። ለዚህ ነው የአይሁድን ባሕል እንዲሁም ቅድመ ኢንደስትሪ አብዮት የነበረውን የምዕራባውያን ባሕል በእማኝነት የጠቀሱት። ይህ ደግሞ ሙሐመድ ለሰው ልጆች ሁሉ ምሳሌ ሊሆን የሚችል የላቀ ስብዕና የነበረው ሰው ነው የሚለውን የእስልምና አእማድ ትምህርት ውድቅ የሚያደርግ ነው። እኛስ ምን አልን? ሙሐመድ በሰባተኛው ክፍለ ዘመን ኋላ ቀር ባሕል ኖሮ ያለፈ አንድ ግለሰብ ካልሆነና ለሰው ልጆች ሁሉ ምርጡ ምሳሌ እንዲሆን የተላከ ከሆነ ስነ ምግባሩ መመዘን ያለበት በሰባተኛው ክፍለ ዘመን ባሕል ሳይሆን የሰው ልጆች በደረሱበት የላቀ ስነ ምግባር ነው፡፡ ለሰው ልጆች ሁሉ ምሳሌ እንዲሆን በፈጣሪ የተላከ ሰው በእርሱ ዘመን ከነበረው ኋላ ቀር ባሕል የላቀ ስብዕና ሊኖረው ይገባል፡፡ ካልሆነ ግን ለሁሉም የሰው ልጆች የሚመጥን ምሳሌ መሆን አይችልም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሙስሊም ወገኖች ሙሐመድ ከነቢያት ሁሉ የላቀ ሥነ ምግባር የነበረውና የእርሱን ምሳሌነት መከተል ለጀነት እንደሚያበቃ ማመናቸው ስህተት ነው፡፡ አሕመዲን ጀበል ሙሐመድ የ6 ዓመት ህፃን አግብቶ በ9 ዓመቷ አብሯት መተኛቱ ትክክል መሆኑን ሊያሳምኑን ያደረጉት ተጋድሎ ሁሉ መቋጫው ሙሐመድ በዘመኑ ከነበረው ኋላ ቀር ማሕበረሰብ ያልተሻለ ስነ ምግባር የነበረው ለሰው ልጆች ምሳሌ ሊሆን የማይበቃ ግለሰብ ነበር የሚል ሆኗል። ስለዚህ ለሰው ልጆች ሁሉ ምርጡ ምሳሌ አድርጎ በቁርአንና በሐዲስ ራሱን ማቅረቡ ሐሰተኛ ነቢይ ያደርገዋል፤ ያልሆነውን እንደ ሆነ በማስመሰል የሚናገር ሰው ሐሰተኛ ነውና። ለሙሐመድ ሐሰተኛነት እንዲህ ያለ ጠንካራ ሙግት በማቅረባቸው አቶ አሕመዲን ሊመሰገኑ ይገባል።
በዚህ ርዕስ ላይ የበለጠ መረጃ ለማግኘት ተከታዮቹን ሊንኮች መጠቀም ትችላላችሁ
https://ewnetlehulu.net/muhammad/mo_marriage_to_aisha/
https://ewnetlehulu.net/mo-and-aisha/
