እግዚአብሔር ኢየሱስን ጌታም ክርስቶስም አደረገው!

እግዚአብሔር ኢየሱስን ጌታም ክርስቶስም አደረገው!


1.በሐዋርያት ሥራ 2:36 ላይ “እንግዲህ እግዚአብሔር ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ ይረዳ፡፡” ይላል፡፡ ታድያ እግዚአብሔር ኢየሱስን “ጌታ” ካደረገው መጀመርያ ምን ነበር? “ጌታ” የሚለው የክብር መጠርያ ከሆነ ያስኬዳል፡፡ ነገር ግን “አምላክ” በሚለው ትርጉም ከሆነ የማይመስል ነው፡፡ ለምን ቢሉ ከጊዜ በኋላ “ጌታ (አምላክ) መሆን ይችላልን? ጥቅሱ የሚለው “ጌታም ክርስቶስ እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ ይረዳ” ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በትክክል ጌትነትን ከጊዜ በኋላ ነው ያገኘው የሚል ነው፡፡ አምላክ ደግሞ ዘለዓለማዊ ነው፡፡ ኢየሱስ እንዴት አምላክ (ጌታ) ሊባል ይቻለዋል?

ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እንደምንረዳው ኢየሱስ “ጌታ (ኩሪዮስ)” የተባለው አምላክ በመኾኑ እንጂ ለነገሥታት በሚኾን መንገድ በማዕርግ አጠራር አይደለም፡፡ የብሉይ ኪዳን የግሪክ ትርጉም በሆነው የሰብዓ ሊቃናት (ሰብቱጀንት) ትርጉም ውስጥ “ያሕዌ” የሚለው የእግዚአብሔር የተፀውዖ ስም “ኩሪዮስ (ጌታ)” ተብሎ ተተርጉሟል፡፡ ይኸው ቃል በግሪክ አዲስ ኪዳን ኢየሱስን ለመግለፅ የገባ ሲሆን ለፍጥረታት በሚሆን መንገድ እንዳልሆነ ማረጋገጫው በብሉይ ኪዳን ነቢያት ለያሕዌ የተነገሩ ጥቅሶች በአዲስ ኪዳን ስለ ኢየሱስ የተነገሩ መሆናቸው መገለፁ ነው፡፡ ተከታዩን ሳጥን ይመልከቱ፡-

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

የያሕዌን ስም የሚጠራ ኹሉ ይድናል (ኢዩ. 2፡32)

የኢየሱስን ስም የሚጠራ ኹሉ ይድናል (ሐዋ. 22፡14-16፣ ሮሜ 10፡9-13)

ያሕዌ የጌቶች ጌታ ነው (መዝ. 136፡3፣ ዘዳ. 10፡17)

ኢየሱስ የጌቶች ጌታ ነው (ራዕይ 1፡5፣ 17፡14፣ 19፡16)

ያሕዌ የኹሉ ጌታ ነው (ዘዳ. 10፡14፣ ኢያሱ 3፡11-13፣)

ኢየሱስ የኹሉ ጌታ ነው (ሐዋ. 10፡36፣ ሮሜ 14፡8-9፣ ማቴ. 28፡18)

ጉልበት ኹሉ ለያሕዌ ይንበረከካል (ኢሳ. 45፡21-23)

ጉልበት ኹሉ ለኢየሱስ ይነበረከካል (ፊል. 2፡10-11)

ያሕዌ ፊተኛውና ኋለኛው ነው (ኢሳ. 44፡6)

ኢየሱስ ፊተኛውና ኋለኛው ነው (ራዕይ 1፡17-18፣ 22፡12-13)

ያሕዌ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋል (መዝ. 130፡7-8)

ኢየሱስ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋል (ማቴ. 1፡21)

ያሕዌ ለእያንዳንዱ ሰው እንደየሥራው ይከፍለዋል (ኢሳ. 40፡10)

ኢየሱስ ለእያንዳንዱ ሰው እንደየሥራው ይከፍለዋል (ራዕይ 22፡12-16)

ለያሕዌ መንገድ የሚጥርግ መልዕክተኛ ይመጣል (ኢሳ. 403)

ለኢየሱስ መንገድ የሚጠርግ መልዕክተኛ (መጥምቁ ዮሐንስ) መጥቷል (ማር. 1፡2-3)

በሳጥኑ ውስጥ በተጠቀሱት የብሉይ ኪዳን ጥቅሶች ውስጥ የሚገኘው “ያሕዌ” የሚለው ስመ-እግዚአብሔር በሰብዓ ሊቃናት የግሪክ ትርጉም “ኩሪዮስ(ጌታ)” ተብሎ የተተረጎመ ሲሆን እነዚሁ ጥቅሶች ኢየሱስን ለማመልከት በግሪክ አዲስ ኪዳን ውስጥ መጠቀሳቸው ኢየሱስ “ጌታ(ኩሪዮስ)” ተብሎ መጠራቱ አምላክነቱን ለማሳየት እንደሆነ ያረጋግጣል፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ “ጌታ” የተባለው ነገሥታት ለክብር በሚጠሩበት መንገድ ካልሆነና አምላክነቱን በሚያረጋግጥ መንገድ ከሆነ ጠያቂው የጠቀሱት የጴጥሮስ ንግግር ትርጉሙ ምን ይኾን?

በዚህ ቦታ የተነገረው ስለ ኢየሱስ ጌትነት ብቻ ሳይኾን ስለ መሢህነቱም ጭምር መኾኑን ልብ ይሏል፡፡ የጠያቂውን አመክንዮ ከተቀበልን “ኢየሱስ ከመጀመርያው መሢህ (ክርስቶስ) አልነበረም ነገር ግን መሢህ የሆነው ከስቅለቱ በኋላ ነው” የሚል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ እንገደዳለን፡፡ ነገር ግን በቁርኣንም ሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ኢየሱስ ሲወለድ ጀምሮ መሢህ መባሉን እናያለን (ሱራ 3፡45)፡፡

የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የሉቃስ ወንጌል ቀጣይ ክፍል በመኾኑ ምክንያት የዚህን ኃይለ ቃል ትክክለኛ ትርጉም ለመረዳት ወንጌላዊው ሉቃስ ስለ ኢየሱስ ጌትነትና ክርስቶስ ስለመኾኑ በወንጌሉ ውስጥ የጻፈውን መመልከቱ አስፈላጊ ነው፡፡ በሉቃስ ወንጌል ውስጥ ኢየሱስ በልደቱ ወቅት እንኳ ጌታና ክርስቶስ ተብሎ ተጠርቷል (ሉቃ. 1፡41-44፣ ሉቃስ 2፡11)፡፡ ጴጥሮስን ጨምሮ ሐዋርያቱ  ጌታና ክርስቶስ መኾኑን በተደጋጋሚ መስክረዋል (ሉቃ. 9፡18-20፣ 10፡17-22)፡፡ ስለዚህ ሐዋርያው እየተናገረ ያለው ኢየሱስ ከጊዜ በኋላ ጌታና ክርስቶስ ስለመኾኑ ሳይኾን ጌታና ክርስቶስ መኾኑን ከሙታን በማስነሣት እግዚአብሔር አብ ማረጋገጫ (Vindication) መስጠቱን ነው፡፡ ይህንን የበለጠ ለመረዳት ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገረውን አንድ ቃል እንመልከት፡-

“ይህም ወንጌል በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለ ተወለደ እንደ ቅድስና መንፈስ ግን ከሙታን መነሣት የተነሣ በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ኾኖ ስለ ተገለጠ ስለ ልጁ ነው፤ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” (ሮሜ 1፡4-5)፡፡

በዚህ ክፍል ግልፅ ኾኖ እንደሚታየው ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው በትንሣኤው ወቅት ሳይኾን እግዚአብሔር ለዓለም ኹሉ ተዓምራዊ በሆነ ኹኔታ ይህንን ያረጋገጠው በትንሣኤው ወቅት መኾኑን እንገነዘባለን፡፡ ጌትነቱና መሢህነቱም እንደዚያው ነው፡፡

ሌላው መታወስ ያለበት ጉዳይ ቢኖር ጌታችን ወደ ምድር የመጣው ክብሩን ጥሎ የባርያን መልክ በመያዝ እንጂ እንደ ጌታና እንደ ንጉሥ እንዳልነበረ ነው (ሉቃ. 22፡27፣ ማቴዎስ 12፡15-21፣ ሮሜ 15፡8፣ ፊልጵሲዩስ 2፡5-8)፤ መለኮታዊ ባሕርዩ ባይለወጥም ነገር ግን በምድር ላይ የተመላለሰው ፍጹም ሰው በመኾን ነበር፡፡ በማንነቱ ጌታ ቢሆንም ሰብዓዊ ባሕርይን በመላበስ በግብር (Function) አገልጋይ ኾኖ ነበር፡፡ የጌትነት ደረጃውን በሙላት የተቀዳጀው ከእርገቱ በኋላ ነው፡፡ ሐዋርያው እግዚአብሔር አብ ኢየሱስን “ጌታና ክርስቶስ እንዳደረገው” ሲናገር ቀደም ሲል እንደተባለው እግዚአብሔር አብ በትንሣኤ አማካይነት የጌትነቱን ማረጋገጫ ከመስጠቱም በተጨማሪ ተልዕኮውን በመፈፀሙ ምክንያት የጌትነቱን ክብር በተግባር ማቀዳጀቱን ለመግለፅ እንጂ  ኢየሱስ ከጊዜ በኋላ ጌታ ሆነ ለማለት ፈልጎ አይደለም፡፡ የጠያቂው ትርጓሜ ከሉቃስ ጽሑፎች ጋር፣ ብሎም ከመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃላይ ነገረ ክርስቶስ ጋር ይጣረሳል፡፡

 

 

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች የተሰጠ መልስ ማውጫ