እባብ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ አፈር ይበላልን?

 


100. እንደ ዘፍጥረት 3፡13 ሔዋን ያሳሳታት እባብ መሆኑን “እባብ አሳሰተኝና በላሁ” ሥትል ተናግራለች፡፡ እግዚአብሔር አምላክ እባብን እንዲህ አለው፦ ይህን ሥራ ሠራህ፤ ከከብቶችና ከዱር እንስሳት ሁሉ ተለይተህ የተረገምህ ሁን፡፡ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ በደረትህ እየተሳብህ ትሄዳለህ፤ ዐፈርም ትበላለህ፡፡” (ዘፍጥረት 3:14) የክርስትናው ጸሐፊ ቲም ፌሎስ በዚህ ጥቅስ ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “እባብ ተፈጥሮው በሆዱ የሚሳብ ሆነ፡፡ በእባብ ተመስሎ የቀረበው ሰይጣን ተፈርዶበት የመጨረሻ ሽንፈቱ ተነገረ፡፡” (ቲም ፌሎስ፣ የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራርያ 1ኛ መፅሐፍ ገፅ 126)

ሀ) “በሕይወት ዘመን ሁሉ … ዐፈርም ትበላለህ፡፡” እንደተባለው እባብ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ አፈር ይበላልን?

እባቦች የአካባቢያቸውን ሁኔታ ለማወቅ አፈር እንደሚልሱ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ይህ አባባል ቃል በቃል አፈር ስለመብላት ሳይሆን ስለ መዋረድ የተነገረ ነው፡፡ “አፈር መብላት” ውርደትን የሚያመለክት የእብራይስጥ ምሳሌያዊ አነጋገር ሲሆን (መዝሙር 72፡9፣ ኢሳይያስ 49፡23) በእባብ ተጠቅሞ ሔዋንን ያታለላት ሰይጣን እንደሚዋረድ ለመግለፅ የተነገረ ነው፡፡

ለ) እባብ እንዴት አድርጎ ሄዋንን አሳሳተ? ወይንስ ሰይጣን በእባብ ተመስሎ አሳታት? ታድያ ሰይጣን በእባብ ተመስሎ ካሳታት ለምን እባብ “ይህን ሥራ ሠራህ፤ ከከብቶችና ከዱር እንስሳት ሁሉ ተለይተህ የተረገምህ ሁን፤ በሕይወት ዘመን ሁሉ በደረትህ እየተሣብህ ትሄዳለህ፤ ዐፈርም ትበላለህ” ተብሎ ተረገመ? ባልሰራው ኃጢአት?

የዘፍጥረት መጽሐፍ የመጀመርያዎቹ ምዕራፎች ቅኔያዊ በመሆናቸው አስተውሎትን ይሻሉ፡፡ በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ እግዚአብሔር በቀጥታ ለእባቡ ሲናገር የምንመለከት ሲሆን በአዲስ ኪዳን ውስጥ ደግሞ ይህ እባብ ሰይጣን መሆኑ ተነግሯል፡- ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ” (ራዕይ 12፡9)፡፡

ከዚህ ጥቅስ በመነሳት እባቡ የዲያብሎስ ተሠግዎ እንደነበር ልንደመድም እንችላለን፡፡ ስለዚህ እባቡ የሰይጣን መጠቀምያ በመሆኑ ተረግሟል፡፡ የሴቲቱ ዘር የእባቡን ራስ እንደሚቀጠቅጥና እርሱም ሰኮናውን እንደሚቀጠቅጥ መነገሩ ጌታችን ወደዚህ ዓለም በመምጣት በመስቀሉ መከራ ሰይጣንን ድል እንደሚነሳ የተነገረ ትንቢት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

[1] መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጉም፣ ኢንተርናሽናል ባይብል ሶሳይቲ፣ 1993፣ 1ቆሮ. 15፡29 የግርጌ ማጥኛ፣ ገፅ 1759፡፡