ኢየሱስ አምላክ ከሆነ አብ ከእኔ ይበልጣል ለምን አለ?
-
ኢየሱስ አምላክ ከሆነ ለምንድነው በዮሐንስ 10:29 ላይ “እነርሱን የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፡፡” እንዲሁም በዮሐንስ 14:28 “ብትወዱኝስ አብ ከእኔ ስለሚበልጥ ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር” ያለው? እንደዚሁም በዮሐንስ 13:16 እና 1ኛ ቆሮንቶስ 11:3 ላይ አምላክ ከኢየሱስ እንደሚበልጥ ተገልጿል ፡፡ ከአምላክ የሚበልጥ ሌላ አምላክ አለን? ወይስ ኢየሱስ “ትንሹ አምላክ” ነው? አብ ከእርሱ እንደ ሚበልጥ ኢየሱስ ሲናገር ክርስቲያኖችን ግን “በፍፁም እኩል ናቸው” ይላሉ ፡፡ ታዲያ ኢየሱስ ይህን ሲናገር እየዋሸ ነውን? ወይስ ክርሥቲያኖች ናቸው የዋሹት? ኢየሱስ ክርስቶስ “አብ ከእኔ ይበልጣል” ሲል ሰብዓዊ ማንነቱን ብቻ የሚመለከት እንጂ “በመለኮታዊ ባህሪ ደረጃ ግን እኩል ናቸው” ብሎ ማሰብስ የቋንቋ አጠቃቀም ሥርዓትን ትርጉም ማሳጣት አይሆንምን?
በመጀመርያው ጥቅስ ላይ በጎቹን የሰጠው አብ በጎቹን ከእጁ ሊነጥቁ ከሚመኙት ሁሉ እንደሚበልጥ ለመናገር ፈልጎ “እነርሱን የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል” አለ እንጂ ራሱን በማካተት እየተናገረ አይደለም፡፡ ከእርሱም ሆነ ከአብ እጅ በጎቹን ማንም መንጠቅ እንደማይችል ከተናገረ በኋላ እርሱና አብ አንድ እንደሆኑ በማሳወቅ በባሕርይ የተካከሉ መሆናቸውን ግልፅ አድርጓል (ዮሐንስ 10፡30)፡፡ ይህ አንድነት የኃይል አንድነትን የሚገልፅ ነው፡፡ አብና ኢየሱስ በኃይል አንድ ናቸው፡፡ ለዚህ ነው ማንም በጎቹን ከአብ እጅ መንጠቅ እንደማይችል ሁሉ ከኢየሱስም እጅ መንጠቅ የማይችለው፡፡ በተጨማሪም በዚሁ ቦታ ላይ ለበጎቹ የዘለዓለምን ሕይወት እንደሚሰጥ በመናገር አምላክነቱን የበለጠ ግልፅ አድርጓል (ቁ.28)፡፡ ከአምላክ በስተቀር የዘለዓለምን ሕይወት መስጠት የሚችል አለን? ከዚህ ንግግር በኋላ አይሁድ ሊወግሩት ድንጋይ ያነሱት ኢየሱስ አምላክ መሆኑን እየተናገረ መሆኑ ስለገባቸው ነው፡- “አይሁድም፦ ስለ መልካም ሥራ አንወግርህም፤ ስለ ስድብ፤ አንተም ሰው ስትሆን ራስህን አምላክ ስለ ማድረግህ ነው እንጂ ብለው መለሱለት” (ቁ.31-33)፡፡ (ኢየሱስ በዚህ ቦታ ላይ ስለ ኃይል እንጂ ስለ ዓላማ እየተናገረ ባለመሆኑ በዮሐንስ 17፡20-21 ላይ ለሐዋርያቱ ከተነገረው አንድነት ጋር ማመሳሰል ትክክለኛውን የሥነ ፍታቴ ሥርኣት የሚጥስ ነው፡፡ የሁለቱ አውድ ለየቅል ናቸው፡፡)
በሌሎቹ ጥቅሶች ውስጥ አብ ከኢየሱስ እንደሚበልጥ መገለፁን ጸሐፊው የተመለከቱት በተለመደው የነጠላ አሃዳዊነት ንፅረተ ዓለም መነፅራቸው ነው፡፡ በእሳቸው እምነት መሠረት አምላክ የተባለ አንድ አካል ብቻ በመኖሩ ከዚያ አካል በምንም መንገድ ሊበልጥ የሚችል ነገር መኖሩ ከተነገረ ያ አካል ከመቅፅበት ከአምላክነት ቦታ ይወርዳል፡፡ ክርስትና ግን አንድ አምላክ ብቻ መኖሩን ቢያስተምርም ይህ አንዱ አምለክ ሦስት አካላት እንዳሉት ስለሚያስተምር በነዚህ አካላት መካከል የሥራ ድርሻ (function) ወይም የደረጃ (rank) ብልጫ ሊኖር ይችላል፡፡ ይህ በእግዚአብሔር በራሱ ሕላዌ ውስጥ የሚገኝ እንጂ ከእርሱ ውጪ የሚገኝ ባለመሆኑ በሥላሴነት ከሚኖረው ከአንዱ አምላክ ውጪ የሚገኝ አካል ብልጫ እንዳለው እስካልተነገረ ድረስ ምንም የሚፈጥረው ችግር የለም፡፡ በነዚህ ቦታዎች የተጠቀሰው “ሜይዞን” የሚለው የግሪክ ቃል ደረጃን እንጂ የግድ የባሕርይ ብልጫን የሚያመለክት አይደለም፡፡ አንድ አካል ከሌላው በሥራ ድርሻ፣ በሥልጣን ወይም በደረጃ ይበልጣል ማለት የባሕርይ ብልጫ አለው ማለት እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ለምሳሌ ያህል የአንድ አገር መሪ በሥራ ድርሻ፣ በሥልጣንም ሆነ በደረጃ በስሩ ከሚተዳደሩት ዜጎች ይበልጣል፡፡ ይህ ማለት ግን እንደ ሰው ያለው ዋጋ (Value) ከማንም ይበልጣል ማለት አይደለም፡፡ ባል የቤተሰብ ራስ እንደመሆኑ መጠን ከላይ በተጠቀሱት መንገዶች ከሚስቱ ሊበልጥ ይችላል ነገር ግን ወንድ እንደ ሰውነቱ ከሴት ይበልጣል ወይም ሴት ከወንድ ታንሳለች ማለት ግን አይደለም፡፡ የግሪክ አዲስ ኪዳን የባሕርይ ብልጫን ለማመልከት “ዲያፎሮስ” የሚል ሌላ ቃል የሚጠቀም ሲሆን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በባሕርዩ ከመላእክት የላቀ መሆኑን ለማመልከት ዕብራውያን 1፡4 ላይ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ በሥላሴ አካላት መካከል የሚገኘውን ግንኙነት ለማመልከት ግን ይህ ቃል ጥቅም ላይ ውሎ አናገኝም፡፡ ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አብ ከወልድ መብለጡ መነገሩ የመለኮታዊ ባሕርይ ብልጫን ሳይሆን የሥራ ክፍፍልን እና ወልድ ሥጋን በመልበስ መለኮታዊ ክብሩን ትቶ ወደ ምድር እንደመምጣቱ መጠን (ፈልጵስዩስ 2፡5-11) የደረጃ ብልጫን ብቻ የሚያመለክት በመሆኑ የኢየሱስን አምላካዊ ባሕርይ ከአብ የሚያሳንስ አይደለም፡፡