ኢየሱስ አምላክ ከሆነ ቸር መባል እንደሌለበትና “ቸር” አንዱ እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን ለምን ተናገረ?

 


  1. ኢየሱስ በማርቆስ 10:18 ላይ “ስለ ምን ቸር ትለኛለህ?” በማለት “ቸር” ለመባል ካልፈለገ እንዴት አምላክ ይባላል? ኢየሱስ ቸር መባል እንደሌለበትና “ቸር” አንዱ እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን ካስተማረ፣ ይህ ብቻ አምላክ አለመሆኑን አይገልጽምን? “ቸር” መባልን እዲህ ከተቃወመ “ከአምላክ እኩል ነው የሚለውን ቢሰማ እንዴት ይቆጣ ይሆን?

ኢየሱስ አምላክ መሆኑን ሰዎች በተቃውሞ መልክም ሆነ አምኖ በመቀበል ሲናገሩ በተደጋጋሚ ሰምቷል ነገር ግን እነርሱ የተናገሩትን ከማረጋገጥ ውጪ ሲቃወም ተሰምቶ አይታወቅም (ዮሐንስ 10፡33፣ 20፡28)፡፡ ሰዎች ለአምላክ የሚገባውን ስግደት እና አምልኮ ሲሰጡት አንድም ጊዜ አልተቃወመም (ማቴዎስ 8፡2፣ 9፡18፣ 15፡25፣ 14፡33፣ 20፡28፣ 28፡9፣ 28፡17፣ ሉቃስ 24፡52፣ ዮሐንስ 9፡38)፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ አምላክ በመሆኑ አምላክ መባሉ ያስደስተዋል እንጂ አሕመዲን እንዳሉት አያስቆጣውም፡፡ ጠያቂው በጠቀሱት ክፍል ኢየሱስ “ቸር አይደለሁም” እያለ አይደለም፤ ነገር ግን ሰውየው ኢየሱስ መምህር ብቻ መሆኑን እያሰበ ከመጣ በኋላ ለአምላክ ብቻ የሚሰጠውን ማዕርግ ስለሰጠው የንግግሩን ትርጉም እንዲገነዘብ ለማሳሰብ “ስለምን ቸር ትለኛለህ?” በማለት ጠይቆታል፡፡ ሰውየው የኢየሱስን ማንነት ተገንዝቦ ቢሆን ኖሮ ኢየሱስ ይህንን ባላለ ነበር፡፡ ነገር ግን መምህር ብቻ መሆኑን እያሰበ ለአምላክ ብቻ የሚሰጠውን ማዕርግ መስጠቱ ትክክል ባለመሆኑ ሊያርመው ይህንን ተናገረ፡፡ ተመሳሳይ የግሪክ ቃል በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከፍጡራን ጋር ተያይዞ ከመጠቀሱ አንፃር (ለምሳሌ ማቴዎስ 12፡35) ይህ የኢየሱስ መልስ ቃሉ በምንም ዓይነት መንገድ ከአምላክ ውጪ ለሌላ ፍጥረት ጥቅም ላይ መዋል የለበትም የሚል ትርጉም የለውም፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ የሰውየውን ልብ ስለሚያውቅ እርሱ በልቡ እያሰበ ባለበት በዚያ መንገድ በራሱ መልካም የሆነው አምላክ ብቻ መሆኑን ሊያሳውቀው ነው ይህንን የተናገረው፡፡ ይህ ደግሞ ኢየሱስ የሰዎችን ልብ የማወቅ መለኮታዊ ችሎታ እንዳለው ያሳያል፡፡ በተጨማሪም ሰውየው የዘለዓለምን ሕይወት ያገኝ ዘንድ ሁሉን ትቶ እርሱን እንዲከተለው በመንገር ለፈጣሪ ብቻ የሚገባውን መሰጠት እና መገዛት ከሰውየው ጠይቋል፡፡ ይህም በክፍሉ ውስጥ የተገለጸ አምላክነቱን የሚያረጋግጥ ሌላ ማስረጃ ነው፡፡