ኢየሱስ አምላክ ከሆነ ተዓምር ለማድረግ ለምን ጸለየ? ተዓምራቱስ የማን ነው?

 

 


 

7. የዮሐንስ ወንጌል 11፡38-43 ላይ “ኢየሱስ ልቡ ዳግመኛ በኀዘን ተነክቶ ወደ መቃብሩ መጣ መቃብሩም በድንጋይ የተገጠመ ዋሻ ነበር፤ እርሱም “ድንጋዩን አንሱት” አለ፡፡ የሟቹም እህት ማርታ፤ ጌታ ሆይ አሁንማ አራት ቀን ስለቆየ ይሸታል” አለችው፡፡ ኢየሱስም ብታምኝስ የእግዚአብሔርን ክብር ታያለሽ ብዬ አልነገርሁሽምን?” አላት፡፡ ስለዚህ ድንጋዩን አነሱ፡፡ ኢየሱስም ወደላይ ተመልክቶ እንዲህ አለ “አባት ሆይ ስለ ሰማኽኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ ሁልጊዜም እንደምትሰማኝ ዐውቃለሁ፤ ይህን መናገሬ ግን በዚሁ የቆሙ ሰዎች አንተ እንደላክኽኝ የምኑ ዘንድ ነው፡፡” ኢየሱስ ይህን ካለ በኋላ በታላቅ ድምፅ “አልዓዘር ና ውጣ!” ብሎ ተጣራ፡፡ የሞተውም ሰው እጅና እግሩን በቀጭን ስስ ጨርቅ እንደተጠቀለለ፤ ፊቱም በሻሽ እንደ ተጠመጠመ ወጣ፡፡ ኢየሱስም “መግነዙን ፍቱለትና ይሂድ” አለቸው፡፡” ሲል ተገልጿል፡፡ ተዓምሩ የማን ነው? ኢየሱስ ጸልዮ “ስለሰማኽኝ አመሰግንሃለሁ” በማለት ፀሎቱ መሰማቱን ገለጸ፡፡ 

ተዓምራቱ የርሱ ነው በሚል እንደይታለሉ ፀሎቱን ማሰማቱን ለምን እንደተናገረ ሲገልፅ “ይህን መንገሬ ግን በዚህ የቆሙ ሰዎች አንተ እንደ ላከኝ ያምኑ ዘንድ ነው” ብሎ ነበር፡፡ ታድያ ኢየሱስ አምላኩን ለምኖ ተዓምር ቢያደርግ ምን ያስገርማል? አምላክ ከዚህ የበለጠ ላሻው መስጠት አይችልምን? ይህንን ተዓምር ያየችው የሟቹ እህት ማርታ ተዓምሩ የራሱ የኢየሱስ መሆኑን አምና ነበርን? ኢየሱስስ ቢሆን “ብታምኝስ የእግዚአብሔር ክብር ታያለሽ ብዬ አልነገርሁሽምን?“ አይደል ያላት? ታድያ ምነው አምላክ ነው ማለታችን?

አሕመዲን ይህንን ጥያቄ የጠየቁት ኢየሱስ አምላክ ነው የሚለው የክርስቲያኖች እምነት በፈጸማቸው ተዓምራት ላይ የተመሠረተ ነው የሚል የተሳሳተ ቅድመ ግንዛቤ ስለያዙ ነው፡፡ በክርስቲያኖች እምነት መሠረት የኢየሱስ ተዓምራት ስለ አምላክነቱ የተናገራቸውን ነገሮች የሚያረጋግጡ ምልክቶች እንጂ ብቻቸውን ተነጥለው የሚታዩ ምልክቶች አይደሉም፡፡ ጌታችን ማንም ነቢይ ተናግሮ የማያውቃቸውን አምላክ መሆኑን የሚያሳዩ ንግግሮችን ከመናገሩ የተነሳ እነዚህ ምልክቶች የኢየሱስ ንግግሮች እውነት መሆናቸውን የሚያረጋግጡና አብም ከኢየሱስ ንግግሮች ጋር መስማማቱን የሚያሳዩ ምልክቶች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል ማርቆስ 2፡5-12 ላይ ኃጢአትን ይቅር የማለት መለኮታዊ ሥልጣን እንዳለው ለማረጋገጥ ሽባውን ፈውሶታል፡፡ ማቴዎስ 14፡22-33 ላይ ንፋሱንና ወጀቡን በቃሉ ፀጥ በማሰኘት በተፈጥሮ ላይ ያለውን ሥልጣን ካሳየ በኋላ በታንኳይቱ ውስጥ የነበሩት ሰዎች “በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብለው ሰግደውለታል፡፡ ከዚህም አልፎ ጌታችን ተከታዮቹ በስሙ ተዓምራትን ያደርጉ ዘንድ ሥልጣንን ሰጥቷል፤ ይህንንም በማድረግ ስሙ የአምላክ ስም መሆኑን አረጋግጧል (ማርቆስ 6፡7-13፣ 9፡38-39፣ ሉቃስ 10፡17-20፣ የሐዋርያት ሥራ 3፡1-16፣ 4፡7-12፣ 9፡33-35፣ 16፡16-18)፡፡ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ሰዎች በነቢያትም ሆነ በየትኛውም ቅዱስ ሰው ስም ተዓምራትን ሲያደርጉ የተመዘገበ ታሪክ የለም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተዓምራትን በማድረግ ብቻ ሳይሆን ተከታዮቹ በስሙ ተዓምራትን እንዲያደርጉ ሥልጣንን በመስጠት ስለ አምላክነቱ የተናገራቸው ንግግሮች እውነት መሆናቸውን አረጋግጧል፡፡

ክርስቲያኖች ኢየሱስ ከአብ ተነጥሎ ወይንም ደግሞ ያለ አብ ፈቃድ ተዓምራትን ያደርግ እንደነበር ስለማያምኑ አሕመዲን ይህንን ለኛ ለማብራራት መሞከራቸው ስለ እምነታችን ያላቸውን የዕውቀት ጉድለት የሚያሳይ ነው፡፡ ኢየሱስ አብ እንደሰማውና ዘወትር እንደሚሰማው በመግለፅ ካመሰገነ በኋላ አልዓዛርን አስነስቶታል፡፡ ያንን መናገር ያስፈለገው ደግሞ እርሱ ከአብ የተላከ መሆኑን የሚጠራጠሩ በቦታው የነበሩ ሰዎች እንዲያውቁ ለማድረግ እንጂ ለራሱ ብሎ አልነበረም፡፡ እርሱ ተዓምራትን ለማድረግ መጸለይ አያሻውም፡፡ ይህንን ደግሞ በግልፅ ቋንቋ ለማርታ ነግሯታል፡-

ማርታም ኢየሱስን፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር፤ አሁንም ከእግዚአብሔር የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንዲሰጥህ አውቃለሁ አለችው፡፡ ኢየሱስም፦ ወንድምሽ ይነሣል አላት፡፡ ማርታም፦ በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንዲነሣ አውቃለሁ አለችው፡፡ ኢየሱስም፦ ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘለዓለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽን? አላት፡፡ እርስዋም፦ አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ እኔ አምናለሁ አለችው፡፡

ማርታ ኢየሱስ በጸሎቱ ሁሉንም ነገር የማድረግ ችሎታ እንዳለው ብታምንም ነገር ግን ወንድሟ በዚያኑ ቅፅበት የመነሳቱን ጉዳይ ስትጠራጠርና በመጨረሻው የትንሣኤ ቀን እንደሚነሳ ስትናገር እናያለን፡፡ ነገር ግን ጌታችን የሕይወት ምንጭ ራሱ መሆኑን “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘለዓለም አይሞትም” በማለት በማስረዳት ሙታንን ለማስነሳት መጸለይ እንደማያሻው ግልፅ አድርጎላታል፡፡ ትንሣኤና ሕይወት ራሱ ኢየሱስ ከሆነ ሙታንን ለማስነሳት መጸለይ ያስፈልገዋልን? እንዲህ ዓይነት ንግግር መናገር የሚችል ከአምላክ በስተቀር ማን ሊሆን ይችላል?  ኢየሱስ የጸለየው ተዓምራትን ለማድረግ መጸለይ ስለሚያስፈልገው አልነበረም፡፡ ነገር ግን በዚያ የነበሩት ሰዎች በአብ የተላከ አንድያ ልጁ፣ መሲሁ መሆኑን እንዲገነዘቡ ለማድረግ ነበር፡፡

በእስላማዊ ትምህርት መሠረት ከአላህ ዘጠና ዘጠኙ ስሞች መካከል አንዱ “አል-ባሂሥ” የሚል ሲሆን ትርጓሜውም “ከሞት የሚያስነሳ” እንደማለት ነው፡፡ ከእነዚህ ስሞች መካከል አንዱን እንኳ ለፍጡር መስጠት የሽርክ ኃጢአት እንደሆነ ይቆጠራል፡፡ ይህም ማለት ያንን አካል ከፈጣሪ እኩል ማድረግ ማለት ነው፡፡ ጌታችን በዚህ ስም ራሱን በመጥራቱ በእስልምና መስፈርት መሠረት አምላክ መሆኑን በፍፁም ግልፅነት ተናግሯል! ኢየሱስ አምላክ መሆኑን የተናገረበት ቦታ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደሌለ የሚናገሩት አሕመዲን በራሳቸው ሃይማኖት መስፈርት መሠረት ኢየሱስ አምላክ መሆኑን መናገሩን ሲያዩ መልሳቸው ምን ይሆን?

ኢየሱስ ያደረገው ተዓምር የአብን ክብር የገለጠውን ያህል የእርሱንም ክብር ገልጧል (ዮሐንስ 11፡4)፡፡ የመጀመርያውን ተዓምር ካደረገ በኋላ እንዲህ ተብሎለታል፡- ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ፡፡” (ዮሐንስ 2፡11)፡፡