ኢየሱስ ህግን የፈጸመ ይድናል ካለ ክርስቲያኖች በኢየሱስ ቤዛነት ይዳናል ለምን ትላላችሁ?

 


  1. ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ሕግንና የነቢያትን ቃል ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ለመፈፀም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም፡፡” (ማቴዎስ 5፡17) እንዲሁም እውነት እላችኋለሁ፤ ሰማይና ምድር እስክያልፍ ድረስ ሕግ ሁሉ ይፈፀማል እንጂ ከሕግ አንዲት ፊደል ወይም አንዲት ነጥብ እንኳን ቢተላለፍ  ሌሎችንም እንዲተላለፍ ቢያስተምር በመንግስተ ሰማይ ታናሽ ተብሎ ይጠራል፤ ነገር ግን እነዚህን ትእዛዘት እየፈፀመ ሌሎችም እንዲፈፅሙ የሚያስተምር በመንግስተ ሰማይ ታላቅ ይባላል፡፡ (ማቴዎስ 5፡18-19) ይላል፡፡ ትእዛዘትን እየፈፀመ እንዲፈፀም የሚያስተምር ሰው ነው በመንግስተ ሰማያት ታላቅ የሚባለው፡፡ ግን ክርስቲያኖች “በኢየሱስ ለሰው ኃጥአት ቤዛ መሆኑን ያመነ ሰው ነው መንግስተ ሰማያትን የሚገባው ይላሉ፡፡ ትእዛዘትን መፈጸም አስፈላጊ እንዳልሆነ ሁሉ ያሚያስተምሩ ክርስቲያኖችም አሉ፡፡ ታድያ ኢየሱስ ያለው ውሸቱን ነበርን? ወይንስ እንዲህ የሚሉት ክርስቲያኖች ናቸው የዋሹት?

ኢየሱስ በዚህ ቦታ ላይ እየተናገረ ያለው ህግን በመጠበቅ ወደ መንግሥተ ሰማያት ስለመግባት ሳይሆን ህግን በመጠበቅ በመንግሥተ ሰማያት ውስጥ ስለሚገኝ ደረጃ በመሆኑ ጠያቂው ሐሳባቸውን የሚደግፍ ጥቅስ አልጠቀሱም፡፡ ጌታችን ለሰው ልጆች ኃጢአት ቤዛ በመሆን እንደሚሞት በተደጋጋሚ ተናግሯል (ማቴዎስ 20፡28፣ 26፡28፣ 14፡24፣ ማርቆስ 10፡45፣ ዮሐንስ 3፡14-15፣ 10፡11፣ 15፡30)፡፡ እውነተኛ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት ይጠብቃሉ፡፡ ትዕዛዛቱን የሚጠብቁት የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ ሳይሆን የእግዚአብሔር መንግሥት ወራሾች ስለሆኑ ነው፡፡ ሕግን መጠበቅ የደህንነት መገለጫ እንጂ የደህንነት ማግኛ መንገድ አይደለም፡፡ እውነተኛ እምነት በሥራ የሚገለጥ እንጂ በቃል ብቻ የሚሆን ባለመሆኑ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንደዳነ የሚናገር ነገር ግን በእርሱ ትዕዛዝ የማይኖር ሰው ሲጀመር አላመነም፡፡  ከነፍስ የተለየ አካል የሞተ እንደሆነ ሁሉ ከሥራ የተለየ እምነትም የሞተ ነው (ያዕቆብ 2፡26)፡፡ በክርስቶስ እንዳመነ የሚናገር ነገር ግን በቀድሞ ክፉ ኑሮው የሚመላለስ ሰው በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ቦታ የለውም (1ቆሮንቶስ 6፡9-10፣ ኤፌሶን 2፡8-10)፡፡

ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖች ሕግን መሻር እንደማይገባቸው ነገር ግን ማፅናት እንደሚገባቸው አስተምሯል (ሮሜ 3፡31)፡፡ እውነተኛ ክርስቲያኖችም ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ከኃጢአት ርቀው የሚኖሩት እንደሆኑም አፅንዖት ሰጥቷል (ሮሜ 8፡1-23)፡፡ እስልምና ሰው ገነት የሚገባው ሕግን በመጠበቅ እንደሆነ ሲያስተምር ክርስትና ግን አማኞች ሕግን የሚጠብቁት በክርስቶስ ሥራ በኩል ገነት መግባታቸውን ስላረጋገጡ እንደሆነ ያስተምራል፡፡ ደህንነት በእስልምና የሰው ሥራ ነው፤ በክርስትና ግን የእግዚአብሔር ሥራ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሥራ ፍጹም እንከን የለሽና ዋስትና ያለው ነው፡፡ የሰው ሥራ ግን መቼም ቢሆን ፍጽምና ሊኖረው ስለማይችል ለእግዚአብሔር መንግሥት ሊያበቃ የሚችል ዋስትና የለውም፡፡ ለዚህ ነው ሙስሊሞች ከክርስቲያኖች በተጻራሪ ወደ ገነት ስለመግባታቸው እርግጠኞች ያልሆኑት፡፡